Artcles

የሰልፎቹ እውነታዎች

By Admin

July 09, 2018

የሰልፎቹ እውነታዎች

ዳዊት ምትኩ

መንግስት በአገራችን ውስጥ በዋና ዋና ጉዳዮች ዙሪያ አገራዊ መግባባትን ለማጎልበት የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ ነው። እስካሁን ድረስ አገራዊ መግባባትን ለማጎልበት እየወሰዳቸው ያሉት እርምጃዎች ህብረተሰቡ ሙሉ ድጋፉን መስጠቱን ከተካሄዱ ሰልፎች ለመረዳት አይከብድም።

በአሁኑ ሰዓት በተለላዩ የአገራችን አካባቢዎች እየተካሄዱ ያሉ የድጋፍ ሰልፎች መንግስት ያደራጃቸውና በመልዕክትም የሚመራቸው አለመሆናቸው ይታወቃል። ህብረተሰቡ በራሱ ተነሳሽነት የሚያከናውናቸው መሆናቸውም ከማንም የሚሰወር አይደለም። አገራችን የተለያዩ ዓይነቶች አስተሳሰቦች ያሉባት በመሆኗ፤ በድጋፍ ሰልፎቹ ላይ የተለያዩ ባንዲራዎችና መልዕክቶች ሊቀርቡ መቻላቸው ነባራዊ ነው።

አሁን በምንገኝበት የለውጥ ሂደት እነዚህን ጉዳዩች ማስቆም አይቻልም። ለውጡን ያመጣው ህዝቡ እንደመሆኑ መጠን የታገለለትን መብትን ልንሸራረፍበት አንችልም። ለውጥ ማንኛውም ዓይነት አስተሳሰቦች በአደባባይ ወጥተው የሚታዩበት ነው። በመሆኑም በሰልፎቹ ላይ የሚታየውን እያንዳንዱን ነገር ለምንና እንዴት? እያልን ትርጉም የምንሰጥ ከሆነ አሁን ለምንገኝበት የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ምላሽ መስጠት አስቸጋሪ ይሆናል። የህዝቦችን ፍላጎት ማስተናገድም አይቻልም።

ከዚህ በተጨማሪ ሰልፎቹ ሙሉ በሙሉ በህዝቡ የተደራጁ፣ በህዝቡ የሚመሩ በመሆናቸው፤ ጠሪም ሆነ ተጠሪ የሌለባቸው ስለሆኑ የህዝቡን መብቶች መጫን አግባብ አይሆንም። በሰልፎቹ ላይ የሚስተዋሉትን የተለያዩ ሃሳቦችን በመመልከት የህዝቡብ የሃሳብ ብዝሃነት ከማክበር ውጭ ምንም ዓይነት አማራጭ ሊኖር አይችልም።

ሰልፎቹን የጠራውና ያስተባበረው እንዲሁም በሃሳብ የደገፈው ህዝቡ ራሱ እንጂ መንግስት አይደለም። በሰልፎቹ ላይ የሚታዩት ጉዳዩች አስደሳች ቢሆኑም ባይሆኑም የህዝቡ ፍላጎቶች ናቸው። ህዝቡ ላለፉት ሶስት ዓመታት የታገለው እንዲህ ዓይነት ፍላጎቶቹን ለመገለፅ ነው። እንዲያው በሰልፎቹ ላይ የሚታዩት የተለያዩ አመለካከቶች በህዝቡ ውስጥ ያሉትን ትክክለኛ ሃሳቦች እንድንረዳና በቀጣይም ጥናት ተደርጎ መፍትሔ ለማምጣት ልዩ ዕድል የሚሰጥ ነው። ስለሆነም የሰልፎቹን እውነታዎች ከእነዚህ ተጨባጭ ሁኔታዎች አኳያ መመልከት አስፈላጊ ነው።

እንደ እኔ…እንደ እኔ በሰልፉ ላይ የሚታዩት የተለያዩ ሃሳቦች የህዝቡ መገለጫዎች ናቸው። ይህ ደግሞ በየትኛውም ደዴሞክራሲያዊ አገር ውስጥ ያለ እውነታ ነው። እንኳንስ ህብረተሰብን የሚያክል አካል ቀርቶ በቤተሰብ መካከል የተለያዩ ሃሳቦች መኖራቸው አይቀርም። በዴሞክራሲያዊ አገር ውስጥ እነዚህ ሃሳቦች ወጥተው እንዲደመጡ ይደረጋል እንጂ ጫና አይፈጠርባቸውም። ከዚህ ይልቅ ያሉትን ልዩነቶች አቻችሎ ለመደመር የሚደረገውን ጥረት መደገፍ ተገቢ ይሆናል።

በአገራችው ውስጥ በተፈጠረው የለውጥ ነፋስ የመደማመጥ፣ የመቻቻል፣ የመከባበርና የአጋርነት ባህላችን እንዲሁም የአብሮነት እሴቶቻችን እየተጠናከሩ ነው። አንድ ማህበረሰብ ማንነቱ እንዲከበርለት የሌላውን ማንነት ማክበር እንዳለበት በማመን በተናጠልና በጋራ ባህሎቻቸውንና ታሪካቸውን ማክበርና ማንፀባረቅ የተቻለበት የለውጥ ሂደት ተጎናጽፈናል። አገራዊ መግባባታችን ከምንግዜውም በላይ በለውጡ ጠንክሯል።

የኢትዮጵያ ባህል፣ ቋንቋ እና ታሪክ ማለት የኢትዮጵያ ህዝቦች ባህሎች፣ ቋንቋዎች እና ታሪኮች ተደምረው የሚፈጥሩት ውህደት ነው። መደመር የምንከተለው ስርዓት መገለጫም ነው። ህዝቡ በሚያካሂዳቸው ሰልፎች ላይ የሚታዩትን ጉዳዩች በመመልከት ለምንና እነዴት ከማለት ዓላማውንና በፍቅር ስንደመር የምናገኘውን ጥቅም ማስላት ያስፈልጋል። እንዴት ልዩነቶችን በማቻቻል በየአካባቢው ግጥቶች እንዳይፈጠሩ መስራት ይኖርብናል በማለት ማሰብ አስፈላጊ ነው።

ህገ መንግስቱ ለሚፈጠሩ ሁነቶች ወቅታዊና አስተማማኝ ምላሽ መስጠት የሚችል ነው። ህገ መንግስቱን ተከትሎም ሊፈጠሩ የሚችሉ አነስተኛ ኑባሬያዊ ተግዳሮቶችን በመፍታት ሁሉም የአገሪቱ ህዝቦች በጋራ ተሳስበውና ተፈቃቅደው በአንድነት ስለሚኖሩባት ኢትዮጵያ ማሰብ ይገባል።

በተለያዩ አካባቢዎች አንዳንድ ለውጡ የማይዋጥላቸው አካላት ግጭቶችን ሊቀሰቅሱ ይችላሉ። እነዚህን ሰው ሰራሽ ግጭቶች ለመከላከልና የህዝቦችን ኢትዮጵያዊ አንድነት ብሎም አገራዊ መግባባት የሚጠናከርበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይሻላል። ለምን እገሌ በሰልፍ ላይ ይህን ይዞ ወጣ፣ እንዲህ ተናገረ ማለት ምንም ዓይነት አገራዊ ፋይዳ የላቸውም። ይልቁንም አገራዊ አንድነት ይበልጥ የሚጠብቅበትን ሁኔታ በመመካከር ማበጀት ያስፈልጋል።

ባለፉት ሶስት ዓመታት የኢትዮጵያ ህዝቦች መብታቸው ተደፍቆ በአድሎአዊና ፍትህ አልባ ሁኔታ ውስጥ በማለፋቸው ዛሬ በየሰልፎቹ ላይ ያሻቸውን ዓይነት ሃሳቦችን ቢያራምዱ ብዙም የሚደንቅ አይደለም። ምናልባትም ለምን እንደታገሉ እየገለጹ ሊሆን ይችላል።

ሰልፎቹ በአገሪቱ ተንሰራፍቶ የኖረውን የተዛባ ግንኙነቶችን ማሳያዎች ሊሆኑም ይችላሉ። ለምን? ብሎ መጠየቅ የሚቻል ቢሆንም፣ ከዚህ ይልቅ ሁሉም ዜጎች ኢትዮጵያን በመገንባት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ የማድረግ፣ በአካባቢ ጉዳዮቻቸው ላይ ወሳኝ የሚሆኑበትን የራስ አስተዳደር የማረጋገጥ ሃቆች ላይ አተኩሮ መስራት የሚገባ ይመስለኛል።

ኢትዮጵያ የምትከተለው ስርዓት ከአገሪቱ ልማት ተመጣጣኝ ጥቅም የሚያገኙበትን መንገድ መቀየስ ይገባል። እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ እንዲደረጅ ማሰብ ያስፈልጋል። አገራዊ መግባባትን አሁን ከተገኘው በላይ እንዲንር መስራት ያስፈልጋል። በአንድነት ውስጥ የተለያዩ ሃሳቦች የሚንሸራሸሩበት ዘላቂ ዴሞክራሲን መገንባት እንደሚቻል በጥልቀት መገንዘብ አስፈላጊ ነው።

እንኳንስ በለውጥ ሂደት ውስጥ ሆነን የዜጎችን ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ለምን እንዲህ ሆነ? እያልን ልንጠይቅ ቀርቶ፤ ከለውጥ ሂደት ውጭ በምንሆንበት ወቅትም ቢሆን የዜጎችን መብቶች ልንጋፋ የምንችል አይመስለኝም። ስለሆነም በሰልፎቹ ላይ የተስተዋሉትን ጉዳዩች እያንዳንዷን ነገር እየተከታተልን እንዴትና ለምን? ከምንል በዋናው የሰልፉ ዓላማና ግብ ላይ ማተኮር ትክክለኛ እይታ ይመስለኛል።