የግብር ግዴታን መወጣት…
ይቤ ከደጃች ውቤ
ግብር፣ መንግሥት ሥራ ካላቸው ዜጎች የሚሰበሰበው ገንዘብ ነው፡፡ ይህ ገንዘብም የህዝቡን፣ ሰላምና ፀጥታ የሚያስከብርበት እና እንደ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት፣ የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት፣ መንገድና ስልክ፣ የመሳሰሉትን መሠረታዊ ፍላጎቶችን የሚያሟላበትን ስልት መተግበሪያ ነው፡፡
ግብር በሀገራችን ለረጅም ጊዜ የቆየ ታሪክ ቢኖረውም ለነገሥታቱ፣ ለሹማምንቱ እና ለጎበዝ አለቆች መንደላቀቂያ ከመሆኑ ውጪ ለሀገሪቱ ያበረከተው በጎ አሻራ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ግብርን ከዜጎች የሚሰበስቡት ሹማምንቱ እና ነገሥታቱ የራሳቸውን ፍላጎት አሟልተው የአካባቢ ሰዎችን ግብር /ግብዣ/ ከማብላት ውጪ ለህዝብ ፋይዳው ያለው ተግባር አልሠሩበትም ነበር፡፡
ዜጎቿ ከመቶ ሚሊዮን በላይ የሆነችው ኢትዮጵያ ህዝቧ አብዛኛው በአርሶ አደርነት የሚተዳደር እና በከተሜዎች ዘንድ እንደ ኋላ ቀር የሚያታይ ዜጋ ቢሆንም ከንጉሡ (ቀዳማዊ ሀይለ ሥላሴ) ዘመን ጀምሮ የሀገሪቱን የውጪ ምንዛሬ ፍላጎት እያሟላ መሆኑ ተጨባጭ ሀቅ ነው፡፡ ለዚህም ቡናና ሰሊጥ የመሳሰሉት ለዉጪ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች ጉልህ ማስረጃዎች ናቸው፡፡
በዳግማዊ ምኒሊክ ዘመን እንደ ባቡር፣ መንገድ፣ ስልክ፣ ፖስታ፣ ትምህርት ቤት፣ ህክምና የመሳሰሉትን በማቋቋም ፈር ቀዳጅ ከመሆናቸው በተጨማሪ ህዝቡ በገበረው ግብር ተጠቃሚ መሆን የሚችልበትን መንገድ ቀይሰዋል፡፡
ያለንበት ወቅት ዘመናዊ ቢሆንም ግብር ሳይገብሩ አንጡራ ሀብት ያካበቱ ብዙ ዜጎች ያሉበት፤ ግብር ለሚገብሩ ዜጎች የበለጠ ተጠቃሚ መሆን የሚያስችል መንገድ ያልተመቻቸበት ነው፡፡ ስለዚህ ሀገራችን እንደ ቻይናና አሜሪካ ያሉት ሀገራት የደረሱበት የዕድገት ደረጃ ለማድረስ ዜጎች ‘’እኔ ለሀገሬ’’ ብለው ግብራቸውን እንዲገብሩ ማስገንዘብ እና ብሔራዊ ስሜት እንዲሰማቸው ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ “የቄሳርን ለቄሳር” እንደሚባለው በእምነት ተቋማት፣ በትምህርት ቤቶች፣ በመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችና ከግብር ሰብሳቢዎች የኮሚኒኬሽን አባላት ኅብረተሰቡ ለመንግሥት ተገቢውን ግብር በመክፈል የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣ የማስገንዘብ ድርሻችንን መወጣት አለብን ፡፡
ሀገራችን ፈጣን እድገት እንድታስመዘግብ ከተፈለገ አንዱና ዋነኛው መሣሪያ ለመንግስት ተገቢውን ግብር መገበር በመሆኑ ዜጎች ይሉኝታ ቢስነትና ስግብግብነትን አስወግደው ተገቢውን ግብር በአግባቡ መክፈላቸው ተገቢ ነው፡፡
የመንግሥትም ሆነ የሌሎች ተቋማት ተቀጣሪ ሠራተኞች በዚህ ረገድ የግብር ሥርዓታቸው የጠራና ግልፅ ነው፡፡ ነጋዴዎች በቅርቡ በሀገራችን እየታየ ያለውን ለውጥ ከግምት አስገብተው ለሀገራቸው ተገቢውን ግብር በማስገባት ለህዝብና ለመንግሥት ድጋፋቸውን በተግባር መግለፅ አለባቸው፡፡ የዜግነት ግዴታቸውን መወጣት እየሠሩና የተሻለ ኑሮ እየኖሩ ግብር የማይገብሩት ዜጎች ለሚመለከተው አካል ማጋለጥ ሁላችንም እንደ ኢትዮያጵዊ ይጠበቅብናል፡፡ ለአቅመ ግብር የደረስንና በሥራ ላይ የተሠማራን ዜጎች ተገቢውን ግብር ከከፈልን መንግሥት ለሕዝቡ ኃላፈነቱን ለመወጣት፣ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጠና፣ በአፍሪካም ሆነ በዓለም ተደማጭነቱ ይጎለብታል፡፡
“ድር ቢያብር አንበሣ ያስር” እንደሚባለው ከድህነት መውጣት የምንችለው ሁላችንም ለሀገራችን የየድርሻችንን አስተዋፅዖ ስናበረክት መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ሥራ እየሠሩ ሀብት እያፈሩ የግብር ግዴታን አለመወጣት ሕግን መተላለፍ ወይም የተሰመረውን ቀይ መስመር ማለፍ መሆኑን መገንዘብ ያሻል፡፡
የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንም ባለሙያዎችና ሌሎች አካላት ግብር በማስገበር በኩል ከአንገታቸው ሳይሆን ከአንጀታቸው ለመሰብሰብ መጣር ዘመናዊነትንና ፍትሐዊነትን ማጥለቅ ከ “እከክልኝ ልከክልህ” ጥቅም ፍለጋ መላቀቅ ሠፊና አስከፊ መሞዳሞድን /ጉቦኝነትን/ ማውለቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታ በተጨማሪ ዕሴት ታክስ /ቫት/ የሚነግዱ አያሌ ነጋዴዎች አሉ፡፡ ነገር ግን ቸልተኛዎቹ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ሠራተኞች በተጨማሪ ዕሴት ታክስ የሚነግዱ ነጋዴዎች ሲያጭበርብሩ ማለትም ንብረታቸውን ሸጠው ወይም አገልግሎት ሰጥተው ከሸማቹ ትኬት ሳይቆረጡ ወደ መንግሥት ካዝና የሚገባውን ገቢ ለራሳቸው ሲያስቀሩ ሃይ ሊል የሚችል አልተገኘም፡፡ ይህም የአደባባይ ሚስጢር መሆኑ ግልጽ ነው፡፡
ተገልጋዮች ምግብ ተመግበው የተዕታ ወይም ቫት ደረሰኝ ሳይሰጣቸው ቢቀር ሳይከፍሉ መሄድ አለባቸው፡፡ ይህ ከሆነ ኅብረተሰቡ በአግባቡ ግብር የሚገብርበት ሥርዓት ይመቻቻል፡፡ በቅርቡ ተመራቂ የሆኑ የሀገራችን ዩኒቨርሲቲዎች ወጣቶች ይህም አንድ የአገልግሎት ዘርፍ መሆኑን ከግምት ገብቶ ለንግዱ ኅብረተሰብ በነፃ አገልግሎት እና ግንዛቤ ሊሰጡ የሚችሉበት መንገድ ቢመቻች በአጠቃላይ መንግሥትና ሕዝብ አትራፊ ይሆናሉ፡፡ የሚያጭበርብሩትን እንኳን ትተን በአግባቡ በተጨማሪ ዕሴት ታክስ የሚሰሩ ነጋዴዎችን ብናበረታታ እና በየዓመቱ መጨረሻ እንደ ምስክር ወረቀት የመሳሰሉ ሽልማቶችን በዕውቅና መልክ ብንሰጥ በማጭበርበርና በዝርፊያ ውስጥ ያሉ ነጋዴዎችን ወደ ትክክለኛው ጎዳና ልንወስዳቸው እንችላለን፡፡
ሸማቾችም ለሚገዙት ዕቃ ወይም ለሚጠቀሙት አገልግሎት የቫት ደረሰኝ ቢጠይቁ ለመንግሥት ድጋፍ በመስጠት ሕገ-ወጥነትን በመከላከል ትልቅ አስተዋፅዖ ያበረክታሉ፡፡ ስለዚህ ችግሩ ያለው ሸማቾችም ላይ ከመሆኑ አንጻር የግንዛቤ መስጫ ሥራ ለዜጎች ቢሰራ ሕዝብና መንግሥት አትራፊ ይሆናሉ፡፡ መንገድ፣ ሆስፒታል፣ ት/ቤት የመሳሰሉት ይገንባልን ብለን ስንጠይቅ እኛስ ግብር በአግባቡ በመክፈል የዜግነት ግዴታችንን ተወጥተናል ወይ ማለት ይኖርብናል፡፡
ኢህአዴግ በቅርቡ ያደረገው ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግርም ሆነ አዲሱ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ያመጧቸው ለውጦች በመደገፍ የአዲስ አበባ መስቀል አደባባይን ጨምሮ በሀገራችን የተለያዩ ከተሞች እንዲሁም በአሜሪካንም ሆነ በተለያዩ የአረብ ሀገራት በአፍቃሪ ኢትዮጵያውያን የተካሄዱት የድጋፍ ሰልፎች ህዝቡን በግባቡ ከያዝነው ከእኛ ጋር መሆኑን እና ለሀገሪቱ ድጋፉን ለማበርከት ዝግጁ መሆኑን አመላካች ነው፡፡ በውጪ ሀገር የሚኖሩትንም ዜጎች ለሀገራቸው አስተዋፅዖ እንዲያበረክቱ የዜግነት ግዴታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የውጪ ምንዛሪ በጥቁር ገበያ ሳይሆን በባንክ እንዲልኩ ለማድረግ የሚያስችል ምቹ አጋጣሚ ነው፡፡
ከላይ እንደተጠቀሰው የሰለጠኑት ሀገሮች አሁን ላሉበት ደረጃ የደረሱት ዜጎች ግብርን አስመልክቶ ለሀገራቸውና ለመንግሥታቸው ሀገሬን ቤቴን ብለው የግብር ግዴታቸውን በአግባቡ መወጣታቸው ነው፡፡ ይህም ሀገራቸውን ለማሳደግና ተሰሚና ተፅዕኖ ፈጣሪ ለመሆን አስችሏቸዋል፡፡ በሀገራችን የታየው ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ላለፉት ሦስት ዓመታት ተፈጥረው የነበሩ ቀውሶችን አስወግዷል፡፡ ከዚህም አልፎ በምሥራቅ አፍሪካ በኢትዮ ኤርትራ እንዲሁም በዶክተር ዐቢይ ጥረት በደቡብ ሱዳን የነበረውን ጦርነትና የሥልጣን ሽኩቻ እንዲጠፋ በአጠቃላይ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጠና ላይ የሠላም ደመና እንዲያዣብብ ያስቻለ ነው፡፡