Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከኡፍ ወደ እፎይይይ…

0 689

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከኡፍ ወደ እፎይይይ…

                                                                                  ሐይማኖት ከበደ

ጭጋግ በሸፈነው የኢትዮጲያ ፖለቲካ ሰማይ ስር ድንገት ብርሀን የፈነጠቁት ትልቅ ተስፋን ለሌሎች ይዘው ብቅ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ቤተ-መንግስት ከገቡ አንድ ሁለት ብለን ቀናትን ቆጥረንላቸው፤ መቶ ቀናት ብለን አለፍን። ታዲያ በእነዚህ መቶ ቀናት ውስጥ ይህን በጭጋግ የተሸፈነውን የኢትዮጲያ ፖለቲካ ለማስተካከል ብዙ ስራዎችን መስራታቸው ይታወቃል። ይህም ስራቸው ህዝቡን በጣም አነሳስቷል። ቃላቶቻቸው ከሰማይ እንደወረደ መና ብዙዎችን አጥግቧል። ኢትዮጲያዊነትን በህዝቡ ልብ ውስጥ የማተምና የማለምለም ትልቅ ስራን መስራታቸው ከሁሉም ኢትዮጲያዊ ልብ ውስጥ ሊጠፋ የማይችል ታሪክ ነው። ለአንድ አገር ህዝብ የአንድነት ምሰሶ እንደሆነ መለያየት ለማንም በምንም ሁኔታ እንደማይጠቅም አውቀው የመደመርን መርህ ይዘው በተለያዩ ችግሮች ሰበብ የጣልነውን የአንድነትና የመተሳሰብን እሳቤ በመደመር እንደገና እንድናነሳው አድርገውናል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ መንበረ ስልጣኑ ከመጡበት ዕለት አንስቶ በሚያደርጓቸው ንግግሮች ሁሉ በእኔነት ጎራ ውስጥ የነበረውን በማውጣት እኔን  ወደ እኛነት የመመለስ ትልቅ ጉልበት አለው። ሌላው ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን በመጡበት ወቅት በአገራችን ውስጥ የነበረው የሰላም ሁኔታ ጥያቄ ውስጥ ነበር። ታዲያ ሰላሟ በራቃት አገር ላይ በቅድሚያ መሰራት ያለበትን ነገር ለይተው በማውጣት በከፍታኛ ሁኔታ የማረጋጋት ስራዎችን በመስራትና አገራዊ መግባባቶች ላይ ትኩረት በመስጠት ሰርተዋል። ከዚያም በማለፍ ከጎረቤት አገሮች ጋር ያለንን የዲፕሎማሲ ግንኙነቶች እንዲጠነክሩ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በይፋ ስራቸውን ከጀመሩ ዕለት አንስቶ በጣም ብዙና አስገራሚ ስራዎች ተሰርተዋል። ከሁሉም በላይ ግን የብዙዎችን ትኩረት የሳበው የኢትዮ ኤርትራ የመደመርና የአንድነት ጉዳይ ነው ይህ ጉዳይ የአለም መንግስታትን ያስደነቀም ጉዳይ ነው። እንደሚታወቀው የሁለቱ አገሮች ችግር ለ20 አመታት ማንም ሊፈታው ያልቻለው ትልቅ ችግር ሆኖ ቆይቷል። ታዲያ ይህ ችግር ብዙ አመታትን ቢያስቆጥርም የመደመርንና የአንድነትን መርህ ይዘው በተነሱት መሪያችን በመፈታት  ለአመታት ተራርቀው የነበሩ የሁለቱ አገራት ህዝቦች መገናኘት ችለዋል። በቅርቡም የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሣያስ አፈወርቂ ኢትዮጵያን በመጎብኘት ይህን እውን አድርገውታል። ይህ ለሌሎች አገራት ትልቅ ምሳሌ ሊሆን እንደሚችል የአለም ሚዲያዎች በስፋት ሲዘግቡት ቆይተዋል።

ጠቅላይሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በእነዚህ ጥቂት ቀናት ውስጥ በጣም ብዙ ሊያስመሰግናቸው የሚችሉ ስራዎችን ሰርተዋል እኛም በጥቂቱ ይህን ካልን በመንግስት ተቋማትስ በእነዚህ ቀናት ውስጥ  ምን ስራዎች ተሰሩ የሚለው ጥያቄ በሁላችንም አዕምሮ ውስጥ የሚነሳ ጥያቄ ነው። በመጀመሪያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያከናወኑት የራሳቸውን ካቢኔዎችን ማዋቀር ነበር ይህ የሆነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይዘውት የተነሱትን አላማ በሁሉም የመንግስት ተቋማት ውስጥ ለማንሰራፋት ምቹ ስለሚሆን ነው። እነዚህ ካቢኔዎች ወርደው ከህዝብ ጋር በመስራት የተጀመሩትን መልካም ተሞክሮዎችን ማስቀጠል ይገባል። እነዚህ የመንግስት ተቋማት አሁን በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጀመሩትን  የለውጥ ጅማሮዎችን ለማስቀጠል ትልቅ ሀላፊነት እንዳለባቸው አውቀውና ተረድተው ለህዝቡ የሚሰጡትን አገልግሎት ሁሉ ቀልጣፋ በማድረግ የሚጠበቅባቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል። አብዛኛውን ጊዜ በአንድ አገር ውስጥ የሚኖሩ ህዝቦችን ወደ አላስፈላጊ ችግሮች የሚከታቸውና ሀገርን እንዲያውኩ የሚያደርጋቸው ትልቁ ነገር የመልካም አስተዳደር ችግር ነው። ሁሉም ተቋማት ይህን አውቀው በውስጣቸው ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግር ማስወገድ ይገባቸውል። ይህ ካልሆነ የተጀመረውን መልካም ጅማሮ መስቀጠል የማይቻል ይሆናል። ሌላኛውና ዋነኛው ነገር ሁሉም የመንግስት ተቋማት ከሌብነትና ከችግር ፈጣሪነት የፀዳን ትውልድ ከመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል። አገራችን በፖለቲካ፣ በማህበራዊና በኢኮኖሚ  መስኮች ተሽላ እንድትገኝ ሁሉም የመንግስት ተቋማት ሀላፊነት አለባቸው። በተለይም ከአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ጋር በቀጥታ ግንኙነት ያላቸው ዋና ዋና የመንግስት ተቋማት በትኩረት መስራት ይጠበቅባቸዋል።

አሁን ላይ ባለው ሂደት ሁሉም የመንግስት ተቋማት በእነዚህ መቶ ቀናት ውስጥ አፈፃፀማቸው ተመሳሳይ ነው ብለን ለመናገር አንችልም። ይህን ማወቅ የምንችለው በሚያስገኙት ውጤት ነው። በአፈፃፀማቸው ጥሩ ውጤትን ያመጡ ተቋማትን በማበረታታትና ለሌሎች አርአያ እንዲሆኑ በማድረግ እንዲሁም ውጤትን ላመጡ ተቋማት ተሞክሮአቸውን  እንዲያካፍሉ በማድረግ የተጀመሩ ለውጦችን ማስቀጠል ይገባል። ተቋማት መልካም ውጤት እንዲያመጡ በአመራር ላይ ያሉ አካላት ከፍተኛ ሚናን መጫወት አለባቸው ይህ ካልሆነ ግን የሚመሩትን ተቋም ውጤታማ ማድረግ አይችሉም። መንግስትም ይህን አውቆ በተለያዩ ተቋማት ውስጥ በአመራር ስፍራ ያሉትን አመራሮችን በማንሳት በሌሎች በመተካት እየሰራ ይገኛል። ለዚህም ጥሩ ማሳያ የሚሆነን በቅርቡ በፌድራል መረሚያ ቤቶች ሲሰሩ የነበሩ አመራሮችን ማንሳቱ ይታወቃል። እነዚህ አካላት በህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጠውን የሰው ልጆችን ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ  መብቶችን ከማስጠበቅ ይልቅ ጥሰትን ስላከናወኑ ከቦታቸው ተነስተዋል። እንደዚህ አይነት ተግባርን ይዘን ለውጡን ማስቀጠል ስለማንችል እንደዚህ አይነት ተግባራትን ከሁሉም የመንግስት ተቋማት ማስወገድ ይገባል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ቀደም ሲል ለፓርላማ እንዳሳወቁት አስፈፃሚ አካላትን ውጤታማ  ለማድረግ እቅዶቻቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ጋር እንዲፈራረሙና ወደ ስራ እንዲገቡ የሚሰሯቸው ስራዎችም  ተቆጥረው እንዲሰጣቸውና ውጤቶችንም ቆጥረው በመቀበል ረገድ ብርቱ ክትትል መደረግ እንዳለበት አሳውቀዋል። ይህ የሚሆነው ተቋማት በስራቸው ጥሩ ውጤትን እንዲያመጡ ከማሰብ ከኳያ ነው። ተቋማትን ውጤታማ ከማድረግ አኳያ እየተሰራ ያለው ስራ በሁሉም ክልሎች ላይ መሰራት ይገባል። የክልል ምክር ቤቶች ሰሞኑን ባካሄዷቸው ሰብሰባዎች የመንግስት የስራ አፈፃፀምን ጠንካራና ደካማ ጎኖችን ለይተው በማውጣት ድክመቶችን ለማስወገድ ሁሉም አካላት የሚጠበቅባቸውን በመወጣት እየመጣ ያለውን መልካም ለውጥ ማስቀጠል እንደሚገባ ገልፀዋል።

በተቋማት የስራ አፈፃፀም ጥሩ ካለመሆኑ  የተነሳ በአገራችን በተለያዩ ቦታዎች የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለተፈጠሩት ችግሮች መንስኤ የሆኑ ድክመቶችን በመለየት ችግሮችን ለመፍታት አደረጃጀትን ፈጥሮ 12 ብሄራዊ ኮሚቴዎችን አቋቁሞ ወደ ስራ ተገብቶ የነበረ ቢሆንም ችግሮቹ በፍጥነት ሊፈቱ የሚችሉት ከኮሚቴው ይልቅ ጉዳዮቹን በቀጥታ በሚመሩ ተቋማት መሆኑ ታምኖበት ወደየ ተቋማቱ ከሄዱ ብኋላ የተጀመረው ሪፎርም የደረሰበትን ደረጃ ምን እንደሆነና ተቋማቱ በዚህ አንፃር ያመጡት ለውጦች ምን እንደሆኑ አሁን ላይስ ምን እየሰሩ እንደሆነ በእርግጥ ውጤታማ እየሆኑ ነውን? የሚሉትንን ተከታትሎ በማየት ለውጥ እንዲመጣና ችግሮች እንዲፈቱ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። በተጨማሪም ሁሉም የመንግስት ተቋማት በአዲሱ የበጀት አመት ባወጡት ዕቅድ ላይ በመወያየት ከነባሩ ጋር በማስተያየት ደካማ ጎኖችን በመለየት በአዲሱ በጀት አመት የታቀዱትን ዕቅዶችን ተፈፃሚ ማድረግ ይገባል። ይህን ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ በሁሉም ተቋማት የሚገኙ ሰራተኞች በስራቸው ተግተው በመስራት ውጤታማ በመሆን ዕቅዱን ማስፈፀም እንዲቻል በአመራር ላይ ያሉ አካላት ዝቅ ብለው ከሰራተኞች ጋር በመወያየትና ችግሮችን በማስወገድ በስራቸውም ውጤታማ የሆኑ ሰራተኞችን በማበረታታት ሁሉም የሀላፊነት ስሜት እንዲሰማቸው ከማድረግ አኳያ ከፍተኛ ሚና መጫወት ይገባቸዋል። ይህ ደግሞ አገራችን በጀመረችው የለውጥ ጉዞ በመቀጠል ከድህነት፣ ከጥላቻና ካለመግባባት የፀዳች ህዝቦቿ በፍቅርና በመተሳሰብ የሚኖሩባት ኢትዮጲያ እንድትፈጠር ያደርጋል።

ሌላው ሳልጠቅስ የማላልፋው ጉዳይ በእነዚህ መቶ ቀናት ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ ባከናወኑት መልካም ተግባር የብዙዎችን ቀልብ የሳበው ሚዲዎቻችን ያመጡት ለውጥ ነው። ሚዲያዎቻችን አሁን ላይ መረጃዎችን በፍጥነት ከማድረስ አኳያ ይበል በሚያስብል መልኩ እየሰሩ ይገኛሉ። ይህ ደግሞ ሊያስመሰግናቸው የሚገባ መልካም ተግባር ነው። እንደሚታወቀው ሚዲያ ለአንዲት አገር እንደ አራተኛ የመንግስት አካል ሆኖ መስራት ይገባዋል ነገር ግን አብዛኛውን ጊዜ ይህን ሲያከናውኑ አይስተዋሉም። ይህ ደግሞ በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዳይኖራቸው አድርጎቸዋል። ይሁን እንጂ አሁን አገራችን በጀመረችው የለውጥ አቅጣጫ የሚዲያዎቻችን በፍጥነት መለወጥ በብዙዎች ዘንድ አነጋጋሪ የሆነ ነገር ነው።

በመጨረሻም ይህን በሚዲያዎቻችን ላይ ያየነውን መልካም ለውጥ በሁሉም የመንግስት ተቋማት ላይ እንዲመጣ በማድረግ አገራችን ከዚህ ቀደም ስትታወቅበት የነበረውን መጥፎ ገፅታ ለመቀየር የሁሉም ዜጋ ሀላፊነትና የሁል ጊዜ ተግባር ሊሆን ይገባል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy