Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ዓለምን በፍቅር ገንዘባቸው አድርገዋል

0 257

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ዓለምን በፍቅር ገንዘባቸው አድርገዋል

 

ስሜነህ

 

የዲሞክራሲ ስርዓት አብዛኛው ሰው የመረጠውን መንግስት ይሰጠናል። ይህ ግን በራሱ መልካም መንግስት ያመጣል ማለት አይደለም። በዲሞክራሲ እንደ ምሳሌ የምትነሳው አሜሪካ፤ በጥቂት ቁጥር ልዩነት አንዴ ዲሞክራቲክ ፓርቲ አለያም ደግሞ ሪፐብሊካን ፓርቲ እየተቀያየሩ የሚነግሱባት ሀገር ናት። ሶስተኛ አማራጭ ፓርቲ እስካሁን አቅም አግኝቶ አያውቅም።

 

ስለዚህም የሚመረጠው መንግስት ባብዛኛው ግማሹ ሕዝብ ያልመረጠው ነው። አንዱ ፓርቲ የገነባውን አንዱ እያፈረሰና እርስ በርስ እየተናቆረ ዲሞክራሲ በሀገረ አሜሪካ ይከናወናል። በዲሞክራሲ ጀምረው በአምባገነንነትም የጨረሱ እንደነ ቱርክ ያሉ ሀገራትም አሉ። ስለዚህ ዲሞክራሲ የሚባለው ጉዳይ ጅማሬ ይሆን እንደሆነ ነው እንጂ፤ በራሱ መድሃኒት አይደለም። ስለዚህ ከምናውቀው ዲሞክራሲ የተሻለ ራዕይ ይኖረን ዘንድ ያስፈልጋል። ለዚያ ደግሞ ኢትዮጵያ መንገድ የጀመረች ትመስላለች።በአዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር።

 

ዶክተር አብይ አህመድ ይቅርታና ፍቅርን መሪ ቃላቸው አድርገው፤ የመደመርን ርዕዮተ ዓለም ፈጥረው፤ ሕዝብን ወደ አንድ ሀሳብ አምጥተዋል። የሕዝብን ልብ በፍቅር ገንዘባቸው አድርገዋል። ምድር እፎይ ብላለች። ተስፋና ደስታ ደንበኛችን ሆነዋል። ምዕራባውያኑን የሚያስንቅ አዲስ ዲሞክራሲያዊ አካሄድ በማስኬድ፤ ራሱን በመደመር ፍቅር ዲሞክራሲ መንግስት እንዲተካ የሚያደርግ ነው።

 

የአሜሪካው የንግድ መሥሪያ ቤት ኃላፊ ጉብኝትን አስመልክቶ አለም አቀፍ ሚዲያዎች የተቀባበሉትን አንድ ጉዳይ እዚህ ጋር ለአብነት እናንሳ። በኢትዮጵያ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ የአሜሪካ ኩባንያዎችና ዲፕሎማቶች በመንግሥት እንደሚወሰዱ ይፋ የተደረጉ የለውጥ ዕርምጃዎች ተስፋ እንዳሳደሩባቸው መግለጻቸውን የተመለከቱት እኒህ ዘገባዎች፤ መንግሥት ይፋ ያደረጋቸው የለውጥ ዕርምጃዎች ለአሜሪካ ኩባንያዎች ብቻም ሳይሆን፣ ለግሉ ዘርፍ ማደግ የሚያስፈልጉና ሲጠበቁ የነበሩ መሆናቸውን በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ሬይነር ማስታወቃቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡

 

የመንግሥት የለውጥ ዕርምጃ እንደሚደገፍ፣ አሜሪካ ለረጅም ጊዜም ሐሳብ ስታቀርብበት እንደነበር የጠቀሱት አምባሳደር ሬይነር፣ በኢኮኖሚውና በንግዱ መስክ የአሜካ ኩባንያዎች ተሳትፎን ሊያሻሽል እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ በኢትዮጵያ የጂኢ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ዳንኤል ኃይሉን ዋቢ ያደረጉ አለም አቀፍ ዘገባዎች ላለፉት 20 ዓመታት በኢትዮጵያ ሲንቀሳቀስ የቆየው ጂኢ ኩባንያ፣ በአቪዬሽን መስክ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ የአውሮፕላን ሞተሮችን በማቅረብና በኤሌክትሪክ ኢነርጂ መስክ በተለይም በታላቁ ህዳሴ ግድብ የሁለት ኃይል ማመንጫ ተርባይኖች ሥራ ላይ በመሳተፍ ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡

 

በአገልግሎት መስክ በተለይም በድንገተኛ ጥገና ለመተሐራ ስኳር ፋብሪካ የሰጠው የማሽን ጥገናን በምሳሌነት ከጠቀሷቸው ውስጥ ይገኝበታል፡፡ መተሐራ ስኳር ፋብሪካ በቅርቡ ባጋጠመው የጎርፍ አደጋ ሳቢያ ላለፉት 50 ዓመታት ሲገለገልበት የቆየው የስቲም ተርባይን ማሽን የደረሰበትን አደጋ በመጠገን በኩል ጂኢ ተሳትፏል፡፡

 

በታዳሽ ኃይሎች የቴክኖሎጂ አቅርቦት መስክ፣ በጤና መስክ በተለይም የተለያዩ የሕክምና መሣሪያዎችን በማስመጣት፣ የላቦራቶሪ አገልግሎት በመስጠት እንዲሁም በኮርፖሬት ኃላፊነት በኩል ስለሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎችም አቶ ዳንኤል ማብራሪያ የሰጧቸው መሆኑን የዘገቡት እኒህ ሚዲያዎች፤ ይሁንና ኩባንያው እስካሁን በነበሩት ሒደቶች ከግዥና ከጨረታ ሥርዓት አኳያ ችግሮች እየገጠሙት እንደሚገኝ፣ በክፍያ መዘግየትና እንደ አብዛኛው የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያም የውጭ ምንዛሪ ችግር እየተፈታተነው እንደሚገኝ የገለጹላቸው መሆኑን አውስተዋል፡፡

 

በጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ የሚመራው አዲሱ የመደመር አመራር  የግልና የመንግሥት የሽርክና አሠራር ሕግ ማውጣቱ ኩባንያው ተሳትፎ ማድረግ በሚፈልግባቸው መስኮች ላይ ለሚኖረው እንቅስቃሴ ትልቅ ተስፋ እንደሰጡት መናገራቸውንም ሌላው ጉዳይ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በመንግሥት ወደ ግል እንደሚዛሩ ከተጠቀሱት ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች ውስጥ ተሳትፎ የማድረግ ጂኢ ፍላጎት እንዳለውም በዘገባዎቹ ተመልክቷል፡፡

 

በኢትዮጵያ ኢንቨስት በማድረግና ከ40 ዓመታት ወዲህም የራሱን የማምረቻ ፋብሪካ በዓለም ደረጃ ሲከፍት የመጀመርያው እንደሆነ  ቢቢሲን ጨምሮ ለሌሎች አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃኖች ያስታወቀው የአልባሳት አምራቹ ፒቪኤችም የሐዋሳ ኢንዱትሪ ፓርክ እንዲመሠረት መንግሥትን በማማከርና በአካባቢ ላይ ብክለት የማያስከትል የፍሳሽ አወጋገድ ሥርዓት እንዲዘረጋ በማገዝ በኩል ሚና እንደነበረው  በኩባንያው የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ዳይሬክተር ማት በትለር መናገራቸውን ዘግበዋል፡፡

 

እ.ኤ.አ. በ2014 ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ፋብሪካ ለመክፈት የወሰነው ፒቪኤች በዓለም ላይ ካለው የምርት ግዥና አቅርቦት ድርሻ ውስጥ 20 በመቶውን ወደ አፍሪካ ለማዞር ካለው ፍላጎት በመነሳት ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱን ጠቅሰዋል፡፡በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ በ20 የውጭ ኢንቨስተሮች የተያዙ 52 የማምረቻ ሼዶች እንደተገነቡና በአሁኑ ወቅትም 17 ሺሕ ዜጎች የሥራ ዕድል እንዳገኙ ያብራሩት ሚስተር በትለር፣ በዚህ ዓመት ከፓርኩ ወደ ውጭ የተላኩ ምርቶች የ100 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንዳስገኙም አስታውሰዋል፡፡


በዶክተር አብይ በተወሰዱ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎች መነሻም በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት ውስጥም ከሐዋሳ ኢንዱስትሪ ወደ ውጭ የሚላከው ምርት 500 ሚሊዮን ዶላር ሊያስገኝ እንደሚችል፣ አሁን የተፈጠረው የሥራ ዕድልም ወደ 60 ሺሕ ከፍ እንደሚል፣ በፓርኩ እሴት ተጨምሮባቸው የሚላኩ ምርቶች በአሁኑ ወቅት 82 በመቶ እንደሆኑና በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥም መቶ በመቶ በኢትዮጵያ የተመረቱ እንደሚሆኑ ማስታወቃቸም በዘገባዎቹ ተመልክቷል፡፡

 

ይህም እንጨት እንጨት የሚል የጨለማ አስተሳሰብ ያበቃለት መሆኑን የሚያጠይቅ ነው። በሌላ በኩል ከለውጡ ጋር ተያይዞ የአሜሪካ ምክትል የንግድ ሚኒስትር ሚስተር ጊልበርት ካፓላን 60 አባላት ያሉት የንግድ ልዑክ በመምራት ባሳለፍነው ወር ኢትዮጵያን  መጎብኘቱ ይታወሳል። ከ23 በላይ ታዋቂ የአሜሪካ ኩባንያዎች ያቀፈው ከፍተኛ ልዑክ፣ በኢትዮጵያ ያለውን የንግድና የኢንቨስትመንት ዕድሎች ገምግሟል፡፡ እንደ ጄኔራል ኤሌክትሪክ፣ ሃኒዌልና ሴብር ያሉ ግዙፍ የአቪዬሽን ቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በልዑኩ ውስጥ ተገኝተውበታል፡፡

 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከተለያዩ የአሜሪካ ኩባንያዎች አውሮፕላን፣ የአውሮፕላን ሞተሮችና ሌሎች የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች የሚገዛ ቢሆንም የአሜሪካ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ያደረጉት ኢንቨስትመንት አነስተኛ መሆኑን በመግለጽ፣ በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ  በቀረበው የመደመር ጥሪ የተገኘው ልኡክ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፈጣን ዕድገትና አፍሪካን ከአሜሪካና ከሌሎች አህጉሮች ጋር በማስተሳሰር የሚጫወተውን ሚና እንደሚያደንቁ ተናግሮ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአሜሪካ ኩባንያዎች ጋር የሚያደርገውን የንግድ ልውውጥ ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚሰራ መሆኑን አረጋግጧል፡፡

 

“የአሜሪካ ኩባንያዎች አፍሪካ ውስጥ የታሉ ብለው ለሚጠይቁ መልሳችን ይኸው መጥተናል የሚል ነው፤” ያሉት የልኡኩ መሪ ሚስተር ካፓላን በኢትዮጵያ፣ በኬንያ፣ በኮትዲቯርና በጊኒ ጉብኝት በማድረግ ያሉትን የኢንቨስትመንትና የንግድ ዕድሎች በመመልከትና እንቅፋቶችን በመለየት ምክረ ሐሳብ ለመንግሥታቸው እንደሚያቀርቡ መጠቆማቸውን እና በቱሪዝም ልማት ዘርፍም ኢትዮጵያና አሜሪካ ተደምረው ሊሠሩ እንደሚችሉ መግለጻቸውን የተለያዩ ሃገር አቀፍና አለም አቀፍ ሚዲያዎች በዘገባዎቻቸው ላይ አስፍረዋል፡፡

 

በዕለቱ የተለያዩ የግዥና ትብብር ስምምነቶች የተፈረሙ ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከጄኔራል ኤሌክትሪክ ለቦይንግ 787 አውሮፕላኖች የሚሆኑ 12 ሞተሮች ለመግዛት ውል ተፈራርሟል፡፡ የአውሮፕላን ሞተሮቹ ዋጋ 444 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ሲሆን፣ በተጨማሪም ለአሥር ዓመት የሚፀና የጥገና አገልግሎት ውል ተፈርሟል፡፡ የጥገና አገልግሎቱ ዋጋ 473.5 ሚሊዮን ዶላር ይገመታል፡፡

 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሃኒዌል ከተባለው ኩባንያ ጋር ሁለት ስምምነቶች ተፈራርሟል፡፡ አንደኛው ለአዲስ አበባ ኤርፖርት ማስፋፊያ ፕሮጀክት የሚውል የቴክኖሎጂ ግዥ ውል ሲሆን፣ ሁለተኛው የኤፒዩ (አጋዥ የአውሮፕላን ሞተር) አገልግሎት ግዥ ነው፡፡ የኮንትራት ውሉ በገንዘብ ሲሰላ 17.4 ሚሊዮን ዶላር ተተምኗል፡፡

 

የአሜሪካ የንግድ ልማት ኤጀንሲ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሰው ኃይል ልማት ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን፣ በዕለቱም ለኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ሥልጠና የሚውል የገንዘብ ድጋፍ ስምምነት ተፈርሟል፡፡ ሴብር የተሰኘው ታዋቂ የአሜሪካ ኩባንያ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ የሰው ኃይል ሥልጠና፣ የቴክኖሎጂ አቅርቦትና ማማከር አገልግሎት ሊሰጥ የሚችልበት ስምምነት ፈርሟል፡፡ የአሜሪካ የንግድ ልማት ኤጀንሲ እስከ 21.2 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚችል መገለጹም በዘገባዎቹ ተመልክቷል፡፡  

 

እኒህና እና ሌሎችም ተመሳሳይ  ዘገባዎች የመደመር ፍቅር ጅማሬያችን ኢትዮጵያን እንዲህ በደስታ በማስከር፤ የመደመር ፍቅር መጨረሻ ለዓለም በረከት  የሚተርፍ እንደሆነም የሚያጠይቁ ናቸው። የመደመር ዲሞክራሲ አዲስ ርዕዮተ ዓለም ለመፍጠር፤ የኢትዮጵያ ልጆች አንድ ላይ ሆነው በመደመር የቤት ስራ ወስደው፤ ለዓለም የሚተርፍ አካሄድ በተምሳሌትነት ሊያበረክቱ ፍጥረት ሁሉ መስማማቱንም የሚያመላክቱ ናቸው። መደመር የሚለው አስተሳሰብ ብርሃናማ አስተሳሰብ ነው። ብርሃን እውቀትና ፍቅርን ያጠቃልላል። ሰው የመደመር ብርሃን ሲበራለት፤ የሙሉነት እውቀት ይዞ በፍቅር መያያዝ ይችላል።   

 

በፍቅር እንደ ጀመርን በፍቅር እንጨርስ። በእውቀት እንደ ጀመርን በእውቀት እንዝለቅ። በብርሃን እንደ ጀመርን በብርሃን ግብ እንድረስ። በኢትዮጵያ መደመር ላይ የሚነሳ፤ ከኢትዮጵያ አምላክ ጋር ይፋለማል። የመደመር ፖለቲካ አገልጋይነት ነው። የስልጣን ኮርቻ ላይ ለመቀመጥ አይሮጥም፤ ሕዝብ ፈረስ አይደለምና።

 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ዋነኛ ጥሪያቸው ለኢትዮጵያ አባት መሆን ነው። ሌላውም ተባባሪ  ለመሆን ይሽቀዳደማል እንጂ በስልጣን ጥማት አይነዳም። በአገልጋይነት መንፈስ ሆነን፤ ዲሞክራሲ እንዲወለድና ሕዝብ አገልጋዩን እንዲመርጥ የሕዝብን ጥቅም የሚያስቀድም አካሄድ መውሰድ ይገባል። በግል ጥቅም ጨለማው እየሰለጠነብን ለስልጣን መናቆርና ማናቆር ይቀራል። የፖለቲካው ሃይል የሚገለጠው በፍቅር ነው።  ሕዝብ በአንድነት የተያያዘው፤ በፍቅር ሃይል ነው። በዚህ አጭር ጊዜ ተዐምር የሰራው የፍቅር ሃይል ነው። ጨለማ ብርሃንን መቋቋም አይችልም። ብርሃን ባለበት ሁልጊዜ ጨለማ ስፍራውን ይለቃል። በፍቅርም ይሸነፋል። ኢትዮጵያን አቅፎ አፍሪካን አሻግሮ በማየት ለመያዝ ይዘረጋል። በዚህ ፍቅር ጉልበት እየተረዳን፤ ለዓለም ትምህርት የሚሆን አዲስ ታሪክ እየፃፍን እንደሆነ ማን ያውቃል? አወይ መደመር።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy