Artcles

ኮንትሮባንድ እና ስደት

By Admin

July 24, 2018

 

ኮንትሮባንድ እና ስደት

አሜን ተፈሪ

በድንበር አካባቢ ከሚታዩ ችግር አንዱ የስደተኞች ጉዳይ ነው፡፡ በወዲያኛው ሳምንት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከድንበር ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በማንሳት ለመወያየት በተዘጋጀው መድረክ የስደተኞች እና የኮንትሮባንድ ጉዳይ አንድ መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ  ነበር፡፡ የድንበር ጉዳይ በከፍተኛ ደረጃ ከደህንነት ጉዳይ በእጅጉ የተያያዘ በመሆኑ፤ ከመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ጋር ብቻ የተያያዘ አጀንዳ ተደርጎ እየታየ አካዳሚክሱ ሲሸሸው ቆይቷል፡፡ ሆኖም የድንበር ጉዳይን መሸሽ ሳይሆን፤ ቀረብ ብሎ በማጥናት መፍትሔ በማሳየት እና ለህዝብ የቀረበ የችግር አፈታት ስልት በመጠቆም ረገድ ምሁራን ሚና ሊጫወቱ ይገባል የሚል አስተየያት በጉባዔው ተነስቷል፡፡  

የዩኒቨርስቲዎች ዋና ሚና ዕውቀት ማመንጨት ነው፡፡ ዕውቀት በማመንጨት ሊጠቀሙበት ከሚችሉ ሰዎች ዘንድ እንዲደረስ ማድረግ ነው፡፡ በመሆኑም በአጠቃላይ 10 ጥናታዊ ጽሑፎች በቀረቡበት አውደ ጥናት ከስደተኞች ጋር የተያያዙ የተለያዩ ጉዳዮች የተነሱ ሲሆን፤ ከስደተኞች ጋር ግንኙነት ያላቸው የመንግስት አካላት ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡ ከስደተኞች ፕሮግራም ጋር ተያይዞ መንግስት አዳዲስ አሰራሮችን እየተከተለ መሆኑም ተገልጧል፡፡

እስከ ቅርብ ጊዜ የነበረው አሰራር ስደተኞችን በመጠለያ በማስፈር፤ ወደ ሦስተኛ ሐገር መላክ እና በስደተኞች በመጠለያ እንዲቆዩ አድርጎ ሁኔታዎች ሲሻሻሉ ወደ መጡበት ሐገር እንዲመለሱ ማድረግ ነበር፡፡ አሁን ግን ስደተኞችን በካም ማስፈር እና በስደተኞች ካምፕ እንዲቆዩ አድርጎ ሁኔታዎች ሲሻሻሉ ወደ መጡበት ሐገር እንዲመለሱ ወይም ወደ ሦስተኛ ሐገር ከመላክ ባሻገር ከአካበባቢው ህብረተሰብ ጋር ተቀላቅለው እንዲኖሩ የማድረግ አሰራር እንደ ፖሊሲ ተይዞ እየተሰራበት ይገኛል፡፡  

አሁን ያለው የኢትዮጵያ የስደተኞች ፖሊሲ፤ ስደተኞች ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር እንዲቀላቀሉ ማድረግን (ኢንተግሬሽንን) የሚደግፍ ነው፡፡ አሁን ባለው እቅድ ከ10 ዓመት በኋላ በኢትዮጵያ ስደተኞች ካምፕ አይኖርም የሚል ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት አንድ የሥራ ኃላፊ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ስደተኞችን በተመለከተ የምታደርገው ጥረት በሰብዐዊ መብት አያያዝ ረገድ በአንዳንድ ወገኖች የሚደርስባትን ወቀሳ እና የሥም ስብራት የሚጠግን ነው፡፡ ወደፊት አዳዲስ ስደተኞችን ከመቀበል በቀር ሌሎች ቋሚ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች አይኖሩም ያሉት ኃላፊው፤ የኢትዮጵያ የስደተኞች ፕሮግራም ከሰብአዊ፤ እርዳታ ወደ ልማት ድጋፍ ይለወጣል ብለዋል፡፡ በዚህ ረገድ የቀረቡት ጥናቶችን ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖራቸው እና ፕሮግራሙንም የሚያጠናክሩ ይሆናሉ፡፡

ኢትዮጵያ ከስደት ጉዳይ ጋር በሦስት መልኩ ትስስር አላት፡፡ ስደተኞችን ታመነጫለች፤ የስደተኞች መዳረሻም ነች፡፡ እንዲሁም የስደተኞች መተላለፊያ ሐገር ነች፡፡ የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር አንድ የሥራ ኃላፊ እንደ ተናገሩት ከሆነ የጀመሩት አዳዲስ ፕሮግራሞች ውጤታማ ይሆኑ ዘንድ ጥናቶች በጣም አስፈላጊ ናቸው፡፡

በአሁኑ ጊዜ የበለጸጉ ሐገራት መንግስታት ስደተኞችን እና ፍልሰተኞችን በተመለከተ የጋራ ስምምነት አጥተው ሲቸገሩ እናያለን፡፡ በዚህም የተነሳ በመንግስታቱ መካከል አለመግባባት እየተፈጠረ ይታያል፡፡ የስደተኞችም ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እና ጉዳዩም ውስብስብ እየሆነ ነው፡፡ በበለጸጉት ሐገራት በመንግስታት ዘንድ የሚታየውም ድንበር የመክፈት ሳይሆን የመዝጋት አዝማሚያ መሆኑ፤ በዘርፉ የተሰማሩን ሰዎችን ወይም ባለሙያዎችን የሚያሳስብ ችግር ሆኗል፡፡ በዚህ የተነሳ የወደፊቱ ነገር ብሩህ ሆኖ አይታያቸውም፡፡ አሁን ትልቅ ትኩረት ሊሰጥ የሚገባው የስደት ምንጭ የሆኑ ምክንያቶችን ለማስወገድ ሥራ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ከሐገር ቤት ወደ ውጭ የሚደረግ ስደት እና ከውጭ ወደ ሐገር ቤት የሚደረግ ስደት እናያለን፡፡  ከሌላ ሐገር መጥተው በኢትዮጵያ እኤአ ከ1988 ዓ.ም ጀምሮ ለሦስት አስርት ዓመታት እየኖሩ ያሉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች አሉ፡፡ በኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ እየኖሩ ያሉት ስደተኞች የሐገሪቱ አቅም ዝቅተኛ በመሆኑ እና ከውጭ የሚገኘውም ድጋፍ ያን ያህል በቂ የሚባል ባለመሆኑ ስደተኞቹ እንደሚጎዱ እና ሐገሪቱም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ስደተኛ በማስተናገድ በተፈጥሮ ሐብት ላይ ጫና ያሰሳድራል፡፡

አሁን አሁን እየተከተልነው ያለው ፖሊሲ የስደተኞች ከማህበረሰቡ ጋር ተዋህደው የሚኖሩበትን ሁኔታ የማመቻቸት እና የሥራ ዕድል አግኝተው ራሳቸውን መደገፍ የሚችሉ እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ወደ ሦስተኛ ሐገር የሚሄዱት ስደተኞች ከአጠቃላዩ አንድ በመቶ እንኳን አይሆኑም፡፡

ቀደም ሲል እንደ ተገለጸው ኢትዮጵያ የስደተኞች መዳረሻ ብቻ ሳትሆን ስደተኞችንም ታመነጫለች፡፡ እንዲሁም የስደተኞች መተላለፊያ ሐገር ነች፡፡ ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ የሚሰደዱ ዜጎች ለስደት የሚዳረጉት በተለያዩ በርካታ ምክንያቶች ነው፡፡ እነዚህን የስደት ምክንያቶች በመለየት ችግሩን የማስወገድ ሥራ ለመሥራት ቢሞከርም እስካሁን ችግሩን ለመግታት አልተቻለም፡፡ የስደት ምክንያቶች ከሆኑት መካከል ድህነት እና የደላሎች ግፊት በሰፊው የሚጠቀሱ ቢሆንም፤ ችግሩ በደላላ ብቻ ሊሳበብ የሚችል አይደለም፡፡ የቤተሰብ ግፊትም አለ፡፡ አንድ ሁለት ልጆች ስደት ሄደው፤ የጎረቤት ኑሮ ትንሽ መሻሻል ሲያሳይ፤ ሌላውም ልጆቹን ለስደት እንዲነሳሱ ያደርጋል፡፡ ከድህነት ጅምሮ ያለው ያለውን ገፊ ምክንያት ማስወገድ ባይቻልም፤ ዜጎች በህጋዊ መንገድ እንዲሄዱ ለማድረግ የተወሰደው እርምጃም ችግሩን አልቀረፈውም፡፡

ዜጎች በህጋዊ መንገድ እንዲሄዱ ለማድረግ የተወሰደው እርምጃም ችግሩን አልቀረፈውም፡፡ በህጋዊ መንገድ ወደ ውጭ ለመሄድ የሚፈልጉ ዜጎች እዚህ አዲስ አበባ መምጣት ይኖርባቸዋል፡፡ እዚህ ለመምጣት እና አስፈላጊውን መስፈርት አሟልቶ ለመሄድ ረጅም ሂደት ይኖራል፡፡ ብዙ ወጪ ያስወጣል፡፡ ይህን ሂደት መሸሽ የሚፈልጉ ዜጎች በህገ ወጥ መንገድ ለመሄድ ይደፋፈራሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ የተቀመጠውን መስፈርት አናሟላም በሚል የህገወጥ መንገድን ይመርጣሉ፡፡ ራሳቸውን ለአደጋ በሚያጋልጥ መንገድ ስደት ይገባሉ፡፡ ይህን ችግር ለማስወገድ በህጋዊ መንገድ መሄድን ቀላል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የጽ/ቤት ሥራዎችን መሉ በሙሉ አዲስ አበባ ማከናወን ሳይሆን፤ ሥራው ከታች ባሉ የአስተዳደር መዋቅሮች ቢጀምር አንዳንድ ችግሮችን ለማቃለል ይቻላል የሚል ሐሳብም በጉባዔው ተነስቷል፡፡

በሌላ በኩል፤ የኮንትሮባንድ ነገር ተነስቷል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ኢ መደበኛ የጠረፍ ንግድን የሚያበረታታ የህግ ማዕቀፍ እና ልዝብ የድንበር ፖሊሲ Soft boarder policy)  ቀርጾ ሊተገብር እንደሚገባ አንድ የአዲስ አበባ ምሁር ሲገልጹ፤ በዓመት በአማካይ አንድ ቢሊየን ብር የሚገመት ኮንትሮባንድ ዕቃ ከውጭ ወደ ሐገር ውስጥ እንደሚገባ በጉባዔው የተሳተፉ አንድ የፌዴራል ገቢዎች እና ጉምሩክ ባለስልጣን ባልደረባ አመለክተዋል፡፡

‹‹ድንበር የማዕከሉ መስታወት ወይም ነጸብራቅ ነው፡፡ የድንበር ጉዳይ ከጸጥታ ሥራ ጋር ብቻ ተቆራኝቶ መታየት አይኖርበትም›› ያሉት ‹‹የምሥራቅ አፍሪካ የጠረፍ ከተሞች እንቅስቃሴ ›› (Borederland Dynamics in East Africa) በሚል ርዕስ የሚካሄድ የጥናት ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶ/ር ፍቃዱ አዱኛ፤ የአፍሪካ የድንበር አካባቢዎች የሚታዩት ታሪካዊ እና ማህበረሰባዊ ተጨባጭ ሁኔታዎች መንግስታት ‹‹ለዘብ ያለ የድንበር ፖሊሲ›› (Soft boarder policy) እንዲቀርጹ የሚያስገድዱ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

መንግስታት ጥብቅ የሆነ ድንበር ፖሊሲ ሲከተሉ በጠረፍ አካባቢ የሚኖረው ማህበረሰብ እንደሚጎዳ የገለጹት እና ህይወቱን ሊያሻሻሽሉ የሚችሉ አካባቢያዊ ምቹ ሁኔታዎችን ወይም በእጁ ያለውን ሐብት መጠቀም እንዳይችል ያደርገዋል ያሉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲው መምህር ዶ/ር ፍቃዱ፤ ጥብቅ የጉምሩክ ህጎች ከጠረፍ ንግድ ሥራ በቀር ሌላ የኑሮ መሠረት የሌላቸውን ዜጎች ህይወት ፈታኝ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

አውደ ጥናቱ በዓለም አቀፍ ድንበር ላይ ያተኮረ ቢሆንም በውይይቱ በክልሎች መካከል ያሉ የአስተዳደር ወሰን ችግሮችም ይነሱ ነበር፡፡ ‹‹የአስተዳደር ወሰኖችን ድንበር አድርጎ የማየት ዝንባሌ ተበራክቷል፡፡ ግጭት በዝቷል፡፡  እንደ ቀድሞው በድንበር እና በአስተዳደር ወሰኖች አካባቢ በሚኖሩ የተለያዩ ብሔረሰቦች መካከል የሚከሰቱ ግጭቶችን በሽማግሌዎች አማካይነት መፍታት የማይቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል›› የሚል አስተያየት ሰጪዎችም ተደምጠዋል ፡፡

በመንግስት ውሳኔ ያገኙ የአስተዳደር ወሰን ችግሮች ጭምር ተፈጻሚ  ሳይሆኑ ከአስር ዓመታት በላይ መቆየታቸውን በአብነት በመጥቀስ ወቀሳ ያቀረቡ የአውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች፤ በድንበር አካባቢ የሚታዩ አንዳንድ ችግሮች ከመልካም አስተዳደር እጦት ጋር እንደሚያያዙ ጠቅሰው፤ በድንበር አካባቢ ‹‹መሬታችን ተነጥቆ ለኢንቨስተር ተሰጠብን፤ ካሣ በአግባቡ አላገኘንም›› በሚል ቅሬታ የሚሸፍቱ ሰዎች መኖራቸውን አመልክተዋል፡፡

በሌላ በኩል፤ የቁም ከብት ንግድ ፈቃድ በተወሰኑ ሰዎች መያዙን እና እነዚህ ንግድ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች ከብት ሳያረቡ ወይም ሳያደልቡ የቁም ከብት ወደ ውጭ በመውሰድ ለመሸጥ ከሚፈልጉ ፈቃድ የሌላቸው ነጋዴዎች በከብት ሰባት መቶ ብር እያስከፈሉ ያለ አንዳች ሥራ ገንዘብ የሚሰበስቡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የፌዴራል ገቢዎች እና ጉምሩክ ባለስልጣንን በመወከል በአውደ ጥናቱ የተሳተፉ አንድ ሰው እንደ ገለጹት፤ ከሚደረገው ቁጥጥር ብልሹነት ወይም ደካማነት የተነሳ የሚያልፈው የኮንትሮባንድ ዕቃ ከሚያዘው በብዙ እጥፍ እንደሚበልጥ ጠቅሰው፤ ‹‹በዓመት ከ400 -500 ሚሊየን ብር የኮንትሮባንድ ዕቃ ይያዛል፡፡ ይህም አኃዝ በ2008 ዓ.ም 905 ሚሊየን ብር ደርሶ ነበር፡፡ ሆኖም በ2009 እና 2010 ዓ.ም በዓመት ወደ አንድ ቢሊየን ብር ገደማ የሚገመት የኮንትሮባንድ ዕቃ ወደ መሐል ሀገር ገብቷል፡፡ ወደ ሐገር ቤት ከሚገባው የኮንትሮባንድ ዕቃም ውስጥ በብዙ ሚሊየን ብር የሚገመት የጦር መሣሪያ፣ አደንዛዥ ዕጽ እና መድኃኒት ነው›› ብለዋል፡፡

ኮንትሮባንድ ንግድ የተሰማሩት ወገኖች በጣም የረቀቀ ስልት እንደሚጠቀሙ እና በአሁኑ ሰዓት ከተቆጣጣሪው ይልቅ ኮንትሮባንዲስቱ የረቀቀ የቴክኖሎጂ አቅም እንዳለው እና ነፍስ ባለው ዶሮ ውስጥ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃ በመደበቅ በኮንትሮባንድ ለማስገባት ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡