Artcles

ሰላማችን በጥቂቶች አይደፈርስም

By Admin

July 28, 2018

ሰላማችን በጥቂቶች አይደፈርስም

ደመላሽ አንጋጋው

ሰላም ለአንድ ሀገር ህዝቦች መሠረታዊ ጉዳይ ነው፡፡“ዜጎች ወልደው መሳም ዘርተው መቃም” የሚችሉት ሰላም ሲኖር ነው፡፡ የሰላም ዋጋው በገንዘብ የሚተመን አይደለም፡፡  ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ግዜ ካለፉት ሦስት ዓመታት ከነበሩት የሁከትና ግጭት ቀውስ የወጣችበት ወቅት በመሆኑ በጣም ወሳኝ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በዲፕሎማሲውም ሆነ በኢኮኖሚው መስክ ፋና ወጊ የሚባል እንቅስቃሴ እያደረገች  ትገኛለች፡፡ ስለዚህ ያሳለፍናቸው የስቃይና የሰቆቃ ዓመታት ተመልሰው እንዳይመጡ ሁላችንም በመደመር ብሔር ከብሔር እና ሀይማኖት ከሀይማኖት ሳንነጣጠል አንድ በመሆን በፍቅር ተሳስረን ልማታችንን ሰላማችንን ማስቀጠል ይኖርብናል፡፡

ስንደመር ሀገራችንን የምናበለፅግበት፣ ከድህነት አረንቋ የምናወጣበት፣  ሀገራችንን ከወራሪ ኃይል የምንከላከልበት፣ በዓለም መድረክ ልቀን የምንታይበትና የምንደመጥበት ፣ ከእርስ በርስ የፖለቲካ ሽኩቻ የምንላቀቅበት እና ከጎረቤት ሀገር ጋር ሰላም የምንፈጥርበት፤ ኃይል፣ ብቃት፣ ወኔ፣ አንድነት፣ መተሳሰብ፣ መከባበር ለአንድነታችን ብርታትና ጉልበት ይሆነናል፡፡ በመደመር ሀሳብ ውስጥ ህዝቦች ለሰላም ሆነ ለልማት ሚናቸው ከፍተኛ ነው፣ የማይቻለውን እውን ያደርጋሉ፡፡ እርግጥ ነው ህዝብ ከህዝብ፣ ህዝብ ከመንግሥት እና ሀገር ከጎረቤት ሀገር ጋር በመደመር ልዩነቶቻችን እንቅፋት ሳይሆኑ ህዝቦች አንድነታቸውን  በአደባባይ ለዓለም ህዝብ አሳይተዋል፡፡ ይህም የሚበረታታ በሀገራችን ሰላም እንዲጎላና ለቀጣናውም ከፍተኛ የሆነ አዎንታዊ አስተዋፅዖ እንዳለው በይፋ ታይቷል፡፡

ነገር ግን የየትኛውም የሀይማኖት፣ የብሔር፣ ዘር እና ቀለም የማይወክሉ የተወሰኑ ተስፋ የቆረጡ ኃይሎች በሀገርም ይሁን ከሀገር ውጭ እየተደረገ ያለውን የእርቅ እንቅስቃሴ ያላስደሰታቸውና ሀገር ሰላም መሆኑ የእነሱን ጥቅም የሚነካባቸው ጥቅም አሳዳጆች ችግር እየፈጠሩ ይገኛሉ፡፡ ይህ ግጭት ማንንም የማይወክልና የምናደርገውን የሰላም ጉዞ ለሰከንድ ያህል እንኳን  የማያደናቅፍ ነው፡፡

እርግጥ ነው የግጭት ትንሽና ትልቅ ስለሌለው ክቡር የሰው ሕይወት ጠፍቷል፣ ከቀላል ጉዳት ጀምሮ እስከ ሞት ድረስ ጥቁር ጠባሳውን አሳርፏል፣ እንዲሁም በንብረት ላይም ቀላል የማይባል ጉዳት ደርሷል፡፡  ለአብነትም ያህል በኢትዮጵያ ሱማሌና በኦሮሚያ ተከስቶ የነበረው ግጭት በንብረት ላይና በሰው ህይወት ላይ ትልቅ ጉዳት አድርሷል፡፡ የኦሮሚያ ክልላዊ  መንግስት ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ እንዳሉት፤ “ግጭቱ ጊዚያዊና ህዝቦች ሳያስቡት የተከሰተ ነው” ብለዋል፡፡ እንዲሁም ጉዳቱ የሁላችንም ነው ያሉት አቶ ለማ መገርሳ ምክንያቱ ደግሞ የሁለቱም ክልል ህዝቦች ኢትዮጵያዊ ናቸው፤ በተለይ ደግሞ የኦሮሚያና የሶማሊያ ህዝቦች ብዙ የጋራ የሆነ ዕሴቶች ያሏቸውና በጋራ ለዘመናት አብረው የኖሩ ናቸው ፣ ይህ ግጭት ሁለቱንም ህዝቦች ማይወክልና የማንኛውንም ሀይማኖትና ባህል የማያንፀባርቅ የግለሰቦች ወንጀል ነው፤ ግጭቱ እንደቀላል መታየት የለበትም አንድምታው ከድንበርና ከሁለቱ ህዝቦች የዘለለ ነው ብለዋል፣ እልባት ካልተሰጠው እንደሀገርም ቀላል የማይባል ጉዳት ያደርሳል ያሉት አቶ ለማ መገርሳ ፤ ሁለቱም ህዝቦች ኢትዮጵያዊ ስለሆኑ ሁሉም ወገኖቻችንና አንድ ህዝብ ሰለሆኑ በማናቸውም ላይ የፍርሀትና የስጋት ስሜት መኖር የለበትም ፣ ግጭቱም እንዳያገረሽ ቀድሞ የነበረው አንድነት አጠናክረው እንዲቀጥሉ የክልሉ መንግሥት የማያዳግም እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ተናግረዋል፣ ቀጣይነት እንዳለውም እምነታቸውን ገልፀዋል፡፡ ሁላችንም አንድ ሀገር ብቻ እንዳለን በማሰብ የሰላም ጉዳይ ለማንም የማይተውና ሁሉም በጋራ በመሆን ሴረኞችን ለሕግ በማቅረብ የህዝቦችን አንድነት ማስቀጠል የሞት ሽረት ጉዳይ መሆን አለበት፡፡

የኢትዮጵያ ሶማሊያ ክልላዊ ፕሬዚዳንት አብዲ መሀመድ እንዳሉት “ይህ የከፋ ግጭት የመጀመሪያና ብዙ ንብረትና የሰው ህይውት ያጠፋ ግጭት” ነው ካሉ በኋላ፣ እርግጥ ነው ሁለቱ ክልሎች ሠፊ የሆነ ድንበር ስለሚጋሩና በድንበር የአካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎች አርብቶ አደር ስለሆኑ መጠነኛ የሆኑ ግጭቶች ብዙ ግዜ ይስተዋላሉ ነገር ግን በሀገር ሽማግሌና በሀይማኖት አባቶች የሚፈቱ ነበር ሲሉ ተናገረዋል፡፡ ፡፡ ይህ ግጭት ዳግም መደገም እንደሌለበትና ለሰላም የክልሉ ህዝቦች ዘብ እንደሚቆሙ ማሳሰቢያ ሰተዋል፡፡

እንዲሁም  በጌዲዮና በጉጂ፣ በሲዳማና በወላይታ፣ በደብር ማርቆስ እና  በባሌ ጎባና አካባቢው ግጭቶች ተከስተዋል፡፡ ግጭቶች እየታየ ያለውን የሰላም ከማወክ የተለየ ዓላማ በሌላቸውና ጥቅማቸውን ከማሳደድ ዉጪ የኅብረተሰቡ ሰላም ደንታ በማይሰጣቸው ቡድኖች ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እርስ በርስ በቋንቋ፣ በባህል፣ እንዲሁም በሀይማኖት የተሳሰሩና እርስ በርስ የተዋለዱ መሆናቸውን ታሪክ የሚመሰክረው ሀቅ ነው፣ ክርስቲያን ሙስሊሙን እንግዳው አድርጎ ሙስሊሙም ክርስቲያኑን እንግዳው አድርጎ በመቀበል እርስ በርስ ተረዳድተውና ተባብረው የሚኖሩ ሕዝቦች ናቸው፡፡ እንዲህ ያለውን መልካም ታሪካችንን በማስተዋል ለተሸነፉት መሣሪያ ላለመሆን መጣር ይኖርብናል፡፡

እነዚህ ጥቂት ኃይሎች በተለይ በተደራጀ መልኩ ወጣቶችን በብር በመደለል የእነሱ ዕኩይ ተግባር ተካፋይ ለማድረግ ሲጥሩ ይስተዋላል፣ ይህ ደግሞ ባህላችንም ታሪካችንም ስላልሆነ ከነዚህ ተግባር መታቀብ ይኖርብናል፣ ለመጣላትም ለመታረቅም ሰላም ይስፈልገናል፡፡ ሰላምን በብር ማግኘት አንችልም፣ ነገር ግን በብር ሰላማችን ሊደፈርስ ይችላል፡፡ ስለዚህ ሰላማችንን መንከባከብ፣  ዘመኑ የሰለጠነና የቴክኖሎጂ ውድድር ስለሆነ ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ልማታችንን ማፋጠን ይኖርብናል፡፡ እንዲሁም ፍቅራችንንም ሆነ ጠባችንን በሰለጠነ መንገድ መሆን ችግሮች ካሉም በጠረፔዛ ዙርያ አልያም በዛፍ ሥር ተጠልለን መወያየትና ሰላማዊ በሆነ መንገድ መፍታት አለብን፡፡

በተለይ ደግሞ ወጣቶች ከስሜታዊነት በፀዳና በተደራጀ መልኩ በመንቀሳቀስ የጥቂቶችን  መሣሪያ ከመሆን ታቅበው ዕኩይ ተግባራቸውን በማጋለጥ ማዋረድ ይኖርባቸዋል፣ እንዲሁም ጥያቄ ካላቸው በሰለጠነና ሕገ- መንግሥታዊ ሥርዓትን በተከተለ መልኩ ጥያቄያቸውን ለመንግሥት አመራሮችና ለሚመለከታቸው አካላት በማቅረብ ችግራቸው  እልባት እንዲያገኝ ማድረግ አለባቸው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ተግባር ደግሞ በሀገራችን የተጀመረውን የፍቅር፣ የአንድነትና የመደመርን ጉዞ የሚያደናቅፍ ተግባር በመሆኑ፣ ወጣቱ በንቃት ካልተከታተለ በሀሰት መረጃ የደብረማርቆስ ወጣቶች የሠሩት ስህተት በሌላው የሀገራችን አካባቢ መደገሙ አይቀርም፣ በተለይ ደግሞ ወጣቱ የኅብረተሰባችን ክፍል ካለው አጠቃላይ ህዝባችን የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል፣ ስለዚህ የወጣቱ ድርሻ ለልማትም ሆነ ለጥፋት ሚናው የጎላ ነው፡፡

የጀመርነው የለውጥ ጉዞ ማንንም የማያገል፣ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ያሳተፈ መሆን አለበት፡፡ ዕድገት፣ ሰላምና ብልፅግና የሚመጣው የትኛውንም ዜጋ በሀይማኖትም ሆነ በፖለቲካ አመለካከት ከአድሎአዊ አሠራር በፀዳ መልኩ ማሳተፍ ሲቻል ብቻ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ የሀገሪቱን ዜጎች በሙሉ ተጠቃሚ ያላደረገ ዕድገት ዕድገት አይባልም፡፡ ሁሉም ዜጎች መሳተፍ ከቻሉ ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ ማለት ነው፣ ካልሆነ ግን ባለፉት 27 ዓመታት ሲታይ የነበረው የተወሰኑ ሰዎች የኢኮኖሚና የፖለቲካ የበላይነት  ላለፍት ሦስት ዓመት ላላስፈላጊ ቀውስና ግጭት ዳርጎን አልፏል፡፡

ስለዚህ ዜጎች በሀይማኖታቸውም ይሁን በፖለቲካ አመለካከታቸው መገፋት ለከፋ ግጭት የሚዳርግ ተግባር ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ጉዳይ ሚዲያዎች ትኩረት በመስጠትና የዘርፉን ምሁራን በመጋበዝ ለሀገሪቱ ህዝቦችና በተለይ ደግሞ ለወጣቱ በማስገንዘብ ዕድገትና ሰላምን በተፈለገው መልኩ ማስኬድ ይቻላል፡፡ ትልቅ ተስፋም ይኖረዋል፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ የሚነሱ ግጭቶች ግን የያዝነውን የመደመር የለውጥ ጉዞ ሊያስቱ የሚችሉና አደገኛ በመሆናቸው ሁሉም ዜጋ ሊከታተላቸው ይገባል፡፡

ሰላም ለአንድ ሀገር ዕድገት ከፍተኛ ሚና አለው፣ ምንም እንኳን ሁሉም ሴክተር ሰላም ቢሻም በተለየ መልኩ የቱሪዝም ዘርፉ ሰላምንና መረጋጋትን ይፈልጋል፡፡ ባለፍት ሦስት ዓመታት ተከስቶ የነበረው አለመረጋጋት የቱሪዝም ዘርፉን ክፉኛ ጎድቶት ነበር፣ ይህ ደግሞ ሀገሪቱ መጠቀም ያለባትን ሳትጠቀም ቀርታለች፡፡ ይሁንና ካለፉት ሦስት ወር ወዲህ አንፃራዊ ሰላም ስለሰፈነ እንዲሁም በፖለቲካው ዘርፍ የለውጥ ጅማሬዎች በመምጣታቸው ለዘርፉ ዳግሞ ማበብ ተስፋ ጭሮበታል፡፡ በ2008ና በ2009 ዓ.ም በግጭቱ ምክንያት የቱሪስት ቁጥር በመቀነሱ ማግኘት የነበረብንን የውጭ ምንዛሬ ሳናገኝ ቀርተናል፣ እንዲሁም የሥራ አጥ ቁጥር እንዲያሻቅብ የራሱን ሚና ተጫውቷል፡፡

ከምንም በላይ ደግሞ ሚዲያ ለአንድ ሀገር ሰላም የመሆንና ያለመሆን ጉዳይ ከፍተኛ የሆነ ሚና ይጫወታል፣ ይህንን በመገንዝብ  ሚዲያዎቻችን ግጭት በሚከሰትበት ጊዜ ተአማኒ የሆነ መረጃ በፍጥነት ለህዝቦች ከአድሎ በፀዳ መልኩ መዘገብና ማሳውቅ ይኖርባቸዋል፡፡ እንዲሁም ግጭት በሚከሰትበት ሰዓት ግጭቱን ከማራገብ ይልቅ ወደ መፍትሔው በማተኮር ቀድሞ የነበራቸውን አንድነትና ትስስር አጉልቶ በመዘገብ የተከሰተ ሁከት በቶሎ እንዲበርድና እልባት እንዲያገኝ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ሚዲያዎቻችን በአንድ ጊዜና ቦታ ሁነው ተደማጭነታቸው የሰፋ በመሆኑ ለሚዘግቧቸውና ለሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ እንዲሁም ግጭት በሚከሰቱባቸው ቦታዎች በመገኘት ትኩስና ተዐማኒ መረጃ ለኅብረተሰቡ ማቅረብ፣ ለግጭቱ ምክንያት የሆነውን ነገር ለይተው በማውጣት  ግጭት ዳግሞ እንዳያገረሽና አስተማሪ ዘገባ መዘገብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተለይ ደግሞ በኢትዮጵያ ሶማሊያ እየተነሳ ላለው ጥያቄ በአግባቡ የሚፈታ ስለመሆኑና ህዝቦች ጥያቄአቸውን በአግባቡና ቅደም ተከተሉን በጠበቀ መልኩ ለሚመለከታቸው አካላት በማቅረብ ችግራቸው እንደሚፈታ ማስተማርና ግንዛቤ መፍጠር ፣ እንዲሁም ግጭቱን ከማራገብ መቆጠብ ይኖርባቸዋል፣ ግጭቱ ግዜአዊና ሕዝቦችን የማይወክል እኩይ ተግባር መሆኑን ማስተማር ግዴታቸው ነው፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት ዶ/ር ዐብይ አህመድ እንደተናገሩት፤ ‹‹በየአካባቢዎች ያሉ ህዝቦች ተደምረው ትልቅ ሀገር መፍጠር እንጅ፤ ወደ አነስ ሁኔታ መግባት የሚፈልግ ህዝብ የለም” ፣ ነገር ግን አንዳንድ ግለሰቦች ህዝብን ከህዝብ የሚያጣላ ያለፈበትና ተቀባይነት የሌለው ተግባር ሲፈፅሙ ይስተዋላሉ ብለዋል፡፡ የሀገር መከላከያ ሚኒስቴርና የፌደራል ፖሊስን በየትኛውም ቀጣና ህዝብን ከህዝብ በሚያጋጩና የሰው ህይወትን በማጥፋት ተግባር ላይ በሚሳተፉ ግለሰቦችና ቡድኖችን ለህግ እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡

እንዲሁም ቀጥለው “የተከሰተው ግጭት ረገብ እንዲል መሀል ገብታችሁ ሀገራዊና ሕገ-መንግሥታዊ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ ፤ ሥራቹህ አክሳሪ እንዳይሆን፣ አጥፊ እንዳይሆን፤ ሙያዊ፣ ጥበባዊና መረጃ ላይ የተመረኮዘ መሆን ይኖርበታል ፣ በተለይ ደግሞ ህዝብ ሳይሞት ንብረት ሳይወድም ሰላም የሚወርድበትን መንገድ ለማምጣት ሙያዊ ብቃታችሁን እንድታሳዩ” ሲሉ ተደምጠዋል ፡፡ ይህም መንግሥት ሰላም ለማስፈን ያለውን ቁርጠኛ አቋም የሚያሳይ ነው፣ አሁን ባለው ሁኔታ ግጭት ተነስቶ በነበረባቸው አካባቢዎችን አንፃራዊ ሰላም መምጣት ችሏል፡፡ ያለው የሰላም ማስፈን ሁኔታም ሥርዓት ባለው መልኩና የሕገ-መንግሥቱን መርህ የተከተለ መሆኑ ታውቋል፡፡ ሰላም ማለት ለሁሉም መነሻና መድረሻ ስለመሆኑ ማስተማርና መዘገብ የዕለት ተዕለት ሥራቸው መሆን አለበት፡፡ እንዲሁም የህዝብ ጥያቄዎች በወቅቱ እንዳይመለሱ በማድረግ ሕዝብን ከመንግሥት ጋር ለማጣላት የሚጥሩ አመራሮችን በማጋለጥ ለሰላም ዘብ መቆም ይኖርባቸዋል፡፡ ይህን በመገንዘብ ህዝቦች ከመንግሥት ጎን በመቆም ለሰላማችን ትልቅ ግምት ሰጥተን በጥቂት ግለሰቦችም ከመነጠቅ መዳን ይኖርብናል፡፡