CURRENT

የተከበራችሁ በተባበሩት አሜሪካ ግዛቶች የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን

By Admin

July 09, 2018

የተከበራችሁ በተባበሩት አሜሪካ ግዛቶች የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን በሙሉ እንዲሁም ለሚዲያው ማህበረሰብ “ግንቡን በማፍረስ ድልድዩን እንገንባ” በሚል መሪ ቃል በሃምሌ 19፤20ና 21 (እ.ኤ.አ ጁላይ 26 27፤ 28 እና 29)በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዶ/ር አብይ አህመድ በሚመራ ከፍተኛ ልኡክ ቡድንና በኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን መካከል ለሚደረገው ታሪካዊ ግንኙነት በተዘጋጀው የጋዜጣዊ መግለጫ ስለተገኛችሁ በራሴና በመላው የኮሚቴ አባላት ሥም  ምሥጋናዬን አቀርባለሁ፡፡

ክቡር ዶ/ር አብይ ያሉትን በመጥቀስ መልእክቱን ልጀምር

“በውጭ አገር የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለስራም ሆነ ለትምህርት በሄደበት ሁሉ ኢትዮጵያን ተሸክማት ይዞራል፡፡ ኢትዮጵያዊ ከኢትዮጵያ ታወጡት እንደሆነ ነው እንጂ ኢትዮጵያን ከኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ አታወጧትም የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ ሁላችሁም በታታሪነታችሁ፤ በእውቀታችሁ እና የትም በሚከተላችሁ የአገራችሁ የጨዋነት ባህሪ የኢትዮጵያ የእሴቶቿ እንደራሴዎች ናችሁ፡፡” ብለዋል፤

የጠቅላይ ሚኒስትራችን ልባዊ እምነት የሆነው ይህ ጥሪ በአገራችን ታሪክ በመጭው ሐምሌ መጨረሻ ይካሄዳል ተብሎ የሚታሰበው ታላቅ ሕዝባዊ ጉባኤና ልዩልዩ የውይይት መርሃ ግብሮች በአገራችን የ50 አመት ታሪክ ውስጥ በይዘቱም ሆነ በመጠኑ የተለየ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቅ ነው፡፡ ልባዊ ይቅርታ እንዲጀመር ብሩህ ተስፋ የተሰነቀ ሲሆን ፍቅርና አንድነት  በአገራችን ኢትዮጵያ እንዲሰፍን በሕዝቦቿ መተማመንና መቀራረብ እንዲጐለብት ወደፊት አርቆ የማየት የአስተሳሰብና የሃሣብ ልእልና ባህል ማምጣት እንድንጀምር የመጀመሪያውን ምእራፍ የሚከፍት ነው፡፡

 

 

በአጠቃላይ ይቅርታ የተሳካ የሚሆነው ሁሉም ወገኖች ከልብ ሲፈጽሙት ችግሩ ዳግም እንዳይመለስ፤ እየቀነሰ ሄዶ እንዲጠፋ ከማድረጉም በላይ  በሰበብ አስባብ የማይናድና አብሮነቱ እየተገነባ የሚሄድ ሲሆን ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለበሰለና ለሰከነ የሃሣብ ነጻነትና ትግል በር ይከፍትና ግለሰቦችና ቤተሰብና ማህበረሰብ በአጠቃላይ በአገር ደረጃ በማያቋርጥ ሁኔታ እያደገ እንዲሄድ ያስችለዋል፡፡ የዚህ የፍቅርና ይቅርታ እርቅና ከልብ መወዳጀት ውጤቱ ሁሉም ወገኖች  አሸናፊ ሲሆኑ ነው፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

አመሰግናለሁ!