Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ዜጎች ወደ ሕጋዊ መንዛሪዎች ይምጡ

0 394

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ዜጎች ወደ ሕጋዊ መንዛሪዎች ይምጡ

ይቤ ከደጃች ውቤ

ዶላር እና ብር ከመራራቅ ይልቅ ወደ መቀራረብ እየተቃረቡ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሥልጣን ከያዙ ወዲህ ለኢትዮጵያ የመጣ የምሥራች ነው፡፡ ከሁለት ሣምንት በፊት በጥቁር ገበያ አንድ ዶላር ብር 36 ይመነዘር ነበር። ዛሬ ላይ ወደ ብር 31 ወርዷል ይባላል። ይህም  ከዚህ ቀደም በነበሩት ቀናት ውስጥ ያልታየ ያልተለመደ ቅናሽ ነው፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ የውጭ ምንዛሪ ምጣኔ ሀብታዊ ወይም ጤንነት የአንድ አገር የውድቀት ወይም የስኬት መለኪያ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያፈነገጡ የጥቁር ገበያ ምንዛሪዎች በሕጋዊ ጉዳይ ወደ ንግድ ባንኮች እንዲመጡም የሚረዳ ነው፡፡

በውጪ ምንዛሪ በጭማሪ የተናወጡ ነጋዴዎች እየተደናገጡም ሆነ በሰበብ አስባቡ ዋጋ በመጨመር በዜጎች ላይ የኑሮ ውድነት ያስከትላሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት የጥቁር ገበያው ገደብ እየያዘ አደብ እየገዛ ተቀባይነት እያጣ ዲያስፖራዎችም ሆኑ ነጋዴዎች ምንዛሪያቸውን በአገር ውስጥ ባንኮች እየላኩ ሕገ ወጥነቱ ሥርዓት በመያዝ ላይ ይገኛል፡፡

ባለፋት ሦስት ዓመታት በአገሪቱ ውስጥ በታዩት ቀውሶች ምክንያት በተከሰተው አለመረጋጋትም ሆነ አንዳንድ ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ገንዘባቸውን በዶላር ቀይረው ወደ ውጪ ያሸሹ እንደ ነበር ምንጮች ይጠቁማሉ፡፡ አንዳንድ የመንግሥት ሹሞች የዚሁ ሌብነትና ዝርፊያ ተግባር አባሪና ተባባሪ በመሆናቸው ጭምር ጥቁር ገበያው ንሯል። የዘረፋትንም ብር ወደ ዶላር በመቀየር ተሳታፊ የሆኑ ይገኙበታል፡፡ በድንበር አካባቢም አንድ ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር በትራክ ተጭኖ ሊወጣ ሲል በቁጥጥር ሥር መዋሉ የቅርብ ጊዜ እውነታ ነው፡፡

በውጪ ምንዛሪ ችግር እየተንገዳገደች ያለችው ኢትዮጵያ “ሳይተርፋት አበደረች”  እንደሚባለው በአደባባይ “ለጥቃቅንና አነስተኛ ነጋዴዎች ድጋፍና ማበረታቻ እንሰጣለን” እያለች ውስጥ ውስጡን ዶላር እያወጣች የቢሮ ወንበሮችና ጠረጴዛዎች ሳይቀር ከውጭ ስታስመጣ የነበረች ‘ታሪካዊ’ አገር ነች፡፡ እነዚህ ዜጎች ጊዜ ቢሰጣቸው ኖሮ ሰሊጥና ቡና ሳይቀር ከውጭ ያስመጡልን ነበር፡፡ በሸማኔ የሚሰሩ የእንስት የጥበብ ልብሶች ሳይቀር ከውጭ የሚመጡበት መንገድ መዝጋት ጊዜ ሊሰጠው አይገባም፡፡ ከፈለጉ ተመሳሳይ ምርት በአገር ውስጥ ሊመረት የሚችልበትን መንገድ አመቻችተውና ቀይሰው በማምረት ለዜጎቻችን የሥራ ዕድል መፍጠር ቴክኖሎጂዎችንም ማጋራት ያሻቸዋል፡፡

በአንድ በኩል በዶላር ችግር እየተንገዳገደች ላለችው አገራችን ዜጎችም ገንዘባቸውን በዶላር ማስቀመጥ ከፈለጉ ንግድ ባንኮች ብሔራዊ ባንኮችን ጨምሮ ምቹ ሁኔታዎችን መቀየስ አለባቸው፡፡ ለዚህም የኬንያንና የጅቡቲን ሆነ የሌሎች አገሮችን ባንኮች ተሞክሮ መቃኘት አስፈላጊ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ መርከብ እና ቱሪዝም ድርጅቶች የውጭ ምንዛሪ በማመንጨት ከፍተኛ ድርሻ ስላላቸው ወገባቸውን ጠበቅ አድርገው ሊሰሩ ይገባል፡፡

በአገሪቱ የታየው ሠላማዊ የሥልጣን ሽግግርና በዜጎች ላይ የታየው ተስፋም የዶላር ግዥው ሩጫ እንዲቀንስ የብር ተፈላጊነት እንዲጨምር የበኩሉን ሚና ይጫወታል፡፡ እየታየ ያለው ፖለቲካዊ መረጋጋትና በመንግሥት የሚደረገው ቁጥጥር በጥቁር ገበያ የሚታየውን የዶላር ፍላጎት አረጋግቶታል፡፡ ወደፊትም የጥቁር ገበያው እንዲጠፋና ዶላርን በሕጋዊ መንገድ መመንዘር እንዲስፋፋ የፋይናንስ አስተዳደሩን ማዘመንና የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ መቅሰም ወሣኝ ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱንና የዋጋ ግሽበቱን ለመቋቋም አንዳንድ የመንግሥት ድርጅቶችን ወደ ግል ለማዛወር ተወስኗል፡፡

ካለፈው ሰኔ ወር አጋማሽ ወዲህ የተጀመረው የድፍድፍ ነዳጅ ማውጣት ሙከራም የውጭ ምንዛሪ የሚገኝበት ዘርፍ ስለሆነ ወደፊት የተወሰነ የራሱ አስተዋፅዖ ይኖረዋል፡፡ ኦጋዴን አካባቢ የተገኘው የተፈጥሮ ጋዝ በየዓመቱ ከአንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል ተብሎ እንደሚገመት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ሰኔ 20 ቀን 2010 ዓ.ም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የድፍድፍ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ መገኘትን አስመልክቶ ለዜጎች ባበሰሩት የምሥራች ነዳጅ ተገኘ ተብሎ ለመቀራመት መሻኮትና መጋጨት ውጤቱ ኪሳራ ነው ብለዋል፡፡ “ለኢትዮጵያውያን የሀብት ሁሉ መሠረት ነዳጅ ሳይሆን ሕዝብ ነው፡፡” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀደም ሲል የተጀመሩ የግብርና ሥራ፣ አግሮ ኢንዱስትሪ የመሳሰሉት ዘርፎች ለአፍታም ቢሆን መስተጓጎል እንደ ሌለባቸው አሳስበዋል፡፡

ኢትዮጵያ ያለ ሦስተኛ ወገን ከሃያ ዓመታት በላይ ሻክሮ የነበረውን የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት እልባት እንዲያገኝ እና ሠላም እንዲመጣ በማድረግና ፈር ቀዳጅ በመሆን በጦርነት ውስጥ ላሉ አገሮች ፋና ወጊ እና ምሣሌ መሆን ችላለች፡፡

በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ብሎም በአፍሪካ አገሮች የብዙ ሕዝብ ባለቤት ኢትዮጵያ በቀጣናው ከፍተኛ ምጣኔ ሀብት አላት። በአገራችን የተፈጠረው ሠላምና መረጋጋት የውጪ ኢንቨስትመንትና የውጪ ምንዛሪን በመሳብ ሚና ይኖረዋል፡፡ ይህም ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መስክ ያላትን ተቀባይነትና ተደማጭነት እንዲጨምር የሚረዳ ብሎም ባለን ርካሽ ጉልበትና የተፈጥሮ ሀብት ተከስቶ የነበረውን የውጪ ምንዛሪ እጥረትን በመቅረፍ የራሱ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ የአገሪቱም ሠላምና መረጋጋት ዲያስፖራው ጥቁር ገበያን ወደ ጎን ብሎ በንግድ ባንኮች በመገልገል በቅርቡ በተከፈተው በዲያስፖራው ፈንድ ተጠቃሚ እንዲሆን በር የሚከፍት ነው፡፡ ይህም ‘’በአንድ ወንጭፍ ሁለት ወፍ’’ እንዲሉ በተከፈተው ሂሳብ ዲያስፖራው ራሱን፣ ቤተሰቦቹንና አገሩን ተጠቃሚ ለማድረግ ያስችለዋል፡፡

በቅርቡ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ አልጋ ወራሽ ሼክ ልዑል አሕመድ ቢን ዛይድ አል ያህያም በኢትዮጵያ ባደረጉት ጉብኝት ወቅት መንግሥታቸው የአንድ ቢሊዮን ዶላር እና የሁለት ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ስምምነት በአጠቃላይ የሦስት ቢሊየን ዶላር የዕርዳታ ስምምነት የውጭ ምንዛሪ እጥረትን በመቅረፍ አስተዋፅዖ ይኖረዋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም በሐምሌ ወር የመጀመሪያ ሣምንት የሰጠው ወደ 15 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ በኢትዮጵያ ተፈጥሮና ጋብ ብሎ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ንረትና እጥረት ረገብ ያደረገዋል፡፡

የዶላር ምንዛሪው በጥቁር ገበያ ቅናሽ እያሳየ እና ተቀባይነት እያጣ የመጣው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አሕመድ ኃላፊነት በያዙ መቶ ቀናት ውስጥ ነው፡፡ የጥቁር ገበያ ከመንግሥት ቁጥጥር የሚያፈነግጥ በገበያ ፍላጎት የሚሮጥና የሚመራ መሆኑ የአንድን አገር ምጣኔ ሀብታዊ ጤንነት የሚጠቁም ነው፡፡

በውጪ ምንዛሪ ገንዘባቸውን በቤታቸው አከማችተው ወይም ደብቀው የሚገኙ ዜጎች በፍጥነት ገንዘባቸውን ወደ ባንክ ገቢ አድርገው እንዲመነዝሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ባለፈው ሣምንት ማስጠንቀቂያ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡  

ባለሙያዎች እንደሚናገሩት የውጭ ምንዛሪ መቀነስ መሬት ላይ ባሉ ነገሮች ብቻ የሚከሰት አይደለም፡፡ የምንዛሪ ምጣኔ አንዳች ኮሽታና ጭምጭምታ በተሰማ ቁጥር ሊናጥና ሊደነግጥ የሚችል “ገበያ” ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዲያስፖራው፣ ለኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የውጪ ምንዛሪ ጥሪ ማቅረባቸው፣ በሶማሌ ክልል ነዳጅ የመውጣቱ ዜና እና በአገሪቱ የሰፈነው አንፃራዊ ሠላም የፖለቲካው ውጥረቱን በማስተንፈሱና በውጭ ያሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች አገራቸው እንዲገቡ፣ ለሠላማዊ ትግል እንዳይገደቡና እንዲንቀሳቀሱ መፈቀዱ የጥቁር ገበያን የዶላር ፍላጎት ያረጋጋዋል፡፡ የውጪ ምንዛሪ የቀነሰውም ምንም ዓይነት የፖሊሲ ለውጥ ሳይታይ ነው፡፡ በያዝነው አዲሱ የበጀት ዓመት አዳዲስ ፕሮጀክቶች እንዳይከፈቱ መደረጉም የዶላር ፍላጎትን በመቀነስ በምንዛሪው በኩል የተወሰነ አስተዋፅዖ ይኖረዋል፡፡

ምንዛሪው በጥቁር ገበያ እየወደቀ መምጣቱ በባንኮች ላይ ያለውን ተቀባይነት የሚጨምር ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ባደረጉት ጥሪ ለማኪያቶ ከሚያወጡት ገንዘብ በቀን አንድ ዶላር ቢያዋጡ በወር 30 ሚሊየን ዶላር ለመሰብሰብ ያስችለናል፡፡ በዚህም የኅብረተሰቡን ፍላጎት ለማሟላት የንፁህ መጠጥ ውኃ እና ትምህርት ቤቶች የመሳሰሉትን ለመገንባት ያስችለናል፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy