Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የእኛ ብቻ…

0 503

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የእኛ ብቻ…

                                                        ደስታ ኃይሉ

ኢትዮጵያ አንፃራዊ ሰላም ያላት አገር ናት። የኢትዮጵያ ሰላም የራሷ ብቻ አይደለም። ካላት ጂኦ ፖሊካዊ ሁኔታ ለቀጠናው አገራትም የአገራችን ሰላም ወሳኝ ነው። ይህም የእኛ ሰላም የምስራቅ አፍሪካ አገራት ሰላም መሆኑን የሚያመላክት ነው። የኢትዮጵያ ሰላም መደፍረስ የቀጣናው አገራት ሰላም መደፍረስ ነው። የእኛ ብቻ የምንለው ሰላም የለንም። ሰላማችን የሁሉም ነው።

ኢትዮጵያ ታላቅ አገር ናት። ህዝቦቿም ታላቅ ናቸው። ከ100 ሚሊዮን በላይ የሚሆነው ይህ ታላቅ ህዝብ በቀጣናው አገራት ውስጥ ተዓምር መፍጠር የሚችል ነው። አሁን በሚገኝበት የአንድነት ቁመና ብቻ ከሁሉም የቀጣነው አገራት ጋር በልማት ተሳስሮ መስራት ከቻለ ምስራቅ አፍሪካን የአህጉሪቱ ተምሳሌት ማድረግ የሚችል አቅም ያለው ነው።

የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነትም ከዚህ አኳያ መታየት ያለበት ነው። የግንኙነቱ ፋይዳ ከሁለቱ ህዝቦች ባሻገር ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ቁልፍ ሚና ይጫወታል የሚባለውመ ለዚሁ ነው። ኢትዮጵያና ኤርትራ ሰላም ከሆኑ ተጠቃሚነታቸው እየጎለበተ ይሄዳል። የመደመር ፖለቲካው በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በቀንዱ አካባቢም እየተካሄደ ነው የሚባለውም ለዚሁ ነው።

የመደመር ፖለቲካው የቀጣናው መሰረት አገራችን በአዲሶቹ መሪዎቿ አማካኝነት የምታካሂደው ዲፕሎማሲ ነው። አገራችን ከቀጣናው አገራት ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነቶችን ለማጠናከርና ዘላቂ ጥቅሟን ለማስከበር መንግስት ሳይታክት እየሰራ ነው።

በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ዋናውን ትኩረት በጎረቤቶች ላይ አድርገው እየሰሩ በመሆናቸው ከሱዳን፣ ከጅቡቲ፣ ከኬንያ፣ ከደቡብ ሱዳንና ከሶማሊያ ጋር አገራችን ያላት ግንኙነት ጠንካራና በጥሩ ደረጃ ላይ እንዲገኝ ማድረግ ችለዋል። ከኤርትራ ጋርም የሰላም ድርድር በማካሄድ የመደመር ፖለቲካው ቀጣናውን እንዲያካልል እያደረጉ ነው።

አገራችን በሶማሊያ ሰላም እንዲሰፍን፣ አገሪቱ ወደ መልሶ ግንባታ እንድትገባና ህዝቡ መሠረታዊ የማህበራዊ አገልግሎቶችን እንዲያገኝ አዲስ ከተመረጠው ከፕሬዚዳንት ፎርማጆ መንግስት ጋር እጅግ ተቀራርቦ ለመሥራት ስምምነት ላይ ተደርሷል።

ከዚህ በተጨማሪም ደቡብ ሱዳን ውስጥ እየከፋ የመጣውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በሚደረገው ጥረት በቅርቡ በአገሪቱ ፕሬዝዳንትና በተቀናቃኛቸው ዶክተር ሪክ ማቻር አማካኝነት የተደረሰው የሰላም ስምምነት ሁሉንም አካላት ያካተተ እንዲሆን የማበረታታት ስራዎችን በመከወን አገራችን የአንበሳውን ድርሻ እየተጫወተች ነው።

ኢትዮጰያ ከጎረቤቶቿ አልፋ ከምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ከሩዋንዳና ከኡጋንዳ፣ ከታንዛንያና ከቡሩንዲ ጋር ያላት ግንኙነትም ጠንካራ ነው። ይህን በጎ የሆነ የሀገራችንን የሁለትዩሽ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ስራው ተጠናክሮ ቀጥሏል።

የመደመር ፖለቲካው በቅድሚያ ከጎረቤት አገራት ለጥቆም ከምስራቅ አፍሪካ አገራት ጋር በጋራ ጥቅምና ተፈላላጊት የሚከናወን ነው። ከዚህ ባሻገርም በአባይ ተፋሰስ ዙሪያ የናይል ኢንሺየቲቭ ማዕቀፍ እንዲጎለብት አገራችን የጀመረችው ስራ ሂደቱን በማነቃነቅ መጫወት የሚገባትን ሚና ለመወጣት እየሰራች ትገኛለች።

የዚህ ሁሉ ጥረት ታዲያ መዳረሻው አገራት በአንድ ላይ ሆነው በዕድገት እንዲጓዙ ማድረግ ነው። በእኔ እምነት መደመር ከአገራችን አልፎ ቀጣናውን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው የሚባለው ከእነዚህ ሃቆች በመነሳት ይመስለኛል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የአካባቢውንና ጎረቤት ሀገሮችን ለጋራ ጥቅምና ሰላም እንዲሰሩ የሚጋብዝ የመደመር ፖለቲካን እየተከተለ ነው። ይህ አካሄድ እንደ ቀድሞዎቹ ፖሊሲዎች የሀገር ውስጥ ጉዳዮችን ቸል በማለትና ወደ ውጭ ብቻ ያነጣጠረ ነው ማለት አይደለም። ቅድሚያ ለአገር ውስጥ ሰላም በመስጠት በአንድነትና በመረጋጋት ላይ ትኩረት ሰጥቷል። ይህን እውን እያደረገ በመሆኑም በአካባቢያችን ብሎም በአፍሪካ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም እንዲፈጠርና የጋራ ልማትና ትብብር እንዲጠናከር የሚያደርግ ነው።  

የመደመር ፖለቲካው ኢትዮጵያ ከማንኛውም ሀገር ጋር የሚኖራት ግንኙነት በመሰረታዊ አገራዊ ጥቅማችን ደህንነት ላይ የተመሰረተ፣ እንዲሁም የልማትና የዴሞክራሲ ሂደቱ ስር እየሰደደና የአገራችን ዕድገት እየተፋጠነ በሄደ ቁጥር ለአደጋ ተጋላጭነታችን እንዲቀንስ የሚያደርግ ነው።

የውስጥ ደህንነታችንን ለማስጠበቅ ዋናው መሣሪያ በአገራችን ውስጥ በመደመር አንድነታችንን እያጠናከርን ልማትና ዴሞክራሲን በሚፈለገው ፍጥነት እውን ማድረግ ነው።

ስለሆነም ኢትዮጵያ በአዲሶቹ አመራሮቿ የውስጭ ጉዳይዋን በበቂ ጥናት ላይ መስርታ ለዕድገታችን አደጋ ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዩችን የመቀነስ፣ ግጭቶች ሲፈጠሩ በባህላዊ የግጭት አፈታት ማህበረሰቡ ራሱ እንዲፈታቸው የማድረግ መንገዶችን በመከተል ላይ ትገኛለች።

አገራችን እየመራ ያለው አዲሱ አመራር አንዱ ማህበረሰብ ከሌላው ጋር ተደምሮ ለአገሩ ዕድገት ማበርከት ያለበትን እውነታ እያስገነዘበች ትገኛለች። በተለይ የመደመር መስመሩ የአገራችንን ቀደምት ልዕልና የሚመልስ መሆኑ አጠያያቂ አይመስልም—ካለው ነባራዊ ሁኔታ ለማወቅ የሚከብድ አይደለምና።

ምናልባትም በዚህ መንገድ ሊፈቱ ያልቻሉትን አመራሩ በአካል ተገኝቶ ፊት ለፊት በማነጋገር ህብረተሰቡ የለውን ባህላዊ እሴቶች ተጠቅሞ ሰላም የማውረድ ሂደትን እየገነባ ነው። ይህ ሂደት የመቻቻል፣ የመደማመጥ፣ የአንድነት መንፈስን በመፍጠር ዘላቂ ሰላምን በመፍጠር ላይ ይገኛል።

አዲሱ አመራር ህገ መንግስቱን መሰረት አድርጎ እየተከተለ ያለው ዲፕሎማሲ በአጭር ጊዜ ከፍታ ማማ ላይ መውጣት የቻለ ነው። እኛ ያለንን በመስጠትና ሌሎች ያላቸውን በመቀበል መርህ ከተለያዩ አገሮች ጋር ያለን ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ የኢንቨስትመንት ፍሰትና ሚዛናዊ የንግድ ትስስር እንዲኖር በማድረግ ላይ ይገኛል። በቅርቡ አገራችንን የጎበኘው የአሜሪካ ልዑካን ቡድን በኢንቨስትመንትና በንግድ ከኢትዮጵያ ጋር ተባብሮ ለመስራት ያሳየው ፍላጎት የዚህ አባባሌ አስረጅ ነው።

አገራችን ከራሷ ባሻገር በአካባቢው የተረጋጋ የፖለቲካ ሂደት እንዲኖር ግጭቶችና ውዝግቦች በሰላማዊ ጥረት እንዲፈቱ ብቻ ሳይሆን የሰላም፣ የትብብርና የመደመር አድማሱ ሰፊ እንዲሆን እያደረገች ነው። የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት ከዚህ አኳያ የሚታይ ነው። በውዝግብ ውስጥ መኖር የጋራ ተጠቃሚነትን እንደማያሰፍን የተገነዘበችው አገራችን፣ ወንድም ከሆነው የኤርትራ ህዝብ ጋር በፍቅር ለመደመር የምታደርገው ጥረት ከዚህ ሃቅ የሚቀዳ ነው። ሰላማችን የእኛ ብቻ ሳይሆን የቀጠናው ጭምር ስለሆነ ይህን የጋራ ትብብርና ተጠቃሚነት መንገድ መከተል ትክክለኛ አካሄድ ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy