የለውጡ “ማግኔት”
ዋሪ አባፊጣ
የኢትዮጵያ ህዝብ ራሱ በትግሉ ባመጣው በለውጥ ሂደት ውስጥ እየቀዘፈ ነው፤ ያለ አንዳች ከልካይ። በህዝብ የኃይል ማዕበልነት የተገኘው ይህ ለውጥ ከፊቱ ደፍሮ የሚቆም ኃይል የሚኖር አይመስለኝም። ለውጡ እንደ ማግኔት በሀገር ውስጥ ከዳር እስከ ዳር እንዲሁም በውጭ የሚገኙ ለውጥ ፈላጊ ኢትዮጵያዊያንን እየሳበ ነው።
ይህ “ማግኔት” የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በማሰብ በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩ ቡድኖችን ቀደም ሲል ከነበሩበት ፍረጃ እንዲሰረዙ ያደረገ ነው። ሰሞኑን የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባርን (ኦነግ)፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባርን (ኦብነግ) እና ግንቦት ሰባትን በ2003 ዓ.ም ከፈረጃቸው የአሸባሪነት ባህር መዝገብ ዝርዝር ላይ በይፋ እንዲሰረዙ አድርጓል። ይህም ሀገራችን ውስጥ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋትና ማናቸውም ዓይነት ሃሳቦች እንዲደመጡ ዕድል የሚሰጥ ነው። ድርጅቶቹም ሀገር ቤት መጥተው ሃሳባቸውን በነፃነት በመግለፅ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ እንዲወዳደሩ የሚያስችል ነው።
ማንኛውም ዴሞክራሲያዊ ተግባር መቋጫው ጥርጣሬንና ግጭትን በማስወገድ ሰላምን፣ መደማመጥንና መቻቻልን መፍጠር ነው። ሰላምን ሊያሳጡ የሚችሉ በሮችን በውይይትና በመነጋጋር መዝጋት ነው። ይህም በሰላምና ዴሞክራሲ ውስጥ ልማትን እውን ለማድረግ ዕድል ይሰጣል። ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱም የፖለቲካውን ምህዳር በማስፋት ሁሉም ነገር በነፃነት እንዲከወን የሚያስችል ነው። የለውጡ መሃንዲስ የሆኑት ዶክተር አብይና ባልደረቦቻቸው በቀደዱት ፈር፤ መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ቁርጠኛ አቋም ይዟል። አሁን ባለንበት ሁኔታ ይህ ተግባር ዜጎች ፍላጎታቸውን በፈለጉት መንገድ እንዲገልፁ የማድረግ ዕድል ያመቻቸ ነው ማለት ይቻላል።
በእኔ እምነት ይህ የሆነውም ዴሞክራሲ ስር ባልሰደደበት ሀገር ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ ልባቸው ሃሳባቸውን ለህዝባቸው ሊያስተዋውቁና በህዝቡ ይሁንታ በሚካሄድ ምርጫ ሀገር ሊመሩ እንደማይችሉ መንግስት ስለተገነዘበ ነው። በመሆኑም በአሸባሪነት ተፈርጀው የነበሩት ቡድኖችን ከሽብርተኝነት ዝርዝር በመሰረዝ ወደ ሀገር ቤት እንዲመጡና ከህዝባቸው ጋር መክረው ለሀገራቸው የሚበጀውን ነገር እንዲከውኑ ማድረጉ እጅግ የሚደነቅ ተግባር ነው። የለውጡ ባለቤት የሆነው ህዝብን ፍላጎት ተከትሎ የሀገራችንን ሰላም አስተማማኝና ዘላቂ እንዲሆን የሚያስችል ብልህ ርምጃም ነው።
እንደ እውነቱ ከሆነ በሀገራችን ውስጥ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት በመንግስት በኩል እየተደረጉ ያሉ ውጤታማ ጥረቶች ማንንም ለማስደሰት አሊያም ለማስከፋት አይደለም። የሀገራችን ህዝቦች የታገሉላቸውን ህገ መንግስታዊ መብቶች በፅኑ መሰረት ላይ እንዲቆሙ ከማሰብ የመነጨ ይመስለኛል።
እንዳልኩት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የሚደረገው የለውጥ ጥረት ዛሬም “ማግኔት” ሆኖ ቀጥሏል። ከዚህ ቀደም ከውጭ ወደ ሀገር ቤት ከገቡት የኦሮሞ ዴሞክራሲ ግንባር (ኦዴግ)፣ የኦሮሞ አንድነት ነፃነት ግንባር (ኦአነግ) እንዲሁም በደርግ ዘመን ከፍተኛ ባለስልጣን የነበሩት አምባሳደር ዶክተር ካሳ ከበደን ጨምሮ ሌሎች ግለሰቦችንና ቡድኖችን የሳበው የለውጡ “ማግኔት”፤ ይህን ፅሑፍ ሳሰናዳ ደግሞ በዶክተር አረጋዊ በርሀ የሚመራው የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር ፓርቲ (ትዴትፓ) ልዑክ ወደ ሀገር ቤት ተመልሷል። ፓርቲው መንግስት ማንኛውም በውጭ የሚገኝ የፖለቲካ ድርጅት ወደ ሀገር ቤት ገብቶ በነፃው ምህዳር በመወዳደር ለሀገሩ እንዲሰራ ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ መምጣቱን ገልጿል።
የፓርቲውን ሊቀመንበር ዶክተር አረጋዊ በርሀ፣ አቶ መኮንን ዘለለውና አቶ ግደይ ዘርዓፅዮንን ጨምሮ ሌሎች አባላትን የያዘውን የልዑካን ቡድን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዩች ፅህፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ በደማቅ ሁኔታ ተቀብለውታል። ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ካሳሁን፤ አሁንም በውጭ ሀገራት የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ መንግስት ጥሪውን እንደሚያቀርባል ብለዋል።
ይህም እውነታ አሁንም ቢሆን ማንኛውም በውጭ የሚገኝ የሀገራችን የፖለቲካ ፓርቲ ሀገር ቤት ገብቶ በመስፋት ላይ በሚገኘው የፖለቲካ ምህዳር ተጠቃሚ እንዲሆን መንግስት ፅኑ ፍላጎት እንዳለው የሚያመላክት ነው።
እናም የፖለቲካ ምህዳሩ መስፋት በወጣቶች ትግል የተገኘ በመሆኑ በውጭ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይህን ዕድል በሚገባ ሊጠቀሙበት የሚገባ ይመስለኛል። ምክንያቱም ዕድሉ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ፓርቲዎች እኩል ተወዳዳሪነትን የሚያሰፍንና ሀገር ቤት ያሉት ማናቸውም ዓይነት እሳቤዎች ተደምጠው ህዝቡ ውሳኔውን እንዲያሳርፍባቸው ስለሚያደርጉ ነው።
የለውጡን “ማግኔት” መደገፍ ያስፈልጋል። ይህ የለውጥ ጎዳና ለማንኛውም ኢትዮጵያዊ ፓርቲ ምቹ ሁኔታን የፈጠረ ነው። ዴሞክራሲውም እንዲያብብ አስተማማኝ ምህዳር እየሆነ ነው። በዚህ የለውጥ ጉዞ ላይ ዴሞክራሲን ለማጎልበት በውጭ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሚዲያዎችና ሲቪክ ማህበራት የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ ይገባል። እንደሚታወቀው የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ዋነኛ መገለጫው አሳታፊነት ነው። የዴሞክራሲ አሳታፊነት ሁሉም ዓይነት አስተሳሰቦች ወጥተው እንዲደመጡ ያደርጋል። ህዝቦች ሊመሯቸውና ሊያስተዳድራቸው የሚችሉ ጠንካራ ሃሳቦችን በማድመጥ ይሁንታቸውን እንዲሰጡ ያደርጋል። ይህም በህገ መንግስቱ በግልፅ እንደተደነገገውም ስልጣን በህዝብ ፍላጎት ላይ በተመሰረተ ድምፅ እውን እንዲሆን ያደርጋል።
በእኔ እምነት ባለፉት ጊዜያት በህዝቡ ውስጥ ያሉት ማናቸውም ዓይነት አስተሳሰቦች በተሟላ ሁኔታ የተከናወኑ አይመስለኝም። ተፎካካሪ ፓርዎች በፍረጃ ምክንያት ወደ ሌላ ፅንፍ እንዲሄዱ ተደርገዋል። ‘ከእኔ ውጭ ሌላ ዓይነት አስተሳሰብ መስማት አልፈልግም’ የሚል ከዴሞክራሲ ቀኖና (doctrine) ጋር አብሮ የማይሄድ አተያይ ሲተገበር ሲሆን ነበር። ይህም የሀገር ውስጥ ተፎካካሪዎችም ይሁኑ በውጭ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሀገራቸውና ለህዝባቸው ‘ያግዛል’ የሚሉትን ነገር እንዳይፈፅሙ አድርጓቸዋል።
እንዲህ ዓይነቱ አሰራር እየተቆራቆስን በጠላትነት እንድንተያይና የሀገራችን ሰላም እንዲታወክ ከማድረግ በስተቀር የፈየደው አንዳችም ነገር ያለ አይመስለኝም። እንዲያውም የሀገራችን የመድብለ ፓርቲ ስርዓት የሚጠበቅበትን ያህል ጉዞ እንዳይራመድ ሽባ አድርጎ ያስቀመጠው ይመስለኛል።
ያለፉት ዓመታት የፖለቲካ ልዮነታችን አንድነታችን ሆኖ እንዳይቀጥል፣ በመነቋቆርና በመነካከስ እርስ በርሳችን እንድንዳማ እንዲሁም ከአጣብቂኝ ውስጥ ወጥተን ወደ ተሟላ የልማት ስራ በሙሉ አቅማችን እንዳንገባ ያደረጉን ናቸው። እናም እነዚህን ችግሮች ለመሻገር በዶክተር አብይ የሚመራው መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሁንም ድረስ ጥሪ ማድረጉ ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑ አያጠያይቅም።
የውሳኔው ትክክለኛነት መገለጫ የፖለቲካ ምህዳሩ በመስፋቱ ሳቢያ በውጭ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በለውጡ “ማግኔት” እየተሳቡ ወደ ሁገር ቤት መግባታቸው ነው። ለውጡ የሀዝብ እንደመሆኑ መጠን የትኛውንም የህዝብ አመለካከት የያዙ ፓርቲዎች ሀገራቸው ውስጥ ገብተው ሃሳባቸውን ለህዝብ ማቅረብ ይኖርባቸዋል።
ታዲያ ይህን ሁኔታ ተፃርሮ መቆም ማለት የህዝቦችን ህገ መንግስታዊ መብቶችን መገደብ ይመስለኛል። እናም መንግስት በህገ መንግስቱ መሰረት እያከናወነ ያለውን የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት የዜጎች ሃሳቦች እንዲደመጡ የማድረግ ስራዎቹ ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል እላለሁ። የለውጡ “ማግኔት”ም ምህዳሩን እጅግ እያሰፋ የተለያዩ ህዝቦችን ድምፅ የያዙ ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ከውጭ መሳቡን ይቀጥል ዘንድ ምኞቴ ነው።