CURRENT

ሥራ ላይ ነን!

By Admin

July 16, 2018

…ሥራ ላይ ነን!

ወንድይራድ ኃብተየስ

 

ኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓቷን ለማጎልበት ጠንክራ በመሥራት ላይ ነች። የሕዝቦቿን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ለማስጠበቅ በርትታ እየታተረች ነው። በርካታ ሕዝቦቿ በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ ጠንካራ አንድነት አጎልብተዋል። አዎ! ባለፉት ጥቂት ዓመታት አንዳንድ አፍራሽ ኃይሎች የፈጠራ ወሬያቸውን ቢነዙም እኛ ኢትዮጵያዊያን ግን የአገራችንን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በማጎልበት ሥራ ላይ ነን።

 

ኢትዮጵያ በአካባቢው ካሉ አገሮች በአጠቃላይ ግብርና ምርት ከፍተኛውን ቁጥር ከመያዟ ባሻገር በዘንድሮው የመኸር ምርት በዋና ዋና ምርቶች ብቻ ከ320 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ሰብል በመሰብሰብ ላይ ነው። የግብርናው ዘርፍ የኢትዮጵያ ዋነኛ ሞተር ነው። አዎ! ማንም የፈለገውን ቢያወራ እኛ ኢትዮጵያዊያን የግብርና ምርታችንን በማዘመን ሥራ ላይ ነን።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተፋሰሱ አገራት መካከል መተማመንን እያጎለበተ መጥቷል። ይህ ፕሮጀክት በኢትዮጵያዊያን ዘንድ የይቻላል መንፈስ እንዲጎለብት አድርጓል። ሕዝቦች በመተባበር ከድህነት መውጣት እንደሚችሉ ተስፋ ሰንቀዋል።  የለውጥ መንገዱን ተያይዘውታል። በመሆኑም የህዳሴው ግድብ ለታዳጊ አገራት ትልቅ ተምሣሌት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። አዎ! ማንም የፈለገውን ቢያወራ እኛ ኢትዮጵያዊያን ለአገራችን ብቻ ሳይሆን ለምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ጭምር የሚተርፍ እንደህዳሴው ግድብ ያሉ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ላይ ነን።  

 

የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በማንኛውም አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አለመግባትና የአገሮችን የጋራ ተጠቃሚነትንመ መሠረት ያደረገ ነው። ኢትዮጵያ በምትከተለው ጠንካራ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ዛሬ ላይ በአፍሪካ ሆነ  በዓለም አቀፍ መድረክ ተሰሚነቷ እንዲጨምር አድርጓታል። ከዚህም ጋር ተያይዞ በአገሮች መካከል ግጭት ወይም ያለመግባባት ሲከሰት የኢትዮጵያ አደራዳሪነት ወይም ሸምጋይነት ግንባር ቀደም ተመራጭ እየሆኑ መጥቷል።

 

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ያላት ተሰሚነት፣ በአፍሪካ ህብረት ያላት የመሪነት ሚና እንዲሁም በኢጋድና በሌሎች ትላልቅ መድረኮች ተደማጭነቷ እየጨመረ መጥቷል። አዎ! ማንም የፈለገውን ቢያወራ እኛ ኢትዮጵያዊያን አገራችን በዓለም አቀፍ መድረኮች ያላት ተሰሚነት እንዲጎለብት በመሥራት ላይ ነን።   

 

በተመሳሳይ ኢትዮጵያ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት በሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ሶማሊያ፣ ላይቤሪያ፣ ሱዳን፣ ዳርፉር፣ አብዬ፣ በደቡብ ሱዳን፣ የሠላም ማስከበር ሥራዎች ላይ ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ ነች። የኢትዮጵያ ህዝባዊ፣ በዲሲፕሊን የታነፀና እጅግ ጠንካራ የመከላከያ ሠራዊት መገንባት ችላለች። ኢትዮጵያዊያን ሠላም አስከባሪ ኃይሎችም በተሰማሩበት አገር ሁሉ በህዝብ የተወደዱና ምሥጋና የተቸራቸው ናቸው። አዎ! ማንም የፈለገውን ቢያወራ እኛ ኢትዮጵያዊያን በጠንካራና በዲሲፕሊን በታነፀው ሠራዊታችን የአህጉሪቱን ሠላም በማስከበር ሥራ ላይ ነን።   

 

ኢትዮጵያ ዘመናዊ የመንገድ ግንባታ፣ የባቡር መስመር ዝርጋታ፣ የአየር በረራ መስመሮች ማስፋፋት፣ የኃይል አቅርቦት በአጠቃላይ የተለያዩ የመሠረተ ልማት አውታሮች ግንባታ በማካሄድ የአካባቢው አገራት ሕዝቦችን ግንኙነት ከፍተኛ ወዳለ ደረጃ እንዲደርስ በማድረግ ላይ ነች። ይህም ኢትዮጵያ የምትከተለው ፖሊሲ የአካባቢው አገሮች በምጣኔ ሀብት ጥቅም እንዲተሳሰሩ ለማድረግና የቀጠናው ሠላም ዘለቄታዊነት እንዲኖረው የምታደርገውን ጥረት ያሳያል።

 

እነዚህ ታላላቅ መሠረተ ልማቶች የቀጠናውን አገሮች ፖለቲካል፣ ምጣኔ ሀብትና ማህበራዊ መስተጋብሮች ያጠናክራሉ። አዎ! ማንም የፈለገውን ቢያወራ እኛ ኢትዮጵያዊያን አፍሪካዊያንን በተለይ በቀንዱ አካባቢ የሚገኙ አገሮችን በመሠረተ ልማት በማያያዝ ሕዝቦች በጋራ ጥቅም እንዲተሳሰሩ በማድረግ በቀጠናው ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን ጠንክረን በመሥራት ላይ ነን።   

መንግሥት የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት የመዋቅር ሽግግር እንዲያደርግ እንዲሁም ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችሉ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ነው። በአገሪቱ በአሁኑ ወቅት 11 የሚደርሱ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚገነቡበት ሥፍራዎች በመምረጥ ወደ ግንባታ ተሸጋግረዋል። ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ከተመረጡ አካባቢዎች አዲስ አባባ ሦስት ክላስተሮች ማለትም ለሚ አንድና ሁለት እንዲሁም ቂሊንጦ አካባቢ፣ ሐዋሳ፣ አዳማ፣ ድሬዳዋ፣ ኮምቦልቻ፣ መቀሌ፣ ባህር ዳር፣ ጅማና ደብረብረሃን ተጠቃሾች ናቸው።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ የከተሞችን የተቀናጀ ዕድገት ያፋጥናሉ፣ ለዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ፣ በተመሳሳይ ለኢንዱስትሪ ልማት የሚያግዝ መሠረተ ልማትን በቀላሉ ለማስፋፋት ስለሚያስችሉ ወጪ ቆጣቢ ናቸው። አዎ! ማንም የፈለገውን ቢያወራ እኛ ኢትዮጵያዊያን የአገራችንን ምጣኔ ሀብት ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የመዋቅር ሽግግር እንዲያደርግ  ጠንክረን በመሥራት ላይ ነን።