ማን ይምራው?
አባ መላኩ
ዘላቂ ሠላምን እውን ማድረግ የሚቻለው በህዝብ ንቁ ተሳትፎ ነው። ለአገሪቱ ሠላም መረጋገጥ መሠረቱ ህዝቡ ነውና። የአንድ አገር ሠላም የሚጠበቀውም በህዝብ ንቁ ተሳትፎ ነው። ስለ ሠላም በሚደረጉ ማናቸውም ክንዋኔዎች ውስጥ የህዝቡ ተሳትፎ ግንባር ቀደሙን ሥፍራ ይይዛል።
የአገሪቱንና የህዝቦቿን ሠላምና መረጋጋት የማይሹ ጥቂት ቡድኖች በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ አንዳንድ አካባቢዎች እየፈፀሙ ያሉት ተግባር ከህዝቡ የተሰወረ አይደለም። ህዝብ ሁሌም ከማንኛውም ተግባር ቀድሞ ግራና ቀኙን ያያል። ህጋዊ አካሄዶችን ያጤናል ይፈትሻል። አሉታዊና አዎንታዊ ጎኖቹን ይመረምራል። ከዚያም ሚዛናዊ ውሣኔን ይሰጣል። የቆየ ልማዱም ይኸው ነው።
ከኢትዮጵያ ህዝብ በላይ ስለሠላም የዘመረ፣ ስለሠላም የሰበከ፣ ስለሠላም ያቀነቀነ አለ ቢባል እሞግታለሁ። የኢትዮጵያ ህዝብ ስለሠላም እጅግ ብዙ ዋጋ ከፍሏል። መንግሥት ሠላምን በተመለከተ አንድ ርምጃ በወሰደ ቁጥር ህዝቡ የጉዳዩ ባለቤት ሆኖ ቀናኢነቱን በተግባር አረጋግጧል። ሕዝቡ በየአካባቢው የሠላሙ ባለቤት ሆኖ የሚንቀሳቀሰውም ለዚሁ ነው።
ወደኋላ መለስ ብሎ ለተመለከተው በተፈጠረው ግጭቶች የሰዎች ህይወት ጠፍቷል። ዜጎች ተፈናቅለዋል። ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት ጉዳት ደርሷል። ዜጎች ከቦታ ቦታ በነፃነት መንቀሳቀስ አልቻሉም፡፡ የመንግሥትና የሕዝብ ተሽከርካሪዎች ተቃጥለዋል፡፡ የኢንቨስትመንት ተቋማትም ከጥቅም ውጪ ሆነዋል፡፡ የማይረሳ መጥፎ ትውስታ ነው።
ህዝብ ከግጭት ቀስቃሽ ቡድኖች ጎን መቆም የለበትም። ይህንኑም ደጋግሞ አረጋግጧል። አጥፊዎችን ማጋለጥ ይኖርበታል። በአጥፊዎች ላይ የርምት ርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል። እንዲወሰድባቸው ሙሉ አቅሙን ተጠቅሟል። ታዲያ እዚህ ላይ ህዝቡ የማይተካ ሚና አለው። አድናቆት የሚቸረውም ለዚሁ ነው። ለዚህም ነው ህዝብ ግንባር ቀደም ዋነኛ ተዋናይ ነው የሚባለው።
ህዝብ በማንኛውም መመዘኛ ሠላሙን ተፃርሮ አይቆምም። ለሠላሙ መረጋገጥ ፀረ ሠላም ቡድኖችን በማጋለጥ ለህግ እንዲቀርቡ ያደርጋል። አጥፊ ቡድኖች ከድርጊታቸው ተቆጥበው ወደ ሠላማዊ ህይወት ለመመለስ ጽኑ ፍላጎት ሲያሳዩ ህዝብ ድጋፍና እገዛውን ይቸራቸዋል። ይህ ተግባር ኅብረተሰቡ ለዘላቂ ሠላም የቱን ያህል የፀና አቋም እንዳለው ማሣያ ነው።
ሕዝቡ የወደፊት ዕጣ ፈንታውን የሚወስነው አገሪቱ የምትከተለው የመደመር፣ የአንድነትና የፍቅር መስመር አጥብቆ በመያዝ ነው። የሠላምን ዋጋ ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ዘወትር ከሠላም ወዳድ ኃይሎች ጎን ይቆማል።
ዛሬ ህዝቡ በየቀየው ላለው የሠላም ሁኔታ ዋነኛ መሠረት ሆኗል። በየአካባቢው የሚፈጠሩ አለመረጋጋቶች መልሰው ራሱኑ እንደሚጎዱት ጠንቅቆ ይገነዘባል። አሁን ለሠላሙ መረጋገጥ ይበልጥ መትጋትን መርጧል። ሠላምን የሚያጎድሉ፣ ልማትን የሚያደናቅፉና ግጭትን የሚያባብሱ መስመሮችን ጠራርጎ ይጥላል። ሕዝቡ በሁሉም አቅጣጫ ከልማቱ በየደረጃው ተጠቃሚ ሆኖ ተፈላጊውን የዕድገት ራዕይ ሰንቆ እየተጓዘ ነው።
የተከሰተውን ግጭት ለማርገብ ሁከት ለመቋቋም ሕዝቡ በባለቤትነት ስሜት የከፈለው መስዋዕትነት በቀላሉ አይታይም። ይህ የሕዝቡ ስሜት የመነጨው የሠላም ዋጋ በምንም ሊለካ እንደማይችል ካለፉት ተጨባጭ ሂደቶች ስለተማረ ነው።
በእርግም ከተግባር የበለጠ ትምህርት ቤት የለም። ሕዝቡ የሠላሙ ዘብ ነው። በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ አካባቢዎች ግጭቶቹን ተከትሎ የህዝቡን ሠላምና ፀጥታ ለማረጋገጥና ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ከአደጋ ለመከላከል ሲባል ኅብረተሰቡ ከመንግሥት ጎን ቆሞ ተግባራዊ ምላሽ እየሰጠ ይገኛል። ይህ አበረታች ውሣኔና ርምጃ ነው። በአገሪቱ ላይ ተደቅኖ የነበረው ስጋት እንዲቀለበስ ለማድረግ በተደረገው ርብርብ የህዝቡ ሚና ተዘርዝሮ አያልቅም።
ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰርቶ መለወጥና ማደግ እንደሚቻል ጠንቅቆ የሚያውቅ ሕዝብ ተፈጥሯል። መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ስለሠላሙ መስፈን ድምጹን ከፍ አድርጎ ይዘምራል። ሠላምና ህዝብ ሊነጣጠሉ አይገባም። በየአካባቢውም የሠላሙ ዋስና ጠበቃ ሆኖ ይንቀሳቀሳል። ይህ የነበረና ያለ አኩሪ ተግባሩ ወደፊትም ተጠናክሮ ይቀጥላል።
ይህ ሠላም ወዳድ ህዝብ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ሠላምን በማወክ ተግባር ላይ የተገኙትን በመገሰፅ፣ ለሠላም እንዲሰሩና የሠላምን እሴት እንዲያውቁ ይጥራል።
በህዝቡ የባለቤትነት መንፈስ የሚዘወር ሠላም እስካለ ድረስ፤ ሰርቶ መለወጥና ማደግ ይቻላል። ህዝቡም ይህንኑ ጠንቅቆ ያውቃል። ለዚህም ነው ህዝቡ በየአካባቢው የሠላሙ ዋስና ጠበቃ ሆኖ እየሰራ የሚገኘው። ይህ በጎ ምግባሩም ተጠናክሮ ይቀጥላል። የሠላም ባለቤትነትን ከህዝብ በላይ ማንም ሊመራው አይችልምና።