Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የኬንያው ጋዜጣ ምን አለ?

0 330

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የኬንያው ጋዜጣ ምን አለ?

ገናናው በቀለ

በቅርቡ የኬንያው “Nation” ጋዜጣ በድረ ገጹ በኒውዮርክ የልማት ኢኮኖሚስት እና የዓለም ፖሊሲ ባለሙያ የሆኑት ሚስተር ኬኔዲ ቺሶሊ “ኬንያ ማደግ ከፈለገች የኢትዮጵያን የዕደገት ፖሊሲ መመልከት አለባት” በሚል ጭብጥ ያቀረቡት ጽሑፍ አስነብቧል። በጋዜጣው ላይ ሚስተር ቺሶሊ በማሳያነት ከ20 ዓመታት በፊት የኬንያውያን ዓመታዊ ገቢ ከኢትዮጵያ በሁለት እጥፍ ይበልጥ እንደነበረ፣ ሆኖም እ.ኤ.አ በ2015 ኢትዮጵያ ከምስራቅ አፍሪካ ባለ ግዙፍ ኢኮኖሚ መሆን መቻሏን አቅርበዋል። እንዲሁም ባለፈው ዓመት ከምታመርተው ዕቃዎችና አገልግሎቶች በአምስት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ኬንያን መቅደም እንደቻለች አስረድተዋል።

በተጨማሪም የአገራችን ዕድገት በተቀመጠው ዕቅድ መሰረት ኢኮኖሚዋ እየተመነደገ ከአፍሪካ ምናልባትም ከዓለም ባለ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትን እያስመዘገቡ ካሉ አገራት ቀዳሚዋ አገር ሆና እንደምትቀጥል አብራርተዋል። ዕድገታችን እየጨመረ ከመጣው የህዝብ ቁጥር ጋር ተመጋጋቢ እንደሆነና የዜጎች ትክክለኛ የነፍስ ወከፍ ገቢም በ42 ነጥብ 77 ዶላር መድረሱን ገልጸዋል።

ይህም ኢትዮጵያ የምትከተለው የልማት ፖሊሲ ለኬንያ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች አፍሪካዊያን ወንድሞቻችንም ምሳሌ ተደርጎ የሚወሰድ እንደሆነም አስረድተዋል። ይህ የሚስተር ቺሶሊ እማኝነት አገራችን የምትከተለው የዕድገት ፖሊሲ ለጎረቤት ወንድሞቻችን በአርአያነት እየቀረበ መሆኑን የሚያረጋግጥ ይመስለኛል።

እርግጥም ይህ የሚስተር ቺሶሊ እማኝነት ዝም ብሎ የተገኘ አይደለም። ይህ የሆነው አገራችን ለግብርና ምርት በሰጠችው ትኩረት እንዲሁም በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በተለይም በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግና ኢንዱስትሪ ዘርፎች የተሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መምጣት በመቻሉ ነው። ስለሆነም ሀገሪቱ ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗን የተገነዘቡ በርካታ የውጭ ኩባንያዎችና ባለሃብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ከፍተኛ ፍላጎት እያሳዩ ነው። ይህ ሁኔታም ኢትዮጵያ ምን ያህል ሁሉም ሀገር የሚፈልጋት መሆኗን ያረጋግጣል።

መንግስት አገራዊው ተጨባጭና ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመከተል ሀገሪቱ ለዘመናት ከምትታወቅበት የድህነትና የኋላቀርነት ታሪክ በሂደት እየቀየረ ከመሆኑም በላይ፤ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ባሰገኘው ልማታዊ እመርታ ለአፍሪካና ለዓለም ተምሳሌት መሆን ችሏል።

እንደሚታወቀው ሁሉ የአንድ ሀገር ህዝብ በምግብ ሰብል ራሱን ችሏል የሚባለው በአገሪቱ ከተመረተው አጠቃላይ ምርት የሚኖረው የነፍስ ወፍ ድርሻ ተሰልቶ ነው። ከዚህ አኳያ የሀገራችን ህዝብ የነፍስ ወከፍ የምግብ ሰብል ድርሻ ሲሰላ በወር ሶስት ኩንታል መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።

ይህም በምግብ ሰብል በአብዛኛው ራሳችንን ወደ መቻል የምንቃረብበት ወቅት ሩቅ አለመሆኑን የሚያመላት ነው። በመሆኑም በምስራቅ አፍሪካ በተደጋጋሚ በሚከሰተው የድርቅና የረሃብ አደጋ ማንም ሰው እንዳይሞት ዋስትና ሆኗል ማለት ይቻላል።

እንደሚታወቀው  ሁሉ የበለጸጉት ሀገሮች  ለመልማት ባደረጉት እንቅስቃሴ  በዓለማችን ሥነ ምህዳር ላይ በፈጠሩት ቀውስ ሳቢያ በሚፈጠረው የአየር ንብረት መዛባት የተለያዩ አህጉሮች በድርቅ አደጋ ይጠቃሉ። ከእነዚህም ውስጥ እንደ አፍሪካ ያሉ ያላደጉ አህጉሮች ባልፈጠሩት ችግር ግንባር ቀደም ሰለባ ይሆናሉ። በተለይም የምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች  የችግሩ መሆናቸው ግልፅ ነው። ኢትዮጵያ የችግሩ ተጠቂ ብትሆንም በተለይ ለግብርናው ዘርፍ በሰጠችው ትኩረት እድገቷን አጠናክራ እየቀጠለች ነው።

በአሁኑ ወቅት ለመካከለኛና ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች የቴክኖሎጂና የማምረት አቅማቸውን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል። ከእነዚህም መካከል የአቅም ግንባታ፣ የገበያ ትስስርን መፍጠር እንዲሁም የኢንቨስትመንት ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ ነው። ይህ ደግሞ የውጭ ምንዛሬ ግኝታችንን ለማሳደግ ያስችላል።

መንግሥት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪን በወጭ ንግዱ ለማጠናከር ባከናወነው ተግባር ውጤት እያስመዘገበ ነው። ለምሳሌ የጨርቃ ጨርቅና የአልባሳት ኢንዱስትሪ፣ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ተስፋ ሰጪ ለውጦች እየታዩባቸው ነው። እንደሚታወቀው ሁሉ ለዘላቂና ፈጣን ዕድገቱ ምቹ የሆነ የማክሮ ምጣኔ ሃብት ሁኔታ ከመፍጠር አኳያ በኢንቨስትመንትና በቁጠባ መካከል ያለው ሚዛን ትልቅ ትርጉም አለው። ይህን ለመከወን መንግስት እየሰራ ነው።

በተለይም በማኑፋክቸሪንግና በግብርና፣ በመሠረተ-ልማት፣ በማህበራዊ ልማት ዘርፎችና በሌሎች መስኮች የሚከናወኑ የግልና የመንግስት ኢንቨስትመንቶች ፈጣን ዕድገትን በማረጋገጥ በኩል የራሳቸውን ሚና እየተጫወቱ ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ማንኛውም ሀገር በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካ መስኮች ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ተጠቃሚ ያደርጋል። ልማቱ እንደ ጨርቃጨርቅ በመሳሰሉ ቀላል የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በርካታ የስራ ዕድል የሚፈጠር እና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትንም በስፋት መሳብ የሚችል ነው። መንግስት በዚህ ረገድ በርካታ ስራዎችን እየሰራ ነው።

ይህም የህዝቦችን ተጠቃሚነት ከፍ እያደረገ ከመሆኑም በላይ፤ የውጭ ምንዛሬም ሊያስገኝ የሚችል ነው። በተጨማሪም የቀላል ማኑፋክቸሪንግ ልማቱን ያፋጥናል፤ ከተሞችን ወደ ላቀ የዕድገት ደረጃ የማሸጋገር ብሎም አዳዲስ ከተሞች እንዲፈጠሩ እያደረገ ነው።

ኢንቨስትመንት በአገራችን እየተስፋፋ መምጣቱም ለእድገታችን ሌላኛው መሰረት ነው። በአሁኑ ሰዓት በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በተለይም በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግና ኢንዱስትሪ ዘርፎች የተሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መጥቷል። አገሪቱ ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗን የተገነዘቡ በርካታ የውጭ ኩባንያዎችና ባለሃብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን እየፈሰሱ ነው።

የኢንቨስትመንት ፖሊሲው በግሉን ባለሃብት መሰራት የሚገባቸውና በመንግስት ሊከናወኑ የሚገቡ ተግባራት ተለይተው በመካሄዳቸው በሁለቱም በኩል ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው። የአገር ውስጥም ይሁን የውጭ ባለሃብቶችን የሚሰማሩባቸውን ዘርፎች በመለየት አንፃራዊ በመሆነ መንገድ ለሀገሪቱ ዕድገት የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ እየተደረገ ነው።

በእነዚህና በሌሎች የእድገት ተግባራት አገራችን በያዝነው ዓመት በዘጠኝና በአስር በመቶ መካከል እድገት እንደምታስመዘግብ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለፓርላማ ሲናገሩ አድምጠናል። ይህም መንግስት አሁን በያዘው መንገድ በማስመዝገብ የኬንያው ጋዜጣ ከጠቀሰው በላይ እድገት ማስመዝገብ እንደሚችል የሚያረጋግጥ ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy