Artcles

ችግር ፈቺዎቹ

By Admin

July 24, 2018

ችግር ፈቺዎቹ

                                                         ሶሪ ገመዳ

በክረምቱ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ወጣቶች በደም ልገሳ፣ አቅመ ደካሞችን በመደገፍ፣ የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በጽዳት፣ በትራፊክ ደህንነት የነፃ አገልግሎት እየሰጡ ነው። ይህ ለአገርና ለወገን እየሰሩ ያሉት ተግባር ሊበረታታ የሚገባው ነው።

ወጣቶች እየሰጡት ካለው የነፃ አገልግሎት በላይ ለአገራቸውና ለወገናቸው በማገልገላቸው ኩራትና የህሊና እርካታ እንዲጎናጸፉ የሚያደርግ ነው። በስራው ላይ ያለተሳተፉ ሌሎች ወጣቶችም አርአያውን መከተል ያለባቸው ይመስለኛል።

ስለሆነም በተለይ በአሁኑ ወቅት ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው እየወጡ ያሉ ተማሪዎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ አቅም መሆን ይችላሉ። ይህም ወጣቶች መልካም ስብዕናን በመላበስ የማህበረሰቡ ችግር ፈቺዎች እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።

ወጣቶች መንግስት የአገሪቱን ህዝብ የሚለውጥ ዕቅድ አቅዶ እየሰራ መሆኑን ያውቃሉ። ወጣቶች በእነዚህ የልማት ዕቅዱ ዓመታት የስራ ባህላቸውንና ተነሳሽነታቸውን እንዲሁም የቁጠባ ባህላቸውን እያዳበሩ ነው። ይሀን የልማት ዕቅድ የመደገፍ አገራዊና ህዝባዊ ግዴታ አለባቸው።

ወጣቶች ስርዓቱ የእነርሱ እንደ መሆኑ መጠን ሊጠብቁት ይገባል። በተለያዩ ጊዜያት እያሰለሱ በየአካባቢው የሚታዩ ግጭቶች መነሻቸውና መድረሻቸው የግል ጥቅማቸውን ለማሳደድ የሚሹ ጸረ ለውጥ አካላት የሚነሱ መሆናቸው ግልፅ ነው። እነዚህን አካላት በመቆጣጠር የአገራችን ልማት እንዲፈፀም ማድረግ አለባቸው።

እንደሚታወቀው ሁሉ የማናቸውም ችግሮች መፍትሔ የሚመነጨው በአገሪቱ በለውጥ ሃይል እንጂ የራሳቸውን አጀንዳ ለማራመድ ሲሉ በህዝቦች ስቃይ ትርፍ ለማጋበስ በሚፈልጉ ሃይሎች አለመሆኑን ወጣቶች ያውቃሉ።

ስለሆነም መንግስት የአዳዲስ ልማታዊ ሃሳቦችና አሰራሮች አመንጪ ብሎም ለወጣቶች ችግር የሚደርስ ህዝባዊ አካል መሆኑን በመገንዘብ ከእነዚህ ሃይሎች አሉባልታ በመራቅ የእነርሱ እኩይ ዓላማ መጠቀሚያ ላለመሆን መትጋት አለባቸው። ከአሉባልታው ለመራቅም በአሁኑ ወቅት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት መሳተፍ ነው።

ወጣቶች በምንም ምክንያት የእኩይ ሴራ አራማጆች መጠቀሚያ መሆን የለባቸውም። ይህን ሥርዓት ታግለውና መስዋዕት በመክፈል ጭምር ያመጡት ወጣቶች ናቸው። ወጣቶች ሰላማቸውን እያረጋገጡ ድህነትን በመቅረፍ ተግባር ላይ መሰለፍ አለባቸው። ከዚህ ተግባር ውስጥ አንዱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ነው።

ወጣቶች በአሁኑ ሰዓት ሆን ተብሎ በአንዳንድ አካባቢዎች የአገራችንን ሰላም ለማወክ በሁከት ጠንሳሽ አካላት የሚቀነባበር እኩይ ሴራ መኖሩን ማወቅ አለባቸው። እነዚህ አካላት የራሳቸውን ውሸት እየጨመሩ ማናቸውንም አገራዊ ችግሮች እያቀጣጠሉ ነው።

ስለሆነም ወጣቶች ይህን እኩይ ሴራ ተገንዝበው የእነርሱን ማንነት ሊታገሏቸውና ቅስቀሳቸውን ሊያከሽፉ ይገባል። ወጣቶች ይህን ማድረግ ካልቻሉ በፌዴራላዊ ሥርዓቱ ያገኙት የነበረውን ሁለንም ጥቅሞች ሊያጡና ወደ ድሮው ዘመን ሊመለሱ ይችላሉ።

ስለሆነም በአንድ በኩል እነዚህን ሃይሎች በመታገል ለውጡን የማስቀጠል በሌላ በኩል ደግሞ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመሳተፍ ድህነትን ለመግታት በሚደረገው ትግል ውስጥ እንደተለመደው ቀዳሚ ተሰላፊ መሆን ይኖርባቸዋል።

ወጣቶች የዚህ አገር ችግር ፈቺዎች ናቸው። ወጣቶች የዛሬ አፍላ የልማትና የዴሞክራሲ ኃይሎችና የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጎች እንደመሆናቸው በትምህርት የታነፀና የተገነባ አቅም እንዲኖራቸው ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷል።

የወጣቶችን ሁለንተናዊ ብቃት በማሳደግ በሀገሪቱ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና መልካም ልማታዊ አስተዳደር ግንባታ እንዲሁም በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ልማት እንቅስቃሴዎች ውስጥ በተደራጀና በተቀናጀ አኳኋን የነቃና ግንባር ቀደም ተሳትፎ እንዲያደርጉና ከውጤቱም በተገቢው መንገድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መንግስት ቁርጠኛ አቋም ይዟል።

የአገራችን ወጣቶች አካበባቢ ከሥራ ስምሪት ጋር ተያይዞ የሚታየውን የተሳታፊነትና ፍትሐዊ ተጠቀቃሚነት ጥያቄ ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት እየተደረጉ መሆናቸውን መረጃዎች ያስረዳሉ።

የእኛ አገር ወጣቶች ከችግር ፈቺነታቸው ባሻገር የነገ ባለተስፋ ናቸው። በትግላቸው ባመጡት ውጥ ከሰማይ በታች ይህን ተስፋቸውን የሚያመክን አንዳችም ሃይል የሚኖር አይመስለኝም። እናም ወጣቶች ይህን ብሩህ ተስፋ በሚገባ በመመልከት እንደ የበጎ ፈቃድ ዓይነት አገልግሎቶች ላይ በስፋት መስራት ይኖርበታል።

እርግጥ ቀደም ባሉት ጊዜያት በመንግስት የስልጣን መዋቅር ውስጥ በተፈጠረው የመልካም አስተዳደር ችግርና ኢ-ፍትሐዊነት ሳቢያ ወጣቶችን በተገቢው መንገድም ከልማቱ ተጠቃሚ ያደረገ አይደለም።

ይህም ወጣቶች ለትግል እንዲነሳሱና ለውጡ እንዲፈጠር አድርገዋል። በአሁኑ ወቅትም በራሳቸው ትግል ያመጡትን ለውጥ በማህበራዊ አገልግሎት መደገፍ አለባቸው። ከእነዚህ ማህበራዊ አገልግሎቶች ውስጥ በክረምት ወራት የሚከናወነው የበጎ ስራ አገልግሎት በመሆኑ ስራው ላይ ያልተሳተፉ ወጣቶች ዛሬውኑ መሳተፍ ይኖርባቸዋል።

ይህል ለመፈፀም ምንም የሚያግዳቸው ነገር የለም። ምክንያቱም ወጣቶች በተፈጥሯቸው ሁሉንም ነገር የመስራት ስሜት የታደሉ ስለሆኑ ነው። እናም በማናቸውም አገራዊ የልማት ትልሞች ውስጥ መሳተፍ አለባቸው።

ይህ ደግሞ የተያዙ ዕቅዶችን ለመፈፀምና የሚፈለገውን ሀገራዊ ዕድገት ለማምጣት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል። ስለሆነም ወጣቶችን አነሳስቶ በማሰራት ረገድ በክረምቱ ወራት በተለይም ከዩኒቨርስቲ የሚወጡ ተማሪዎችን መጠቀም ይገባል።

ቀደም ሲል እንደገለጽኩት ወጣቶች የዚህች አገር ገንቢዎች ናቸው። አገራችንን ከድህነት ለማውጣት በሚደረገው ትግል ችግረ ፈቺዎች ሆነው መንቀሳቀስ አለባቸው። እንደ ኢትዮጵያ ያለ በርካታ ቁጥር ወጣት ያለው አገር በየጊዜው የወጣቶችን አቅም ቢጠቀም ልማታዊ ፋይዳው ከፍተኛ ነው። ስለሆነም ወጣቶች በአገራቸው ያመጡትን ለውጥ በበጎ አገልግሎት ስራዎች እየደገፉ ለውጡ ተጠናክሮ እንዲሄድ ማድረግ ይችላሉ።

በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ የሚሳተፉ ወጣቶች አገራቸውንና ህዝባቸውን ከመጥቀም ባሻገት የህሊና እርካታንም ያገኛሉ። አገራቸው የምትገኝበትን የኢኮኖሚ ሁኔታንም ይደግፋሉ። ስለሆነም በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ ያለተሳተፈ ወጣት በችግር ፈቺነት የስራው አካል ለመሆን ዛሬውኑ መመዝገብ ይኖርበታል።