Artcles

“ዘ ስካይ ኢዝ ዘ ሊሚት”

By Admin

July 24, 2018

“ዘ ስካይ ኢዝ ዘ ሊሚት”

 

ስሜነህ

 

ግንኙነቱ ጠ/ሚ ዶክተር አብይ   በአስመራ በቤተ መንግስት እንደተናገሩት “የላቀ ትስስር” ወይንም የኤርትራ ፕሬዝደንት በአንድ ወቅት እንደተናገሩት “ዘ ስካይ ኢዝ ዘ ሊሚት” (the sky is the limit) ኣንዳሉት ሁሉ በጋራ የሚቋደሱበትን/የሚጋሩበት ሁኔታ የሚያበስር ከተኛንበት የቀሰቀሰን የታሪክ ምእራፍ ነው።

 

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሰለ ኤርትራ ሆነ ለአፍሪካ ቀንድ ያላቸው ራእይ በአደባባይ የተናገሩት ከ3 ወር በፊት የጠ/ሚኒስትርነቱን ስልጣን በተረከቡ ጊዜ ባደረጉት ንግግር መሆኑ የታወሳል። በአዲስ አበባ የኤርትራን ልኡክ የተቀበሉበት ፣ ቀጥለውም ወደ አስመራ በመጓዝ የጀመሩት ተግባራዊ መንገድ ላለፉት አመታት በርካታ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ሲናፍቁት የነበረ ጉዳይ ስለመሆኑም ወደኤርትራ የሄደው የኢትዮጵያ የመጀመሪያው የህዝብ ተጓዥና ኤርትራውያኑም ወደአደስ አበባ በገቡ ሰዓት የነበረው ትእይንት በሚገባ አረጋግጧል።

የኤርትራና የኢትዮጵያ ህዝቦችን ግንኙነት አዲስ ሳይሆን ጥቁሩን መጋረጃ የቀደደ እነ ከእንቅልፍ የመንቃት አይነት ነው።  ይህ ግንኙነት አዲስ ባይሆንም ልዩና ታላቅ፣ የወደፊት ትውልዶች በታሪክ ማህደሮች ሆነ በልብ ወለድ ድርሰቶች ጭምር የሚያነቡት፣የሚያከብሩትም መሆኑ ግን ሊተባበል አይችልም። በሁለት ሳምንታት ውስጥ በአዲስ አበባና በአስመራ ያየናቸው ታላላቅ ታሪካዊ ክንውኖችን ለማየት መብቃት በራሱ ታላቅ ጸጋ ነው። ትልቅ ብስራት፣ ትልቅ ደስታ።   

 

በመከባበር ላይ የተመሰረተ የወንድማማች ህዝቦች ግንኙነት የእነዚህን የተለየ የዘመናት ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ስነልቦናዊና፣ ስትራቴጂካዊ ትስስር ያላቸው ህዝቦች ሰላም ከማረጋገጥ አልፎ ከፊታቸው የተደቀኑት፣ በመወሳሰብ ላይ የሚገኙ አለም አቀፋዊና ከአፍሪካ ቀንድ ጋር የተገናኙ የጂኦኤኮኖሚክ፣ በጂኦፓለቲካና ጂኦስትራቴጂክ ነባራዊ ሁኔታዎች (realities) ጋር ስጋቶችን በጋራ ለመቋቋም፣ ከእነዚህ ሚመነጩ የጋራ መልካም እድሎችን ደግሞ ለኤርትራና ለኢትዮጵያ ህዝቦች የጋራ ጥቅም፣ የጋራ ብልጽግና፣ የጋራ ደህንነት፣ ጠ/ም አብይ  በአስመራ በቤተ መንግስት እንደተናገሩት “የላቀ ትስስር” ወይንም የኤርትራ ፕሬዝደንት በአንድ ወቅት እንደተናገሩት “ዘ ስካይ ኢዝ ዘ ሊሚት” (the sky is the limit) ኣንዳሉት ሁሉ በጋራ የሚቋደሱበትን/የሚጋሩበት ሁኔታ የሚያበስር አዲስ የታሪክ ምእራፍ ነው።

 

ሌላም ሌላም ብዙ ማለት ቢቻልም ሄዶ ሄዶ ዛሬ ላይ ለተደረሰው ውጤት እንዲመጣ በጎ ያለሙና የሰነቁ ህልሞችና ሃሳቦች አቸናፊ ለመሆን በቅተዋል። ባለፉት አመታት ያራመድናቸው ሃሳቦች፡ ራእይና ህልማችን እውን የመሆን ጅማሮውን ለማየት በቅተናል። ብዙ ስራ፣ ብዙ ትግልም ይቀራል። መተማመን፣ መከባብር፣ መተሳስብ፣ በሁለቱም ወገን የአጭር ጊዜ ጥቅም ላይ የሚያሰላ የብልጣ ብልጥነት ስሌት ትላንት እንዳላዋጣ ተረድቶ ለወደፊቱ ግንኙነታችን ሩቅ አዳሪና ስትራቴጅካዊ አስተሳሰብ ከቅንነት ጋር መጋመድ ከተቻለ፣ በጣም ሩቅ ልንጓዝ እንችላለን።   

 

እንደሚታወቀው በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የፈለገው መንግሥት በቦታው ቢቀመጥ፣ የፈለገው የፖለቲካ ሁኔታ ቢፈጠር ምንም ሊደረጉና ሊበጠሱ የማይችሉ ነገሮች አሉ፡፡ በእሰላሙም በክርስቲያኑም አካባቢ ለዘመናት የቆየ ግንኙነት ካለ መሠረታዊ የሆነ ሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት አለ፡፡ ያንን የፖለቲካ ፍፃሜ ሊቀይረው አይችልም፡፡ በሕዝቦች መካከል ለዘመናት የቆየ የቋንቋ፣ የባህልና ሌሎችም ግንኙነቶች ካሉ እነዚህ ግንኙነቶች ምንም ዓይነት አጥር ቢሠራ ሊታጠፉ የሚችሉ አይደሉም፡፡ የደም ደመና ሊሸፍን ቢችል እንኳ ያ ደመና ሲያልፍ ሊገለጥ ይችላል፡፡ አሁን ያለው እውነት በደም ደመና ተሸፍኖ የነበረው ነገር እየተገለጠ መሆኑ የሚያመለክት ነው፡፡ እናም ከዚህ ከደመናው ባሻገር አንድ ነገር እንዳለ ይገባናል፡፡ ተራው ሕዝብ ከዚያ በላይ የሚሄድ ነገር እንዳለ ይረዳል፡፡ ተራው ሕዝብ ሪፈሪንደሙ የታሪክ መጀመርያ ወይም መጨረሻ እንዳልሆነ ይገባዋል፡፡ ስለሆነም ስለሚቀጥለው ያስባል፡፡ ካነጋገሩ ለሚቀጥለው በሚሆን በሚያመችና በሚጠቅም መልኩ የሚያስብ ይመስለናል፡፡  

ወጣቱና ያለ አንዳች ልዩነት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ቀልብ የማረኩት እንዲሁም ከሀገራችን አልፈው በጎረቤትና በበርካታ ሀገራት መንግስታትና ተቋማት ተቀባይነታቸው እጅጉን እያደገ የመጣው የወቅቱ የኢህአዴግ ሊቀመንበርና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የአመራር ፍልስፍና ዋነኛ መርህና መገለጫ የሆነው የእንደመር ጥሪ በሀገር ውስጥ ጠንካራ ሀገራዊ አንድነትና ብሔራዊ መግባባት በአዲስ መንፈስ እንዲፈጠር ከፍተኛ በጎ ተፅዕኖ እየፈጠረ ይገኛል፡፡  

 

ባለራዕዩ ዶ/ር አብይ አህመድ የወቅቱን የሀገራችንን መሪነት ሲረከቡ ባደረጉት ተስፋ ሰጪ ንግግራቸው በርካቶች ቢደመሙም ንግግራቸው እንዲህ በአጭር ጊዜ ውስጥ በዚህ ፍጥነት እውን ሆኖ አያለው ብሎ የሚያስብ አካል ግን እምብዛም ሊሆን እንደሚችል የበርካቶቻችን እምነት ነበር፡፡ አዲሱን የአመራር ስራቸውን ባልተለመደ ሁኔታ እጅግ በተስፋ ተሞልተው ትልልቅ ጉዳዮችን ማሳካት እንደሚችሉ በማራኪ ንግግር የጀመሩት እኚህ ወጣት ጠቅላይ ሚኒስትር በታታሪነት ሌተቀን ተግተው ተግባራዊ እንዲሆኑ በሚወስዷቸው የለውጥ እርምጃዎች ህልም የሚመስሉ እቅዶቻቸውን እጅግ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተግባር በመቀየር ታላቅ መሪ መሆናቸውን አሳይተውናል፡፡

ባለራዕዩና ወጣቱ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር በሀገራችን አንጋፋ መሪ መሆናቸውን ገና ከጅምሩ እያሳዩን ይገኛል፡፡ በተለይም በሀገራችን ኢትዮጵያና በጎረቤታችን ኤርትራ መንግስታት መካከል ከ20 ዓመታት በፊት ተፈጥሮ የቆየውን ቁርሾ ለመቀየር እንዲሁም ይህንን ቁርሾ ተከትሎ በተለይ ደግሞ ከሌላ ማንኛውም ጎረቤት ሀገራት በተለየ ሁኔታ በሁለቱ ሀገራት ህዝቦች መካከል ቀደም ሲል ለረጅም ዘመናት የነበረውን ጠንካራ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ተቋርጦ ከነበረበት መመለስ ችለዋል። ተለያይተው የቆዩ የአንድ ቤተሰብ አባላትን ከማገናኘት አንስቶ በርካቶችን ከዘመዶቻቸውና ከወዳጆቻቸው እንዲገናኙ ለማድረግና በሁለቱ ሀገራት አዋሳኞች ላይ የነበረውን ሞት አልባ ጦርነት በሰላም ለመቀየር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ቅድሚያ ከሰጧቸው ውጥኖች አንዱ ስኬት መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡

 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በባዕለ ሲመታቸው ባደረጉት ንግግር ይህንኑ የሁለቱን ሀገራት ጉዳይ በዘላቂነት ለመፍታት እንደሚሰሩ  መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ይህንኑ ተከትሎ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በግንቦት ወር መጨረሻ ባደረገው ስብሰባው ከኤርትራ ጋር ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና የአልጀርሱን የሰላም ስምምነት ለመተግበር የሚያስችል ውሳኔ ማሳለፉ የሚታወስ ሲሆን የኤርትራ መንግስትም ተመሳሳይ አቋም እንዲወስድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ጥሪያቸው ሲያቀርቡ ተስተውሏል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ታላቁ የሰላም ጥሪ ተቀባይነት በማግኘቱ ኤርትራዊያን በፕሬዚዳንቷ አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ አማካኝነት የኢትዮጵያን የሰላም ጥሪ መቀበላቸውንና የልዑካን ቡድን ወደ አዲስ አበባ ለመላክ መዘጋጀታቸውን ሲገልጹ በርካቶችን በማስደሰት በወቅቱ ንግግሩን ሲታደሙ የነበሩ ኤርትራዊያን ቤተሰቦች የመሪያቸውን ለሰላም፣ ለአብሮነትና ለቀድሞ ግንኙነት ዳግም በር የሚከፍት እርምጃ መወሰን በደማቅ ጭብጨባ አድምቀዋል፡፡

 

ይህንን የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በሀገራቱ መካከል ተፈጥሮ የቆየውንና የጋራ ሰላምን ያሳጣ የ20 ዓመታት ቁርሾ ለመፍታት የጋራ ፍላጎት መኖሩን ተከትሎ ሰሞኑን ማስተዋል እንደተቻለው ባሳለፍነው አጭር ጊዜ ውስጥ ተከታታይ ታሪካዊ ድሎች ተመዝግበዋል፡፡ የሁለቱም ሀገራት ተወካዮች ይህንኑ በተመለከተ ባስተላለፉት መልዕክት ሀገራቱ ለረጅም ጊዜ በመካከላቸው የፈጠሩት ሰላም አልባ ግንኙነት ትልቅ ስህተት እንደነበረና የሁለቱንም ሀገራት ዜጎች ተጎጂ ያደረገ ውሳኔ መሆኑን በጋራ መግባባት ገልፀዋል፡፡ ይህም በመሆኑ የሁለቱን ሀገራት የጋራ ሰላም ለመመለስ በቀጣይ ጊዜ መፍጀት እንደማይገባና ሀገራቱ በመሪዎቻቸው ደረጃ ተገናኝተው መምከርና በጋራ የሰላም ውሳኔ ላይ መድረስ እንደሚገባቸው የጋራ መተማመን ላይ አድርሷቸዋል፡፡

 

የሁለቱን ሀገራት ሰላም ለማስፈን ከራሱ ከሰላም ውጪ በሌላ በምንም ነገር ማረጋገጥ እንደማይቻል ቀድሞም የገባቸው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በተመሳሳይ ባለፈው እሁድ በእሳቸው የሚመራ የልዑካን ቡድን በመያዝ በአስመራ ጉብኝት ባደረጉ ሰዓት በአስመራ የነበረው ሁኔታ የሁለቱን ሃገራት ህዝቦች የሰላም ጥማት የሚያጠይቅ ነው፡፡ የአስመራ ጎዳናዎች በሁለቱ ሀገራት ሰንደቆችና መሪዎች ምስል አሸብርቀው በበርካታ ዜጎች ከህጻናት እስከ አዛውንት እናቶችና አባቶች በአጠቃላይ በከፍተኛ ደስታ ተሞለተው ለኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን ደማቅ አቀባበል ማድረጋቸውን ልብ ይሏል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የሚመራው ልዑካን ቡድን አስመራ ሲደርስ የአስመራ ጎዳናዎችን ላጨናነቁት ነዋሪዎች የተለየ ትርጉም የነበረው ለረጅም ጊዜ ሁሉም ሲመኙት የቆዩትን ተዘርዝሮ ሊያልቅ የማይችለውን የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች ክፉኛ ተጎጂ ያደረገውን ያለፉትን 20 ዓመታት ከባድ ቁርሾዎችና ኪሳራዎችን በማስቀረት ከሰላምና ከፍቅር ውጪ ምንም ኪሳራ ያልነበረውን የቀድሞውን በፍቅርና በአብሮነት እርስ በእርስ ተሳስሮ መኖርን በአዲስ ምዕራፍ ለመክፈት ትልቅ እርምጃ መሆኑ ነው፡፡

 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአስመራ አንድ ቀን ብቻ አድረው ባሳለፉት በጣም አጭር የሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ቆይታቸው የሁለቱን ሀገራት በተለይም ዜጎቻቸውን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ በርካታ ውጤቶችን ከማስገኘት ባለፈ ታሪካዊ ድልን የተጎናፀፉበት ነበር፡፡ ባሳለፍናቸው ሁለት አስርት ዓመታት ለረጅም ጊዜ እየተወዘፈ የመጣውንና በቁርሾ የተሞላውን የሁለቱን ሀገራት የእርስ በእርስ ግንኙነት ሰላማዊ እንዲሆን ማድረግ በሁለቱም ሀገራት ዜጎች ዘንድ የበርካቶች ከፍተኛ ፍላጎትና ምኞት እንኳ ቢሆን፤ ከሁለቱም ህዝቦች ወደርየለሽ ፍላጎትና ምኞት ባለፈ ማን ምን ማድረግ አለበት ብሎ ለማሰብ እንኳ ሁኔታዎች በጣም አስቸጋሪ በሆኑበት፣ ለዚሁ ተጠያቂው በግልፅ በማይታወቅበትና የሁለቱም ሀገራት መሪዎች በራቸውን ዘግተው አንዳቸው ሌላኛቸውን ከመውቀስና ተጠያቂ ከማድረግ ባለፈ ችግሩን ለመቅረፍ የመፍትሄ ሃሳብ አቅርበው ገፍተው ጥረት ሲያደርጎ እምብዛም ባለተስተዋለበትና በርካቶች እንዲሁ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲህ መፍትሄ ይገኛል ብለው ማሰብ በተዉበት በጠቅላይ ሚኒስትራችን ግንባር ቀደም ተነሳሽነትና ተዋናይነት በአጭር ጊዜ ውስጥ ከሁለቱ ሀገራት ባለፈ ከቀጠናው ሀገራት አንስቶ ለመላው አፍሪካም ሆነ ለመላው አለም ሀገራት የሚሆን ተምሳሌታዊ ስራን በመስራት ከፍተኛ ውጤትን ተጎናፀፈዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የሁለቱን ሀገራት ቁርሾ ለመፍታት ባደረጉት ጥረት ቅድሚያ የሰጡት በርካቶቻችን አስቀድመን በዋናነት ልናነሳው ስለምችለው የድንበርና ሌሎች ተያያዥ ቁሳዊ ጉዳዮች ሳይሆን የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች በመካከላቸው በተቋረጠው እርስ በእርስ በመተሳሰብ፣ በፍቅር፣ በመዋደድና በአብሮነት በአንድነት ተሳስሮ የመኖር ግንኙነት ለረጅም ጊዜ ያጡትን ቀደምት የረጅም ዘመናት ቁሳዊ ዋጋ የማይገኝላቸውን የጋራ እስቶቻቸውንና ሰላማቸውን ዋነኛ ትኩረታቸው አድርገው ቅድሚ በመስጠት እንዲመለሱ ማድረግን ነው ፡፡

 

ይህንንም በተመለከተ ባስተላለፉት መልዕክት ተቋርጦ የቆየውን የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች ሰላምና በመዋደድና በመፈቃቀር እርስ በእርስ እንደአንድ ቤተሰብ አብሮ የመኖር ግንኙነታቸውን ወደ ቀድሞው እንዲመለስ ማድረግ ከተቻለ እንዴት ሊፈቱ ይችላሉ ብለን አክብደንና አግዝፈን የምንመለከታቸውን ሌሎች ጉዳዮችን ለመፍታት እንደማንቸገርና እንዲሁም አብሮነታችንን በሚገባው ደረጃ እንዲጠናከር ማድረግ ከተቻለን በመካከላችን ያለውን የድንበር ጉዳይን ጨምሮ ትልቅ ችግር መስለው የሚታዩን ሌሎች ጉዳዮች ተራ መሆናቸውንና ለመፍታትም እንደማንቸገር እንገነዘባለን ነበር ያሉት፡፡ ውጤቱም እንዲሁ ተመሳሳይና ለበርካቶቻችንም ያልተጠበቀና ሁሉንም ያስደመመ በመሆን የወቅቱ ዋነኛ መነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ አዲስ ምዕራፍ ለሁለቱ ሀገራት ሰላም ወዳድና አብሮ መኖርን ባህላቸው ላደረጉ ህዝቦች ወደር የለሽ ደስታን አጎናፅፏል፡፡

 

በበሳል የአመራር ዘይቤያቸውና በአጭር ጊዜ ውስጥ እያሳዩ ባለው ስኬታማ ለውጥ በሀገር ውስጥ የዜጎችን ልብ በፍቅር መግዛት የተካኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በአስመራ ቆይታቸው የኤርትራዊያንን ልብ እንዲሁ በይቅርታና በፍቅር ማርከው የጉብኝታቸውን ግብ በስኬት አጠናቀዋል፡፡ በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ በፍፁም ቅንነት ሁለቱን ሀገራት በሚመለከት የሚያራምዱትን የዲፕሎማሲ አቋምና ከፍተኛ ፍላጎት ወደ አቻቸው የኤርትራው መሪ እንዲጋባ የማድረግ ስራ በስኬታማነት አከናውነዋል። በቆይታቸው ወቅት ከነበረውና በፍፁም ደስታና የፊት ፈገግታ የተሞላ የሁለቱ መሪዎች የእርስ በእርስ ግንኙነት በርካታ አብነቶችን በማንሳት መገንዘብ ለማንም በቂ ይሆናል፡፡

 

ይቅርታንና ፍቅርን ለማንገስ ወደ አስመራ ይዘውት የተጓዙትን የዲፕሎማሲ ውጥን መሪዎችን ጨምሮ መላ ኤርትራዊያን በቅንነትና በሙሉ ፍላጎት የጋራ እንዲያደርጉት ያስቻለና ተመሳሳይ አፀፋ በማስገኘት ሁለቱም ሀገራት በመሪዎቻቸውና በህዝቦቻቸው ዘንድ ለረጅም ጊዜያት ሳይጠቅማቸው ይዘው ያቆዩትን ጎጂውን ሁሉ አራግፈው በመጣል ስለ ሰላም፣ ይቅርታና እንዲሁም በመዋደድና በፍቅር በጋራ አብሮ ስለመኖር አንድ አይነት ቋንቋንና ተመሳሳይ መልዕክቶችን መናገር ችለዋል፡፡

 

ኤርትራዊያን በፕሬዚዳንታቸው አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ አማካኝነት ከኢትዮጵያዊያን ጋር ለመደመር አዲስ አበባን ከ20 ዓመታት በኋላ ሊጎበኙ ችለዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ አንስቶ ፊታቸው ላይ የሚታየው ከፍተኛ የደስታ ስሜት እስከ መጨረሻ የጉብኝታቸው ማብቂያ ድረስ ሳይለያቸው መዝለቅ የቻለ ሲሆን፤ ያለፉባቸው ጎዳናዎች ሁሉ እሳቸውን እንኳን ደህና መጡ ለማለት በታደሙ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሞልተውና ተጨናንቀው የሞቀ አቀባበል ተደርጎላቸው ወደ አዲስ አበባ በመምጣታቸው ስለሁለቱ ሀገራት ሰላማዊ ግንኙነት መጀመር የመላ ህብረተሰቡ ደስታ ወደርየለሽ መሆኑንና በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ተመሳሳይ የአስመራ ጉብኝት ህብረተሰቡ ካሳየው ደስታ ጋር አንድ መሆኑንና የሁለቱም ሀገራት ህዝቦች ፍላጎት አንድ መሆኑን በሚገባ እንዲገነዘቡ አድርጎ አልፏል፡፡ በተለያዩ ቦታዎች በመዘዋወር በተደረገላቸው በርካታ የአቀባበል መስተንግዶና ስነ ስርዓት እንዲሁ በሚገባ መደሰታቸውንና ሰላማዊ ግንኙነቱ ሁለቱንም ሀገራት የሚመለከት ጉዳይ እንደሆነና የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማስቻል በቀጣይም ሀገራቱ በጋራ መስራት እንደሚገባቸው ለፕሬዚዳን ኢሳያስ አፈወርቂ በሚገባ ያሳየ ነበር፡፡

 

የእስካሁኑ የኢትዮጵያና ኤርትራ መንግስታት አዲስ የግንኙነት ስምምነትና የህዝቦቻቸው በይቅርታና በፍቅር እንደቀድሞው በአብሮነት ለመኖር ያሳዩት ከፍተኛ ደስታና ፍላጎት ከመጀመሪያው አንስቶ የሁለቱን ሀገራት ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚነት እውን እንዲሆን በሚያስችሉ በበርካታ የጋራ ጉዳዮች ላይ በቀጣይ አብሮ ለመስራት መግባባትን ያሳዩ የሁለትዮሽ ግንኙነት ድሎች ታጅቦ እስከ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የአዲስ አበባ ቆይታ መጠናቀቅ ድረስ መዝለቅ የቻለ ነበር፡፡  

 

ከፕሬዚዳን ኢሳያስ አፈወርቂ የአዲስ አበባ ጉብኝት ጋር ተያይዞ ከ25 ሺ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎ በተገኙበት የእሁዱ የሚሊኒየም አዳራሽ የዝግጅት መድረክ ላይ በንግግራቸው ባስተላለፉት መልዕክት የቀጣይ ግንኙነታቸውን ስኬታማነት ለማገዝ ሀገራቱ የየበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት ያላቸውን ተነሳሽነትና ፍላጎት አሳይተዋል፡፡ ለአብነትም የኤርትናን ህዝብ ሰላምታና ፍቅር ለኢትዮጵያ ህዝብ ይዤ መጥቻለው ያሉት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ “በኢትዮጵያና በኤርትራመካከል የተፈጠረውን ሰላምና የሚታሰበውን የጋራ ልማት ማንም ኃይል እንዲፈታተነው አንፈቅድም” ያሉትን ብናነሳ የዚሁ የመሪዎቹ ከፍተኛ ተነሳሽነትና ፍላጎት መኖር ማሳያና ከብዙዎቻችን ተስፋና እምነት ጋር ተመሳሳይ ያደርገዋል፡፡ አክለውም “በጋራ ጥረታችን ባለፈው ችግር የከሰርነውን አስመልሰን ወደፊት ሁሉንም ነገር እናሸንፋለን” ማለታቸው ኤርትራዊያን የጠቅላይ ሚኒስትራችንን የእንደመር ጥሪ ተቀብለው መደመራቸውን ያሳየንም ጭምር ነው፡፡

 

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በበኩላቸው እንዲሁ የኢትዮጵያና ኤየርትራን አዲስ የግንኙነት ምዕራፍ አስመልክቶ በሀገራቱ መደመር ዙሪያ በንግግራቸው ካስተላለፉት መልዕክት ሀገራቸው ያላትን ከፍተኛ ተነሳሽነትና ፍላጎት መኖር በሚገባ ያሳየ ነበር፡፡ “የእኛ የመደመር እሳቤ ከሂሳብ የመደመር እሳቤ የላቀ ነው፡፡ የእኛ የመደመር እሳቤ የልዩነት ግንብን ማፍረስ ነው፡፡ እኔና ኢሳያስ ስንደመር ሁለት ሳይሆን እኛ ነው የምንሆነው፡፡ እኔና ኢሳያስ ስንደመር እኛ ሆነን እንባዛለን፡፡ ”

 

የቀደመው የቤተሰብ እና የወንድም ህዝብ ወዳጅነት ወደ ቦታው ሊመለስ ሃያ ዓመታትን ማስቆጠር ግድ ቢልም ዛሬ ግን ታሪክ እንዲህ ተቀይሯል፡፡ ማሰሪያው በአዲስ መንፈስና አስተሰሰብ ጠብቋል፡፡ የሁለቱም አገራት መሪዎች “ከአሁን በኋላ በእነዚህ ህዝቦች መካከል የሚገባ ማንም የለም፡፡ ያንን የሚያስብ ካለም ራሱን ቢሰበስብ ይሻላል” ሲሉ በመደመረቸው፤ በአንድታቸው የማይደራደሩ መሆናቸውን በህዝቦቻቸው ፊት ቃል  

 

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በጋራ ያጣነውን፤ በጋራ ለማግኘት፤ ስለባለፈውም በጋራ ለፍተን ህዝበችንን ልንክስ ዳግም ወደ ትስስራችን ቃልኪዳን ለመመለስ መንገዱን ጀምረናል ብለዋል፡፡ ትስስሩን ለማደስ ከባለስልጣነት እና የልዑካን ቡድን ጉዞ በዘለለ በአጭር ጊዜ ውስጥ የህብረተሰብ ክፍሎችን ወደ አካተተ እንቅስቃሴ ተገብቷል፡፡

ሀምሌ 11 ቀን 2010 ዓ.ም ንብረትነቱ ኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነው ቦይንግ 787 ድሪም ላይነር ዘመናዊ አውሮፕላኖች ከአዲስ አበባ ተነስተው ለ20 ዓመታት የተዘጋውን የኢትዮ-ኤርትራ የበረራ አየር ክልልን እየሰነጠቁ 465 መንገደኞችን አሳፍረው አስመራ በሰላም ሲያስርፉ አስመራ ዳግም ፌሽታ ከልጆቿ ጋር ተቋድሳለች፡፡ ግዘፉ አየር መንገዳችንም እናትና ልጅ፤ ልጅና አባትን ባልና ሚስትን ከሃያ ዓመታት በኋላ ዳግም በማገናኘት ደስታው እጥፍ ድርብ ሆኖ ሰንብቷል፡፡

ይህንን በረራ ተከትሎ መንገደኞችን ከሚያመላልሱ የበራራ መስመሮች መካከል የአስመራው አንዱ  ሆኖ ተደምሯል፡፡ ከህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ በዘለለ በቀጣይ ቀሪዎቹ በአየር ክልሉ የበራራ መስመሮች ስራ ሲጀምሩ የሁለቱ ሀገራት አየር መንገዶች ከሚያደርጉት በረራ በተጨማሪ የሌሎች ሀገራት አየር መንገዶች በመስመሮቹ ስለሚጠቀሙ ለኢትዮጵያም ሆነ ለኤርትራ ኢኮኖሚያቸውን የሚደጉም በረከት ይዞ እንደሚመጣ አያጠራጥርም፡፡

 

በሁለቱም አገራት የሚገኘው ህዝብ የናፈቀውን ቤተሰብ ለመቀበል ቤቱን እንደሚያሰናዳ ሁሉ በመኪና ከሌላኛው ቤታችን አድርሶ ሊያመላልሱን አሊያም በኢኮኖሚ ሊያስተሳስሩን አራት መስመሮች እድፋቸውን አራግፈው፤ ከተጫጫናቸው ድብርት ለመላቀቅ ዳግም በመታደስ ላይ ናቸው፡፡ ከአዲስ አበባ- አስመራ የሚወስዱ በአድግራት-ዘላምበሳ፤ በመቀሌ-አድዋ-ራማ፤ በጎንደር- ሁመራ እንዲሁም በአዋሽ አርባ-ቡሬ-አሰብ የሚወስዱ መንገዶች ተለይተዋል፡፡ የህዝብን እንቅስቃሴ እና የኢኮኖሚ ልውውጦችን ለማሳለጥ በቀጣይ የአዳዲስ አማራጭ መንገዶች ግንባታ ሊካሄድ እንደሚችል የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ጠቅሷል፡፡

 

በሁለቱ አገራት መካከል የሰላም አየር መስፈኑን ተከትሎ የተራራቀ ቤተሰብ፤ የተነፋፈቀ ዘመድ-አዝማድ፤ አብሮ አደግ እና ጎረቤት የትዝታ ማቁን ጥሎ ለመገናኘት ቀጥሮ መያዝ ጀምሯል፡፡ ከዚህም በዘለለ አብሮ ስለማደግ እና ስለመበልጸግ አሻግሮ መመልከት ተጀምሯል፡፡አሁን በምስራቅ አፍሪካ የተነሳው የሰላም ማዕበል የአካባቢውን እምቅ የሰው እና የተፈጥሮ ኃብት ወደ ብልጽግና ሊመነዝር፤ ጥላቻን አርቆ ሰብዓዊነትን ሊያነግስ በወንድማማች ህዝብ ይሁንታ አግኝቷል፡፡ አለምም ህልም የሚመስለውንና ዳግም እየታደሰ ያለውን ግንኙነታችንን በአገራሞት በዓይኑ ሊመለከት በጆሮው ሊሰማ ተገድዷል፡፡