CURRENT

እሳት የማይነካቸው እሳት ጫሪዎች                                                                                

By Admin

July 21, 2018

እሳት የማይነካቸው እሳት ጫሪዎች                                                                                

                                                 እምአዕላፍ ህሩይ

በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች አልፎ…አልፎ የሚታዩ ግጭቶች አሁን በምንገኝበት የለውጥ ሂደት ውስጥ ፈፅሞ ተቀባይነት የላቸውም። ለውጡ አንድነትን የሚደግፍና የሚያበረታታ እንጂ ለግጭቶች ቦታ ያለው አይደለም። ዘመኑ የመደመር እንጂ፣ በእኔነት ስሜት በታጠሩ የብሔርና የአስተዳደር ወሰን ጉዳይ ግጭቶች የሚፈጠሩበት ወቅት አይደለም።

በመደመራችን ውስጥ ልዩነቶች ቢኖሩም፤ በመናበብ፣ በመተሳሰብና በኢትዮጵያዊነት የአንድነት ስሜትና ጨዋነት የሚፈቱ ናቸው። ባለንበት የለውጥ ዘመን ለግጭት መንስኤ የሚሆኑ ጉዳዩች እየተዘጉና አስተሳሰቡም እየመከነ መጥቷል። ይህ አስተሳሰብ እየመከነ ባለበት በአሁኑ ወቅት፤ በአንዳንድ አካላት ግጭቶችን ለማቀጣጠል የሚያደርጉት ሩጫ፤ ህዝባዊ መሰረት የሌለውና የህዝቦችን በሰላም ተከባብሮና በአንድነት ተሳስቦ የመኖር እሴቶች በገሃድ የሚጋፋ አካሄድ ነው።

በተለይ በኢትዮጵያ ሶማሌና በኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች አሁንም ግጭቶች መቀጠላቸውን እየሰማን ነው። በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎችም ይሁን በሌሎች አካባቢዎች እየተስተዋሉ ያሉ ግጭቶች መሬት ላይ ያለውን ነባራዊ እውነታ የሚወክሉ አይደሉም። በክልሎቹ የወሰን አካባቢዎች የሚካሄዱ ግጭቶች የህዝቦች ፍላጎት ነው ብሎ የሚያስብ ካለም ርግጥ እርሱ መሳሳቱን መገንዘብ ይኖርበታል። ምክንያቱም በየትኛውም ሀገር ውስጥ ግጭት የህዝቦች ፍላጎት ሆኖ ስለማያውቅ ነው።

እንደ እውነቱ ከሆነ፤ በሁለቱ ተጎራባች ወንድም ህዝቦች የወሰን አካባቢዎች የቀጠለው ግጭት፤ በህዝቦች የቆዩ ባህል፣ ወግና እሴቶች እንዲሁም ባህላዊ የግጭት አፈታት እልባት ሊያገኝ የሚችል አሊያም ስርዓቱ ባለው አሰራር መሰረት መፍትሔ ሊያገኝ የሚችል ነው። ሆኖም ግጭቱ በአንዳንድ አካላት ገፋፊነት ኃላፊነት በጎደለው ሁኔታ ልዩነቶችን በማጎን በህዝቦች መካከል መቃቃርን በመፍጠር ችግሩን ለማባባስ ሴራዎች ሲቀመሩ መመልከት የተለመደ ሆኗል።

ርግጥ የህዝቦችን ጊዜያዊ ችግር ተንተርሶ ግጭቶችን ማጎን ተገቢ አይደለም። ተጠያቂነትንም ያስከትላል። መደመርና አንድነት በሚሰበክበት በአሁኑ ወቅት፤ በቁጥጥር ስር ሊውል የሚችል አነስተኛ ግጭትን የስፋት መጠን እጅግ በመለጠጥ የሀገራችንን ሰላምና መረጋጋት በማወክ ለውጡን ለመቀልበስ መሞከር የፀረ ለውጥ አራማጆች ተግባር እንጂ የማንም ሊሆን አይችልም።

ይህ ደግሞ ባለው እጅግ አነስተኛ ሁኔታ ላይ የሚታዩትን ነባራዊ አለመግባባቶች ላይ እሳት ከጎረቤት በገል ጭሮ ወይም ክብሪት ለኩሶ የዜጎችን ህይወት ለማጥፋትና የዜጎችን ጎጆ ለማንደድ የሚደረግ አደናቃፊ ሩጫ መሆኑ የታወቀ ነው። ሁኔታው በሁለቱ ክልል መንግስታት አሊያም በኢትዮጵያ ሶማሌም ይሁን በኦሮሚያ ህዝቦች መካከል በተፈጠረ ቁርሾ ምክንያት ያልተከሰተ መሆኑ እየታወቀ፤ ጉዳዩን የብሔር መልክ ለማስያዝ በአንዳንድ አካላት የሚደረግ የኋሊዮሽ ሩጫ አደገኛና ኃላፊነት የጎደለው ነው። የኢትዮጵያዊነት ወዝና ሽታን ያልተላበሰ መሰሪ ተግባርም ነው።  

በኢትዮጵያ ሶማሌና በኦሮሚያ ህዝቦች የወሰን አካባቢዎች የቀጠለው ግጭት የአካባቢዎቹን ህዝቦች የማይገልፅ ስለ መሆኑ ማስረጃ ለማቅረብ ሩቅ መጓዝ አያስፈልግም። ምክንያቱም የሁለቱ ተጎራባች ክልል ህዝቦች ለዘመናት በጋራ የኖሩ፣ ተጋብተው የተዋለዱ፣ በታሪክ የተሳሰሩ፣ በባህል የተቆራኙ እንዲሁም በሃይማኖት የሚገናኙ ብሎም ደጉንም ይሁን ክፉውን ዘመን እንደ ሁለት ሳይሆን እንደ አንድ ህዝብ በመደጋገፍ አብረው የተሻገሩ ናቸው።

ይህ ዘመናትን የተሻገረና አብሯቸው የኖረ ትስስር፤ በምንም ዓይነት ምድራዊ ስሌት ለፀብና ለግጭት መንስኤ የሚሆን አይደለም። በዚህ ዓይነት የህይወት ቁርኝት ውስጥ አብሮ የዘለቀ ህዝብ ለላቀ ትስስር እንጂ ለፀብ ቦታ የለውም። ሁለቱ ህዝቦች ለአስተዳደር ወሰን ተብሎ በሁለት ክልሎች ይተዳደሩ እንጂ፣ አንድ ናቸው። ካላቸው ጥቂት “ሰዋዊ” ልዩነት ይልቅ አንድነታቸው በእጅጉ የጎላ ነው። ቢቆጠሩ የአንድ እጅ ጣት የማይሞሉ ልዩነታቸውን ከማንሳት፣ ተዘርዝሮ የማያልቀው ህልቆ መሳፍርት አንድነታቸው የቁርኝቱን ጥልቀት የሚናገር ነው።

የዚህ ፅሑፍ አንባቢ፤ ‘ታዲያ በዚህ አንድ ሊባል በሚችል ህዝብ መካከል ምን ይሉት አዋኪ ሃይል ገባ?’ የሚል ጥያቄን በውስጡ ሊያነሳ ይችላል። ጥያቄው ተገቢ ነው። ሆኖም አዋኪዎቹ ጥቂት እሳት የማይነካቸው እሳት ጫሪዎች መሆናቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል። ቀደም ሲል እንዳልኩት፤ የችግሩ ፈጣሪዎች ክብሪት አቀጣጣዩች ናቸው። እነዚህ ጥቂት አካላት ግጭቶችን በረጅም እንጨት እየቆሰቆሱ እነርሱ ዳር ሆነው እሳቱን መሞቅ የሚፈልጉ የለውጥ እንቅፋቶች ናቸው።

አዋኪዎቹ እሳትን እያቀጣጠሉ እሳቱ የማይነካቸው አሊያም ክብሪትን ለኩሰው ፍንጣሪው የማያገኛቸው ናቸው። በሌላ አባባል፤ በሰው እጅ እሳት ለመጨበጥ የሚፈልጉ ሃይሎች ናቸው ብለን ልንገልፃቸው እንችላለን። ዓላማቸውም፤ በአሁኑ ወቅት በመላው የሀገራችን ህዝቦች ውስጥ በፍጥነት እየጎመራና እየሸተ ያሉትን የፍቅር፣ የይቅርታና የመደመር ጉዞ ለማደናቀፍ መሞከር ነው። በሀገራችን ታሪክ ታይቶ የማይታወቀውን የለውጥ ማዕበል በሚችሉት አቅም ሁሉ ለማስጓጎል እሳቱ ሳይነካቸው እሳት ለማቀጣጠል የሚጥሩ ናቸው።

እነዚህ ጥቂት አካላት ይህን ህዝብን ከህዝብ ጋር የማጋጨት እኩይ ተግባራቸውን በህብረተሰቡ ውስጥ አሊያ ከውጭ ሆነው ሊከውኑ ይችላሉ። መነሻቸው፤ የህዝቦችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና የድሃውን ጉሮሮ ለማርጠብ ከወዲሁ ግብ ሰንቆ ህዝቦችን በአንድነት ጥላ ስር በማሰባሰብ ላይ ያለውን ለውጥ ማደናቀፍ ስለሆነ፤ ለዜጎች ህልፈተ- ህይወት ወይም ከኖሩበት ቀየ መፈናቀል አንዳችም ግድ የላቸውም።

ፍላጎታቸውም በህዝቦች መስዕዋትነት፣ ስቃይና እንግልት የተገኘውን ለውጥ የኋሊት ለመጎተት መጣር ነው። የምንገኝበት ወቅት በህዝብ የሚመራ የለውጥ ማዕበል መሆኑ ግን ይህን ፍላጎታቸውን ሊያሳኩ አይችልም። ምክንያቱም በአንድ በኩል፤ በህዝቦች መካከል የቆየው ግጭትን የመፍታት ባህል መኖሩ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሀገራችን የምትከተለው ፌዴራላዊ ስርዓት ራሱን የቻለ የግጭት አፈታት ስርዓት ያለው ስለሆነ ነው።

በዚህ መሰረትም የኢትዮጵያ ሶማሌና የኦሮሚያ ክልሎች በአዋሳኝ አካባቢዎች የፌዴራል ሃይል እንዲገባ ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት፤ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊትና ፌዴራል ፖሊስ ወደ አካባቢዎቹ ገብተው ስራቸውን በኃላፊነት ስሜት በመወጣት ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጥሩ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

ይህን ተከትሎም የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር አቶ ሞቱማ መቃሳ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ፤ መከላከያ ሰራዊቱ ግጭት ወደ ተፈጠረባቸው አካባቢዎች በማቅናት ስራውን በተገቢው መንገድ እያከናወነ መሆኑን ገልፀዋል። ይህ ሰላምና መረጋጋትን በአካባቢዎቹ የማስፈን ስራ ስርዓቱ ግጭትን የሚፈታበት ህገ መንግስታዊ አሰራር ያለው መሆኑን የሚያሳይ ነው። የፀጥታ ሃይሎቹ ብቅ ጥልም እያለ የሚከሰተውን የዜጎች ህይወት መጥፋት ለማስቆም፣ ሁኔታው ላይ እሳት የማቀበል ስራን የሚፈፅሙ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ የማድረግ ስራዎችን ይከውናሉ።

ይህ ተግባራቸውም በአሁኑ ወቅት በህዝቦች ውስጥ የተፈጠረው ብሩህ ተስፋና ስሜት ጎልብተው እንዲቀጥሉ እንዲሁም ከዚህ በተቃራኒ የሚስተዋሉ ተገቢ ያልሆኑ ድርጊቶችን ለመከላከል የሚያስችል ነው። ከክልሎቹ አዋሳኝ አካባቢዎች የሚወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ በአካባቢዎቹ አንፃራዊ ሰላም እየተገኘ መሆኑን ነው። ይህም ዶክተር አብይና ሁለቱ ክልሎች የወሰዷቸው ርምጃዎች ትክክል መሆናቸውን የሚያሳይ ነው።

ያም ሆኖ ይህ አንፃራዊ ሰላም እንዲጠናከር፤ በየአካባቢው የሚገኙ ዜጎች በትግላቸው ያመጡትን ለውጥ ለማደናቀፍ በህዝቦች መካከል ግጭትን በመፍጠር እነርሱ እሳቱ ሳይነካቸው እሳት የሚያቀብሉ አካላትን ለማጋለጥ እያከናወኑ ያሉትን ስራዎች አሁንም አጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል።