Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ብልህነት ነው!

0 486

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

…ብልህነት ነው!

                                                        ታዬ ከበደ

በአገራችን እየተካሄደ ያለው ይቅርታና ፍቅር አገራዊ መግባባትን የሚያጠናክሩ፣ የህዝቦችን አብሮነት የሚያጎለበቱ ናቸው። በአሁኑ ሰዓት መንግስት በርካታ ነገሮችን እያየ በለሆሳስ ማለፍን ስለ መረጠ እንጂ፣ አንዳንድ አካላት የሚፈጽሟቸው ድርጊቶች ከህግ የወጡ መሆናቸው ግልጽ ነው። እነዚህ ተግባሮች መገለጫቸው ህዝቦችን ማሸበር፣ የኢኮኖሚ አሻጥር መፈፀምና አንዱን ብሔር ከሌላው ጋር ማጋጨት የመሳሰሉ ተግባሮች ናቸው።

በእኔ እምነት መንግስት በቀጣይ በእንዲህ ያሉ ኢ-ህገመንግስታዊና ግባቸው ለውጡን ማደናቀፍ የሆኑ ተግባሮችን መታገስ የሚኖርበት አይመስለኝም። ምንም እንኳን የለውጡ አደናቃፊዎች ሴራ ባዶ ሙከራና ከመንግስት እይታ ያልተሰወረ ቢሆንም፣ ሁኔታውን ግን ሳይቃጠል በቅጠል ብሎ መግታት ይገባል። ምክንያቱም በአሁኑ ሰዓት አንዳንድ አካላት መንግስት ሰላምና መረጋጋትን በአገራችን እንዲመጣ እየወሰዳቸው ያሉት እርምጃዎችን መንግስት ተዳክሟል የሚል የተሳሳተ ትርጉም በመስጠት በወንጀል ላይ ወንጀል እየደራረቡ መስራት በመቀጠላቸው ነው።

ሆኖም ይህ አስተሳሰባቸው ትክክል አይደለም። ስለሆነም እነዚህ አካላት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ማሰር፣ ማባረርና መግደል ቀላል ናቸው፤ ነገር ግን አገራዊ መግባባትንና አንድነትን አያመጡም” ያሉትን አባባል በደንብ ተገንዝበው ከተግባራቸው ተቆጥበው ለአገር ሰላም፣ አንድነትና አገራዊ መግባባት መስራት ይኖርባቸዋል።

መንግስት የእነዚህን አካላት ሁሉንም ተግባሮች እየተመለከተ የሚያልፈው ታጋሽና ሆደ ሰፊ በመሆኑ እንጂ፣ እነርሱ እንደሚያስቡት ለውጡን ለማደናቀፍ የሚያደርጉትን ሴራን ስላላወቀ አልያም አቅም ስላነሰው እንዳልሆነ በመገንዘብ እንዲሁም ትዕግስትን መረዳት ብልህነት መሆኑን ተረድተው ከእኩይ ተግባራቸው በመቆጠብ ወደ ትክክለኛው ህጋዊ መስመር መግባት አለባቸው። ከእንግዲህ መንግስት እንዲህ ዓይነት ተግባር የሚፈፅሙ አካላትን እንደማይታገስ መገንዘብም የሚኖርባቸውም ይመስለኛል።

እነዚህ አካላት የአገራችን ህዝቦች በህይወት ዘመናቸው በውስጣቸው ያጎለበቷቸውን የመቻቻል፣ የመከባበርና በሰላም አብሮ የመኖር ትሩፋቶችን በማደብዘዝ ወንድማማች ህዝቦች ውስጥ ቅራኔ የሚፈጥሩ ጉዳዩችን በመጠንሰስ ወይም በማባባስ ይሰራሉ።

በተጨማሪም በተጎራባች ወንድም ህዝቦች አንዳንድ የድንበር አካባቢዎች የተፈጠረው ጊዜያዊ ግጭት በህዝቡ የቀየ የግጭት አፈታት አሰራር ውስጥ እንደምን እልባት ሊያገኝ እንደሚችል ከማሳየት ይልቅ ኃላፊነት በጎደለው መልኩ እሳት ላይ ቤንዚን የማርከፍከፍ ስራን ያከናውናሉ። ልዩነቶችን ከማጥበብ ይልቅ በማስፋፋት በህዝቦች መካከል መቃቃርን ለመፍጠርም ይሰራሉ።

ይህም ለዘመናት ተከባብረው የሚኖሩ ህዝቦችን ወደ አላስፈላጊ ግጭት ውስጥ እንዲገቡ የሚያደርግ ነው። እነዚህ አካላት ጥቅማቸው የተነካባቸውና እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል በሚል የእንስሳ አስተሳሰብ የሚመሩ ናቸው። ይሁን እንጂ ከእንግዲህ እንዲህ ዓይነት ሃሳብ ከእንግዲህ በህዝቡም ይሁን በመንግስት በኩል ምንም ዓይነት ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ማወቅ ያለባቸው ይመስለኛል።

እነዚህ አካሎች በአገራችን ውስጥ የአስተዳደር ወሰንን እንደ ድንበር በመቁጠር አሊያም በማስወት በሁለት ወንድማማች ህዝቦች መካከል ‘እገሌ ድንበርህን ወሰደብህ’ እያሉ ሁከት ለመፍጠር ሲጥሩ ተመልክተናል።

ዶክተር አብይ በቅርቡ እንዳሉት፣ እዚህ አገር ውስጥ የአስተዳደር ወሰን እንጂ ድንበር የሚባል ነገር የለም። ድንበር ያለው በኢትዮጵያና በኤርትራ፣ በኢትዮጵያና በሱዳን ወይም በኢትዮጵያና በኬንያ መካከል እንጂ ለማስተዳደር እንዲያመች በማሰብ በሁለት ክልሎች መካካል የተቀመጠው የአስተዳደር ወሰን አይደለም።

ምንም እንኳን በአገራችን ፌዴራላዊ ስርዓት ውስጥ ኢትዮጵያ የምትከተለው አሰራር በአጎራባች ክልሎች ውስጥ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት የሚከተለው የራሱ ሂደት ያለው ቢሆንም፣ በተለያዩ አካባቢዎች ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮች መኖራቸው አይቀርም።

እነዚህን ችግሮች የህዝቦችን አንድነት በሚያጠናክር መልኩ ማከም እንጂ ወደ ለየለት ቀውስ ውስጥ እንዲገቡ ማድረግ ለማንም የሚበጅ አይደለም። አገርንና ህዝብን የሚጎዳ አደገኛም ተግባር ነው።

ይሁን እንጂ አሁን ያለንበት የለውጥ ሂደት የኋሊት መመለስን የሚፈቅድ አይደለም። እንዲህ ዓይነቱን ህዝብንና አገርን የሚጎዳ ተግባር መንገስተ ከእንግዲህ ሊታገስ የሚገባው አይመስለኝም። የድርጊቱ ዓላማ የተጀመረውን ህዝባዊ ለውጥ ለማደናቀፍ በመሆኑም የለውጡ ባለቤት የሆነው ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በጽናት ሊያወገዘውና ሊታገለው ይገባል። በዚህም በውስጡ ተሰግስገው ድርጊቱን የሚፈፅሙ አካላትን በመለየት ለህግ ማቅረብ ይኖርበታል።

እነዚህ አካላት ግጭቶች በህዝቡ ባህላዊ ልማድ መሰረት ሲወገዱ ወደ ኢኮኖሚ አሻጥረኝነት ሲቀየሩም ተመልክተናቸዋል። በገበያው ውስጥ የዋጋ ንረት እንዲፈጠር መሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችን ይደብቃሉ፣ ያከማቻሉ። በዚህም ሳቢያ ገበያው ላይ የሌለ አርተፊሻል እጥረት እየፈጠሩ ህዝቡን ያማረራሉ።

ሌላው ቀርቶ ቤታቸው ውስጥ ጥሬ ገነዘብ በማስቀመጥ የገንዘብ ዝውውሩ እንዲስተጓጎል በማድረግ ኢኮኖሚውን ለማዳከም ያሴራሉ። ዶላርን በኮንትሮባንድ መነገድ ከአገር ሊያስወጡ ሲሚክሩ በጉምሩክ ሰራተኞች በየጊዜው እንደሚያዙም የወቅቱ ዜና ከሆነ ሰንብቷል። ይህ ሁሉ ጥረታቸው ግን ከመንግስት እይታ የተሰወረ አይደለም። በገሃድ የሚታወቅና በሆደ ሰፊነት የሚታለፍ ነው።

ይሁን እንጂ እነዚህ አካላት አሁንም የኢኮኖሚ አሻጥር ከመፈፀም ስላልተመለሱ ይህን የመንግስት ቻይነት ወደ ሌላ ፅንፍ ከመሄዱ በፊት ተግባራቸውን በማቆም ከህዝቡ እድገት ላይ እጃቸውን ማንሳት የሚኖርባቸው ይመስለኛል። ምክንያቱም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሰሞኑን ለፓርላማ እንደገለፁት፣ አንድን መንግስት አምባገነን የሚያደርጉት የዜጎች ምላሽ ነው። ስለሆነም በዚህ የእርቅና የይቅርታ ዘመን መንግስትን ገፋፍተው ወደ አላስፈላጊ ሁኔታ ከማስገባታቸው በፊት ከተግባራቸው ሊታቀቡ የሚገባቸው ይመስለኛል።

ሁኔታን ተመልክቶ ከችግር ፈጣሪነት ራስን ማቀብ ብልህነት ነው። ከዚህ በተቃራኒው መጓዝ ግን አላዋቂነት ነው። ‘እኔ ያልኩት ብቻ እውነት ነው’ የሚል ከዴሞክራሲ ያፈነገጠ አስተሳሰብ ጊዜው ያለፈበትና ኋላ ቀርነት ነው። እንኳንስ በለውጥ ሂደት ውስጥ ቀርቶ በተረጋጋ ማህበረሰብ ሂደትም ቢሆን ፈፅሞ ተቀባይነት የሌለው አስተሳሰብ ነው። ስለሆነም አንዳንድ አካላት የህዝቡ ፍላጎት የሆነውን ለውጥ ለማደናቀፍ የሚያደርጓቸው ጥረቶች ከባዶ ማሻቶች ውጭ የሚያስገኙላቸው አንዳችም ነገር ባለመኖሩ እጃቸውን ሰብስበው መቀመጥ ብልህነት መሆኑ ሊነገራቸው ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy