ኢትዮጵያ በመገናኛ ብዙኃን እይታ
ከሚፍታህ
በዓለማችን የሚገኙ የተለያዩ የሚዲያ አውታሮች ኢትዮጵያ ድፍድፍ ነዳጅ የማውጣት ሙከራ ማካሄዷን አስመልክቶ ሲዘግቡ ሰንብተዋል፡፡ Poly-Gcn በተባለው የቻይና ኩባንያ አማካይነት ሙከራው መካሄዱንም ጨምሮ ፅፈዋል፡፡ ሰኔ 20 ቀን 2010 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር አብይ አህመድ ከኩባንያው የሥራ ኃላፊዎች ጋር በፅህፈት ቤታቸው ተገኝተው እንደተነጋገሩና በመንግሥት ሙከራው መካሄዱ ተገልጿል፡፡ አቶ አብዲ ኢሌ የኢትዮ ሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት እና ከፍተኛ የፌዴራል እና የክልል የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ድፍድፍ ነዳጅ ለማውጣት የሙከራ ሥራ መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡ በዚሁ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እንደገለፁት የሀገራችን የእድገት መሰረት በነዳጅ የተንጠለጠለ አለመሆኑና እድገታችንም በተፈጥሮ ሀብት ላይ የተመሰረተ እንዳልሆነ ጨምረው ገልፀዋል ሲል ዘገባው ያመለክታል፡፡
Bloomberg እንደዘገበውም በኢትዮጵያ ኦጋዴን ክልል የተገኘውን ድፍድፍ ነዳጅ በመሸጥ በመጀመሪያው ዓመት ብቻ ከሽያጩ 1 ነጥብ 2 ቢሊዬን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ እንደምታገኝ ትንበያውን አስቀምጧል፡፡ ኢትዮጵያ ለዘይት፣ ለጋዝና ለነዳጅ ግዥ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ ወጪ እንደሚቀንስና ኢኮኖሚዋን ለማዳን ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረው መግለፃቸውን ዘገባው ያሳያል፡፡ የነዳጅ ማምረቻውም ሙሉ ለሙሉ ወደ ስራ ሲገባ በአንድ የበጀት ዓመት ብቻ እስከ ሰባት ቢሊየን ዶላር ሊያስገኝ እንደሚችል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጨምረው መግለፃቸውን አካተዋል፡፡
የኢትዮ-አሜሪካ የንግድ ትስስር እየጠነከረ መምጣቱን Exchange.com በሀተታው ዘግቧል፡፡ ይህ ድህረ ገፅ እንደፃፈው ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ የውጭ ሀገራት ታላላቅ የኢንቨስትመንት ኩባንያዎች አይን ውስጥ ገብታለች ብሏል፡፡ ድህረ ገፁ አክሎም አሜሪካ በቀሉ ቦይንግ ካምፓኒ የሀገሪቱ ዋነኛ አጋር መሆኑን በመጥቀስ በአሁኑ ሰዓት ደግሞ የአሜሪካ መልቲ ቢሊየነሮች ካምፓኒ በኢትዮጵያ ልዩ ልዩ የኢንቨስትመንት ስራዎች ለመሰማራት ስምምነት መፈራረማቸውን አስታውቀዋል፡፡ በቅርቡም ብዙ የአሜሪካ የንግድ የልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ጉብኝት እንዳደረገ ድህረ ገፁ ጨምሮ ዘግቧል፡፡ ከዚህም የንግድ የሉዑካን ቡድን ውስጥ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች አዳዲስ ኤርፖርቶችን ሊገነቡ የተዘጋጁ ካምፓኒዎች እንዳሉም ጽፈዋል፡፡
በተመሳሳይ ዜናም Eturbonews ጨምሮ እንደፃፈው የአሜሪካ የንግድ ልዑካን ቡድን የኢትዮጵያን እና የአሜሪካን የንግድ ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገልፀዋል ሲል አስነብቧል። በGilbert Kaplan የሚመራው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በአፍሪካ ንግድ ዘርፍ አማካሪ አባላት ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን የንግድ ትስስር ለማጠናከር ቃል መግባታቸውን የኢትዮጵያን አየር መንገድ በጎበኙበት ወቅት መግለፃቸውን አስታውቀዋል፡፡ የአሜሪካ የንግድና የልማት ኤጀንሲ እና “Sabre Corporation” በመተባበር ለኤርፖርቶች ድርጅት እስከ 21 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶለር እና የቴክኒክ ስልጠና ድጋፍ ለማቅረብ መስማማታቸውን ድህረ ገፁ ጠቁሟል፡፡
በተጨማሪም የ444 ሚሊየን ዶላር ዋጋ ያላቸው 12 የኤሌክትሪክ ሞተሮች እና የ473 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር የሚያወጡ የመለዋወጫ እቃዎችን ለማቅረብ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ስምምነት መፈራረማቸውን ፅፈዋል፡፡ Gulftoday arabianbusiness.com የዱባዩ አለም አቀፍ ኩባንያ ዲፒ በኢትዮጵያ ሁለገብ የሎጅስቲክስ ማከማቻ ለመገንባት ጥናት እያካሄደ እንደሚገኝ ዘግቧል። ሁለገቡ የሎጅስቲክ ማከማቻ ግንባታው ወደብ አልባ የሆነችውን ኢትዮጵያ ምርቶቿን ወደ ተለያዩ ሀገራት በተቀላጠፈ መልኩ ለመለክ እንደሚያስችላት ኩባንያው ማስታወቁን በዘገባዎቻቸው አመላክተዋል። ከጉምሩክ እና ከደሴት ድርጅቶች ጋር ባደረጉት ስብሰባ ሁለገብ የሎጅስቲክ ወደቡ ከበርበራ ወደብ እቃዎችን በመቀበል ወደ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት እንዲከፋፈል ያደርጋልም ብለዋል። የኩባንያው ሥራ አስፈጻሚ እና የአስተዳደር ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሱልጣን አህመድ ቢን ሰሊም ከጉምሩክ እና ከደሴት ድርጅቶች ጋር ባደረጉት ስብሰባ ሁለገብ የሎጀስቲክ ወደቡ ከበርበራ ወደብ እቃዎችን በመቀበል ወደ ተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት እንዲከፋፈል ለማድረግ እንደሚያስችል ከስምምነት ላይ መደረሱን ዘገባዎቹ አስታውቀዋል።
Prensa Latina ኢትዮጵያ በኡራጋይ ያለውን እምቅ የአየር መንገድ ገበያ ልታጠና መዘጋጀቷን በኢትዮጵያ የኡራጋይ አንባሳደር የሆኑት Alejandro Garofali መናገራቸውን ዘግቧል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኡራጋይ ያለውን የአየር መንገድ ዘርፍ እምቅ ገበያ ለማጥናት በሚቀጥሉት ወራቶች ወደ Montevideo የሚያቀኑ የአጥኚ ቡድን እንደሚልከ አምባሳደሩ ማስታወቃቸውን ዘገባው አመላክቷል። Theeastafrican.Co.Ke ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን ለውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ክፍት አንደደረገች ዘግቧል፡፡ ጠ/ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን በከፊል እና በሙሉ ለሽያጭ ክፍት በማድረግ እና በኢኮኖሚው ውስጥ የአገሪቱ መከላከያ የሚጫወተውን ድርሻ በመቀነስ የተለያዩ የገበያ ሪፎርሞችን እያፋጠኑ ይገኛሉ ሲል ገልጿል። ከተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች የሦስት ቢሊየን ዶላር የቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ድጋፍ የሚሆን ገንዘብ በማግኘቱ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዘርፍ ሪፎርሞች የበለጠ እየተበረታታ ይመስላል ሲል አትቷል። Africanews OMN አዲስ አበባ ቢሮውን መክፈቱን ተከትሎ የድርጅቱ ዳይሬክተር ጀዋር ሞሃመድ ወደ ኢትዮጵያ ሊገባ መሆኑን አስታውቋል፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ OMN በአሸባሪነት የተፈረጀ ሚዲያ እንደነበር ያወሳው ዘገባው በመሥሪያ ቤቱ ምርቃት ሥነ ስርዓት ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ “ጣቢያው ከዚህ በኋላ በሞባይል ስልክ ዜና የማይሰራ በመሆኑ ደስ ብሎኛል’’ ማለታቸውን አስታውቋል። Africanews ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የአፋር ክልልን የቱሪዝም አቅምን ለማሳደግ እንደሚሠሩ ቃል መግባታቸውን ዘግቧል። ዶክተር አብይ አህመድ በክልሉ ሊገነባ የታቀደውን የኢንዱስትሪ ፓርክ የመሠረተ ድንጋይ ለማኖር ሰኔ 21/2010 በሰመራ ተገኝተው ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ባደረጉት ውይይት የአፋር ክልል ያለውን ተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ ሃብቶችን በመጠቆም ክልሉ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆንና እንደሚሠሩ ቃል መግባታቸውን ድረገጹ አመላክቷል። አፋር ክልል ካለው የተፈጥሮ ሃብት በተጨማሪም ለቀይ ባህር ቅርብ በመሆኑ የተነሳ ስትራቴጅካዊ ጥቅሙም የጎላ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለው መናገራቸውን አስታውቋል። Bloomberg KCB የተሰኘው የኬንያው ግዙፍ ባንክ በኢትዮጵያ ቅርጫፉን በመክፈት ወደ ስራ መግባት እንደሚፈልግ መግለጹን ዘግቧል። ባንኩ ይሄን ያለው፣ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ፣ የተለያዩ የፖሊሲና የኢኮኖሚ
ማሻሻያዎችን በማድረግ፣ የውጭ ኢንቨስተሮች በቴሌኮም፣ በአየር መንገድ እና በተለያዩ የስራ ዘርፎች ሼር እንዲኖራቸው እና በሀገሪቱ እንዲሰማሩ ፍላጎት መኖሩን መግለጻቸውን ተከትሎ መሆኑን ድረገጹ አስታውቋል። በአፍሪካ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያሳየች በምትገኘው ኢትዮጵያ ውስጥ ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት Joshua Oigara ገልጸዋል ያለው ዘገባው ኢትዮጵያ ምቹ የሆነ ገበያ ያላት ሀገር መሆኗንና የተለያዩ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች የሚታዩባት መሆኑንም ዋና ስራስኪያጁ መግለጻቸውን አስታውቋል። በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት በዘርፉ የመሳተፍ እድል እንደሚኖራቸው ሙሉ እምነት እንዳላቸው ስራ አስኪያጁ Joshua Oigara መናገራቸውን አካቷል። ALLIANCEFORSCIENCE የተሰኘ ድረገጽ ኢትዮጵያ የጤፍና የበቆሎ ዝርያዎችን በማሻሻል የግብርናውን ምርታማነትና ጥራት እያሳደገች ነው ሲል ዘግቧል። በቅርቡ በሀገሪቱ ምርምር ተቋማት የተገኙት ሁለት ዝርያዎች፣ Bacillus thuringiensis (Bt) የተሰኘውን የአፈር ውስጥ ባክቴሪያ መቋቋም የሚችሉ መሆናቸውን የጠቆመው ዘገባው የተለያዩ መድሃኒቶችን ከመጠቀም የሚያላቅቅ መሆኑን አስታውቋል። የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ለሁለት ዓመታት ያክል በዘርፉ የመስክ ጥናት ሲያደርግ እንደነበረና በዚህም የተሻሻለ የጥጥ ዝርያ ማግኘት መቻሉን ድረ ገጹ አስታውቋል። የጥናቱ ሪፖርት ለሚመለከተው አካል ለግምገማ ቀርቦ፤ የተገኘው የተሻሻለ የጥጥ ዝርያ ከኢትዮጵያ አየር ንብረት ጋር ተስማሚ እንደሆነም መረጋገጡን አስታውቋል።