Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ስለሠላም እናቀንቅን…

0 242

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

 

                                                         አባ መላኩ                  

በየጎጡ፣ በየአካባቢው፣ በየመንደሩ ላለው የሠላም መረጋጋት ሁኔታ ዋነኛው መሠረት መላው ሕዝብ ነው። በየአካባቢው በሚከሰት ማናቸውም የፀረ ሠላም ድርጊት መልሶ ተጎጂው ራሱ ሕዝቡ በመሆኑ ለሠላሙ ይበልጥ መትጋት ይጠበቅበታል። እንዲህ ዓይነቱ ሠላምን የሚያጎሉ፣ ልማትን የሚያፋጥኑ፣ ንትርክን፣ ግጭትንና ሁከትን የሚያስቀሩ መንገዶችን መከተል ባይቻል ኖሮ፤ የተጀመረውን የፀረ ድህነት ዘመቻ አጠናክሮ ባልቀጠለ ነበር። ከልማት ዕቅዱም በየደረጃው ተጠቃሚ ሆኖ ተፈላጊውን የዕድገት ራዕይ ሰንቆ ባልተጓዘም ነበር። አሁን እያለመ ላለውና ለሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ስኬት ባልተጋ ነበር።

ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ከተቀረፁ፣ ዜጋውን ከዳር እስከ ዳር የሚያንቀሳቅስ መንግሥት ካለና በዚሁ መሪ አካል አስተባባሪነት ብሎም በሕዝቡ የባለቤትነት መንፈስ የሚጠበቅ ሠላም እስከተፈጠረ ድረስ ሰርቶ መለወጥና ማደግ ይቻላል። ይህንንም የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠንቅቆ ያውቃል። ለዚህም ነው በየአካባቢው የሠላሙ ባለቤት ሕዝቡ ራሱ ዋስና ጠበቃ ሆኖ እየሰራ የሚገኘው። ይህ አኩሪ ተግባሩም ወደፊት ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል። የሠላም ባለቤትነትን ለማረጋገጥ ከርሱ በላይ ማንም ሊመራው አይችልምና።

ከተግባር የበለጠ ትምህርት ቤት የለም። ዛሬ ይህ ሕዝብ የሠላሙ ዘብ ሆኖ በተጠንቀቅ ቆሟል። በኢትዮጵያ አንዳንድ ሥፍራዎች የተፈጠረውን አለመረጋጋት ተከትሎ የሕዝቡን ሠላምና ፀጥታ ለማረጋገጥ ሲባል ብርቱ ጥረቶች ተደርገዋል። መንግሥትም በዚህ ረገድ ቁርጠኝነቱን በትናንት እለት በግልጽ ቋንቋ አረጋግጧል። ከዚህም የከፋው ሁኔታ በተለይም በአገሪቱ ላይ ተደቅኖ የነበረውን አደጋ ለመቀልበስ በተደረገው ርብርብ የሕዝቡ ሚና ቀላል አልነበረም።   

ይህ ሠላም ወዳድ ሕዝብ ከዚህ ቀደም በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በሁከት ተግባር ላይ የተገኙ ወጣቶችን ገስጿል፤ መክሯል። ለሠላም እንዲሰሩና የሠላምን እሴት እንዲያውቁ በስፋት አስተምሯል።

የየትኛውም አገር ሠላም የሚረጋገጠው በሕዝቦች ቅን አስተሳሰብና መልካምነት እንደሆነ ፀሀይ የሞቀው እውነታ ነው። የኢትዮጵያንና የሕዝቦቿን ሠላምና መረጋጋት መጠበቅ ፋታ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም። ሕዝብ ሁሌም ከማንኛውም ተግባር በፊት ግራና ቀኙን ለይቶ የሚያይ፣ ህጋዊ አካሄዶችን የሚያጤን፣ አሉታዊና አዎንታዊ ጎኑን የሚገነዘብ ብሎም ሚዛናዊ ውሣኔ የመስጠት ባህል ያለው ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝብ የሠላምን ጥቅም ጠንቅቆ የተረዳ ነው፡፡ በማሆኑም ለሠላሙ ሲል እጅግ ከፍተኛ ዋጋ ከፍሏል፤ እየከፈለም ይገኛል፡፡ ስለ ሠላም በተቀነቀነ ቁጥር ሕዝቡ ቀድሞ ከሥፍራው የሚገኘው ያለምክንያት አይደለም። ሠላሙ፣ ተስፋው፣ ኑሮና ሕይወቱ ስለሆነ ነው፡፡  በተለያዩ ወቅቶች ሕዝቡ የየአካባቢውን ሠላም በመጠበቅ ረገድ ያሳየው ኃላፊነትን በተገቢው ሁኔታ የመወጣት እንቅስቃሴ ሁሌም ሊጠቀስ የሚገባው ነው። ይህም ተግባር የሠላሙ ባለቤት ሕዝቡ ራሱ ስለመሆኑ መልካም አስረጂ ነው።

ወቅትን እየጠበቀ ብቅ…ብቅ የሚለው ሠላምን የማደፍረስ ተግባር አሁንም በአንዳንድ ቦታዎች ቢታይም በሠላም ወዳዱ ሕዝብ እንደሚጨናገፍ እሙን ነው። ለሠላምና መረጋጋት ዋነኛ ተዋናይ ሕዝብ እንደሆነ ሁሉ የአገሩም ባለቤት ሕዝብ ነው፡፡ ሠላምና መረጋጋት ለአገር ዕድገትና ልማት ያለው ድርሻም ከሁሉም የጎላ ነው። ከቅርብ ዓመታት በፊት እንደታየው መረጋጋት የማይታይባቸው የዓለም አገሮች ምን ያህል ለከፋ ቀውስ፣ ትርምስና እልቂት እንደበቁ በተለይ በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ሁኔታ ያስረዳናል።

በአንድ አገር ውስጥ ትርምስና ሁከት እንዲፈጠር፣ ብጥብጥና ሁከት እንዲኖር፣ ሥርዓተ አልበኝነት እንዲሰፍን፣ ሁሉም ነገር ከቁጥጥር ውጭ እንዲወጣ ዜጎችን የማተራመስ ሁኔታ ከመክፋቱ በፊት እንቅስቃሴውን በእንጭጩ መቆጣጠር ተገቢ መሆኑን መንግሥት በግልጽነት አቋሙን ግልጽ አድርጓል።

ጥቂት ቡድኖች አመቺና አዋጪ ነው ብለው የሚያምኑበትን  አመጽና ሁከት እንዲቀሰቀስ የተለያዩ ሥልትና ዘዴዎችን ለመጠቀም ጥረት ሲያደርጉ ይስተዋላል። ይህንን ዘዴያቸውን በተለያዩ ቦታዎች ተግባር ላይ ለማዋል ሲፍጨረጨሩም ታይተዋል፡፡ ይህ መሰሪ ዓላማ ይህ መሰሪ ሴራ በሕዝቦች አንድነትና የጋራ መከታነት እንደሚከሽፍ እሙን ነው። ይህ ሁሉ መውተርተር ለዜጎች ጥቅምና መብት በመቆርቆር አይደለም፡፡ ይልቁንም የራስን ሰፊ ጥቅም ለማስከበርና የጀመሩትን አገርን የመዝረፍ ሁኔታ ለማስቀጠል አጉል የሚያደርጉት መፍጨርጨርና መሯሯጥ ነው።

ሕዝብ ደግሞ በማንኛውም መስፈርት ሠላሙን አጥቶ ሊኖር አይገባውም። በመሆኑም ለሠላሙ እውን መሆን አጥፊዎችን በማጋለጥ ለህግ ያቀርባል። ይህም ሠላሙን ምን ያህል ጠባቂ መሆኑን የሚያሳይ ተግባር ነው። ሕዝቡ የወደፊት ዕጣ ፈንታው የሚወሰነው አገሪቱ በምትከተለው ሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ መሆኑን ስለሚያውቅ ሁሌም በተጠንቀቅ ይቆማል። ዜጋው ከሠላም ወዳድ ኃይሎች ጋር የሚቆምና የሠላምን ጠቀሜታ ስለሚገነዘብ ከምንጊዜውም በላይ በየአካባቢው ለሠላሙ ዘብ ይቆማል።  

የተጀመረውን ሠላምና ልማት ለማስቀጠልና በዚያውም ልክ ዴሞክራሲው እንዲያብብና እንዲጎለብት የተደረገው ጥረት እንዳለ ሆኖ ይህ ሕዝብ በአንዳንድ ክልሎች ውስጥ የተከሰተውን ግጭት ለማስቀረት በባለቤትነት የተከፈለው መስዋዕትነት በቀላሉ አይታይም። ሕዝቡ ስለ ሠላም ያለው ስሜት የመነጨው ከምንም ተነስቶ አይደለም፤ ይልቁንም የሠላምን እሴት በምንም ሊለካው እንደማይችል ያለፉት ተጨባጭ ሂደቶች ስላስተማሩት እንጂ። ሁሌም ስለሠላም ያቀነቅናል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy