Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

እንደ ዋዛ…

0 587

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

እንደ ዋዛ…

                                                 እምአዕላፍ ህሩይ

ከመሰንበቻው መገናኛ ብዙሃን በማረሚያ ቤቶች ሲከናወኑ የነበሩና በገሃድ ክቡሩን የሰው ልጅ ሰብዓዊ መብቶችን የሚጋፉ ዘግናኝ ተግባሮችን፤ ሲያሳዩን፣ ሲያስደምጡንና ሲያስነብቡን ነበር። ህብረተሰቡም ይህን አሳዛኝ ክስተት የውይይት አጀንዳ አድርጎት በእጅጉ አዝኗል። ርግጥ በህግ ጥላ ስር የነበሩ ታራሚዎች በህገ መንግስቱ ላይ የተጠቀሰው የአያያዝ ሁኔታ ተንዶ የስቃይ ሰለባ መሆናቸውን የተመለከተ ማንኛውም ዜጋ ቢያዝን ትክክል ነው። ምክንያቱም ማንኛውም ዜጋ በኢትዮጵያዊ ወገኑ ላይ የሚፈፀሙ ማናቸውም ጉዳዩች ስለሚያሳስቡት ነው።

እንደ እውነቱ ከሆነ፤ ይህ የመብት ጥሰት በግልፅ የሚታወቅና የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴም ቀደም ሲል ለ17 ቀናት ባካሄደው ጥልቅ ተሃድሶ፤ በማረሚያ ቤቶች ውስጥ ስለሚፈፀመው የመብት ጥሰት አምኖ ይቅርታ ጠይቋል። እንዲሁም የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጉዳዩን አስመልክቶ ስለሚፈፀመውት የመብት ጥሰቶች ዝርዝር ማብራሪያ ማቅረቡ የሚታወስ ነው።

ገዥው ፓርቲም ቢሆን ቀደም ሲል ከጠየቀው ይቅርታ ባሻገር፤ ችግሩን ለመፍታትና ፈፃሚዎችም ይሁኑ አስፈፃሚዎች ላይ አስተማሪ የእርምት ርምጃ እንደሚወስድ ለህዝቡ ቃል መግባቱን እናስታውሳለን። በዚህ መሰረትም፤ በቅድሚያ በህግ አግባብ በቁጥጥር ስር የዋሉ፣ ነገር ግን ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ድረስ በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች በህገ ወጥ መንገድ ሲካሄዱ የነበሩ የጭካኔ ተግባሮች ሳቢያ ‘ከታራሚነት ወደ ተሰቃይነት’ የተሻገሩ ዜጎች የነበሩበትን ሰቅጣጭ እውነታ ህዝቡ እንዲያውቀው መደረጉ ትክክለኛ አሰራር ነው። ‘ለምን?’ ከተባለ፤ እንዲህ ዓይነቱ ጉዳይ አሁን ባለንበት የለውጥ ሂደት ውስጥ መደበቅ፤ በታራሚዎቹ ላይ መልሶ የመብት ጥሰት መፈፀም ማለት በመሆኑ ነው። ይህ ደግሞ በአዲስ አመራር በለውጥ ባቡር ላይ በተሳፈረችው ኢትዮጵያ ውስጥ ፈፅሞ ተቀባይነት የሌለው ጉዳይ ነው—ለውጡ እየተካሄደ ያለው እንዲህ ዓይነቱን አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለማስቀረት ጭምር ስለሆነ።

የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የተፈፀመባቸው እነዚያ በህግ ጥላ ስር የነበሩና ያሉ ግለሰቦች ቀደም ሲል በህሊናቸውና በአካላቸው ላይ ጉዳት ደርሶባቸው ሲያበቃ፤ አሁን ደግሞ እነዚህ ዜጎች ስለ ደረሰባቸው የመብት ጥሰት እንዳይናገሩ አፋቸውን መሸበብ መልሶ ሰብዓዊ መብታቸውን መንፈግ ነው የሚሆነው። ኢ-ህገ መንግስታዊም ነው። እናም የችግሩ ገፈት ቀማሾች ስለ ደረሰባቸው አሰቃቂ ድርጊት ከመነሻው እስከ መድረሻው ድረስ የነበረውን ሁኔታ መግለፃቸው ህገ መንግስታዊ መብታቸው መሆኑን መገንዘብ የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ይህም ገዥው ፓርቲ የገባውን ቃል እንዲፈፅም የሚያደርገው ነው።

በእኔ እምነት ሰሞኑን የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ሶስት ከፍተኛ አመራሮችን ከኃላፊነታቸው አንስቶ በምትካቸው ሌሎች የስራ ኃላፊዎችን መመደቡ ቃል የተገባው ነገር ተፈፃሚነት አንድ ርምጃ ነው። ያም ሆኖ እስከታችኛው የስራ እርከን ድረስ በዚህ ዓይነት አሰቃቂ ኢ-ህገ መንግስታዊ ተግባሮች ላይ የተሳተፉ ፈፃሚዎችም ይሁኑ አስፈፃሚዎች አስተማሪ በሆነ መንገድ ሊጠየቁ ይገባል።

ምንም እንኳን በሀገራችን በተቀጣጠለው የለውጥ ማዕበል ዜጎችን ያሰቃየ ማንኛውም ሰው እንደሚጠየቅ ባውቅም፤ በአጥፊዎች ላይ የሚወሰደው ርምጃ ከላይ ብቻ ተንጠልጥሎ መቅረት ያለበት አይመስለኝም። ስለሆነም ማረሚያ ቤቶቹ ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ድረስ የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች ሲጥሱ የነበሩ በመሆናቸው የተጠያቂነት ስራውም እስከ ታች ድረስ መዝለቅ አለበት እላለሁ።        

ሁላችንም እንደምናስታውሰው ከዛሬ ሶስት ወር በፊት ሀገራችንን ለቀውስ ዳርገዋት ከነበሩ ጉዳዩች መካከል አንዱና ዋነኛው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ነው። ኢትዮጵያ በህገ መንግስቷ ላይ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ሳይሸራረፉ እንደምታከበር አስፍራ ስታበቃ፤ መልሳ የራሷን ህገ መንግስት በመፃረር የዜጎችን መብቶች መጋፋቷ በምንም ዓይነት ምድራዊም ይሁን ሰማያዊ ምክንያት ተቀባይነት የሌለው አሰራር ነው።

በየትኛውም ዴሞክራሲያዊ ሀገሮች ውስጥ ሰብዓዊ መብቶች የሚከበሩት ዜጎች ሰው በመሆናቸው ብቻ የሚጎናፀፏቸው ስለሆኑ ነው። እነዚህ ሰዎች በሰውነታቸው ብቻ ያገኟቸው መብቶች እየተጣሱ እንደ ዋዛ የሚታለፉ አይደሉም። ክብሩን የሰው ልጅ ማንቋሸሽም ጭምር ነው። እንደሚታወቀው ሰብዓዊ መብቶች ከሰው ልጅ ስብዕና ጋር የተቆራኙና አንድ ሰው፣ ሰው ሆኖ በመፈጠሩ ብቻ የሚጎናጸፈው ተፈጥሯዊ መብቶች ናቸው። ማንም የሚከለክላቸው አይደሉም። ማንም እንዳሻውም የሚያዝባቸውም አይደሉም። በጥንቃቄና በተገቢው መንገድ ክብር ተሰጥቷቸው ተግባራዊ የሚሆኑ ናቸው።

ስለሆነም እነዚህን መብቶች የኢትዮጵያ መንግስትም ይሁን ስራውን የሚፈፅሙት አስፈፃሚ መስሪያ ቤቶች ስለፈለጉ ለዜጎች የሚሰጧቸው፣ ሳይፈልጉ ደግሞ የሚነፈጉ አይደሉም። ምክንያቱም በሀገሪቱ ውስጥ የተካሄደው ረጅም ጦርነት መነሻው የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አለመኖር ከመሆኑም በላይ፤ ላለፉት ሶስት ዓመታት በሀገራችን የተከሰተው ቀውስ መነሻው ይኸው የሰብዓዊ መብት እጦት ስለነበረ ነው።

ባለፉት ጊዜያት ዜጎች ተገድለዋል፤ የህሊናዊ ቁስለትና የአካላዊ ጉድለት ሰለባ ሆነዋል። እጅግ አንገት የሚያስደፉ ጉዳዩች ተፈፅመዋል። የአካል መቆረጥ፣ የዘር ፍሬ መበላሸት፣ የዓይን መፍሰስ፣ ግርፋት፣ ጭለማ ቤት ማቆየት…ወዘተ. ኢ-ህገመንግስታዊ ተግባሮች ተከናውነዋል። እነዚህ ተግባሮች በሀግ መንግስቷ ላይ የሰብዓዊ መብቶችን ያረቀቀች፣ እንዲፈፀሙም ቁርጠኛ ነኝ ከምትል ሀገር የሚጠበቅ አይደለም።

መብቶችን በህገ መንግስቱ ላይ አስፍረን ስናበቃ፣ በአፈፃፀም ላይ የተገላቢጦሽ የምናከናውን ከሆነ መልሶ ከህገ መንግስቱ ጋር መጋጨት ነው። ከህገ መንግስቱ ጋር በመጋጨት ህዝብን መምራት አይቻልም። ምክንያቱ ህገ መንግስቱ ህዝቡ በፍላጎቱ እንዲረቀቅ የተስማማበት በመሆኑ  ነው።

የህዝብን ስምምነትን ወደ ጎን ብሎ ሰብዓዊ መብቶች መጣስ ህጋዊ ተጠያቂነትን ያስከትላል። ህገ መንግስቱን የሚፃረር ማንኛውም አሰራር ተፈፃሚነት ሊኖረው አይችልም። እናም በማረሚያ ቤቶች ሲፈፀሙ የነበሩ ኢ ህገ መንግስታዊ ተግባሮች ለህዝብ መቅረባቸው ወደፊት በእነዚያ ቦታዎችም ይሁን በሌሎች አካባቢዎች ተመሳሳይ ድርጊቶች እንዳይፈፀሙ የሚያስተምር ይመስለኛል።

በማረሚያ ቤትም ይሁን በሌሎች የፍትህ ማስፈፀሚያ አካሎች ውስጥ ወደፊት እንዲህ ዓይነቶች ከህገ መንግስቱ ጋር የሚጋጩ ተግባራት እውን እንዳይሆኑ ህብረተሰቡ መብትና ግዴታውን ጠንቅቆ ማወቅና እንደ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዓይነት ከጉዳዩ ጋር አግባብነት ያላቸው ጉዳዩችን ለሚመለከቱ አካላት ተገቢውን ጥቆማ መስጠት ይኖርበታል። ይህም ማናቸውም ዓይነት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደተፈፀሙ ወዲያውኑ አስተማሪ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ የሚያደርግ ነው።

በጥቅሉ ‘ማረሚያ ቤቶች’ ስማቸው እንደሚገልፀው በህግ ጥላ ስርየሚገኙ ዜጎች የሚታረሙበትና የሚታነፁበት እንዲሁም መልካም ስነ ምግባርን ተላብሰው ከህብረተሰቡ ጋር እንዲቀላለቀሉ የሚደረጉበት እንጂ፣ ስቃይንና ግፍን የሚቀበሉበት ቦታ አይደለም። ይህ ሁኔታ እንደ ዋዛ የሚታለፍ አይደለም። እውነታውን ታራሚዎችም ይሁኑ ህብረተሰቡ በሚገባ ማወቅ አለባቸው። ያም ሆኖ በአሁኑ ወቅት እየተከናወነ ያለው ሰብዓዊ መብትን የማስከበር ህገ መንግስታዊ ተግባር፤ ታራሚ ዜጎች በህገ መንግስቱ ላይ የሰፈሩት መብታቸውን በተገቢው መንገድ እንዲጠቀሙ የሚያደርግ ስለሆነ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል እላለሁ።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy