Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

    የማይቀለበሰው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ

0 277

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

    የማይቀለበሰው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ

   ይልቃል ፍርዱ

ዲሞክራሲ በአንድ ጀምበር በአንድ መአልትና ሌሊት የሰፈነበት የአለም ክፍል  የለም፡፡ዲሞክራሲ የዘመናት ግንባታ ውጤት ነው፡፡በትውልድ ፈረቃ እያደገ እየሰፋ ባሕል ሁኖ እየተወረሰ ጥበቃ እየተደረገለት የሚያብብ የሚያፈራ ነው፡፡ዲሞክራሲ ከትምህርት መስፋፋትና ማደግ ጋር ነው የበለጠ የሚያድገው፡፡

 

የዲሞክራሲ ተቋማት ግንባታ እያደገ እየጎለበተ ሊሄድ የሚችለው ሰፈ በሆነ መልኩ የሕብረተሰቡን ተሳትፎ በወሳኝት በማሳደግ ነው፡፡ሰብአዊ መብትን ሕገ መንግስቱን በአግባቡ ማወቅ ማክበር ማስከበር ዲሞክራሲን ከማስፋት አንጻር እንዴት መጠቀም እንደሚገባው ማስተማር ማሳወቅ ሕብረተሰቡም የራሴ ነው ብሎ እንዲጠብቀው በማድረግ ነው የበለጠ ሊያድግ የሚችለው፡፤

 

የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ የአንድ ወቅት ክንውን አይደለም፡፡ረዥም አመታትን የሚያስቆጠር ሰፊ ድካምን የሚጠይቅ የቤት ስራ ነው፡፡የበለጸጉት ሀገራት ዛሬ  የደረሱበት ደረጃ ለመድረስ ብዙ መቶ አመታትን ተጉዘዋል፡፡በሂደት እየዳበረና እየጎለበተ የሚሄድ የሚራመድ በየግዜው አዳዲስ ለውጦችን የሚያመዘግብ ነው፡፡

 

በየሀገራቱ የሕዝብ መሰረታዊ ዲሞክራሲያዊ መብቶች መሰረታዊ መገለጫ ተደርጎ የሚወሰደው በተለይም በምርጫ ወቅት በብሔራዊ ደረጃ የሚከናወነው ሂደት ነው፡፡ በብቃት ሀገሬን ይመራል ያስተዳድራል የያዘው ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ ማሕበራዊ ወዘተ ፕሮግራሞች  ለሀገሬና ለእኔም ይበጃል ብሎ ሲያምን ሕዝብ በምርጫ ወቅት የሚሰጠው ድምጽ የመደገፍና የመቃወም መብቱ አይነተኛ የዲሞክራሲ መገለጫ ተደርጎ ነው ይወሰዳል፡፡

 

ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያራምዱት ፖሊሲ በትምህርት በጤና በፖለቲካው በማሕበራዊና በኢኮኖሚው ስራ አጥነትን ከመቅረፍ በውጭ ግንኙነት ፖሊሲና በመሳሰሉት የሚያራምዱት ፖሊሲ ነው በሕዝቡ ዘንድ ለመመረጥና  ላለመረጣቸው ወሳኝ ሁነው የሚቀርቡት፡፡፡ይሄ በምርጫ ሂደት ወሳኝ የዲሞክራሲ ሂደት ተደርጎ ይታያል፡፡

 

ፍጹም የሚባል ዲሞክራሲ በአለም ላይ የለም፡፡ሊኖርም አይችልም፡፡የዲሞክራሲ መስፋትና ማደግ ሀገርንና ሕዝብን የበለጠ ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡ዲሞክራሲያዊ መብቶች በብዙ መልኩ የሚገለጹ ናቸው፡፡ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ የመሰብሰብ የመደራጀት ተንቀሳቅሶ የመስራት መብት የፈለጉትን የመረጡትን እምነት በነጻነት የመከተል የማራመድ መብት ሀብት የማፍራት የመሸጥ የመለወጥ መብት የመዘዋወር መብት  የፕሬስ ነጻነት ወዘተ መብቶች ሁሉ የሰው ልጅ ሰው በመሆኑ ሊከበሩለት የሚገቡ ሰብአዊ መብቶች ናቸው፡፡

 

የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት 2/3 ኛው በሰብአዊ መብቶች ላይ ያተኮረና በሕግ የተከበሩ መሆናቸውን ቢደነገግም በሹሞችና በተለያየ ኃላፊነት ላይ በነበሩ ሰዎች ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሲካሄዱ ኖረዋል፡፡አሁን እየተሰራ ያለው ስራ ይሄንኑ የማስተካከልና የዜጎች ሕጋዊና ሰብአዊ መብት በሕገ መንግስቱ መሰረት እንዲከበር የማድረግ ነው፡፡ በተካሄደው ስር ነቀል የተሀድሶ ለውጥ የተጀመረው ዲሞክራሲን የማስፋቱና የማጎልበቱ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ሂደቱ አይገታም፡፡

 

የዲሞክራሲ መብቶች ጠባቂና ተከራካሪ አስከባሪ ሕዝብ ነው፡፡የተጀመረው ዴሞክራሲን የማስፋት ሂደት በሕዝብ መሰረትነት የቆመ እስከሆነ ድረስ የሚነቀንቀው አይኖርም፡፡ መንግስት እየመራው ያለው የለውጥ እንቅስቃሴ የመላውን ሕዝብ ድጋፍና ይሁንታ አግኝቶአል፡፡በመላው ሀገሪቱ በአራቱም ማእዘናት ከሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ ከምስራቅ እስከ ምእራብ መሀል ሀገርን ጨምሮ የታየው እጅግ የገዘፈ የሕዝብ ድጋፍ በታሪክ ውስጥ ለቀጣዩ ትውልድም በምሳሌነት የሚዘከር ነው፡፡

 

ሕዘዝቡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሪነት የሚካሄዱትን ሀገራዊ የለውጥ እንስቃሴዎች በመደገፍ ያለአንዳች ጎትጓች በራሱ ተነሳሽነት የተለያዩ የድጋፍ ቲሸርቶችን አሳትሞ ከልብ በመነጨ ድጋፍና ፍቅር ከየቤቱ ፈንቅሎ በመወውጣት ያካሄደው የድጋፍ ትእይንተ ሕዝብ መንግስት ያገኘውን ታላቅ የሕዝብ ድጋፍ ያረጋግጣል፡፡ይህንን የሕዝብ ድጋፍ በአግባቡ በብዙ መልኩ ለሀገራዊ ልማትና እድገት ለሰላምና መረጋጋት ፈርጀ ብዙ ችግሮቻችንን ተደጋግፈን ለመፍታት ወደተሻለ ሀገራዊ መግባባትም ለመሸጋገር የሚረዳ ቁልፍ ነጥብ ነው፡፡ሀገራዊ ችግሮቻችንን ልዩነትን በማስፋት ሳይሆን በመደማመጥ በመግባባት በመነጋገር በሰለጠነ መንገድ ለመፍታት ያስችለናል፡፡

 

ይህ ዛሬ በሀገር ደረጃ የሚታየው ታላቅና ግዙፍ ለውጥ የመጣውና የተገኘው ኢሕአዴግ ቀደም ሲል በተደጋጋሚ በአባል ድርጅቶቹ ውስጥ ባካሄዳቸው ተደጋጋሚ ግምገማዎችና በውስጥም ባደረጋቸው ትግሎች በመጨረሻም እልህ አስጨራሽ በሆነው የ17 ቀናቱ የአሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ከሚቴ የጥልቅ ተሐድሶ ውጤትና ውሳኔ መሰረት ነው፡፡  

 

በአሁኑ ሰአት ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይና የሚመሩት መንግስት ተግባራዊ እያደረገ ያለው የመጨረሻውን የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔዎችንና ቀደም ሲል ተወስነው ወደተግባር ሳይለወጡ የቀሩትን የተሀድሶ ለውጥ ውሳኔዎች ነው፡፡መንግስት በሀገር ደረጃ የዲሞክራሲ ምሕዳሩን ለማስፋት የዲሞክራሲ ግንባታውን እውን ለማድረግ በተጨባጭ የታዩ ሰፊ ሀገራዊ መግባባቶችን የፈጠሩ እርምጃዎችን ወስዶአል፡፡

 

ከፌዴራል እስከ ክልል ቀበሌ ባለው አደረጃጀት በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ታራሚዎች  በይቅርታ ተፈተዋል፡፡ታራሚዎችን የመልቀቁ ሂደቱ በጠቅላይ ሚኒስቴሩ በጎ ፈቃድ የተመሰረተ ሳይሆን በአገሪቱ የይቅርታ ሕግ ላይ ብቻ የተመሰረተ ነው፡፡የተፈቱት እስረኞች በሙሉ በሶስተኛ ወገን ላይ ጉዳት ያደረሱ አለመሆናቸው በደንብ ተጣርቶ የተካሄደ ሲሆን ይቅርታው የሚመለከታቸው ታራሚዎች በቀጣይም እየተጣራ የሚፈቱ ይሆናል፡፡

 

የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታው ሀገራዊ መግባባቱና የዲሞክራሲ ምሕዳሩን የማስፋቱ የዜጎችን ሰብአዊ መብት በሕገመንግስቱ መስረት የተከበረ እንዲሆን የመስራቱ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሎአል፡፡ ስኬታማና ውጤታማም እየሆነ ነው፡፡ዲሞክራሲውን ከማጎልበት አንጻር መንግስት በቁርጠኝነት ሰፋፊ ርምጃዎች በመውሰዱ በተግባር ተተርጉመዋል፡፡

መንግስትን በመቃወም መሳሪያ አነስተው ወደ ትጥቅ ትግል ገብተው የነበሩ የተለያዩ ተቃዋሚ ድርጅቶች መንግስት በሰላም ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ለሀገራዊና  ለዲሞክራሲ ግንባታ በነጻነት እንዲሳተፉ ባደረገው ጥሪ መስረት በትጥቅ ትግል ላይ የተሰማሩ ኃይሎች ትግላቸውን አቁመው ሰላማዊ ትግሉን መቀላቀል ችለዋል፡፡

 

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ በሰላማዊ መንገድ ሲታገሉ ከነበሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር  በፈለጉት ርእሰ ጉዳይ ለመነጋገር ዝግጁነቱን ከማሳየቱም ባሻገር ቀደም ሲል አብረው ይሰሩ የነበሩ ያሉ ቢሆንም አሁን ደግሞ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ሀገር ውስጥ በመግባት አብረው ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡ይህም በመንግስት በኩል የተወሰደ ግዙፍና ስርነቀል የሆነ እርምጃ ነው፡፡

በውጭ ሁነው ይሰሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን የተቃዋሚ ሚዲያዎች ተቃዋሚ ኃይሎች ወደ አገራቸው መመለስ መጀመራቸው መንግስት እያደረገ ላለው መሰረታዊ የተሀድሶ ለውጥና እርምጃ በታላቅ ስኬትነት የሚገለጽ ነው፡፡የመደመር ለውጡ የላቁ ሀገራዊ ውጤቶችን በማስመዝገብ ሀገራዊ ጉዞውን በድል ቀጥሎአል፡፡

 

ማጠቃለያ

የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ የበለጠ ውጤታማ የሚሆነው ሕዝብና መንግግሰት በጋራ ቆመው ተጋግዘው ሲሰሩ ብቻ ነው፡፡በአሁኑ ሰአት መንግስት በቁርጠኝት እየወሰዳቸው ባሉት እርምጃዎች መነሻነት ሰፊ ሀገራዊ ለውጦች በተጨባጭ እየታዩ ይገኛሉ፡፡ለውጡ በሕዝብ ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡የሚገታውም ሆነ የሚገዳደረው ኃይል አይኖርም፡፡  ለውጦቹ የዲሞክራሲ ስርአቱን ግንባታ ለማፋጠን፤ የዲሞክራሲ ምሕዳሩን ለማስፋት የላቀ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር ቁልፍ ሚናዎችን ይጫወታሉ፡፡የአገር ውስጥ ሚዲያዎች በተለይም የመንግስት ሚዲያዎች ቀደም ሲል ሕዝቡ ያነሳ ከነበረው ቅሬታና ብሶት አንጻር ዘገባቸውን ሚዛናዊ ማድረግ መጀመራቸው በአድናቆት የሚገለጽ ነው፡፡ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡›አንዳንድ የአገሪቱ ሕጎች በተለይ ከዴሞክራሲ ስርዓቱ ጋር ቀጥታ ግንኙነት አላቸው ተብለው የተለዩ (የጸረሽብር፤መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መተዳደሪያና የመገናኛና የመረጃ ነጻነት)ሕጎች የተወሰኑ አንቀጾቻቸው እንዲሻሻሉ በባለሙያዎች እየታዩ ይገኛሉ፡፡ በሀገራችን የበለጠ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለማስፋት የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታውንም ለማሳደግ በመንግስት በኩል እየተወሰዲ ያሉ እርምጃዎችን ያሳያል፡፡ዜጎችን የበለጠ የመብታቸው ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡በአጠቃላይ ሲታይ በአሁኑ ሰአት በመንግስት እየተወሰዱ ያሉት እርምጃዎች ከዚህ ቀደም ያልነበሩና ያልታዩ ሲሆኑ ሀገራችን በታላቅ የለውጥና የተሀድሶ ምሕዋር ውስጥ መሆኗን የሚመሰክሩ ናቸው፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy