Artcles

ምክንያታዊነት እና ውጤቱ

By Admin

July 16, 2018

ምክንያታዊነት እና ውጤቱ

                                                         ይሁን ታፈረ

የህዝቦችን  ፍላጎት መሰረት ያደረገውን የለውጥ ሂደት ለማደናቀፍ በየአካባቢው የሚደረጉ መፍጨርጨሮች ተገቢ ብቻ ሳይሆኑ ምንም ዓይነት ትርጉም የሌላቸው ናቸው። በአሁኑ ሰዓት ህዝብና መንግስት እጅና ጓንት ሆነው እየሰሩ በመሆናቸው መፍጨርጨሮቹ የትም የሚደርሱ አይደሉም። ሰሞኑን በምዕራብ ኦሮሚያ የተከሰተውን ግጭት የአካባቢው ወጣቶች (ቄሮዎች) ከክልሉ መንግስት ጋር በመተባበር በወሰዱት እርምጃ አካባቢው በፍጥነት ወደ መረጋጋት እንዲመለስ አስችለዋል።

በዚህም ወጣቱ በአካባቢው በተከሰተው ግጭት የተዘጉ መንገዶች እንዲከፈቱ በማድረግ እንዲሁም ሁከት ለመፍጠር ሲሯሯጡ የነበሩ አካላትን ለይቶ ለህግ አሳልፎ የመስጠት ስራዎችን አከናውነዋል። ይህም ወጣቱን ምክንያታዊ እንዲሆን ማድረግ ከተቻለ፣ ማንኛውንም ነገር መፍታት እንደሚቻል የሚያረጋግጥ ክንዋኔ መሆኑን ያረጋገጠ ነው። ምክንያታዊነት አገርንና ህዝብን ከማናቸውም እኩይ ተግባሮች መጠበቅ የሚያስችል አስተሳሰብ መሆኑንም ያስገነዝበናል።

እንደሚታወቀው ሁሉ በህግ ካለተደነገገ በስተቀር በየትኛውም ሀገር ውስጥ የሚኖር ዜጋ የህግ የበላይነትን በመፃረር እንዳሻው ሊኖር አይችልም። የዜጎች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በህግና ሥርዓት የሚመራ ካልሆነ የትኛውም ወገን የመኖር ዋስትና ሊኖረው አይችልም። የመኖር ዋስትና በሌለበት ሀገር ውስጥ ደግሞ ሰላምና መረጋጋት ይጠፋና እንደ ሰው ለመንቀሳቀስ የማይቻልበት ደረጃ ላይ የሚደረስ ይደረሳል።

መንግስት ባለበት ሀገር ውስጥ ማንም ሰው ከህግ በላይ ሊሆን አይችልም። በመሆኑም መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር እየደረጋቸው ከመጣው መንገድ መውጣት የለበትም።

መንግስት መብትም፣ ኃላፊነትም ሆነ ግዴታ ያለበት አካል በመሆኑ በህጉ አግባብ መሰረት ተጠርጣሪዎችን ህግ ፊት በማቅረብ ተገቢውን ትምህርት የሚያገኙበትን ሁኔታ በመፍጠር የተጎጂዎችን እምባ ማበስ ይኖርበታል። ይህን ካላደረገ ህዝቡንም ይሁን በህዝቡ የተመሰረተውን ስርዓት በአግባቡ ሊጠብቅ አይችልም።

ይህ የመንግስት የህግን ልዕልና የማረጋገጥ እርምጃ በህዝቦች ደም ስልጣን ላይ ለመውጣት ለሚሹ አሸባሪዎች፣ ፀረ-ሰላም ኃይሎችና ፅንፈኞች፤ እዚህ ሀገር ውስጥ እነርሱ የሚመኙት ዓይነት ምህዳርና ህዝብ አለመኖሩን እንዲገነዘቡ ያስችላል።

እንዲሁም አንዳንድ ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎችም የዛሬዋ ኢትዮጵያ ህዘቦች መቻቻልን መፍጠር የቻሉ እንዲሁም ዴሞክራሲያቸውን ስር እንዲሰድ ለማድረግ የህግ የበላይነትን የሚያፀና ሥርዓትን ዕውን በማድረግ ላይ የሚገኙ እንጂ፤ በደማቸው ፍላፃነትና በአጥንታቸው ወጋግራነት የገነቧት ሀገራቸው እነርሱ እንደሚመኙት ዓይነት በጩኸት፣ በህገ-ወጥነትና በሴራ የምትናጋ አለመሆኗን እንዲያውቁ ያደርጋል።

የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝቦች የለውጥ ቀልባሾችን፣ አሸባሪዎችንና ሴረኞችን ሊፈጥሩ የሚችሉትን ችግሮች በሰከነና ብልሃት በተሞላበት ሁኔታ ፍትሐዊነትንና የህግ የበላይነትን እያረጋገጡ እንዲሁም ለሚፈፀምባቸው ማናቸውም የትንኮሳ ተግባራት ተገቢውን ምላሽ እየሰጡ ይጓዛሉ። የትኛውም መፍጨርጨር ይህን ሁኔታ ሊቋቋመው አይችልም።

ዛሬ አገራችን ውስጥ ምክንያታዊነት እየጎለበተ መሆኑን ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው የምዕራብ ኦሮሚያ ወጣቶች ያከናወኑት ድርጊት ማሳያ ነው። እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ለህግ የበላይነት የሚኖረው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። ወጣቱ አካባቢውን ሁከት እያነፈነፉ ህግን ለመጣስ ከሚሹ አካላት እንዲጠብቅ ያደርገዋል። የሰላሙ ጠባቂ ራሱ ሆኖም የለውጥ አደናቃፊዎችን አደብ ሊያስገዛቸው ይችላል።

ስርዓቱ የዛሬው ወጣት ነው። ወጣቱ የስርዓቱን ባለቤት ነው። የዛሬው ወጣት (ቄሮ) በማንነቱም ይሁን በኑሮው አንገቱን ደፍቶ የሚሄድ አይደለም። በትግሉ ለውጥ ማምጣት የቻለ ነው። በዚህም ዛሬ ቀና ብሎ በማንነቱ በመኩራት እንዲሁም በአገሪቱ በመመዝገብ ላይ ከሚገኘው ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት መጠን ተጠቃሚ ሆኖ ወደ አዲስ የለውጥ ምዕራፍ እየገሰገሰ ነው።

ምክንያታዊ አስተሳሰብንም እየተላበሰ ነው። ችግሮች ቢኖሩም በምክንያታዊ አስተሳሰብ እንደሚፈቱ ያውቃል። ይህ አቋሙ ለውጥ አደናቃፊዎችን ከህግ ፊት ሲያቀርባቸው ታይቷል። ችግሮቹን በግልፅ ውይይት በማሳየትና የሚፈቱበትን አግባብ በማመለላከት ጭር የመፍትሄ አካል እየሆነ ነው።

ባለፉት ዓመታት ውስጥ ኢኮኖሚው ቢያድግም መጠነ ሰፊው ድህነት ከፍተኛ ስለነበር ሁሉንም ማዳረስ አልቻለም። ሆኖም በዶክተር አብይ መሪነት ለውጦች እየተመዘገቡ መሆናቸውን ወጣቱ ያውቃል። ይህ የለውጥና የነጻነት አውድ በሂደት እንደሚጠቅመውም ይገነዘባል።

በምክንያታዊነት የሚያምነው ወጣት ባለፉት ዓመታት የሚገባውን ጥቅም ባያገኝም፣ በአሁኑ ወቅት በራሱ ትግል የፈጠረው ለውጥ እንደሚጠቅመው ይገነዘባል። መንግስትና ህዝቡ በድህነት ላይ በከፈቱት ዘመቻ በዋነኛነት ተጠቃሚ የሚያደርገው ይህንኑ ወጣት ነው።

መንግስት ለ2011 ዓመት የያዘው በጀት ድህነት ተኮር የሆነው በዋነኛነት ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል እንዲጠቀም ከማሰብ ነው። ሆኖም ይህን ጥቅሙን የሚጋፉ ጥቅማቸው የተነካባቸው አካላት ችግር ሊፈጥሩና ለየለውጡን አቅጣጫ ለማሳት ጥረት ሊያደርጉ ስለሚችሉ በየአካባቢው ዘብ ሆኖ መቆም አለበት።

ለውጡን እየመራው ያለው መንግስት የሚፈጠሩ ማናቸውንም ችግሮች የመፍታት አቅምም ይሁን ብቃቱ አለው። ወጣቶች ያሉባቸውን ጊዜያዊ ችግሮችንም ይፈታል። ወጣቱ በሚዛናዊ አስተሳሰቡ መንግስት ያለበትን ችግር እንደሚፈታ በመገንዘብ መጪው ጊዜ የእርሱ መሆኑን ማወቅ አለበት።

ወጣቱ አሁን በያዘው ህግና ስርዓትን በማስከበር ሃላፊነቱ መቀጠል አለበት። በማንኛውም ወገን መደናገር አይኖርበትም። ለውጡ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ብቻ ሳይሆን ነጻነትንም አብሮ ያጎናጸፈ ነው። በወጣቱ ትግል የተገኘውን ነፃነት ተጠቅመው ሌላ አጀንዳ የሚዘረጉ አደናቃፊዎችን በተጠናከረ ሁኔታ ሊቃወማቸው ይገባል። ያም ሆኖ ወጣቱ ስርዓቱ የእርሱ እንደ መሆኑ መጠን ሊጠብቀው ይገባል።

በተለያዩ ጊዜያት ብቅ ጥልም እያሉ በየአካባቢው የሚታዩ ግጭቶች መነሻቸውና መድረሻቸው ስርዓቱን በውል ካለመገንዘብ አሊያም የግል ጥቅማቸውን ለማሳደድ የሚሹ አካላት ናቸው። እነዚህን አካላት ዓላማቸው በደም የተገኘውን ለውጥና ነጻነት ማደናቀፍ ነው። ታዲያ እነዚህን አካላት እንደ አመጣጣቸው በመመለስ አደብ ለማስገዛት መንግስት ማናቸውንም ተግባሮች እየከወነ ነው። ወጣቱም የያዘውን ምክንያታዊ አስተሳሰብ በማጠናከር ለውጡን የመጠበቅ ሃላፊነት አለበት።

የለውጡን አቅጣጫ ለማሳከር የመፍጨረጨሩ አካላት የራሳቸውን ድብቅ አጀንዳ ለማራመድ ሲሉ በተለያዩ አካባቢዎች ችግር ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ ናቸው። ስለሆነም በአሁኑ ሰዓት እያደረገ እንዳለው በየአካባቢው የለውጥ አደናቃፊዎችን ለህግ አሳልፎ በመስጠት ለውጡን መጠበቅ ይኖርበታል። በምዕራብ ኦሮሚያ በወጣቱ ዘንድ የታየው ምክንያታዊ አስተሳሰብ ምን ውጤት እንዳመጣ ማረጋገጫ ነውና።