Artcles

ራስንና አገርን…

By Admin

July 09, 2018

ራስንና አገርን…

                                                      ደስታ ኃይሉ

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወጣቶች በክረምት ማድረግ የሚገባቸውን ጉዳዩች አስመልክው በተለያዩ ወቅቶች አቅጣጫ አስቀምጠዋል። በቅርቡ እንኳን የአገሪቱን በጀት አስመልክቶ ለህዝብ ተወካዩች አባላት ማብራሪያ ሲሰጡ፣ የአገራችን ወጣቶች በክረምቱ ሁለት የእረፍት ወራት አገራቸውን በምን መንገድ መጥቀም እንደሚችሉ በማሳየት በበጎ አገልግሎት ስራ ተሳታፊ መሆን እንደሚገባቸው ምክረ ሃሳብ ማቅረባቸው ይታወሳል።  

እርግጥ የበጎ አገልግሎት (Volunteerism) በሁሉም የዓለማችን አካባቢዎች የሚካሄድ ሰናይ ምግባር ነው። በጎ አገልግሎት ተማሪን ብቻ የሚመለከት አይደለም። ሁሉም በተሰማራበት የስራ መስክ በእረፍት ጊዜው አገሩንና ህዝቡን የሚያግዝበትና የሚደግፍበት አንድ መንገድ ነው። በዚህ ተግባር እረፍት ጊዜን ወደ ስራ በመለወጥ ብቻ አገርን ኢኮኖሚ መደገፍ ይቻላል። ለምሳሌ አቅመ ደካማዎችን በማገዝ አገራችን ለስራው የምታወጣውን ገንዘብ ማዳን ይቻላል።

ስለሆነም ወጣቶች በሁለት ወራት የእረፍት ጊዜያቸው ታናናሾቻቸውን በማስተማር፣ በሽተኞችን በመደገፍ፣ በማህበራዊ አገልግሎቶች ላይ ንቁ ተሳታፊ በመሆንና በመሰል ክንዋኔዎች ላይ በመሰማራት አገራቸውን መደገፍ ይችላሉ። የሚሰጡት በጎ አገልግሎትም በገንዘብ ሲተመን ለሀገራችን ኢኮኖሚ የሚኖረው ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን መገንዘብ አለባቸው።

በእኔ አስተሳሰብ በበጎ አገልግሎት ስራዎች ወጣቶች በክረምቱ ወራት ሁለት ነገር ሊያሳኩ ይችላሉ። አንደኛው፣ ራሳቸውን ራሳቸውን ከአልባሌ ቦታዎች እንዲጠብቁ የተመቻቸ ሁኔታን ይፈጥራሉ። ሁለተኛው ደግሞ፣ አገራቸውንና ህዝባቸውን በመርዳት ገንዘብ ሊፈጥር የማይችለውን የህሊና እርካታ ያገኛሉ። ይህም ራስንና አገርን መጥቀም ነው።

መጪው አዲስ ዓመት እየተቃረበ ነው። ወጣቶች ‘በአዲሱ ዓመት ከደባል ሱስ እላቀቃለሁ፣ በትምህርቴ አዲስ ውጤት አስመዘግባለሁ…እና ሌሎች’ ዕቅዶችን ሊይዙ ይችላሉ። ይህ ነባራዊ ነው። ታዲያ በዕቅዳቸው ውስጥ አገሬንና ህዝቤን በክረምቱ ወራት በበጎ አገልግሎት ተሳትፌ አግዛለሁ የሚል ነገርም መጨመር ይኖርባቸዋል።

ወጣቶች አገራቸው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ይዛ እየሰራች መሆኑን መገንዘብ አለባቸው። ይህን ዕቅድ ለማሳካት ከፍተኛ በጀት ያስፈልጋል። በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ የገንዘብ አቅሟን መቆጠብ ይኖርበታል።

ኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች የምታወጣውን ገንዘብ መቀነስ አለባት። ይህን የቁጠባ ባህል ወጣቶች መደገፍ አለባቸው። በግላቸው ከሚያከናውነኑት የቁጠባ ባህል በተጨማሪ በአገር ደረጃ ቁጠባውን በመደገፍ የድርሻቸውን መወጣት አለባቸው። በእኔ እምነት አገራቸውንና ህዝባቸውን ለማገዝ የበጎ ስራ አገልግሎት ምቹ ምክንያት ነው።

ወጣቶች በበጎ አገልግሎቶች የስራ ባህልንና ተነሳሽነትን ሊማሩበትም ይችላሉ። አገራቸው የበለጠ እንድታድግና ድህነትን ለማሸነፍ የምታደርገውን ትግልም ግንዛቤ ያገኛሉ። ትምህርታቸውን ጨረሰው ወደፊት ወደ ስራ ዓለም ሲገቡ ምን ማድረግ እንደሚኖርባቸው ይማራሉ።

በግላቸው እነዚህንና ሌሎች ሁኔታዎችን በመቅሰም መፃዒ ህይወታቸው ምን መሆን እንዳለበት ከወዲሁ የውሳኔ ሃሳብ በውስጣቸው ሊይዙም ይችላሉ። በዚህም ለህይወታቸው መነሻ የሚሆን ነገርን በመያዝ ራሳቸውን መጥቀም ይችላሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቅርቡ ለወጣቶች ባቀረቡት ምክረ ሃሳብ (Proposal) “ወጣቶች በክረምት ወቅት ነፃ አገልግሎትን በመስጠት ለኢኮኖሚው አስተዋፅኦ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።” ብለዋል። ይህም እነርሱ ለሚያከናውኑት ስራ መንግስት የሚያወጣውን ገንዘብ የሚያድን መሆኑን አስታውቀዋል።

ለምሳሌ ያህልም በሀገራችን ውስጥ አንድ ሚሊዩን የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች አሉ ብለን ብናስብ እንኳን (ትክክለኛ ቁጥሩን ማለት አይደለም)፣ ለስልሳ ቀናት እነዚህ ተማሪዎች የአስረኛ ክፍል ተማሪዎችን ቢያስተምሩ በገንዘብ የማይተመን ድጋፍ ማድረግ ይችላሉ። ይህም ለማትሪክ የሚቀመጠው ተማሪ ጥሩ ውጤት እንዲያመጣ ከማድረግ ባሻገር የትምህርት ጥራቱን የሚደግፍ ተግባር ይሆናል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ለህብረተሰቡ ተጨባጭ ለውጥ በሚያመጡ ጉዳዩች ላይም ማዋል ይቻላል። ለአብነት ያህል ወጣቶች በህብረተሰቡ የጤና ችግር፣ አካባቢን በመጠበቅና የሰዎች ዝውውርን በመከላከል ስራዎች ላይ ሊሳተፉ ይችላሉ። ስልሳ ቀናት ከተሰራባቸው ማህበረሰቡን በማገልገል በኢኮኖሚው ላይ ለውጥ ማምጣት ያስችላሉ።

በተለያዩ ሆስፒታሎች ውስጥ አስታማሚ የሌላቸውን ዜጎች በማስታመም፣ ኤች አይቪ/ኤድስን ለመከላከል በሚደረጉ ጥረቶች ላይ በመሳተፍና ሌላው ቢቀር በሆስፒታሎች ውሰጥ የጤና ትምህርት ሲሰጥ አብሮ በማገልገል ማህበረሰቡን መደገፍ ይቻላል። በአካባቢ ፅዳት ላይ መሳተፍም ማህበረሰባዊ ፋይዳ ያለው ተግባር መሆኑን ወጣቶች ሊገዘቡት ይገባል።

በየቀበሌውና በየመንደሩ በመዘዋወር ስለ ቆሻሻ አወጋገድ ህብረተሰቡን ማስተማር ይችላሉ። የአፍሪካና የአገራችን መዲና የሆነችውን አዲስ አበባን እንደ ምሳሌ ብንወስድ፣ በዚህች ከተማ ውስጥ ያለውን የቆሻሻና የመጥፎ ጠረን እንዴት ማስወገድና መከላከል እንደሚገባ ህብረተሰቡን በማስተማር ለውጥ ማምጣት ይቻላል።

በዚህ ተግባራቸውም ከየአካባቢው ወጥቶ በየመንገዱ የሚተኛው ፍሳሽ እንዲሁም እንደነገሩ የሚጣለው ቆሻሻ የከተማዋን ገፅታ ከማበላሸት ባለፈ በርካቶችን ለተለያዩ የጤና ችግሮች እንደሚያጋልጥ በማስተማር የህብረተሰቡን ጤና እንዲጠበቅ ማድረግ ይችላሉ።

የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የዓለማችንና የአገራችን አሳሳቢ የሆነውን ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከልም ሊውል ይችላል። በፌዴራልና በክልል ደረጃ ፓስፖርት በሚሰጥባቸው አካባቢዎች እየተገኙ ስለ ህገ ወጥ ስደት አስከፊነት ለተጓዦች በማሰተማር የግንዛቤ ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ። በቤት ለቤት ቅስቀሳም የችግሩን መንስኤና በምን ምክንያት ዜጎች እየተሰደዱ እጅግ ለከፋ አደጋ እንዲጋለጡ ማስተማር የሚችሉ ይመስለኛል።

በክረምቱ የተራቆቱ አካባቢዎችን ለመታደግ ችግኝ በመትከል የአካባቢን ስነ ምህዳር ለመጠበቅ በሚደረገው ጠረት ውስጥም ግንባር ቀደም ተሳታፊ ሊሆኑ ይችላሉ። የስነ ምህዳር ችግር በተለይ እንደ እኛ ላለ በየጊዜው በተፈጥሮ የአየር ንብረት ለውጥ ለሚጠቃና ዜጎቹም የድርቅ ሰለባ ለሚሆኑበት አገር አደጋውን ከኢኮኖሚና ከአገራዊ ክብር አኳያ በመመልከት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ሊያከናውኑ ይችላሉ። በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በወጣቶች ሊሸፈኑ የሚገባቸው ስራዎች በርካታ ቢሆኑም፣ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ይህን ስራ በመፈፀም ራሳቸውንና አገራቸውን ሊጠቅሙ እንደሚችሉ መገንዘብ ይኖርባቸዋል።