CURRENT

“…ጣጣቸው ብዙ ነው”

By Admin

July 17, 2018

“…ጣጣቸው ብዙ ነው”

                                                             ሶሪ ገመዳ

መንግስት ለ2011 ዓ.ም የያዘው በጀት ከአጠቃላይ የአገሪቱ ከበጀተችው ውስጥ 64 በመቶው  ለድህነት ቅነሳ ተኮር የልማት ስራዎች የተያዘ ነው። በጀቱ ድሃ ተኮር መሆኑ መንግስት ምን ያህል ድሃውን ህብረተሰብ ለመጥቀም መፈለጉን የሚያመላክት ይመስለኛል። ታዲያ ይህ በጀት ከየትም የሚመጣ ሳይሆን ህብረተሰቡ ከሚከፍለው ግብር የሚሰበሰብ ነው።

ስለሆነም ድሃ ተኮሩ በጀት ለታሰበለት ዓላማ እንዲውል በበጀት ዓመቱ ህብረተሰቡ የሚጠበቅበትን ዓመታዊ ግብር በወቅቱና በታማኝነቱ መክፈል ይኖርበታል። መንግስት ለህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት መስጠት የሚችለው ዜጎች ግብርን በወቅቱና በታማኝነት መክፈል ሲችሉ ብቻ ነው።

እናም “ግብርና እና ሞት ሲዘገዩ ጣጣቸው ብዙ ነው” እንደሚባለው፤ ዜጎች የሚጠበቅባቸውን ግብር በወቅቱና በታማኝነት በመክፈል አገራችን የጀመረችውን የለውጥ ሂደት ስኬታማ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

ግብር የሚከፈለው ድህነትን ለመቀነስ ነው። ግብር ከፋዩ የህብረተሰብ ክፍል የሚከፍለው ግብር የውዴታው ግዴታ መሆኑን ማወቅ ይኖርበታል። ግብር ሳይከፍል የሚኖር ህዝብ የትም አገር የለም። ግብር መክፈል አገርን ለማጠንከርና የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ከዳር ለማድረስ የሚያግዝ ነው።

በተለይም አገራችን ለሁለተኛ ጊዜ በነደፈችው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ የተወጠኑና ስራቸው የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ለማስከናወን ግብር ከዜጎቿ መሰብሰብ ግዴታዋ ነው።

ይህ ካልሆነ ፕሮጀክቶቹን በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ እውን ማድረግ አይቻልም። ፈጣንና ተከታታይ ዕድገትን ማምጣትም የሚታሰብ አይሆንም። በእነዚህ ፕሮጀክቶች ተጠቃሚዎቹ ዜጎች ናቸው። ዜጎች ግብር በመክፈላቸው የድህነት መጠንን ለማገዝ ያስችላል።

ህዝቡ በአገሩ ውስጥ በሚከናወን እድገት ቀጥተኛ ተጠቃሚ እንዲሆን በቅድሚያ ጠንካራ መንግስት ሊኖረው የግድ ይላል። ጠንካራና ለሀዝቡ የሚሰራ መንግስት እንዲኖር ደግሞ ዜጎች ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ግብራቸውን መክፈል ይኖርባቸዋል። ጉዳዩ የራስ ተጠቃሚነት በመሆኑም ግብርን በአገራዊ ፍቅር መክፈል የማንኛውም ዜጋ በውዴታ ላይ የተመሰረተ ግዴታ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም።

እንደሚታወቀው ሁሉ ኢትዮጵያ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ የልማት ፕሮጀክቶችን ለመገንባት አቅዳለች። አገራችን በምታራምደው የፊሲካል ፖሊሲ መሰረት በ2012 ዓ.ም ፍፃሜውን የሚያገኘው የሁለተኛው የዕድገት እቅድ የወጪ በጀትን በሂደት በዋናነት በሀገር ውስጥ ገቢ በመሸፈንና የበጀት ጉድለት ዝቅተኛ እንዲሆን በማድረግ ለዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት ምቹ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ ለማስፈን ያለመ መሆኑ ተመልክቷል።

በመሆኑም ባለፉት ዓመታት የታክስ ፖሊሲዎቹን በተሻለ ሁኔታ በማስተዳደር የመንግስት ገቢ ከፍተኛ ዕድገት እንዲያሳይ ተደርጓል። ሆኖም የታክስ ገቢው እያደገ ከመጣው የመንግስት የወጪ ፍላጎት አንፃር ብዙ የሚቀረው ሆኖ ተገኝቷል።

እንዲሁም የታክስ ገቢው ዕድገት እየሳየ ቢመጣም፣ ምጣኔ ሃብቱ ሊያመነጭ ከሚችለው ጋር ሲነጻጸር የሚጠበቀውን ያህል መሻሻል አሳይቷል ተብሎ የሚገመት አይደለም። እናም ማሻሻሉ ጎልብቶ የህዝቡ ተጠቃሚነት እንዲደረጅ ግብር መክፈል ወሳኝ ተግባር መሆን ይገባዋል።  

እንደሚታወቀው ሁሉ ባለፉት ዓመታት የታክስ ገቢው ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ ብዙም ለውጥ ማሳየት አልቻለም። እናም በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን የታክስ ገቢው ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ ወደ 17 በመቶ ለማሳደግ ታቅዷል። በተለይም ቀደም ባሉት ዓመታት ውስጥ በምንም ዓይነት የተክስ ስሌት ውስጥ ያልነበሩ ነጋዴዎችን ወደ ታክስ ስርዓቱ ማስገባት ይገባል።

የታክስ አስተዳደር መረጃ ሥርዓቱን ይበልጥ ማጠናከርና አሟጦ ጥቅም ላይ ማዋል፣ የታክስ ከፋዮችና የህብረተሰቡ በአጠቃላይ የታክስ ትምህርትና ግንኙነትን ማሳደግ፣ የታክስ ህግን ማስከበር እና የታክስና ገቢዎች መዋቅር ተቋማዊ አቅም ማሳደግ አሁንም ተገቢ ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተከናወኑ ነው።

በያዝነው የዕቅድ ዘመን የታክስ ስርዓቱን በጥብቅ ዲስፕሊን ተፈፃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው። በተጨማሪም የመንግስት ፋይናንስ አጠቃቀሙ ውጤታማነትን ለማሳደግ፣ የተሟላ ግልፅነትና ተጠያቂነት ለማስፈን፣ ብክነትን ለማስወገድና በጀቱን በቁጠባ ለመጠቀም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ስራው እየተከናወነ ነው።

ይህም ከህዝቡ በታክስ መልክ የሚሰበሰበው ግብር እንዳይባክንና ለታሰበለት ዓላማ እንዲውል በጥብቅ የሚሰራበት ይሆናል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶከተር አብይ አህመድ ለፓርላማ በቅርቡ ስለ ተያዘው በጀት በቁጠባና ለታለመለት ዓላማ እንዲውል አስፈፃሚው አካል በዲሲፕሊን ሊጠቀም እንደሚገባ ያሳሰቡትም ለዚሁ ነው።

በመንግስት የሚከናወኑት ማናቸውም ስራዎች በዋነኛነት ህዝቡ በሚከፍለው ግብር ላይ የተመሰረቱ መሆናቸውን ነው። እርግጥ ዜጎች ግብር ካልከፈሉ ምንም ዓይነት የልማት ስራዎችን ማከናወን አይቻልም። ከላይ እንደጠቀስኩት ግብር ካልተከፈለ መንግስት በእርዳታና ብድር ብቻ ለመኖር ይገደዳል።

ይህ ደግሞ መላው ስራው ብድርና እርዳታ ለሰጡት አካላት አስፈፃሚ እንዲሆን ያደርገዋል። ዜጎችም በአገራቸው መጠቀም አይችሉም። እናም ግብር መክፈል አገልግሎትን በጥራት ከመንግስት ለማግኘትና እንደ ግብር ከፋይ በከፈልኩት ግብር አልተጠቀምኩም ብሎ ለመጠየቅም የሚያስችል ነው።

መንግስት የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች በጥራት ለማግኘትና ጥራት ሳይኖራቸው ከቀረቡም ቅሬታ አቅርቦ እንዲስተካካል ለማድረግ ግብር መክፈል ያስፈልጋል። ስለሆነም መንግስት ከዜጎቹ ተገቢውን ግብር መሰብሰብ ከቻለ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች በዚያው ልክ ጥራታቸው፣ ፍትሐዊነታቸው፣ ዴሞክራሲያዊነታቸውና ሁሉን አቀፍነታቸው ያድጋል።

ይህም የህዝቡን የእርካታ ስሜት በዚያው ልክ እየጨመረ እንዲሄድ ያደርገዋል። ግብር መክፈል ከተጠቃሚነት ባሻገር፣ የህብረተሰቡን ክብርና ኩራትን የሚጨምር መሆኑን እንድንገነዘብ ያደርገናል። ስለሆነም የአገራችን ህዝብ “ሞትና ግብር ሲዘገዩ ጣጣቸው ብዙ ነው” እንደሚለው፣ ግብርን በወቅቱና በጊዜ መክፈል የራስን ጥቅም ማደርጀት ስለሆነ ሃፊነታችንን በአገር ስሜት ልንወጣ ይገባል።