Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ተሞክሮው…!

0 363

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ተሞክሮው…!

                                                      ይሁን ታፈረ

የአገራችንን ህዝብ እርስ በእርሱ ለማባላት የተሰለፉት ጥቅማቸው የተነካባቸው ስግብግብ ፖለቲከኞችን በየአካባቢው እያፈናቀሉ ነው። አሁንም ይህ የሴራ ፖለቲካቸው አደብ አልገዛም። ተቻችሎና ተካባብሮ የኖረውን ህዝብ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ እርስ በእርሱ ለማባላት የማይቆፍሩት ጉድጓድ፣ የማይወጡት አቀበትና የማይወርዱት ቁልቁለት የለም። በዚህም ሳቢያ ወንድምን ከወንድም ጋር በስውር ሴራቸው በማባላት ዜጎች ተፈቃቅረው፣ ተሳስረውና ኑሮ መስርተው ከኖሩበት አካባቢ እንዲፈናቀሉ እያደረጉ ነው።

ያም ሆኖ የፌዴራልና የክልል መንግስታት ችግሩን ለመፍታት ትኩረት ሰጥተው በመስራት ላይ ይገኛሉ። በዚህም ተፈናቃዮችን በድብቅ ሴራ አራማጆች ችግር ፈጣሪነት ከተፈናቀሉ በኋላ እንዲደገፉ ብርቱ ጥረት እየተደረገ ነው። ከዚህ አኳያ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እያከናወነ ያለው ተግባር ለሌሎች አካባቢዎች ሊቀመር የሚችል ተሞክሮን የሚያስተላልፍ ነው።

ክልሉ ዜጎችን በማፈናቀል ተግባር ውስጥ ተሳትፈዋል ወይም ሃላፊነታቸውን በአግባብ አልተወጡም የተባሉ የመንግስትና የድርጅት አመራሮችን  ከመባረር እስከ ህግ መጠየቅ የሚደርስ የእርምት እርምጃ ወስዷል። ይህ እርምጃውም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ማስታወቁ አይዘነጋም።

ክልሉ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ተፈናቃዮች ወደ ቀድሞ ቦታቸው እንዲመለሱ ኮሚቴ አቋቁሞ ከመስራት ባሻገር ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ተገቢውን እርዳታ በማድረግ ላይ ይገኛል። ይህ አጥፊዎች ላይ እርምጃ የመውሰድና ተፈናቃዩችን የማቋቋም እንዲሁም ድጋፍ የማድረግ የክልሉ ጠንካራ ስራ ለሌሎች አካባቢዎችም በተሞክሮነት ሊቀመር የሚችል አሰራር ነው።

በእኔ አስተሳሰብ የኦቦ ለማ ቲም የወሰደው እርምጃ የትኛውንም ኢትዮጵያዊ በእኩል ዓይን የሚመለከትና ማንኛውም ዜጋ በየትኛውም የአገሪቱ አካባቢ የመኖር ህገ መንግስታዊ መብትና ዋስትና ያከበረ ነው። ኢትዮጵያዊነትና አንድነት እንዲሁም እኩልነት በክልሉ ውስጥ ምን ያህል ቦታ እንዳለው የሚያሳይና አገራዊ መግባባትን በማጎልበት ረገድ የሚያበረክተውን ሚና ለመረዳት አይከብድም። ስለሆነም ይህን ተግባር የከወነው ክልሉ ሊመሰገንና ሌሎች ክልሎቹም ተግባሩን በአርአያነት ሊወስዱት የሚገባ ነው።

እርግጥ ከማናቸውም ችግሮች በስተጀርባ ግጭቶችን ተገን አድርገው የራሳቸውን አጀንዳ ለማሳከት የሚጥሩ ኃይሎች መኖራቸው ይታወቃል። በጥቂት ጊዜያት ውስጥ በአዲስ መንፈስ የተጀመረውን የሰላም፣ የመልካም አስተዳደርና የአንድነት ጉዞ ለመቀልበስ በመሯሯጥ ላይ የሚገኙ ኃይሎች የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ ሰላምን ለማድፍረስ፣ የዕድገት ግስጋሴያችንን ለማደናቀፍ ደፋ ቀና እያሉ ነው። ተግባራቸው ግን የሚያስገኝላቸው ምንም ውጤት የለም። ይሁን እንጂ እነዚህን ሃይሎች የማያስተናግድ ምህዳር እንዳይኖር ክልሎች ጠንክረው ሊሰሩ ይገባል።

ይህን ለመከወን የተሰጣቸውን ህዝባዊ አደራ መወጣት የማይችሉና የማይፈልጉ፣ ለግል ጥቅማቸው ያደሩ አልፎ…አልፎ ደግሞ ድብቅ የጥፋት ኃይሎች ፖለቲካዊ ተልዕኮ ይዘው በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ ኃይሎችን በቁርጠኝነት መታገል ያስፈልጋል። ከመታገል ባለፈም ልክ የኦሮሚያ ክልል እንዳደረገው የእርምት እርምጃ በመውሰድ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል።

በተለይም ግጭትን ቦታ ለማሳጣት አንድነታችንን ሊያናጉ የሚሹ ሃይሎችን መታገል የግድ ይላል።

እነዚህ ሃይሎች አገራዊ አንድነትን የማይቀበሉ፣ የህዝቦች አንድነት ሳይሆን የድንበር ጉዳይ የሚያሳስባቸው ናቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ የአስተዳደር ወሰን እንጂ ድንበር የሌለ መሆኑን እንኳን በቅጡ ያልተገነዘቡ ናቸው። ወይም ለማወቅ አይፈልጉም።

እነዚህ ሃይሎች የህዝቡን ሃብት ግጠው የበሉና ሁሉንም ለእኔ እና ለእኔ ብቻ በማለት የሚያስቡ ስግብግቦች ናቸው። ማናቸውንም ነገሮች በግላዊነት መንፈስ የሚዝኑ ግለኞች ናቸው። ይህን ጥቅማቸውን የሚነካባቸውን ማንኛውም አካል በድብቅ ሴራቸው ለማባላት ወደ ኋላ አይሉም።

ተቻችለው የኖሩ ህዝቦችን በጥላቻና በጥርጣሬ እንዲተያዩ እንዲሁም ዕድሉን ሲያገኙ እንዲጠቃቁና እንዲጠፋፉ ተግተው የሚሰሩ ናቸው። ከጥቅማቸው ውጭ ስለየትኛውም ህዝባዊ ተጠቃሚነት ደንታቸው አይደለም። የእነርሱን ጥቅም እስካስጠበቀ ድረስ ማንም ቢሞት፣ ቢቆስልና ንብረቱ ቢወድም ጉዳያቸው አይደለም።

እርግጥ ግጭት እንደ እኛ ያለና ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን መርስቶ አንድ የጋራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብን ለመገንት በሕገ መንግስቱ ላይ ሳይቀር ያሰፈረ ህዝብ ውስጥ ቦታ የለውም። የድንበር አስተሳሰብ ቦታ ሊኖረው አይችልም። እዚህ ያለው እዚያ ሄዶ የመስራት፣ እዚያ ያለው እዚህ መጥቶ ካልሰራ የህዝቦች አንድነትና ተጠቃሚነት ሊረጋገጥ አይችልም።

የኦሮሚያ ክልል ተምሳሌታዊ ተግባር ኦሮሚያ ውስጥ ያለው ዜጋ አማራ ክልል ሄዶ፣ አማራ ክልል ያለውም ኦሮሚያ ሄዶ እንዲሁም መስራት እንዳለበት ያስተማረ የአንድነት ማሳያ ነው።

የክልሉ ፕሬዚዳንት ለማ መገርሳ ሰሞኑን ‘ማንኛውም ዜጋ በየሄደበት በየትኛውም ክልል ተዘዋውሮ የመስራት መብት አለው’ በማለት የተናገሩት ለዚሁ ነው። በምክንያትነትም ዜጎች የመንቀሳቀስና በየትኛውም ክልል ሄዶ ሃብት የማፍራት ህገ መንግስታዊ መብት ያላቸው መሆኑን ያስረዱትም እንዲሁ ከዚህ አኳያ የሚታይ ነው።

እርግጥ ህዝቦች በጋራ ሰላም የመሆን፣ በጋራ የመልማትና የማደግ፣ በጋራ ዴሞክራሲን ለማጎልበት እምነትና ፈቃዳቸውን በህገ መንግስታቸው ላይ ሳይቀርገልፀው ሲያበቁ፤ በጥላቻና በተሳሳተ አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ ተግባር ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም።

በአሁኑ ወቅት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ለተፈናቃዩች ድጋፍ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ነው። ክልሉ ተፈናቃዩችን በመደገፍ ረገድ የሚያከናውነው ተግባር እጅግ አበረታችና ለሌሎችም ተሞክሮ የሚሆን ነው።

ሆኖም ተፈናቃዩችን የመደገፍ ተግባር የክልሉ መንግስት ብቻ አይመስለኝም። አርአያነቱ ወደር የማይገኝለት ቢሆንም፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በተለመደው ኢትዮጵያዊ ባህልና ጨዋነት ከኦሮሚያ ብቻ ሳይሆን ከየትኛም ቦታ ለሚፈናቀል ዜጋ ድጋፍ ሊያደርግ የሚገባ ይመስለኛል። ይህም የክሉን ተነሳሽነት ይበልጥ የሚያጎለብትና ሌሎች ክልሎችም በተምሳሌትነት ተግባሩን በፍጥነት እንዲቀምሩት በር የሚከፍት ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy