በመደመር የተገኙ ትርፎች!
በፍሬህይወት አወቀ
ኢትዮጵያ በጀመረችው አዲስ ምዕራፍ “መደመር” በሚለው ጥልቅ በሆነ አስተሳሰብ ከብዙዎች ጋር በፍቅር በሠላምና በአንድነት ለመጓዝ ማርሽ አስገብታ መሪዋን ጨብጣለች። እዚህም እዚያም ታጥረው የነበሩ አጥሮች፣ ጥጋጥጎች፣ ጎጦች፣ በውስጥም በውጭም የተፈጠሩ መከፋፈሎችና መራራቆች በመደመር ስሌት እየተጠጋጉና በፍቅር ማግኔት እየተሳሳቡ ይገኛሉ። በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገራት የብዙዎችን ትኩረት የሳበና በአዲስ የታሪክ ምዕራፍ የከፈተው የኢትዮጵያና የኤርትራ ሠላማዊ ግንኙነት ዓለምን ያስደመመ ክስተት ነው።
ኢትዮጵያ ያለማንም ጣልቃ ገብነት በራስ ተነሳሽነትና በወሰደችው ቁርጠኛ አቋም የኢትዮጵያና የኤርትራ ዝምታ ተሰብሮ ችግሮች እልባት አግኝተዋል። የጥላቻ ግንቡ ፈርሷል፤ የፍቅር ድልድይም ተገንብቷል። በፍቅር ድልድዩም የመለያየት ታሪክ አብቅቷል። በመሆኑም አገራቱ መደመርን መርህ አድርገው ለሠላም፣ ለፍቅር፣ ለአንድነትና በጋራ ለመልማት ያደረጉትን ስምምነት ተከትሎ የአገራቱ የቀደመው ግንኙነትና ሁለንተናዊ አንድነት ባልተጠበቀ ፍጥነት ቦታውን እየያዘ ይገኛል።
እልባት ያገኘው የኢትዮ ኤርትራ መልካም ግንኙነት ከሁለቱ አገራት ባለፈ ለክፍለ አህጉሩ አዲስ የሠላም፣ የፍቅርና የብልፅግናን ተስፋ የፈነጠቀ ትልቅ ድል ነው። “በአንድነትና በመደመር የማንሻገረው ችግር አይኖርም” እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እነሆ ለሁለት አሥርት ዓመታት ሻክሮ የነበረው ግንኙነት ወደ ሠላም፣ ልማትና አንድነት ተሸጋግሯል። ከዚህም በላይ የህዝብ ለህዝብ ትስስሩ ተጠናክሮ ቀጥሏል። በአገራቱ ዜጎች መካከልም ለ20 ዓመታት ተዳፍኖ የቆየው እጅግ የጠለቀና የመጠቀ፣ የመፈላለግ፣ የመነፋፈቅ፣ የአንድነትና የመደመር ስሜቶች ያለ ማንም ከልካይ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊና ኤርትራዊ ገፅ ላይ ተንፀባርቋል፤ እንደመጽሐፍም ተገልጿል፤ ተነቧል።
በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የነበረው ጦርነትም ሆነ ሠላም አልባ ፖሊሲ (No war No Peace) የትግራይና የአፋር ክልል በእጅጉ የተጎዱ ናቸው። ከ17 ዓመታት በላይ በዘለቀው ይህ የኢትዮ ኤርትራ ወይ ሠላም ወይም ጦርነት የሌለው ግንኙነት በተለይም የትግራይ ህዝብን በእጅጉ የጎዳና ግንባር ቀደም የችግሩ ገፈት ቀማሽ ሆኖ መቆየቱን የተለያዩ ምሁራን ሲገልፁ እንደነበር ይታወቃል።
“መለያየት ሞት ነው ለተዋደደ ሰው…” እንዳለው ድምፃዊው የሞት ያህል ገዝፎ ለሁለት አሥርት ዓመታት ተከምሮብን የነበረው የመለያየት፣ የድብርትና የማሸለብ ጊዜን ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በወሰዱት ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት ተሻግረነዋል። የጥላቻና የበቀል አቧራን ከላያችን ገፈን አራግፈን ቀና ብለናል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሚሊኒየም አዳራሽ በተደረገው ደማቅ ዝግጅት ባደረጉት ንግግር “አገር እንደሰው ናት፤ እኛ እንደሆነው ትሆናለች። ብንፋቀር ፍቅር ታዘንባለች፣ ይቅር ከተባባልን ፈውስ ታፈልቃለች፣ ብንተጋ ብልፅግናን ታጎርፋለች፣ ብንማር ትሰለጥናለች፣ ብንከባበር ብንተባበር ትከብራለች፣ ትገዝፋለች፣ ትልቃለች…” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ያደረጉትን የሠላም ጥሪ ተከትለው አዲስ አበባን የጎበኙት የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሣያስ አፈወርቂም በአዲስ አበባና በዙሪያዋ እንዲሁም በሀዋሳ ያሉ ኢትዮጵያውያን ባደረጉላቸው ደማቅ አቀባበል ተደስተዋል። ይህንኑ በሚሊኒየም አዳራሽ በነበረው መድረክ በአማርኛ ቋንቋ ሲገልፁ “ያለፈውን በባህላችንና በታሪካዊ ጥልቅ ጥቅሞቻችን ላይ የተቃጣውን ጥላቻ፣ ቂም በቀልና ውድመት ለመንዛት የተሞከረውን ሴራ አሸንፈን ለሠላም፣ ለልማት ለብልፅግናና ለመረጋጋት በሁሉም መስክና ድንበር አብረን በጋራ ለመስራት ቆርጠን ተነስተናል። ማንም ይሁን ማን ይህን ፍቅራችንና ሠላማችንን ለመበተንና ለማወክ፣ እርጋታችንና ህብረታችንን ለማሸበር፣ ልማታችንና ዕድገታችንን ለማደናቀፍና ለማውደም እንዲፈታተነን አንፈቅድም። በጋራ ጥረታችንም የከሰርነውን በመመለስ ለመጪው ጊዜ ግዙፍ ሁነቶችን ሰርተን እንደምናሸንፍ እርግጠኞች ነን” ብለዋል።
ዕለቱ የወንድማማችነት ፌሽታ የታየበትና በአንድነት በፍቅር እንዲሁም በይቅር ባይነት አገራቱ የተደመሩበት ዕለት ነው። ሁለቱ አገራት ሊደርሱ ካሰቡበት የሚያደርሳቸውን መንገድ ጠርገው ጉዞ ጀምረዋል። ይህ ጉዞም በተጀመረው ፍጥነትና እጅግ ጥንቃቄ በተሞላበት አካሄድ መራመድ ከቻለ የውጤቱ ተጋሪ መሆን እንችላለን። ለዚህም እያንዳንዱ ዜጋ የሚወረውረው መልካም ጠጠር የጎላ አስተዋፅኦ አለው።
በአሁኑ ወቅት የሁለቱ አገራት መንግሥታት የወሰዷቸው ርምጃዎች እጅግ ፈጣንና የዓለም አገራትን ያስደመመ ትልቅ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ነው። ከዚህም በላይ አገራቱ ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ብሎም ፖለቲካዊ ግንኙነታቸውን በማጠናከር ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ ጀምረዋል። በተለይም በአስከፊው ጦርነት ግንባር ቀደም ተጎጂ የነበሩና በድንበር አካባቢ የሚኖሩት የአፋርና የትግራይ ህዝቦች የመጀመሪያው ተጠቃሚዎች ናቸው።
በመሆኑም አሁን የተጀመረው ለውጥ እነዚህን ህዝቦች በቅርበት ከኤርትራ ወንድምና እህት ህዝቦች ጋር ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማጎልበት፣ የእርስ በርስ ትስስራቸውን ለማጠናከር፣ በጋራ ለመስራትና በአንድነትና በፍቅር ተደምረው በጋራ ለመልማት የሚያስችል ትልቅ ዕድልና አዲስ ታሪክም ነው።
አገራቱ በጀመሩት አዲስ ታሪክ ከተስማሙባቸው ነጥቦች መካከል ጦርነት ማቆም፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ማጠናከር፣ የስልክ፣ የየብስና የአየር ትራንስፖርት እንዲሁም የወደብ አገልግሎት መጀመር ናቸው። እነዚህ ውጤቶች በመደመር የተገኙ ትርፎች ናቸው። ባለፉት ጊዜያት የኤርትራን አየር ክልል ማቋረጥ ባለመቻል ሲደረጉ የነበሩ ረዥም በረራዎችም በተደረሰው ስምምነትና በተሰራው አዲስ ታሪክ ማሳጠር ተችሏል። ይህም ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ጠቃሚና የመደመራችን ትርፍ፤ የአንድነታችን ማጥበቂያ ልጓም መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው።
ከዚህም በላይ የተፈጠረው ሠላም ወደ ንግድ ግንኙነት መሸጋገር ችሏል። ይህም አገራቱን የበለጠ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው ይጠበቃል። በተለይም ወደብ ለሌላት ኢትዮጵያ የአሰብ ወደብን መጠቀም ትልቅ እፎይታን የምታገኝ ይሆናል። የኤርትራም ተጠቃሚነት የአንበሣውን ድርሻ የሚይዝ ነው። ወደቡ አገራቱን በምጣኔው ሀብት ዘርፍ ተጋግዘው በጋራ መልማት የሚችሉበትን ትልቅ አቅምና ዕድል ይፈጥራል።
ምጽዋ ከአሰብ ቀጥሎ ሁለተኛው የኤርትራ ወደብ ነው። የሁለቱ አገሮች ድንበር እኤአ በ1998 በጦርነት ምክንያት እስከሚዘጋ ድረስ ለኢትዮጵያ ወጭና ገቢ ንግድ ትልቅ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ወደብ ነበር። በአሁኑ ወቅት ወደቡ ከፍተኛ እድሣት የሚፈልግ ቢሆንም ለሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል ትልቅ የወደብ አገልግሎት መስጠት ይችላል። በተለይም ለምፅዋ ወደብ ቅርብ የሆኑት የትግራይና አማራ ክልሎች ተጠቃሚ ይሆናሉ።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያና ኤርትራ በመካከላቸው የነበረውን ግጭት ለማቆም በይፋ የሠላም ስምምነት መፈራረማቸውን ተከትሎ እየጎመራ የሚታየው ለውጥ አንድነትና መቀራረብ ይበል የሚያሰኝ ነው። ይህ ወደ ቀጥታ ግንኙነት የተሸጋገረው የሁለቱ አገራት ትስስር ከአጎራባች አገራቱ ባለፈ በተለይም ቀጠናው በዓለም የሚታወቅበትን አለመረጋጋትና የሠላም እጦትን ማስቀረት ይችላል።
Prev Post
Next Post
- Comments
- Facebook Comments
Follow Us @ethiopiaprosperous
porn videos