Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አንድ ህዝብ፣ ሁለት ሃገር

0 818

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አንድ ህዝብ፣ ሁለት ሃገር

አባ-ዲዱ ቢሊሳ

ሰሞኑን በኢትዮጵያና በኤርትራ መሃከል ያለው ግንኙነት ባለፉት ሃያ ዓመታት ከነበረው ፍጹም የተለየ ገጽታ ይዟል። የኢትዮጵያና የኤርትራ (ምድሪ ባህሪ) ህዝቦች  ወንድማማችነት በሺህ የሚቀጠሩ ዓመታትን የተሻገረ ነው። የእነዚህ ሃገራት ህዝቦች እንደ ሁለት የሚታዩም አይደሉም፤ አንድ ናቸው። ፍጹም ተመሳሳይ ቋንቋ ይናገራሉ፣ በተመሳሳይ ባህልና ወግ አይኖራሉ፣ ሰፊ የጋራ ታሪክ አላቸው፣ በመልከዓ ምድርም ይዋሰናሉ። በመጀመሪያ ኤርትራን ኢትዮጵያን የለያት የአውሮፓ ቅኝ ግዛት ነው። አውሮፓዊቷ ጢሊያን ከተደጋጋሚ ሙከራ በኋላ በ1860 ዎቹ ተሳክቶላት ኤርትራን  መቆጣጠር ቻለች። ኤርትራን ነጻ መንግስት አድርጎ ለሁለተኛ ጊዜ የለያት ደግሞ በኢትዮጵያ የነበሩ አምባገንን የመንግስት ስርአቶች በህዝቡ ላይ የጫኑት ጭቆና ነው።

የጣሊያን የቅኝ ግዛት ህልም በኤርትራ የተገደበ አልነበረም። የተቀረውንም የኢትዮጵያ አካባቢ በቅኝ ግዛትነት የመያዝ ህልም ነበረው። ይሁን እንጂ በቀይ ባህር በኩል ዘልቆ የኤርትራን ደጋማ አካባቢ የተቆጣጠረው የጣሊያን ወራሪ ሃይል ወደደቡብ የሚያደርገው ግስጋሴ መረብን አሻግሮ የቅኝ ግዛት መሬት ማግኘት አልቻለም። የጣሊያን ወራሪ ሃይል አድዋ ላይ ድል ተመታ። በወቅቱ የነበረው የኢትዮጵያ ሃይል ወራሪውን ጢሊያን ከዚያ አልፎ ከምድረ ባህሪ (ኤርትራ) ምድር ጠራርጎ ማስወጣት የሚያስችል አቅም አልነበረውም። የኢትዮጵያ ሃይል ነጻ የማውጣት ጉዞውን ወደምርሪ ባህሪ ቢቀጥል ኖሮ፣ የቀረውንም የሃገሪቱን ክፍል ማስጣል በማይችልበት ሁኔታ ሊመታ ይችል እንደነበረ ታሪክ ያስረዳል።

ያም ሆነ ይህ፤ ራስ አሉላ ጢሊያንን ድባቅ የመቶባቸው ዶጋሊና ጉንደት፤ የጣልያን ሃይል ቀይ ባህርን አልፎ ብቅ ሲል ተንደርድረው ለመምታት እንዲመቻቸው የከተሙባት አስመራን የያዘችው ምድረ ባህሪ (ኤርትራ) ከነህዝቧ የጣሊያን ቅኝ ግዛት ስር ወደቀች። እናም የዳግማዊ ምኒሊክ ኢትዮጵያ፣ ከምድሪ ባህሪ ዜጎቿ መነጠልን ለመቀበል ተገደደች። የኤርትራ ምድር በጢሊያን ስር ብትወድቅም፣ የኤርትራ ህዝብ ግን ከወንድሞቹ ኢትዮጵያውያን አልተነጠለም፤ በአካልም በመንፈስም። ኤርትራ በጣሊያን ቅኝ ግዛት ስር በነበረችባቸው ዓመታት ኤርትራውያን ወደኢትዮጵያ እየመጡ በፈለጉት የሃገሪቱ አካባቢዎች ይኖሩ ነበር። ወደኢትዮጵያ ይመጡ የነበሩ ኤርትራውያን፣ ኢትዮጵያዊነት ለማግኘት ጥያቄ ማቅረብ አይጠበቅባቸውም ነበር። ከተቀረው ነጻ የኢትዮጵያ ምድር፤ ወለጋ፣ ጎንደር፣ ቤኒሻንጉል ወዘተ  ተነስተው በሌላ የሃገሪቱ አካበቢዎች የሚኖሩ ዜጎችን ያህል የማይጠየቅ የኢትዮጵያዊነት መብት ነበራቸው። ይህ እውነታ የኢትዮጵያውያንና የኤርትራውያን ወንድማማችነት ምን ያህል የማይበጠስ ረጅም ስር እንዳለው ያሳያል።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የፋሽስት ጣሊያን፣ ጀርመንና ጃፓን ህብረት፤ በአሜሪካ፣ ሩሲያ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ቻይና ካናዳ . . . ህብረት ሲመታ ጢሊያን ሁሉንም በቅኝ ግዛት የያዘችውን ምድር በሃይል ለቃ ወጣች። በዚህ ጊዜ ጢሊያን ኤርትራንም ለቃ ወጣች፤ በ1934 ዓ/ም። ጢሊያን ኤርትራን ለቃ ብትወጣም የእንግሊዝ ወታደራዊ ሃይል ሞግዚት ሆና በጢሊያን እግር ተተካ። ይሄኔ የኤርትራ ህዝብ ከኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ ጋር ተዋህዶ ለመኖር ትግሉን አጧጧፈ። ኤርትራን ከኢትዮጵያ የማዋሃድ እንቅስቃሴውን በግንባር ቀደምትነት ይመራ የነበረው የሃገር ፍቅር ማህበርም በዚህ ወቅት ጎልቶ ወጣ። በዚህ ወቅት ኤርትራውያን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን ያሳዩ ነበር።

እኔ የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ የኢትዮጵያ አካል በነበረችው ኤርትራ ለጥቂት አመታት ኖሬ ነበር። በዚህ ወቅት በአስመራ ከተማ የቀብር ስርአት ሲፈጸም ለቀስተኞች ከአስከሬን ፊት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ እያውለበለቡ ይሄዱ እንደነበረ ተመልክቻለሁ። ኤርትራውያን የነጻነት ጥያቄ አንስተው መራራ የትጥቅ ትግል በማካሄድ ላይ በነበሩበት በዚያ ወቅት፣ ይህ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ የማውለብለብ ነገር ግራ ቢገባኝ፣ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ለማወቅ አዛውንቶችን ጠየኩ። ይህ ልምድ ኤርትራ በእንግሊዝ ሞግዚትነት ስር በነበረችበት ወቅት የኢትዮጵያዊነትን ስሜት ለማንጸባረቅ ተጀምሮ በዚያው ወግ ሆኖ የቀረ መሆኑን አጫወቱኝ። ልብ በሉ የኤርትራውያን የኢትዮጵያዊነት ስሜት ይህን ያህል ጥልቅ ነው።

ይህ የኤርትራ ህዝብ ጥያቄና ትግል እ ኤ አ በ1944 ዓ/ም ተሳክቶ ኤርትራ በህዝበ ውሳኔ በፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ጋር ተቀላቀለች። ኤርትራ የራሷ ፓርላማ ኖሯት ራስዋን በራስዋ እያስተዳደረች ነበር ከኢትዮጵያ ጋር የተዋሃደችው። ይሁን እንጂ ብዝሃ ብሄር ኢትዮጵያን በፈላጭ ቆራጭ ንጉሰ ነገስት ሲያስተዳድር የነበረው ዘውዳዊ ስርአት፣ ኤርትራ በተለይ ያገኘችው ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ወደሌሎቹም ብሄሮች ሊዛመት ይችላል የሚል ስጋት ስላሳደረበት የፓርላማውን ውሳኔ አግቶ ኤርትራን እንደአንድ ጠቅላይ ግዛቱ ከኢትዮጵያ ጋር አዋሃዳት፤ እ ኤ አ በ1955 ዓ/ም። ይህ ሁኔታ ኢትዮጵያዊነታቸውን የሚወዱትን ኤርትራውያን አላስደሰተም። እናም የነጻነት ትግል ጀመሩ። ከሶስት አስርት ዓመታት ከፍተኛ የህይወት መስዋዕትነት የጠየቀ የነጻነት ትግል በኋላ ኤርትራ በ1983 ግንቦት 18 ከኢትዮጵያ አምባገነን ገዢዎች መዳፍ ወጣች። ለሁለት ዓመታት ያህል በዴፋክቶ እውቅና ቆይታ በ1885 ዓ/ም በተካሄደ ህዝበ ውሳኔ ከ99 በመቶ በላይ የናጽነት ድጋፍ ድምጽ፣ ኤርትራ ነጻ መንግስት ሆና ተመሰረተች። አንድ የሆነው የሁለቱ አካባቢ ህዝብ ዳግም ተከፈለ። አንድ በቅኝ ገዢዎች፤ ሁለት ነጻነትን ለማግኘት።

በዚህ ሁሉ ሂደት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ህዝብ መሃከል ያለው ግንኙነት አንድም ችግር አልገጠመውም። በኤርትራና በተቀሩት የኢትዮጵያ አካባቢዎች አብረው ይኖራሉ፣ ጋብቻ ይፈጽማሉ፣ በአበልጅነት፣ በጡት መጥባት፣ በሞጋሳ ዝምድና ይመሰርታሉ፣ አብረው በሽርክና ይነግዳሉ፣ አብረው እድርና እቁብ ያደራጃሉ፣ ከቄስ ትምህርት ቤት እስከ ዩኒቨርሲቲ አብረው ይማራሉ . . .። ይህ ብቻ አይደለም የኤርትራ የነጻነት ታጋዮች ከኢትዮጵያውያን የነጻነት ታጋዮች ጋር ነጻነትን መሰረት ያደረገ የዓላማ አጋርነትም ነበራቸው። አብረው በአንድ ግንባር ተዋግተዋል፤ አብረው ወድቀዋል፤ በአንድ ጉድጓድም ተቀብረዋል።

በአጠቃላይ ኤርትራን ከኢትዮጵያ የለያት ከአምባገነን ዘውዳዊና ወታደራዊ ስርአት ነጻ የመውጣት ፍላጎት እንጂ ህዝቡ ሊለያይ በማይችልበት ሁኔታ የተጋመደ ነው፤ እንደሰርገኛ ጤፍ ሊለያይ በማይችል ሁኔታ የተሰባጠረ ነው። ኤርትራ በ1985 ዓ/ም ነጻ መንግስት ሆና መመስረቷም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ላይ አንዳችም ተጽእኖ አላሳረፈም። ይሁን እንጂ ይህ በቅኝ ግዢዎችና በአምባገነን መንግስታት ያልደበዘዘ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በ1990 ዓ/ም ድንገት ቡዳ በላው። ኢትዮጵያና ኤርትራ በድንበር ምክንያት አለመግባባት ውስጥ ገቡ። ይህ አለመግባባት ወደወታደራዊ ግጭት፣ በኋላም ወደአጠቃላይ ጦርነት ተሸጋገረ።

ይህም ቢሆን ግን የሁለቱ ህዝቦች ወንድማማችነት ላይ ተጽእኖ አላሳረፈም። የሁለቱ ሃገራት ግጭት ሲቀሰቀስ በርካታ ኤርትራውያንና ትውልደ ኤርትራውያን በኢትዮጵያ የኖሩ ነበር። በርካታ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንም በኤርትራ ይኖሩ ነበር። የግጭቱን መቀስቀስ ተከትሎ ሁለቱም ሃገራት የደህንነት ስጋት ሊሆኑ ይችላሉ ያሏቸውን  አንዱ የሌላውን ዜጎች ከሃገራቸው ሲያስወጡ የነበረው አሸኛኘት የሁለቱ ሃገራት ህዝቦች ትስስር ምን ያህል ጥብቅ እንደሆነ ያሳያል። በኢትዮጵያ የነበሩት ኤርትራውያን ሲሸኙ ሁለቱ ሃገራት ጸብ ውስጥ የገቡ አይመስሉም ነበር። ኢትዮጵያውያን ዘመዶቻቸው፣ ጎረቤቶቻቸው፣ የንግድ ሸሪኮቻቸው፣ የስራ ባልደረቦቻቸው ወዘተ እያለቀሱ ነበር የሸኟቸው።

ጦርነቱ አብቅቶ የግጭቱ መንስኤ የሆነው የድንበር ጉዳይ እልባት ሳይበጅለት ሁለቱ ሃገራት ሰላምም ጦርነትም ያልሆነ ወይም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ እንደገለጹት ሞት አልባ ጦርነት ውስጥ በቆዩባቸው ዓመታትም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ምንም አልቀዘቀዘም። በርካታ ኤርትራውያን ወደኢትዮጵያ ይመጡ ነበር። ኤርትራውያኑ በራሳቸው ቋንቋና ባህል መኖር በሚችሉባት ኢትዮጵያ ባይተዋርነት ሳይሰማቸው እንደሃገራቸው ሲኖሩ ቆይተዋል። የኢፌዴሪ መንግስት ለኤርትራውያን ስደተኞች ከሌሎች ሃገራት ስደተኞች በተለየ በሁሉም የሃገሪቱ አካባቢዎች ካለምንም ገደብ ከህዝቡ ጋር – ከዘመዶቻቸው ጋር መኖር እንዲችሉ በአዋጅ ፈቅዶላቸዋል። ኤርትራውያን ስደተኞች አዲስ አበባም፣ አዳማም፣ መቀሌም፣ አድዋም፣ ወዘተ እንደኢትዮጵያዊ ሲኖሩ ቆይተዋል። ከዚህ በተጨማሪ ኤርትራውያን ወጣቶች እሰከ ሁለተኛ ዲግሪ ድረስ በመንግስት የትምህርት ተቋማት የነጻ የትምህርት እድል ሲሰጣቸው ቆይቷል። በጋብቻና በአበልጅነት፣ በጉርብትና መዛመዱም እንደቀጠለ ነበር።

የቀደሙት የኢፌዴሪ ጠቅላይ መኒስትሮች በሁለቱ ሃገራት መንግስታት መሃከል ያለውን ግንኙነት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን በሚመጥን አኳኋን የማሻሻል ፍላጎት የነበራቸው ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች አልተሳካላቸውም። ጠቅላይ መኒስትር ዶ/ር አብይ ወደስልጣን መውጣታቸውን ተከትሎ፣ በበዓለ ሲመታቸው ላይ ባደረጉት ንግግር ለኤርትራ መንግስት ያስተላለፉት የሰላም ጥሪ ግን ተሳክቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ድንቅ ስኬት ተመዝግቧል።

የኤርትራ መንግስት የሃገሪቱን ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችን ያካተተ ልኡክ ወደኢትዮጵያ በመላክ የመንግስታቱን ግንኙነት የማደሱ እርምጃ አንድ ተብሎ ተጀመረ። በመቀጠል የኢትዮጵያ ጠቅላይ መኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ወደኤርትራ ተጉዘው ጉብኝት አደረጉ፤ ከኤርትራ መንግስት ጋርም ስምምነቶችን ተፈራረሙ። የኤርትራ ህዝብ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ፣  ምናልባት ለጉብኝት ወደሌላ ሃገር በሄዱ መሪዎች ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ወንድማዊ አቀባበል አድርጎላቸዋል። ይህ የኤርትራ ህዝብ ስሜትና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረገው ወንድማዊ አቀባበል ድንገት የመጣ አይደለም። ለሺህ ዓመታት የዘለቀው የሁለቱ ሃገራት ህዝቦች የወንድማማችነት ግንኙነት ነጸብረቅ ነው። የኤርትራ መንግስትም ለጠቅላይ መኒስትር ዶ/ር አብይ ከህዝቡ ስሜት ጋር የሚመጣጠን ደማቅ አቀባበል አድርጎላቸዋል። ይህ እጅግ የሚደነቅ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አስመራ ላይ ከኤርትራው ፕሬዝዳንት ጋር የትብብር ስምመነቶችን ተፈራርመዋል። ትልቁ ስምምነት ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የቆየውን ጦርነትም ሰላምም ያልሆነ ሁኔታ (ሞት አልባ ጦርነት)  የሚያስቀረው የጦርነት ማብቃትን የሚመለከተው ስምምነት ነው። ሁለቱ መሪዎች በኢትዮጵያና በኤርትራ ጦርነት እንዳይኖር ተስማምተዋል። በስምምነታቸው መሰረት የሁለቱን ሃገራት ህዝቦች የሰላም ፍላጎት በሚመጥን አኳኋን በሂደት የድንበር ጉዳያቸውንም ለመፍታት ተስማምተዋል። ከዚህ በተጨማሪ ለዘመናት የዘለቀውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ቀድሞ ወደነበረበት ሁኔታ ለመመለስ የየብስና የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ትስስር ለማስጀመር ተስማምተዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሃምሌ 10፣ 2010 ዓ/ም ወደኤርትራ በረራ ይጀምራል። ሁለቱ መንግስታት በወደብ ልማትና አገልግሎት በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል። በአጠቃላይ ስምምነቱ የሁለቱን ሃገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ወደነበረበት ይመልሳል፤ ይህን ግንኙነት የሚመጥን ኢኮኖሚያዊ ትስስርም ያስከትላል። የሁለቱ ሃገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትም የህዝብ ለህዝብና የኢኮኖሚ ግንኙነቱን በሚመጥን መልክ እንዲጠናከር ያደርጋል።

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወረቂም ቅዳሜ ሃምሌ 7፣ 2010 ዓ/ም በኢትዮጵያ ጉብኝት ለማደረግ አዲስ አበባ ይገባሉ። ኤርትራውያን ወንድሞቹን የሚወደው የኢትዮጵያ ህዝብ ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ ደማቅ አቀባባል ለማደረግ ተዘጋጅቷል። እሁድ ሃምሌ 8፣ 2010 ዓ/ም የሁለቱ ሃገራት የሰላም ግንኙነት የሚበሰርበት 25 ሺህ ሰዎች የሚታደሙበት ፌሰቲቫል ይካሄዳል፣ በሚሊኒየም አዳራሽ። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በዚህ ፌስቲቫል ላይ ይታደማሉ።

የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት መታደስ ሁለቱን ሃገራት ብቻ አይደለም ተጠቃሚ የሚያደርገው። የምስራቅ አፍሪካን ሰላም በማረጋገጥ ረገድም ምትክ የሌለው ድርሻ አለው። ከምስራቅ አፍሪካ ሃገራት በተጨማሪ የአፍሪካ ህብረት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ ምእራባውያን መንግስታት፣ የአውሮፓ ህብረት . . . ሁለቱ ሃገራት የፈጸሙትን የሰላም ስምምነት ያደነቁትና ተፈጻሚነቱን ለማገዝ ያላቸውን አቋም የገለጹት ለዚህ ነው።

በአጠቃላይ፤ የኤርትራና የኢትዮጵያ ህዝብ ግንኙነት በሺህ የሚቆጠሩ ዘመናትን ያስቆጠረ፣ ሊበጠስም ሊላላም የማይችል ነው። ኤርትራውያን ነጻ መንግስት የመሰረቱት ከኢትዮጵያ ህዝብ ለመራቅ ሳይሆን በኢትዮጵያ የነበሩ አምባገነኖች ከጫኑባቸው ጭቆና ነጻ ለመውጣት ነው። የኤርትራ ነጻ መንግስት መሆን በአንድ የተገመደውንና እንደሰርገኛ ጤፍ የተሰባጠረውን የኤርትራና የኢትዮጵያ ህዝብ ሊለያይ አይችልም። የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝብ በሁለት መንግስት ስር የሚኖር አንድ ህዝብ ነው። እናም ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የደበዘዘውን ግንኙነት አድሰው በመንግስት ለመንግስት ግንኙነት ለመደገፍ የጀመሩት ጉዞ ግንጥል ጌጥ ሳይሆን በነባራዊ ሁኔታ አስገዳጅነት የመጣና አስፈላጊም ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy