Artcles

ተቋማቱና የህዝብ እርካታ

By Admin

July 24, 2018

ተቋማቱና የህዝብ እርካታ

                                                        ይሁን ታፈረ

ህዝቡን እያማረሩ ያሉትን አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ለመፍታት አንዳንድ የመንግስት ተቋማት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰዱ ነው። ይሁን እንጂ አሁንም የሚፈለገውን ያህል እርካታ መፍጠር አልተቻለም። ስለሆነም ችግሮቹን ለመፍታት አፋጣኝ እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል።

በተለይም የህብረተሰቡ የዕለት ተዕለት መጠቀሚያ የሆኑ እንደ መብራት ሃይል፣ ውሃና ቴሌ የመሳሰሉ ተቋማት ችግሮቻቸውን በመፍታት የህዝቡን እርካታ መፍጠር ይኖርባቸዋል። ችግሮቹ ሲፈጠሩም የተፈጠሩበትንን ሁኔታ ከነምክንያታቸው በፍጥነት ለህብረተሰቡ ማሳወቅና ማስረዳት አለባቸው።

ችግሮቹ በሂደት እልባት የሚያገኙ ከሆኑም ይህንኑ በቀዳሚነት ለህዝቡ በማሳወቅ ግልፅነት የሰፈነበትን አሰራር መፍጠር ይጠበቅባቸዋል። እንዲህ ዓይነቱ አሰራር በህዝብ ሃብት የሚንቀሳቀሱ ተቋማት ህዝብን በማክበር ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ የሚያደርግ እንደሆነም ሊገነዘቡ ይገባል። ታክስ ከፋዩን ህዝብ ማክበር የመልካም አስተዳደር ተቀዳሚው ተግባር ነውና። ህዝቡም በእነዚህ ተቋማት ውስጥ የመልካም አስተዳደር ችግር ፈጠር ለምንና እንዴት ብሎ መጠየቅ አለበት።

እንደሚታወቀው ሁሉ ባለፉት ዓመታት የመልካም አስተዳደር ጉዳዩች የህዝቡን እርካታና አመኔታ ሊያተርፉ ባለመቻላቸው መንግስት በየደረጃው በአስፈፃሚዎቹ ላይ የተለያዩ ርምጃዎችን ከመውሰድ አልቦዘነም። በጥናት ላይ ከተመሰረተና የችግሩ ምንጭ ምንና የት መሆናቸውን ከማወቅ ባሻገር፣ በፌዴራልም ይሁን በክልል ደረጃ ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ አስተማሪ ርምጃዎችን ወስዷል።

ለመልካም አስተዳደር ተፈፃሚነት ማነቆዎች ናቸው የሚባሉትን ችግሮች ሊቀይሩ የሚችሉ አሰራሮችን በመዘርጋት ረገድም ብዙ ርቀት መጓዝ ተችሏል። ሆኖም አሁንም ከላይ በጠቀስኳቸው መስሪያ ቤቶች ውስጥ መሻሻል አይታይም። ይህም አሁንም የህዝቡን እርካታ መፍጠር አልቻለም።

እርግጥ በማንኛውም አገር ውስጥ መልካም አስተዳደር የሚታሰበው ስርዓቱ ተግባሩን ለማከናወን ካለው በጎ ምልከታ አኳያ ነው። ምንም እንኳን በአገራችን የተፈጠረው ለውጥ መልካም አስተዳደርን በሂደት ለመፈፀም ቁርጠኝነት ቢኖረውም፤ ይህ የለውጡ ቁርጠኝነት ወደ አስፈፃሚው አካል በተለይም ወደ ታችኛው የስልጣን እርከን እየወረደ በሄደ ቁጥር የመሸርሸር ሁኔታ እየተስተዋለ ነው።

በአንዳንድ የታችኛው የስልጣን እርከን ላይ የህዝብ መሆኑ ተዘንግቶ ፈፃሚዎች እንዳሻቸው ህዝቡን ያንገላቱታል። ከአቅም ማነስ በመነጨም ለህዝቡ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ አይሰጡም። እናም ከመልካም አስተዳደር አሁንም ያልተፈቱ ችግሮች መፈታት አለባቸው።

አስፈፃሚዎች ራሳቸው የመልካም አስተዳደር ችግር ፈጣሪዎች ሆነው ሳለ በራሳቸው ምክንያት ምክንያት የሚሰጡ አካላትን በመለየት የህዝቡን እርካታ ማረጋገጥ ይገባል። መልካም አስተዳደር የተግባር እንጂ የወሬ ጉዳይ ባለመሆኑ አስፈፃሚዎች ሰርተው ህዝባዉ ርካታን መፍጠር አለባቸው።

ህዝባዊ እርካታን ለመፍጠር የስልጣኑ ባለቤት የሆነውን ህዝብ በጉዳዩ ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ ማድረግ አለበት። ይህም የመልካም አስተዳደር ጉድለት ያለበት የትኛውም ተቋም ህዝቡ በህገ መንግስቱ የተጎናፀፈውን ስልጣን በአግባቡ እንዲረዳና የእርሱም ተቀጣሪ መሆኑን እንዲገነዘብ የሚያደርገው ነው።

ተቋማቱ ለህዝቡ ጥያቄ ፈጣን ምላሽ የሚሰጥበትን ማዕቀፍ ማበጀት አለባቸው። ስለሆነም ህብረተሰቡ ከተቋማቱ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት በመመስረት የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ሃላፊነቱን መወጣት አለበት። ይህን አሰራርም ተቋማቱ ከሌላቸው መፍጠር ይኖርባቸዋል።

ይሀም ችግሮች በህዝቡ ውስጥ እንዳይጠራቀሙና አመኔታን ማስገኘት የሚያስችሉ ናቸው ችግሮችን በቅንነት ተቀብሎ ከስር ከስር ለመፍታትም ያግዛል። ስለሆነም ህዝቡን በማሳተፍ የሚከሰቱ ችግሮችን ፈጥኖ ማረም ያስፈልጋል።

ችግሮች እንዳይከማቹና በህዝቡ ውስጥ የቅሬታ መነሻ እንዳይሆኑ ተቋማቱ ጠንክረው መስራት አለባቸው። በአሁኑ የለውጥ ወቅት ህዝብን ማዕከል ያደረጉ፣ የተሟሉና ሊያስሩ የሚችሉ አሰራሮች ተፈጥረዋል። እነዚህን የህዝብ ተጠቃሚነት ማዕቀፎች መተግበር ይገባል። አንዳንዱ ችግር ሆን ተብሎ ባለማስፈፀም ጭምር የሚገለፅ ነው። ሰንካላ ምክንያቶች የአፈጻጸም ችግር ማሳያዎች እየሆኑ ነው። እናም ለህዝብ መስራት ክብር በመሆኑ የህዝቡን እርካታ በሚያረጋግጡ ጉዳዩች ላይ መስራት እንደሚያስፈልግ ተቋማቱ መረዳት አለባቸው።

እርግጥ ህዝቡ የመልካም አስተዳደር ችግር ፈጣሪዎች የትኛዎቹ ተቋማት እንደሆኑ በዕለት ተዕለት ህይወቱ የሚያጋጠመውን የመልካም አስተዳደር ችግርም ጠንቅቆ ያውቃል። በእነዚህ ተቋማት ላይ ህዝቡን ማዕከል ያደረገ ትግል በማካሄድ መንግስት እያደረገ ያለውን ጥረት መደገፍ ያስፈልጋል።

ህዝቡ በትግሉ ውስጥ እንዲሳተፍ ለማስቻል በአስፈፃሚ መስሪያ ቤቶች ውስጥ ህዝብን የሚያሳትፍ አሰራር መዘርጋት ይገባል። የአሰራር ስርዓት ከተዘረጋ እያንዳንዱ አስፈፃሚ ተግባሩን በስርዓቱ መሰረት እንዲፈፅም ያስችላል።

ህዝቡ በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ቁርጠኛ አቋም መያዝ አለበት። መንግስት ያለ ህዝቡ ቀጥተኛ ተሳትፎ ምን ሊያደርግ አይችልም። አሁንም ቢሆን ከህዝቡ ጋር የተጀመረው የፊት ለፊት ውይይትን መሰረት በማደረግ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የሚፈጥሩ ተቋማትን ማሳሰብ ይገባል። በዚህም ተቋማቱ የሚታወቅ የአሰራር ስርዓትን እንዲፈጥሩ ማድረግ ይቻላል።

በአሰራር ስርዓት የሚመራ ማንኛውም ተቋም በተቀመጠለት ህግና ስርዓት ብቻ ተግባሩን ይፈፅማል። በዚህ መንገድ ህዝባዊ አገልጋይነቱን የሚያረጋግጥ ማንኛውም አመራር ይሁን አስፈፃሚ ችግር የሚፈጥርባቸውን ቀዳዳዎችን ሊያገኝ አይችልም።

ምናልባትም ቀዳዳዎች ካሉ ተቋሙ በተገልጋዩ መገምገሙ ስለማይቀር የሚኖረው ክፍተት ይሸፈናል። ይህም በተቋማቱ ውስጥ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለውጥ እንዲኖራቸው ያግዛል። ሆኖም አሁንም ቢሆን ተቋማቱ የህዝቡን እርካታ ለመፍጠር መስራት ይኖርባቸዋል።