ሶሪ ገመዳ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አገራችን የገጠማትን የውጭ ምንዛሬ ተመን ለማረጋጋት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። የምንዛሬውን ችግር ለመቅረፍ የተባበሩት አረብ ኢምሬቶችን በማግባባት አንድ ቢሊዮን ዶላር በቀጥታ ወደ ብሄራዊ ባንክ እንዲገባ ማድረጋቸው ችግሩን ከመቅረፍ አኳያ የጎላ ድርሻ አለው። በኢንቨስትመንት መስክም ሁለት ቢለዮን ዶላር መዋዕለ ነዋይ እንዲያፈሱ መወሰናቸው የዶክተር አብይን ጥረት የሚያሳይ ነው። ይህ ጥረታቸውም በአጭር ጊዜ ውስጥ የዶላር ጥቁር ገበያ እንዲያሽቆለቁል ያደረገ ነው።
ዳያስፖራው ከቀን ማኪያቶ ላይ አንድ ዶላር ቀንሶ ለወገኑ እንዲለግስ እንዲሁም በዕውቀት፣ በጉልበትና በሃሳብ አገሩን እንዲደግፍ ላቀረቡት ጥሪ ዳያስፖራው የሰጠው ቀና ምላሽና በምላሹም የዳያስፖራ ፈንድ መከፈት መጀመሩ ከውጤታማ ተግባራቸው ውስጥ ተጠቃሽ ነው። በዚህም ሳቢያ በአሁን ሰዓት የጥቁር ገበያውን ተመን ማረጋጋት ችለዋል። ይህ ጥረታቸውም ጥቁር ገበያው ዶላርን ከባንክ ጋር ተቀራራቢ በሆነ ዋጋ እንዲመነዝር ያስገደደው ነው።
እንዲሁም በዶክተር አብይ መሪነት ኢትዮጵያና ኤርትራ በፈጠሩት ሰላም የአገራችን የቦንድ ገበያ እጅጉን አሻቅቧል። የቦንድ ገበያው መጨመሩ የአገራችንን የውጭ ምንዛሬ ግኝት እንዲጨምር ያደረገ ነው። እነዚህ ሁሉ ጥረቶች ተደምረው አገራችን የውጭ ምንዛሬ ችግሯን እየፈታች ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰሞኑን እንደተናገሩት ዶላር በእጃቸው የሚገኝ ዜጎች ዋጋው ሊቀንስ ስለሚችል ወደ ባንክ እንዲያስገቡ አሳስበዋል። የመንግስትም ይሁን የግል ባንኮች ዶላር ይዘው ለሚመጡ ወገኖች ተገቢውን አገልግሎት እነዲሰጡም አዘዋል። ይህም በዶላር መቀነስ ምክንያት ዜጎች እንዳይጎዱ ካላቸው ፍላጎት የመነጨ ነው። እርሳቸው ዜጎች እንዳይጎዱ ሲያስቡ ዜጎችም ተገቢውን ምላሽ መስጠት ይኖርባቸዋል። ምክንያቱም የዶክተር አብይ ዶላር አስገቡ ጥሪ መልሶ በዋነኛነት የሚጠቅመው ዜጎችን ስለሆነ ነው።
እንደሚታወቀው ሁሉ ባለፉት ጊዜያት መንግስት የዶላር ተመንን ከፍ ያደረገው በዋነኝነት እየተዳከመ ያለውን የኤክስፖርት ገበያ ለማጠናከር ነው። በአንድ አገር ውስጥ ኤክስፖርት ምርት ሊጠናከር ካልቻለ በውጭ ምንዛሬ ረገድ ችግር መፈጠሩ አጠያያቂ አይሆንም።
እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ አገሪቱ ለልማቷ ጠቃሚ የሆኑ ነገሮችን ከውጭ እንዳታስገባ ማነቆ ይሆናል። ስለሆነም አገራችን በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የያዘችውን ትልም እውን ለማድረግ እንዲህ ዓይነቶቹ እርምጃዎች ወሳኝ ይሆናሉ።
የአገራችን ዕድገት፣ የመሰረተ ልማት ኘሮግራሞቻች፣ የግል ኢንቨስትመንትና የንግድ ስራዎች የሚፈልጉትን የውጪ ምንዛሪ በአስተማማኝ ሁኔታ ለማቅረብ እና በውጪ ዕርዳታና ብድር ያለን ጥገኝነት መቀነስ ያስፈልጋል። ይህ እቅድ ሶስተኛ ዓመቱን ባገባደደው የልማት እቅድ ላይ መገለጹ ይታወቃል። ተግባራዊ ለማድረግም ጥረት እየተደረገ ነው።
አሁን ባለን የኢኮኖሚ ቁመና ኤክስፖርት ላይ በመረባረብ ኢኮኖሚያችን በአገር ውስጥ ገበያ ብቻ ሳይታጠር በሰፊው የዓለም ገበያ ላይ ተመስርቶ በፍጥነት እንዲያድግ ማድረግ ያስፈልጋል። እንዲሁም በዓለም ገበያ ገብተን ምርቶቻችንን በስፋት ለመሸጥ ያቀድነው ተወዳዳሪነታችንን ማጐልበት ይገባል።
ኢኮኖሚያችን በፍጥነት እያደገ ባለበት በኤክስፖርትና በኢምፖርት መካከል ክፍተት መኖሩ የሚጠበቅ ቢሆንም ጉድለቱ እየሰፋ መጥቶ የተጠቀሰው ደረጃ ላይ መድረሱ ግን አሳሳቢ ነው።
ቀደም ባሉት ዓመታት የታየው ደካማ የኤክስፖርት አፈፃፀም አስተማማኝ የውጪ ምንዛሬ ግኝት በማረጋገጥ ለፈጣን ዕድገታችን አስፈላጊ የሆኑ መሣሪያዎችና ዕቃዎች ከውጪ በማስገባት ዕድገታችን ለማስቀጠል አና ከውጪ ብድርና ዕርዳታ ጥገኝነት ለመላቀቅ ትልቅ ማነቆ ሆኗል።
በግሉ ዘርፍ የሚካሄዱ ሰፋፊ የኢንቨስትመንትና የንግድ እንቅስቃሴዎች እንደዚሁም በመንግስት የሚካሄዱ ትልልቅ የመሠረተ ልማት፣ የኢንዱስትሪና የማህበራዊ ልማት ኘሮግራሞች ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ የሚፈልጉ በመሆናቸው የኤክስፖርት መዳከም እየተፋጠነ ያለውን ልማት ሊያደናቅፍ እንደሚችልም ግንዛቤ ተወስዷል።
እርግጥ ይህ የሆነው ለኤክስፖርት ገቢ አፈፃፀም መዳከም ዋናው ምክንያት የማምረት አቅማችን በሚፈለገው ደረጃ አለማደግና በዚህም ምክንያት የማኑፋክቸሪንግና የግብርና ሸቀጦች በከፍተኛ መጠን፣ በተለያየ ዓይነትና በከፍተኛ የጥራት ደረጃ ማቅረብ አለመቻሉ ነው።
ይሁን እንጂ አንዳንድ የግብርናና የማኑፋክቸሪንግ ሸቀጦች የተወሰነ የመጠን ጭማሪ ያሳዩ ቢሆንም ታቅዶ ከነበረው ጋር ሲነፃፀር እጅግ አነስተኛ ነው። ለምሳሌ ያህል በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ በዕቅድ ዘመኑ ወደ 200ሺ ቶን የሚጠጋ ቡና ኤክስፖርት ለማድረግ የተቻለ ቢሆንም በ2007 ይደረስበታል ተብሎ ከነበረው ጋር ሲነፃፀር ሲሶ ያህል ብቻ ነበር። በተመሳሳይ የአበባ ምርት ኤክስፖርት ከእጥፍ በላይ ለማሳደግ ተይዞ የነበረው ግብ እና አፈፃፀሙ ፍፁም የማይቀራረቡ ነበሩ። በአሁኑ ወቅት ግን ሁኔታዎች እየተቀየሩ ነው።
በግብርናው ዘርፍ የኤክስፖርት ሰብሎች የሆኑት አበባ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ቡናና ሰሊጥ እንዲሁም የጥራጥሬ ሰብሎች ኤክስፖርት የተደረገው መጠን ይደረጋል ተብሎ ከታቀደው በእጅጉ ያነሰና በማኑፋክቸሪንግ ነባር ኢንዱስትሪዎች በከፍተኛ አቅማቸውና በጥራት እንዲያመርቱና በተጨማሪ አዳዲስ ኢንቨስትመንትን በስፋትና በጥራት መልምሎ ወደ ስራ ማስገባት በታቀደው ልክባለመቻሉ ለኤክስፖርት የማምረት አቅማችን ዝቅተኛ ሆኖ ቆይቷል።
በአሁኑ ወቅት የሀገራችን ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነው ግብርና ምርታማነቱ መሻሻል ያሳየ ቢሆንም፣ በሚፈለገው ደረጃ ላይ ባለመድረሱ ለኤክስፖርት የምናቀርባቸው የግብርና ውጤቶች በመጠን፣ በጥራትና በዓይነት ውሱን ሆነው ቆይተዋል። ሆኖም አሁን እየተከናወነ ባለው ስራ እነዚህ ሁኔታዎች እየተቀየሩ ነው።
የኤክስፖርት ዘርፍ አፈፃፀም የዕድገታችንን ዘላቂነት መረጋገጥ የሚወስን ቁልፍ ጉዳይ በመሆኑ ለኤክስፖርቱ የሚደግፉ ግብዓቶችን ከውጭ ማግኘት ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ የብር መጠንን በመቀነስ ኤክስፖርትን ማበረታታት ይገባል። ይህን ለማድረግ የሚያስችል የዶላር ግኝት በአጭር ጊዜ ውስጥ እውን እየሆነ ነው።
በያዝነው እቅድ በኤክስፖርት ዘርፍ እመርታ ማምጣት የግድ ነው። ይህን ለመፈፀም ደግሞ ዶላር ማግኘት ያስፈልጋል። በጠቅላይ ሚኒስትር ክተር አብይ አህመድና በመንግስታቻው በአጭር ጊዜ ውስጥ ችግሩን ለመቅረፍ እየተወሰዱ ያሉት ጥረቶች ውጤታማ እየሆኑ ነው። እነዚህን ጥረቶች ማገዝ የዜጎች ድርሻ መሆኑ መዘንጋት አይኖርበትም።