Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሠላምና የህግ የበላይነት መከበር ከትናንቱ ዛሬ

0 394

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሠላምና የህግ የበላይነት መከበር ከትናንቱ ዛሬ

ሞገስ ተ

ሠላም ሊተመንበት የሚችል የዋጋ ልኬት የለውም። ያለ ሠላም ልማት፣ ዕድገት፣ አብሮነት፣ ወጥቶ መግባት፣ መማርና ነግዶ ማትረፍ ሊታሰቡ አይችሉም። ኢትዮጵያውያን ለሠላም የሚሰጡት ቦታ እጅግ ከፍተኛ ነው። ኢትዮጵያውያን አገር አቋርጦ ድንበር ተሻግሮ የመጣውን የኢጣልያ ጦር በህይወትና በንብረታቸው ዋጋ ከፍለዋል። ሀገርን ለባዕዳን አሳልፈን አንሰጥም በማለት በዘመናዊ መሳሪያ ታጥቆ የመጣውን ፋሽስት አዋርደው መልሰዋል። በዚህም የተረጋጋ ሰላማቸውን በኩራትና በምሳሌነት አጣጥመዋል።

የሠላም እጦት ሞትን፣ የአካል መጉደልን፣ የንብረት መውደምን፣ ስደትንና ረሃብን በአጠቃላይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስን አስከትሎ የሚያልፍ መሆኑን በቅርቡ በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች ተከስቶ የነበረውን ግጭት ማስታወስ በቂ ምሳሌ ነው፡፡

ቤተሰብ፣ ህብረተሰብ፣ ሀገርና ህዝብ ያለ ሠላም በፅኑ መሠረት ፀንተው ሊቆሙ አይችሉም። ምክንያቱም የሁሉም ነገር መሠረት የሚጀመረው ከሠላም፣ ከፍቅርና ከአንድነት ነውና የሠላም ጡብ ማኖር ለሁሉም ነገር ወሳኝ ነው።

የአገሪቱ መሠረት ሠላምና የህዝቦቿ አንድነት ነው። ይህ የህዝቦች አንድነት የሚፀናው ደግሞ ከመሰረቱ ሠላምና የህግ የበላይነት ሲሰፍን ነው። ያለ መሠረት መፅናት፣ ያለ መሠረት ማደግ አይቻልም። የሠላም መሠረቱ ከተናደ ትልቅ ሀገር መሆን፣ መደመር፣ መበልፀግ ወይም መግዘፍ አንችልም። ምክንያቱም መሰረታችንን ካላፀናን መውደቅና መፈረካከስ የማይቀር መሆኑ ግልፅ ነው። ስለዚህ ይህንን የሁሉ ነገር መሠረት የሆነውን  ሠላምና የህግ የበላይነት ፀንቶ እንዲቆምና እንዳይሸረሸር መጠበቅ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው።

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ እየታየ ያለውን የለውጥ እንቅስቃሴ ተከትሎ አልፎ አልፎ ግጭቶች ሲከሰቱ ይስተዋላል። ለእነዚህ እንቅፋቶችም መንግሥት አስፈላጊውን እርምት እየሰጠ ይገኛል። ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የዴሞክራሲና የሠላም ርዕዮት ዓለም ውስጥ በሚያራምደው የሠላምና የፍቅር ዕሴት ውስጥ ሠላምና የህግ የበላይነት መስፈን የእግር እሳት የሆነባቸው ፀረ ሠላም ሃይሎች አሉ። በዚህም እኩይ ተግባራቸው የህዝብን አንድነትና የመደመር ዕሴት ለመቀልበስ በቅርቡ  በመስቀል አደባባይ በተደረገው የድጋፍና የመደመር ሰልፍ ላይ አንደመርም እንቀነስ ሲሉ ታይተዋል። ይህ የመቀነስ ዕራያቸውም በሠላም ወዳዱ ህዝብ ከሽፏል።

ምክንያቱም በአራቱም ማዕዘናት ያሉ ህዝቦች የሚፈልጉትን የሠላም፣ የዲሞክራሲና የህግ የበላይነት መስፈን ለሁለንተናዊ ለውጥ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው፡፡ ለዚህም ነው ህብረተሰቡ ለውጡን ከጫፍ እስከ ጫፍ ሠላምን እያስተጋባ ያለው፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ሠላም፣ አንድነት፣ ይቅርባይነትንና መደመርን ትተው የህዝቡ ሠላም ሰላማቸውን የነሳቸው ሃይሎች ህግን በመጣስ በአንድነቱና በአብሮነቱ ላይ ውሃ ለመቸለስ የሚያደርጉት ሙከራ ጠቅላይ ሚኒስቴር ደክተር አብይ እንዳሉት “አልተሳካላቸውም አይሳካላቸውምም”

ለህግ የበላይነት መስፈን ህብረተስቡ ከማንም በላይ በወቅቱ ግንባር ቀደም ተዋናይ መሆኑን ያሳየበት ጊዜም ነበር። እያንዳንዱን ነገር በጥንቃቄና በሰከነ መልኩ በመመልከት ወንጀለኛን በመያዝ ለህግ በማቅረብ ደረጃ የላቀ ተሳትፎ  አድርጓል። በዚህም ሊመሰገን ይገባዋል። ከዚህ ባለፈም በቀጣየነት ለሰላሙ ዘብ መቆም እንዳለበት ይታመናል።

አገራዊ መግባባትን ለመፍጠርና ፍቅርን ለማጠንከር መንግሥት ሁኔታዎችን ሁሉ በይቅርታ ማለፍን መረጠ እንጂ የህግ የበላይነት መስፈንን ለድርድር አያቀርብም፡፡ ምክንያቱም የህግ የበላይነት ሲከበር ነው ህዝብም የሠላም አየር መተንፈስ የሚችለው፡፡ ይህ የፍቅር፣ የሠላም፣ የአብሮነትና የመደመር እሴቶቻችን ከኢትዮጵያዊነት ባህላችን ጋር ተዳምረው የኢትዮጵያዊነት ባህላችን የበለጠ እንዲደምቅ አስችለውታል።

በመሆኑም መንግሥት በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ሠላም፣ ይቅርታና መደመርን ለማስፈን ቀን ከሌት እየተጋ ይገኛል። ይህም በዜጎች ላይ የተስፋ ጭላንጭል እንዲያጭር ከማድረጉም በላይ ሠላም፣ ይቅርታና ፍቅር ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በአገሪቱ እየተዘመረ ነው።

መንግሥትም ሠላምና የህግ የበላይነት ማስፈን ዋና አላማው በመሆኑ በጥፋት ሃይሎች ላይ የማያዳግም ህጋዊ የእርምጃ እርምት ለመስጠት እየሰራ ይገኛል፡፡  የሰው ልጅ ፍቅር ሊገዛ የሚችለው በፍቅር ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም መጠላለፉ፣ መቃቃሩ፣ መፋጨትና መጋጨቱን አይተነዋል ለማንም አልጠቀመም። ለዚህም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እንዳሉት ማሰር፣ ማባረርና መግደል ቀላል ናቸው፤ ነገር ግን አገራዊ መግባባትን አያመጡም፡፡ አገራዊ መግባባትን ሊያመጣ የሚችለው ፍቅር፣ አንድነትና መደመር ስለሆነ በዚህ የተቃኘ የመልካም ሰብዕና ባለቤት መሆን ስንችን የድምር ውጤታችን ማሳያ ሆኖ ልናገኘው የምንችለው የጋራ እድገትና ለውጥ ነው። ለመለወጥ ደግሞ ከልብ የመነጨ የፍቅርና የአንድነት መንፈስ በቂ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች መኖሪያ ትልቅ ሀገር እንደመሆኗ ወደ አገራዊ መግባባት ሊያመጡን የሚችሉ መቻቻል፣ ይቅር ባይነትና ሆደ ሰፊነትን ልንላበስ ይገባል። ምክንያቱም ፍቅር ሁሉንም ነገር ያሸንፋልና፡፡ የማይቻል የሚመስለውን በመደመር በይቻላል መንፈስ ማድረግ ይቻላል፡፡ ስለዚህ ለአንድ አገር ሁለንተናዊ ዕድገት መቻቻልና መከባበር ሊተካ የማይችል ሚና ይጫዎታሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩም ከበዓለ ሲመታቸው ጀምረው አበክረው የሚያወሱት ስለአንድነት፣ ስለአብሮነት፣ ስለይቀር ባይነት ነው፡፡ ምክንያቱም ያለ ፍቅር ሁሉም ነገር ባዶ ስለሚሆን በፍቅር መተሳሰር ግን ዋጋው ትልቅ በመሆኑ ነው። ኢትዮጵያም በተጎናፀፈችው የብሔር ስብጥር የዓለም የቱሪስት መዳረሻ ሆና ትገኛለች፡፡ የብሄር ብሔረሰቦች እኩልነትም ብዛህነትን በማስተናገድ ረገድ ልዩ አድርጓታል። ህዝቦቿም ለዘመናት አብረው ኑረዋል ለወደፊቱም ይኖራሉ፡፡ የብሔር ልዩነት ውበት እንጂ ልዩነት ጥላቻና ቅራኔ መፍጠር የለበትም ይልቁንም አንዱ ለአንዱ ሞገስና ፀጋ አጎናፅፏት ይገኛል፡፡

ከዚህም ከዚያም የሚፈጠሩ ትንንሽ ግጭቶች ለአጠቃላይ ኢትዮጵያ አለመረጋጋት ማሳያ ተደርገው መቅረብ የለባቸውም፡፡ ምክንያቱም ግጭቶቹ መሠረት የሌላቸውና ማንኛውንም ብሄርም ሆነ ሃይማኖት የማይወክሉ ግለሰባዊ  ስሜት የሚያንፀባርቁ ናቸው፡፡ በመሆኑም ታይተው በቶሎ የሚጠፉ ስለሆኑ እንኳን ለአገር አለመረጋጋት ለተከሰቱበት አካባቢም እምብዛም ተፅዕኖ የላቸውም፡፡

የፌዴራል ሥርዓቱም ግጭቶች እንደይከሰቱ ተበሎ ሥርዓቱን ጠበቆ የተዘረጋ ነው፡፡ በመሆኑም ጥቃቅን ግጭቶች እንጂ ትላልቅ ግጭቶች ሲከሰቱ አይስተዋልም፡፡ ስለሆነም እነዚህ ትንንሽ ግጭቶች ነገም ከነገ ወዲያም እንዲህ ያሉ ነገሮች መኖራቸው አይቀርም፡፡ ስለዚህ እነዚህ ግጭቶች በሚከሰቱበት ወቅት ህብረተሰቡ ከመንግሥት ጠባቂ ሳይሆን በራሱ የሚፈታበትን መንገድ በማበጀት ዘላቂነት ያለው ሠላምና የህግ የበላይነት በማስፈን በዕድገት ጎዳና መራመድ መቻል ይገበዋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy