Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ማረሚያ ቤት ወይስ ሥቃይ ቤት!

0 475

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ማረሚያ ቤት ወይስ ሥቃይ ቤት!

                                            ሞገስ ፀ

የሰው ልጅ  በማወቅም ሆነ ባለማወቅ እንዲሁም ስሜታዊ በመሆን ወንጀል ይሰራል፡፡ ሁሉም ሀገሮች ደግሞ የተለያየ የወንጀል መቅጫ ህግ አላቸው። በመሆኑም በተመሳሳይ ወንጀል የተለያየ የፍርድ ውሳኔዎችን ይወሰናሉ፣ የወንጀል መክበድና መቅለል እንደ ሀገራቱ ባህል፣ ሀይማኖትና እሴት ይለያያል፡፡ በኛ ሀገርም ወንጀል ሰርተው ማረሚያ ቤቶችን የሚጎበኙ ትንሽ የማይባሉ ታራሚዎች አሉ፡፡ በተለይ ደግሞ አብዛኛው ማለት በሚያስችል ሁኔታ ታራሚወቻችን ወጣቶችና  የፖለቲካ እስረኞች መሆናቸው በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት የሌለውና ትችት ሲሰነዘርበት የቆየ ነው፡፡

ባለፉት ጥቂት ዓመታት የለውጥ ችቦ አቀጣጣዩን ወጣት የህብረተሰብ ክፍል በጅምላ፣ በመሰለኝና በደሳለኝ ወደ ማረሚያ ቤቶች ሲታጎሩ ማየት የዕለት ተዕለት ተግባር ሁኖ ነበር፡፡  ብዙዎች እንደሚሉትና እንደታዘብነው ማረሚያ ቤቶቻችን ወንጀለኛችን ያስተምራሉ ወይ የሚለው ጥያቄ አጠያያቂ ነው። ምክንያቱም እስር ቤቶቻችን የስቃይና የሰቆቃ ቤቶች ናቸው። ከማስተማር ይልቅ ኢ-ስብአዊ በሆነ አያያዝ በድብደባ የታራሚዎችን አካል በማጉደል ህገ- መንግስቱ በማይፈቅደው መልኩ በታራሚዎች ላይ ወንጀል ሲፈፀሙ ይስተዋላል፡፡

በተለይም ባለፍት ሦስት ዓመታት ውስጥ በአማራ፣ በሶማሊያ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና በኦሮሚያ ክልል ያሉ ወጣቶች ከየቤታቸው ተለቅመው ያለ ወንጀላቸው የእስር ሲሳይ ሆነዋል፡፡ ማረሚያ ቤቶቻችንም ጋጣቸው ሞልቶ ኢኒቨስትመንት ይመስል ተጨማሪ የማስፋፊያ ቦታና በጀት አስበጅተው ሲነቀሳቀሱ ይስተዋላሉ፡፡ ማረሚያ ቤቶቹ የተቋቋሙበት ዋና አላማቸው ወንጀለኞችን በማስተማር የፀፀት ስሜት ተሰምቶት ተምሮ እንዲወጣ ማድረግ ቢሆንም በእኛ ሀገር ይህ ሲሆን አይስተዋልም፡፡

ዴሞክራሲያቸው ከእንጭጭነት ያሸጋገሩ ሀገሮች ከግዜ ወደግዜ ማረሚያ ቤቶቻቸውን በመዝጋት ላይ ሲሆኑ እኛ ደግሞ በመገንባት ላይ እንገኛለን። ላለፍት 27 ዓመት እንጭጭ ነው እየተባለ ያለው ዴሞክራሲያችን መች ይሆን ፍሬ የሚያፈራው? ለእስር ቤቶቻችን የሚወጣውን ገንዘብና የሰው ሀብትስ ወደ ልማት የሚቀየረው መች ይሆን? እርግጥ ነው ለ27 ዓመታት እንጭጭ የነበረው ዴሞክራሲያችን በሦስት ወር ውስጥ መጎምራት ጀምሯል፡፡ ለምን ይሆን እስር ቤቶቻችን ከህገ- መንግስታችን ውጭ በሆነ መልኩ የህግ ታራሚዎች ላይ ኢ-ሰብአዊ የሆነ ድርጊት የሚፈጽሙት?  አንቀጽ 21(1) እንዲህ ይላል “በጥበቃ ስር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች ሰብአዊ ክብራቸውን የሚጠብቁ ሁኔታዎችን የመያዝ መብት አላቸው” ይላል። እንዲሁም (2) “ከትዳር አጋሮቻቸው፣ ከቅርብ ዘመዶቻቸው፣ ከጓደኞቻቸው፣ ከሀይማኖት አባቶቻቸው እና ከህግ አማካሪያቸው ጋር ለመገናኘትና እንዲጎበኙአቸው እድል የማግኘት መብት አላቸው” ይላል፡፡

ነገር ግን ከዚህ ተቃራኒ በሆነ መንገድ የታራሚ ዘመድ መጥቶ መጠየቅ አይችልም። ከማንኛውም ሀይማኖታዊና ማህበራዊ ተቋም ጋር እንዲገናኙ አይፈቀድም።  ይባስ ብለው በህግ አስከባሪዎች መገረፍ፣ ምግብ መከልከልና የተፈጥሮ ህግን በጣሰ መልኩ እንዳይተኙና እንዳይፀዳዱ ማድረግ የተለመደ የእስር ቤቶቻችን ተግባሮች ናቸው፡፡ ማረሚያ ቤት ተብለው ተቋቁመው ተግባራቸው ግን የስቃይ ቤት በመሆኑ ለብዙ ሰዎች የእግር እሳት  ሆነዋል፡፡ የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ማረሚያ ቤት የገባ ዘመድን እንደሞተ መቁጠር ተጀምሯል፡፡ በታክሲ ስሄድ እንዲህ ሲባባሉ ሰማሁኝ ወንድምህ ሰላም ነው ብሎ ሲጠይቀው ሞቷል እኮ አለው። እንዴ የህግ ታራሚ አይደለም እንዴ ሲለው እሱስ ልክ ነህ ያው ቃሊቲ ስለሆነ እንደሞተ ቁጠረው ብየ ነው።

የዚህ ሰው ተስፋ መቁረጥ የመነጨው ብዙ የህግ ታራሚዎች ፍርዳቸውን ጨርሰው ይወጣሉ ተብሎ ሲጠበቅ ህልፈተ ህይወታቸው ይሰማል። ካልሆነ ደግሞ ሲገቡ ይዘውት የነበረውን ጤናቸውን አጥተው ይወጣሉ፡፡ ዜጎቻችን ሕገ-መንግሥታዊ  መብታቸውን በመጠየቃቸው ብቻ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብታቸው ተጥሷል፡፡ ከታራሚዎቹ አንደበት እንደሰማነው ታፍነው ወደማያውቁት ስፍራ ተወስደው ማስፈራሪያ ደርሶባቸዋል፣ ብርሀን እንዳያገኙ በጭለማ እስር ቤት ተወርውረዋል፣ ታስረው በኤሌክትሪክ  ሽቦ ተገርፈዋል፣ ጥፍራቸው ተነቅሏል፣ አይናቸው ፈሷል፣ እግራቸው ተቆርጧል ሌላም ሌላም… አንዳንድ ወንድሞቻችን የዘር ፍሬያቸው ተኮላሽቶ ከጥቅም ውጭ እንዲሆን ተደርጓል። እህቶቻችንም ሴትነታቸውን ተከትሎ ዘግናኝ ግፍና በደል ተፈጽሞባቸዋል። አንዳዶችም በእስር ቤቱ ጥበት ተፋፍገው መኖራቸው ሳያንስ በእሳት ተቃጥለዋል። ህክምና ተነፍገዋል፡፡ ጥቂቶች በእስር ቤት ውስጥ የሚደርሱባቸውን በድሎች በችሎት ፊት ቀርበው ቢያስረዱም እንኳን ሃይ ባይ ዳኛ ሳያገኙ ቀርተዋል፡፡

አብዛኛዎቹ ግን ይቅርታ እና አመክሮ ለማግኘት ሲሉ የተፈጸምባቸውን  በደል እንኳን ለፍርድ ቤቶች ለማስረዳት አይደፍሩም ሰሚም አላገኙም፡፡

ሚዲያዎቻችን በሕገ-መንግሥቱ የተሰጣቸውን የአመለካከትና ሀሳብን በነጻ የመያዝና የመግለጽ መብታቸውን ተጠቅመው መሥራት እንዲችሉ ሁኔታዎች ተመቻችተውላቸዋል፡፡ በተለይም የመንግሥት ሚዲያዎች  ቀደም ሲል የነበረውን አድሏዊ አሰራር አስወግደው ነጻና ገለልተኛ ሆነው እንዲሠሩ ተበረታትዋል፡፡ ዛሬ የመንግሥት ሚዲያዎች የህዝቡን ብሶትና ምሬት ማውራት በመጀመራቸው ተደማጭነታቸው ከፍ ብሏል፡፡ ቀዳሚና ታማኝ የመረጃ ምንጭም እየሆኑ መጥተዋል፡፡   

በዚህም መሠረት ባልተለመደ መልኩ ከሰሞኑ ባስተላለፉት ፕሮግራም  በየእስር ቤቶቹ በዜጎች ላይ ይፈጸም የነበረውን ግፍና በደል አስመልክተውናል፡፡ እውነት ይህ ሁሉ ግፍ በአገራችን እስር ቤት የተከሰተነውን? በሚል እጃችንን በአፋችን ላይ ጭነን እንድንመለከት አድርገውናል፡፡

መንግሥት በራሱ አመራሮች በዜጎቹ ላይ የተፈጸመውን ግፍና በደል በራሱ ሚዲያ ለህዝቡ እንዲተላለፍ ማድረጉም አዲስ የለውጥ ምዕራፍ ስለመጀመሩ አንድ ማረጋገጫ ነው፡፡ ሚዲያና የኮሚኒኬሽን ዘርፉ በእንደዚህ አይነት ኢሕገ-መንግሥታዊ ተግባር ላይ የተሰማሩ ኃይሎች እራሳቸው መታረም እንዲችሉ ማስተማር ይኖርበታል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ሚዲያችን ከዕለት ወደ ዕለት እያሳየ ላለው ለውጥ ሳናደንቅ አናልፍም ፡፡

ሚዲያው በፌደራል ማረሚያ ቤቶች የነበረውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በከፊል አሳየን እንጂ በክልል ማረሚያ ቤቶች ያለውም ሁኔታ ከዚህ የተለየ አይሆንም፡፡ ሚዲያ የፌደራል ማረሚያ ቤቶችን ታራሚዎችን አያያዝ በተመለከተ ልክ ለህዝብ እንዳጋለጠው በክልል ደረጃም ወረዶ ለህዝብ ይፋ ማድረግ ይኖርበታል። በተለይም በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በትገራይና በደቡብ ከፍተኛ የሆነ የለውጥ ፈላጊ ሀይል ስላለ ብዙ ወጣቶች ለእስር ተዳርገዋል። ስለሆነም የተከሰሱበት ወንጀልና በምን አይነት ሁኔታ እንደሚገኙ በጥብቅ መመርመርና መከታተል ያስፈልጋል፡፡ እነዲሁም ከፌደራል ማረሚያ ቤቶች ቀጥሎ በእነዚህ ክልሎች ውሥጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ታራሚዎች በማረሚያ ቤቶች ስለሚገኙ ስለ ሰብአዊ መብት አያያዝ በተመለከተ በጥልቅ መፈተሽ አለበት፡፡ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች የራሳቸውን ችግር በመቅረፍ ለክልል ማረሚያ ቤቶች አርያ መሆን አለባቸው፡፡

እንዲህ ዓይነት የኅብረተሰብ ብሶቶች የሚነሱባቸው ጉዳዮችን እየነቀሱ ማቅረብን ሚዲያው ትኩረት ሰጥቶ መሥራት የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህ የመብት ጥሰቶች ቀደም ሲል በሚዲያ የመዳሰስ እድል አግኝተው ቢሆን ኖሮ ጉዳቶችን በእንጭጩ መቅጨት በተቻለ ነበር፡፡    

ሚዲያ አንዱ አላማው ማስተማር ነው፡፡ ስለሆነም ይህ በዜጎች ላይ የተፈጸመው አካላዊና ስነልቦናዊ የመብት ጥሰት ትክክል ያለመሆኑን ለኅብረተሰቡ ማስተማርና በቀጣይም ስህተቱ እንዳይደገም ግንዛቤ ማስጨበጡ ተገቢ ነው፡፡ በእርግጥ ስሜት ቀስቃሽ የሆኑና ግጭቶችን ሊያራግቡ የሚችሉ ዘገባዎችን ማቅረብ ሌላ ነገርን አስከትሎ ቀውስ ሊመጣ ስለሚችል ሚዲያዎች ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡  

መገናኛ ብዙኃን የአገሪቱን ሕገ-መንግሥትና የፕሬስ ሕጉን መሰረት በመድረግ አሁን የተፈጠረውን ሰፊ የፖለቲካ ምህዳር ተጠቅመው የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲጠበቁ መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ አዲሱን የለውጥ እንቅስቃሴ ተከትሎ ብዙ ታራሚዎች ምህረት ተደርጎላቸዋል፡፡ ይህም መንግስት ለዴሞከራሲና ለስብአዊ መብት ያለውን ቁርጠኛ አቋም የሚያነፀባርቅ ነው፡፡ ምንም እንኳን ብዙ ታራሚዎች ይቅርታ ቢደረግላቸውም አሁንም በዘር፣ በቀለም፣ በሀይማኖትና በፖሊቲካ ልዩነት የታሰሩ አያሌ ወጣቶች አሉ፡፡ ስለሆነም መንግስት ማረሚያ ቤቶችን በአግባቡ በመመርመር ይህንን እየታየ ያለውን አሰቃቂ የታራሚዎች አያያዝ ማሻሻል ይኖርበታል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy