Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

እስከዚያው ድረስ…

0 515

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

እስከዚያው ድረስ…

                                                           ሶሪ ገመዳ

ከአገር ውጭ ተሰዶ በህገ ወጥ መንገድ መጓዝ ዋጋ የሚያስከፍል የሚያስከፍል መሆኑን እየተመለከትን ነው። ‘የእገሌ አገር ህዝብ በኮንቴይነር ሲጓዝ በእገሌ አገር ተያዘ፣ እገሌ በተሰኘ ባህር ላይ ይህን ያህል ዜጎች ሞቱ…ወዘተ’ የሚሉ ዜናዎችን ማድመጥ የተለመደ ሆኗል። እነዚህ ክስተቶች ዜጎች በማወቅም ይህን ባለማወቅ በህገ ወጥ መንገድ የሚያደርጓቸው ጉዞዎች ውጤት መሆናቸው አይካድም።

እርግጥ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ተሰድጄ ንብረት አፈራለሁ ወይም ጥሪት እይዛለሁ ብሎ እስካመነ ድረስ የሚከለክለው አካል የለም። ህገ መንግስታዊ በምቱም ነው። ይሁን እንጂ መንግስት ባመቻቸው ህጋዊ መንገድ መጓዝ ይኖርበታል። ይህን ህጋዊ መንገድ ያለመከተል ከላይ የጠቀስኳቸውን ዓይነት አስከፊ ዋጋዎችን እንደሚያስከፍል መገንዘብ ያስፈልጋል።

መንግስት የሁሉም ዜጎች መብት ለመጠበቅ ሲል ወደ ውጭ ሄደው ለመስራት ለሚፈልጉ ዜጎቹም ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ ነው። ይህም ዜጎች ወሰ ውጭ ሲሄዱ እንግልት፣ ስቃይና አደጋ እንዳያጋጥማቸው የሚያደርግ ነው። አዋጅ የማውጣት፣ ከመንግስታት ጋር የመፈራረምና የአገር ውስጥና የውጭ ህጋዊ የሰራተኛ አገናኞችን ህጋዊነት የማረጋገጥ…ስራዎች ተጠቃሽ ናቸው።

እርግጥ ህገ ወጥ ስደትን ለመከላከል ዘላቂው መፍትሔ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን እንዳሉት በጥናት ላይ ተመርኩዘው የሚከናወኑ ተግባሮች ናቸው። ጥናት ሲከናወንም የህገ ወጥ ስደቱ አነሳሽ ምክንያት፣ የችግሩ የኋላ ታሪክ ስፋትና ጥልቀት፣ በአሁን ሰዓት ችግሩን እያባባሱ ያሉ ጉዳዩችና የመፍትሔ ሃሳቦች ይቀመጣሉ።

ይህ አካሄድ በበቂ ጥናት ላይ የተመሰረተ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት የሚያስችል ነው። ችግሩ በማህበረሰቡ ውስጥ በግልጽ የሚታይ እንደመሆኑ መጠን ማህበረሰቡም የመፍትሔው አካል ተደርጎ የሚታይ ነው። ሆኖም እስከዚያው ድረስ ዜጎች በአገራቸው ውስጥ ለመስራት ካልፈለጉ፣ ህገ ወጥ መንገዶችን መከተል የለባቸውም። በአዋጅ በተደነገገው መሰረት ጉዟቸውን ማከናወን ይኖርባቸዋል። ህገ ወጥ መንገዶች ገንዘብን፣ ጊዜን፣ ጉልበትንና አላስፈላጊ መስዕዋትነቶችን የሚያስከፍሉ ናቸው። እነዚህ መንገዶች የሞት ጎዳናዎች ናቸው።

አንድ ዜጋ ህጋዊ ሆኖ በመንግስት ዕውቅና አግኝቶ መብቱና ክብሩ ተጠብቆለት የሚሰራበት ምቹ ምህዳር ተፈጥሯል። እዚህ አገር በመከናወን ላይ ካለውና በአዲሱ አመራር ይበልጥ እየሰፋ ባለው ልማታዊ ተግባር ባሻገር፣ ዜጎች ወደ ውጭ ሄደው እንዲሰሩ በመንግስት የወጣው የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት አዋጅ ቁጥር 923/2008 ወጥቷል። ከአዋጁ ባሻገር የትኛው የአገር ውስጥ የስራ ስምሪት ኤጀንሲ ህጋዊ እነደሆነና የትኛው ህጋዊ እንዳልሆነ ይታወቃል። ተጓዦች እነዚህን ሁሉ ሃቆች በሚገባ ለይተው ማወቅ አለባቸው።

ከዚህ ውጭ አንድ ዜጋ ባሻው ቦታ የመንቀሳቀስ መብት ስላለው ብቻ ራሱን ለአደጋ ቤተሰቡን ደግሞ ለችግርና ለስጋት አጋልጦ ህገ ወጥ መንገድን መጠቀም አይኖርበትም። ህጋዊ መንገድን መከተል ራስን ከአደጋ ቤተሰብን ደግሞ ከሃሳብና ከሰቀቀን መታደግ ነው።

በህጋዊ መንገድ ወደ ውጭ መጓዝ የህገ ወጥ ደላላዎችንና ኤጀንሲ ነን ባዩችን የተሳሳተ መንገድ ያስቀራል። እንዲሁም ራስን ከአደጋና ከውርደት እንዲሁም የአገርን ክብር ለመጠበቅ ያስችላል።

እርግጥ ለህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መፍትሔው በመንግስት አዋጅ ላይ ብቻ የተጣለ ሊሆን አይችልም። በመንግስት በኩል የታሰበው ጥናት እስኪጠናቀቅ ድረስ ህብረተሰቡ የመፍትሔው አካል ሆኖ ህጋዊነትን ሊያሰፍን ይገባል።

ህብረተሰቡ በየቀየው የህገ ወጥ ዝውውሩ አቀናባሪና ስደተኞችን ወደ ሞት የሚገፉ እነማን እንደሆኑ ያውቃል። ህዝባዊው ጥረት ከመንግስት ህጋዊ አሰራር ጋር መቆራኘትም አለበት። ይህም ተጨባጭ መፍትሔ የሚሰጠው ጥናት ተጠናቅቆ ወደ ተገባር እስኪገባ ድረስ ህግና ሀጋዊትን ለማስፈን ያግዛል።

ህብረተሰቡ ባርነት የሆነው ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እውነታ ዋነኛ ተጠቂ የሚሆኑትና በህገ ወጥ ደላላዎች ሊታለሉ የሚችሉት ወጣቶች ዘንድ ጠንክሮ መስራት አለበት። ወጣቶች ፓስፖርት ለማውጣት በየክልሉ ወደሚገኙ የኢሚግሬሽን ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶች ሲሄዱ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ስለሚያስከትለው አደጋ፣ በአገር ላይ ስለሚኖረው የገፅታ ግንባታ ችግርና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዩችን በማንሳት ማስተማርና ፓስፖርቱም ለህጋዊ ተግባር ብቻ መዋል እንደሚገባው ማስገንዘብ ያስፈልጋል።

በመንግስት በኩል የታሰበውና ስር ነቀል ለውጥ ሊያመጣ የሚችለው ጥናት ተጠናቅቆ ወደ ተግባር እስኪገባ ድረስ፤ በየቦታው የሚከናወኑ የማስገንዘብና የማስረዳት ተግባሮች የአንድ ወቅት ክንዋኔዎች መሆን የለባቸውም። ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ተከታታይ የስርጸት ስራዎች መሆን የሚገባቸው ይመስለኛል።

‘ችግሮችን መፍታት ከራስ ይጀምራል’ እንደሚባለው ህገ ወጥነትን በመከላከል ረገድ የመጀመሪያው ተግባር የሚጀምረው ከቤተሰብ ነው። የአስተሳሰብ ልህቀት መሰረቱ ቤተሰብ ነው። ቤተሰብ ገና ለገና በልጄ ያልፍልኛል በሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ ልጁን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ሊመራው አይገባም። ምናልባት ልጁ ህገ ወጥነትን በመሻት ጉዞውን ወደ ውጭ ለማድረግ ከፈለገ ቤተሰብ ሊገታው ይገባል።

መንግስት የዜጎቹን ህይወት ከአደጋ ለመከላከል ህገ ወጥ ስደትን ለማስቀረት ጥናት እያካሄደ መሆኑን ለልጆች የማሳወቅ ቀዳሚው ሃላፊነት የቤተሰብ ነው። ባለንበት የለውጥ ሂደት ውስጥ ችግሮችን ለመፍታት ሁሉን አቀፍ ርብርብ እየተደረገ ነው። ህገ ወጥ ስደትንም ለመግታት መንግስት ሃላፊነት ወስዶ እየሰራ ነው። የጥናቱ ግኝት ወደ ስራ እስኪገባ ድረስ ቤተሰብ ልጆቹ ህጋዊ መንገዶችን እንዲከተሉ ማረድረግ ይኖርበታል።

ወጣቶች ከእድሜያቸው ለጋነት አንፃር ብዙውን ጊዜ ጊዜያዊ ሁኔታዎችን እንጂ በጥልቀት አንድን ሁኔታ የሚመለከቱ አይደሉም። በችኮላም ወደ አላስፈላጊ አደጋ ውስጥ ራሳቸውን ሊያስገቡ ይችላሉ። በየአካባቢው የሚገኙ ህገ ወጥ ደላላዎች ደግሞ ይህን የወጣቶችን ‘ስስ ብልት’ ስለሚያውቁ ሊያሳስቷቸው የመቻላቸው እድል ከፍተኛ ነው።

ታዲያ ይህን ችግር ለመቅረፍ ቤተሰብ ጠንካራ ሃላፊነቱን መወጣት አለበት። አንዴ ወጣቶች ተሳስተው ህገ ወጥ መንገድን መርጠው ከተጓዙ ሂደቱን መቀልበስ አይቻልም። ስለሆነም ልጆቹን በቀና መንገድ የመቅረፅና የመገሰጽ ሃላፊነት ያለበት ወላጅ ህጋዊ መንገድን ለወጣቶች ማመላከት ይኖርበታል። ይህ ህጋዊ መንገድ መንግስት ጥናቱን አጠናቆ ወደ መፍትሔው እስኪገባ ድረስ የዜጎችን ህይወት የሚታደግ በመሆኑ በጥብቅ መያዝ ያለበት መሆኑን መዘንጋት አይገባም።    

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy