Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በከርሰ ህሊና ውስጥ ባሉ ኃይሎች የተጀመረው ለውጥ አይቀለበስም

0 339

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በከርሰ ህሊና ውስጥ ባሉ ኃይሎች የተጀመረው ለውጥ አይቀለበስም

ሞገስ ተ

የአንድ አገር ምጣኔ ሀብት ሊያድግ የሚችለው በፍትሃዊነት፣ በቅንነትና በታማኝነት ሊሰራና ሊያሰራ የሚችል የምጣኔ ሀብት  ማህበረሰብ ሲፈጠር ነው፡፡ ቀጣይነት ያለው የምጣኔ ሀብት እድገት ሲመዘገብ የአንድ አገር የለውጥ ማሳያ ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ ኢትዮጵያም ቀድሞ ከነበረችበት የምጣኔ ሀብት  ዕድገት ወደ ተሸለ የምጣኔ ሀብት ዕድገት በመሸጋገር ላይ ትገኛለች፡፡

ሽግግሩ ግን እንዲሁ አልጋ በአልጋ ሳይሆን ከፊቷ የተጋረጡ በርካታ ፈተናዎች አሉባት፡፡ እነዚህ ፈተናዎችም ስግብግብነት፣ ራስ ወዳድነትና አልጠግብ ባይነት ናቸው፡፡ እነዚህን ፈተናዎችም በታላቅ አገራዊ የአብሮነት ዕሴት በመገንባት ላይ ያለው መንግስት ታላቅ የቤት ስራዎች መሆናቸው አያጠያይቅም፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ዜጎች በአገራቸው ሃብት ላይ የእኩል ተጠቃሚነት መብታቸው እንዲጠበቅላቸው የዘወትር ምኞታቸው ነው፡፡ ስለሆነም መንግስት ይህን በአንክሮ ተመልክቶ ፈተና ውስጥ የገባውን የምጣኔ ሀብት  ስርዓት ዕልባት ሊሰጠው እንደሚገባ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ይህ ስር የሰደደ የምጣኔ ሀብት ችግር ደግሞ መፍትሄ ካልተበጀለት ጥቂቶች በበላይነት የሚመሩት የምጣኔ ሀብት ስርዓት ሆኖ ይቀጥላል፡፡

ኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ መጠነ ሰፊ ግጭቶችን አስተናግዳለች፡፡ እነዚህ ግጭቶችም ሊከሰቱ የቻሉት በመልካም አስተዳደር እጦትና በአገራዊ ሃብት ላይ የእኩል ተጠቃሚነት መብት ባለመረጋገጡ ነበር፡፡ ከዚህም የተነሳ መንግስት የህዝቡን ስሜት በመረዳት የአመራር ለውጥ በማድረግ የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ስፊ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ በዚህ ተግባሩም ምንም እንኳ አዲሱ አመራር ወደ ስልጣን ከመጣ የሦስት ወር ቆይታ ቢሆንም በጅማሮው ህዝቡ ይበል የሚያሰኝ መሆኑን በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የድጋፍ ሰልፍ በማካሄድ አጋርነቱን ገልጿል፡፡

ይህ አጋርነትም ትልቅ መልዕክት ከበስተጀርበው ይዟል፡፡ መልዕክቱም በአገራችን ሀብት ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይህ እኩል ተጠቃሚነት ግን ሊረጋገጥ እሚችለው በመንግስት ብቻ ሳይሆን ሁሉም ዜጋ የድርሻውን መወጣት ሲችል ጭምር ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን በአንድ እጅ እንደማጨብጨብ ይቆጠራልና፡፡

ምጣኔ ሀብታዊ አሻጥር በመፍጠር የህዝብን የለውጥ ፍላጎት መግታት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ምጣኔ ሀብት ውስጥ ግለሰቦች በሚጫወቱት ቁማር ህዝቡ ላይ ጫና መፍጠሩ አይቀርም፡፡ ስለሆነም ይህንን ጫና የመመከት ኃላፊነት የመንግስት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የተቀጣጠለው ሰላም ለምጣኔ ሀብት  መረጋጋት ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረከተ ይገኛል። ነገር ግን አንዳንድ ሀይሎች የህዝብን የለውጥ ፍላጎት አቅጣጫ ለማስቀየር አስበውና አልመው አርቲፊሻል የገበያ ስርዓት ለመፍጠር ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው፡፡

ይህንን ኣሻጥር “ሳይቃጠል በቅጠል” እንዲሉ ሁሉም ዜጋ አላስፈላጊ የሆነ የዋጋ ጭማሪ በንግዱ ማህበረሰብ ሲከሰት ለምንና እንዴት እንደሆነ በማጣረት ለሚመለከተው አካል መጠቆምና ህጋዊ እርምት አንዲወስዱ ማድረግ ይጠበቃል። ምክንያቱም የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ የማይጥማቸው ኃይሎች ለውጡን ወደ ነውጥ ለመቀልበስ ይሰራሉና  ይህ ደግሞ በማህበረሰቡ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳደሩ ግልፅ ነው።

የስኳር፣ የዘይትና መሰል ሸቀጦች ላይ የዋጋ ጭማሪ ብቻ ሳይሆን የተወሰነ ቦታ በድብቅ አከማችቶ በማስቀመጥ በህዝቡ ላይ ጫና ለማሳደር ቀን ከሌት ለእኩይ ተግባር የሚተጉ ኃይሎች ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ህብረተሰቡ በጋራ በመሆን ሊታገላቸው ይገባል፡፡ ምክንያቱም ይህ ድርጊት ስር ከሰደደ ለግጭትም መንስኤ በመሆን ጥላቻን ሊያባብስ ይችላል፡፡ ስለሆነም ሁኔታዎችን በሰከነ መንገድ በማየት ስህተት መሆናቸውን አስረድተን በመልካሙ መስመር እንዲጓዙ ማድረግ ይጠይቃል፡፡  

በተጨማሪም ህብረተሰቡ እነዚህን በከርስ ህሊና ውስጥ ያሉ ኃይሎችን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ እንዲታረሙ ስለሚገባ መከታተልና መቆጣጠር ይገባል፡፡ ምክንያቱም ድርጊቱ በቸለልተኝነት ሊተው የሚገባ ጉዳይ ስላልሆነ በነቃ ተሳትፎ ማውገዝ የሚቻልበትን ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ መንግስትም የመሰረታዊ የመገልገያ ሸቀጦች እጥረት እንዳይከሰት ተገቢውን ስራ እየሰራ ገበያውን ማረጋጋት ይጠበቅበታል። ስለዚህ ህበረተሰቡ ምንም አይነት መረጃ በፍጆታ እቃዎች ላይ እጥረት አለ ሲባል ጥቆማ ማድረግ ከማንኛውም ህብረተሰብ የሚጠበቅ በመሆኑ በባለቤትነት መያዝ አለበት፡፡ ይህምም አገሪቱ ለተያያዘችው የለውጥ እንቅስቃሴ እንቅፋት መሆኑ አይቀሬ ነውና።

ኢትዮጵያ በተከታታይነት እያስመዘገበችው ላለው የምጣኔ ሀብት ዕድገት በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው የግብርናው ክፍለ ምጣኔ ሀብት  ነው፡፡ ይህ የግብርናው ዘርፍ ደግሞ ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር የምጣኔ ሀብት ስርዓት ለሚያደርገው ሽግግር ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ ዕድገቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ደግሞ ሁሉንም ዜጋ ማሳተፍ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ግብርናው በቴክኖሎጂ የታገዘ ከሆነ ለሚደረገው ለውጥ እንቅስቃሴ ድርሻው የጎላ ነው፡፡ ከግብርናው የምጣኔ ሀብት  ዘርፍ በተጨማሪ ነዳጅ ለአገሪቱ አቅም በመፍጠር ለምጣኔ ሀብት ው ዕድገት የበኩሉን አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡

ለዚህም አብነት ሊሆን የሚችለው በቅርቡ ስራ የጀመረው በሶማሌ ክልል ካሉብና ሂላላ አካባቢ ስራውን የጀመረው የነዳጅ ምርት ነው፡፡ ይህ ነዳጅ ኢትዮጵያ በፖሊ ጂሲኤል የተባለው የቻይና ኩባንያ በሶማሌ ክልል ነዳጅና ጋዝ ለማውጣት መመስረቱ የሚታወስ ሲሆን ነዳጅ ለመውጣት በስፍራው ያለው የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ከስድስት እስከ ስምንት ትሪሊን ኪዩቢክ ድፍድፍ ነዳጅ እንደሚወጣ ይገመታል፡፡ ይህ ደግሞ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል፡፡ በመሆኑም የውጭ ምንዛሬን በመቀነስ ምጣኔ ሀብቱ እንዲሻሻል ያደርጋል፡፡

በኡጋዴን ካሉብና ሂላላ አካባቢዎች ፍለጋውን ሲያካሂድ የነበረው ይህ ድርጅት ሰኔ 21/10/2010 ዓ.ም በይፋ የነዳጅ ማውጣት ስራውን ጀምሯል፡፡ ድርጅቱም በቀን 400 በርሚል ድፍድፍ ነዳጅ እንደሚወጣም ታውቋል፡፡ ነገር ግን ለአንድ አገር የምጣኔ ሀብት  ዕድገት ነዳጅ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ እንደ ግብርናው ዘርፍ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ከአሁን ቀደም ምንም አይነት የነዳጅ ምርት አልነበረም፡፡ ይህም የነዳጅ ምርት በምጣኔ ሀብት ዘርፍ ነበረው ድርሻ ከዚህ ግባ እሚባል አልነበረም፡፡ ከሁሉም ግን ትልቁ እና ወሳኙ ነገር የግብርናው ዘርፍ የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል፡፡ ምክንያቱም አገሪቱ የምትመራው በግብርናው ዘርፍ ነው፡፡ ስለሆነም የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡

በቅርቡ በሶማሌ ክልል የነዳጅ ድፍድፍ መገኘቱን ተከትሎ አንዳንድ የተዛቡ መረጃዎች ህብረተሰቡን በአልሆነ የተሳሳተ ተስፋ ውስጥ እንዲገባ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ እነዚህን የተዛቡ መረጃዎች ደግሞ ህብረተሰቡ ግንዛቤ እነዲኖረው ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም የነዳጅ መገኘት ለአገሪቱ የምጣኔ ሀብት  ዕድገት የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ተጨማሪ ይሆናል እንጂ ለህብረተሰቡ እንደ ፍጆታ እቃዎች የሚቀርብ አይደለም፡፡ ስለዚህ አንዳንድ የተዛቡ የወሬ አራጋቢዎች ለህብረተሰቡ ያልተገባ ወሬ በማናፈስ ውዥንብር ውስጥ ማስገባት የሚፈልጉ ኃይሎች መኖራቸው ስለማይቀር ትክክለኛ መረጃ መያዝ ተገቢነት አለው፡፡

በአገሪቱ ድፍድፍ ነዳጅ መገኘቱ ከረጅም ጊዜ አኳያ ተስፋ ሰጭ ነው ተብሏል፡፡ ነገር ግን አሁን የተከሰተውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ይቀንሳል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ምክንያቱም ገና በጅማሮ ላይ ያለ በመሆኑ መስራት ይጠይቃል፡፡ አንዳንዶች ግን ገና ከጅማሮው የአገሪቱን ችግሮች መፍትሄ የሚያገኙ ይመስላቸዋል፡፡ ዳሩ ግን ትልቅ የቤት ስራ የሚጠይቅ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል፡፡ ስለሆነም ይህ አስተሳሰብ ትክክልኛ አቅጣጫ ይዞ እንዲቀጥል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ወቅቱንና ጊዜውን የዋጀ መረጃ በመስጠት ረገድ ሚዲያውና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፉ በሁኔታው በደንብ መስራትና ማስገንዘብ ይጠበቅበታል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy