Artcles

ግብርናውም ተደምሯል

By Admin

July 17, 2018

ግብርናውም ተደምሯል

ስሜነህ

 

በኬንያና በሌሎች አገሮች ውስጥ እስከ 30 በመቶ የበቆሎ ሰብል ማውደሙ የሚነገርለት ተምች፣ ዓምና በኢትዮጵያ ያደረሰው ውድመት አምስት በመቶ ገደማ እንደሆነም ከግብርና ሚንስቴር ሰሞኑን የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህ የሆነው በአይሲቲና ሌሎችም የቴክኖሎጂ ዕገዛዎች መረጃዎች ለገበሬው በስፋት ቀድመው እንዲደርሱና ጥንቃቄ ማድረግ በመቻሉ መሆኑም በመረጃው ተመልክቷል፡፡

 

በአሁኑ ወቅት በናይጄሪያ ‹‹ሳውዝ አርሚዋርም›› የሚል መጠሪያ የተሰጠው ተምች ከበቆሎ ባሻገር ሁሉንም ዓይነት ሰብሎች እያጠፋ እንደሚገኝ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን የጠቀሱት የግብርና ሚንስቴር ሚንስትር ዴኤታ ዶክተር ኢያሱ፣ ተምቹ በወረርሽኝ መልክ ወደ ኢትዮጵያ ሊመጣ የሚችልበት ዕድል ሰፊ በመሆኑ ከወዲሁ ተዘጋጅቶ ለመጠበቅ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን በቴክኖሎጂ በመታገዝ ማካሄድ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

 

አዲሱ የግብርና ኤክስቴንሽን ስትራቴጂ ለገበያ መርና ለወጪ ንግድ ትኩረት የሰጠ መሆኑ በተደጋጋሚ ተገልጿል። የአምራቹ ገቢ በከፍተኛ ደረጃ ለመጨመር ገበያው ላይ በጥራት እና በዓይነት ተመራጭ የሆኑ ውጤቶች መፈለጋቸው አይቀሬ ነው። አስፈላጊውን ምርት በማቅረቡ የአምራቹ ገቢ ሲጨምር ደግሞ እያንዳንዱ አምራች ለቀጣይ የምርት ዕድገት የሚያስፈልጉትን ግብዓቶችና የፍጆታ እቃዎችን በብዛት የመግዛት አቅሙ ይጠናከራል።

 

የፍጆታ እቃዎቹ ደግሞ የሚዘጋጁት በፋብሪካዎች እና በአነስተኛ አምራቾች በመሆኑ ኢንዱስትሪዎቹ ሰፊ ገበያ ይፈጠርላቸዋል። የግብርና ምርት ሲጨምር ደግሞ የወጪ ንግድም አደገ ማለት ነው። በዚህም ከአርሶ አደሩ ጀምሮ እስከ ተቋማቱ ድረስ የካፒታል ክምችት እንዲያድግ ዕድል ይፈጥራል። ጉዳዩ ተያያዥ እና እያንዳንዱን ዜጋ የሚደምር ሥራ ነው።

 

በዚህ ሂደት ውስጥ ባለፉት ዓመታት የተለያዩ ስትራቴጂዎች እና የተግባር አፈጻጸሞች መከናወናቸው በመረጃዎቹ ተመልክቷል ። በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እየተተገበሩ ለሚገኙ ስትራቴጂዎች ሁሉ እምብርት ነው የሚባለው የግብርና መር ኢንዱስትሪ ልማት ነው። በተለይ በግብርና ኤክስቴንሽን ሥራዎች አርሶ አደሩ ዘመናዊ አመራረት በመከተል ምርት እንዲያድግ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑ መገንዘብ ይቻላል።ግን ደግሞ ግብርናው ከቴክኖሎጂ ጋር የተደመረበት መንገድ ይበል የሚያሰኝ እና መድረሻችንንም ከወዲሁ የሚያመላክት ነው።

 

ሶፊያ የተሰኘችው ሰው መሰሏ ሮቦት በኢትዮጵያውያን የተጎበኘችበት የዘንድሮው የአይሲቲ ዓውደ ርዕይ ካስተናገዳቸው በርካታ ኩነቶች መካከል አንዱ የግብርናው እና የቴክኖሎጂው ዘርፍ መደመራቸውን  የተመለከተው መድረክ ይጠቀሳል፡፡ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ከግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ላለፉት አራት ዓመታት ሲተገብረው በቆየው የሞባይል አጭር መልክዕት አገልግሎት አማካይነት ሲሰጥ ስለቆየው አገልግሎት በመድረኩ ታይቷል ፡፡

 

ማክሰኞ፣ ሰኔ 26 ቀን 2010 ዓ.ም. በተካሄደውና “አይሲቲ  ለግብርና ልማት” በተሰኘው ሥነ ሥርዓት ወቅት እንደተጠቀሰው፣ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ከኢትዮ ቴሌኮም በተሰጠው የኔትወርክ አገልግሎት አማካይነት ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ ከ30 ሚሊዮን በላይ የአርሷደር ጥሪዎችን በ8028 ነፃ የስልክ መስመር በኩል ያስተናገደ ሲሆን፤ ከ3.6 ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎችን ደምሯል።  

 

የአርሶአደሩን የዕለት ተዕለት ጥያቄዎች ከማዕከል እየተቀበሉ የሚያስተናግዱ፣ የግብርና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን በማሳተፍ በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች አገልግሎቱ ሲሰጥ መቆየቱን የጠቀሱት መረጃዎች፤ የማዳበሪያ አጠቃቀምን፣ የምርጥ ዘር፣ የፀረ ተባይና ፀረ አረም አጠቃቀምና መሰል ጥያቄዎች ያሏቸው በርካታ አርሶአደሮች በሚልኩት የድምፅና የጽሑፍ ጥያቄ መሠረት ማብራሪያና ምክር ሲሰጥ መቆየቱም ተጠቅሷል፡፡

 

ኤጀንሲው በአራቱ ክልሎች ለሚገኙ የግብርና አምራቾች አገልግሎት በሙከራ ደረጃ ባስጀመረበት ወቅት፣ ከድንች፣ ሽንኩርትና ካሮት አምራቾች ዘንድ በቀን 500 ጥሪዎችን በመደመር እንደጀመረ አስታውሶ፣ ይህ የጥሪ ብዛት ቀስ በቀስ ወደ 57,400 ጥሪ በማደጉ የሙከራውን ሥራ ወደ ሙሉ ትግበራ ለማስገባት የሚያስችል ውጤት ማግኘቱን አትቷል፡፡

 

የጥሪ ማዕከሉ የሚያስተናግደው የአርሶ አደሮችን ጥያቄዎች ብቻም ሳይሆን የግብርና ልማት ወኪሎችን፣ የባለሙያዎችና የሌሎችንም ጥሪዎች ሲሆን፣ የግብርና ባለሙያዎችና የኤክስቴንሽን ሠራተኞች ዕውቀታቸውን ይበልጥ ለማስፋት የሚረዷቸው ማብራሪያዎችን ከጥሪ ማዕከሉ ስለሚያገኙ በየጊዜው ተጠቃሚ ከሆኑት ውስጥ እንደሚገኙበት ተጠቅሷል፡፡

 

በአገሪቱ ግብርና ውስጥ የኢንፎርሜሽንና የኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ አገልግሎት ወሳኝ ሆኗል፡፡በየወቅቱ የሚከሰቱ የሰብል በሽታዎችን ቀድሞ ለመከላከል፣ ወረርሽኞች ሲከሰቱም የመስፋፋት አቅማቸውን ለማካደም ግብርናው ከአይሲቲ መደመር አለበት። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የወረርሽኝ አደጋ እየጋረጠ የመጣውን የ‹‹መጤ ተምች›› ወይም አሜሪካን ፎል አርሚዋርም እየተባለ የሚጠራውን ነፍሳት በዚህ አጋጣሚ ልብ ይሏል።

 

በርካታ አገሮች የሚጠቀሙት ዘር የሚፈልጋቸውን ግብዓቶች፣ የውኃ አጠቃቀም፣ የማዳበሪያ፣ የኬሚካልና መሰል ይዘቶች ቀድሞ በማስላት ምን ያህል ምርት በምን ያህል ቦታ ሊገኝ እንደሚችል ሁሉ ቀድመው የሚተነብዩበት የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ ደርሰዋል፡፡

 

በአንፃሩ የኢትዮጵያ ግብርና አነስተኛ ሜካናይዜሽን ለመተግበር ጅምር ላይ ሲሆን፣  የግብናው እና የአይሲቲ መደመር የሚያቀርባቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶችና አጠቃቀማቸው ልክ እንደበለጸጉት ሁሉ በአየር ትንበያ፤ ወይም በዝናብ መጠንና ሥርጭት፣ አልያም በማዳበሪያ አጠቃቀምና መሰል ይዘቶች ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ያስችላል። የመጀመሪያ ደረጃ መረጃዎችን ከማሠራጨት ባሻገር በመስኖ ሥራዎች፣ በድኅረ ምርት፣ በገበያና በሌሎችም የእሴት ሰንሰለቶች ውስጥም ሚናው የጎላ ይሆናል።  

 

ወረዳኔት በተሰኘው የቴሌኮም የአገልግሎት መረብ አማካይነት ግብርና ዘርፍ በርካታ አካባቢዎችን ተጠቃሚ እንዳደረገ ይታወቃል፡፡  ከዚህ ቀደም በወረቀት ሰነድ በሚደረግ የግብይት ሥርዓት ላይ የተመሠረተው የቫውቸር አገልግሎት በርካታ የሙስናና የማጭበርበር ችግሮች የነበሩበት አገልግሎት ለአርሶአደሮች ሲቀርብ መቆየቱን ተጠቅሶ፣ በአሁኑ ወቅት ግን አምስት ሚሊዮን ገደማ አምራቾች ያለምንም የገንዘብ ንክኪ በስልካቸው አማካይነት የ7.6 ቢሊዮን ብር ግምት ያለው የሰባት ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ግዥ መፈጸም የቻሉበት የቴክኖሎጂ ሥርዓት መተግበሩንም የተመለከቱ መረጃዎች ወጥተዋል፡፡

 

የኤሌክሮኒክስ ቫውቸር (ኢቫውቸር) ሥርዓት አርሶአደሮችን ከአነስተኛ ፋይናንስ አቅራቢ ድርጅቶች ጋር በመደመር፣ አርሶአደሮቹ የሚፈልጉትን የማዳሪያ ወይም የምርጥ ዘር መጠን ግዥ ሲፈጽሙ፣ ከማዕከል በሚደረግ ግንኙነት የፋይናንስ ግብይቱ በኤሌክትሮኒክ ዘዴ የሚካሄድበት ሥርዓት ነው፡፡ አርሶአደሩ በብድር ጭምር ተጠቃሚ የሚሆንበት ይህ ሥርዓት፣ በአሁኑ ወቅት በአራቱም ክልሎች እየተስፋፋ ስለመምጣቱ የግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡