Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ጥላቻና ግጭት ድምር ያፈርሳል

0 994

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ጥላቻና ግጭት ድምር ያፈርሳል

አባ-ዲዱ ቢሊሳ

በኢትዮጵያ መጪው ጊዜ ሰላማዊ እንደሚሆን፣ የፖለቲካ ምህዳሩም ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ ሰፍቶ ዴሞክራሲ በጉልህ የሚጎለብትበት እንደሚሆን ሁኔታዎች ያመለክታሉ። ተስፋ ይታያል። በሌላ በኩል ደግሞ በአንዳንድ የሃገሪቱ አካባቢዎች አስከፊ ግጭቶች እያጋጠሙ ነው። ህግን መሰረት ያላደረጉ እርምጃዎች የሚወሰዱበት ሁኔታም እየተለመደ መጥቷል። በኦሮሚያ በደቡብ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ያጋጠመው ለበርካቶች ሞት፣ ከ 7 መቶ ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች መፈናቀል ምክንያት የሆነውን ግጭት ልብ ይሏል። ባለፈው ዓመት መሸኛና በያዝነው ዓመት መግቢያ ላይ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሱማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች በተነሳ ግጭት ተመሳሳይ የህይወት መጥፋትና መፈናቀል አጋጥሞ እንደነበረ ይታወሳል። በቅርቡ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢ ያጋጠመው ግጭት የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሱማሌ ግጭት ያስከተለው መፈናቀልና ሌሎች ተጽእኖዎች ባልተቃለሉበት ሁኔታ ያገጠመ ነው።

በዚሁ ሰሞን በምእራብ ኦሮሚያ በተለይ በምስራቅና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች ከተሞች ግጭቶች አጋጥመዋል። በኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልሎች አዋሳኝ በሆኑት ጭናክሰንና ሚኤሶ አካባቢዎች ባጋጠመ ግጭት የንጹሃን ህይወት ጠፍቷል። የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወረቂ በኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት ለመዘገብ ከድሬ ዳዋ ተነስተው ወደአዲስ አበባ በመጓዝ ላይ የነበሩ የድሬ ቴሌቪዥን ጋዜጠኞችና አሽከርካሪያቸው ላይ ድብደባ ተፈጽሟል፤ ሚኤሶ ከተማ ላይ። በዚህ ድብደባ ከባድ ጉዳት የደረሰበት አሽከርካሪ በድሬ ዳዋ ድል ጮራ ሆስፒታል ሲረዳ ቆይቶ ህይወቱ ማለፉን ሰምተናል። በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ማኦ ኮሞ ባጋጠመ የእርስበርስ ግጭት በሰዎች ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል። በደቡብ ሲዳማና ወላይታ እንዲሁም ጉራጌ ዞኖችም ሰዎች የሞቱባቸው፣ ንብረት የወደመባቸው ግጭቶች አጋጥመዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ከቀናት በፊት በአማራ ክልል ደብረማርቆስ ከተማ፣ ክልሉን የሚያስተዳድረው ብአዴን አንድ ከፍተኛ አመራርን እንፈልጋለን በሚል ሰበብ በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል። በዚሁ ክልል ሃዊ ዞን፣ ዚጋም ወረዳ፣ ቀላሽ ከተማ የመሰረተ ልማት መሟላት ጥያቄያችን ምላሽ አልተሰጠውም በሚል መነሻ ወደአካባቢው ህዝቡን ሊያወያዩ የሄዱ የዞን አመራሮችና የጸጥታ አካላት በወጣቶች ታግተዋል። ወጣቶቹ ያገቷቸውን አመራሮች በአደራ ለፖሊስ ሰጥተው ፖሊስ ሰዎቹን በመልቀቁ በተነሳ ግጭት በአራት ግለሰቦች ላይ የመቁሰል ጉዳት ደርሷል።

እነዚህ ከብዙ በጥቂቱ የተነሱ ግጭቶችና ህግን መሰረት ያላደረጉ እርምጃዎች አሁን በሃገሪቱ ገዢ እየሆነ ከመጣው የእርቅ፣ ይቅርታ፣ ፍቅርና መደመር ጽንሰ ሃሳብ ጋር አይጣጣሙም። እርቅ፣ ይቅርታ፣ ፍቅርና መደመር የፈጠሩት ብሩህ ተስፋ፣ የስጋት ጨለማ መንታ እንዲያበቅል አድርገዋል። አሁን መንታ መንገድ ላይ ነን።  የሰው ህይወት የሚቀጥፉት፣ ንብረት የሚያወድሙትና በአጠቃላይ ስጋት የሚፈጥሩ ግጭቶችና የህግ የበላይነት ጥሰቶች የህዝቡን ተስፋ አደብዝዘውታል። አሁን ወደሃላፊነት የመጣው የተሃድሶው አመራር በወሰዳቸው የይቅርታ፣ የፍቅርና የመደመር እርምጃዎች የተፈጠረው ተስፋ ነው የደበዘዘው። ተስፋው የጨለመ ህዝብ ደግሞ የለውጡ አካል የመሆን አቅም ያንሰዋል።

ግጭቶች በሶስት ወራት ውስጥ በተወሰዱ እርምጃዎች ተስፋ የፈጠረው መንግስትና አመራሩ፣ እርምጃዎቹን ቀጥሎ ለህዝቡ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ የመስጠት ትኩረቱ እንዲበተን ያደርጋሉ። መንግስት ዘላቂ ስራዎች ከመስራት ይልቅ እዚያም፤ እዚህም የሚያጋጥሙ ግጭቶችን በመፍታት፣ መፈናቀልና የንብረት ማጣት የመሳሰሉ አሉታዊ ተጽእኖዎችን በማቃለል ድንገተኛ ስራዎች ስሊጠመድ ዘላቂ ተግባራቱ ተወዝተው ይቀራሉ ወይም ይንቀራፈፋሉ። የዘላቂ ተግባራቱ መወዘትና መንቀራፈፍ ተመልሶ የህዝብ ቅሬታ የፈጥራል፤ ቅሬታው  ለከረረ ተቃውሞና ግጭት ምክንያት ይሆናል። ይህ ሃገሪቱን የግጭትና ትርምስ አዙሪት ውስጥ ይከታታል። ተስፋ የፈጠረውጥ የለውጥ እርምጃም ይደናቅፋል።

የኢፌዴሪ መንግስት የሃገሪቱን የፖለቲካ ምህዳር ለማስፋትና ሃገራዊ መግባባት ለመፍጠር ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ ወንጀል ተከሰው የተፈረደባቸውን በብዙ ሺህ ለሚቆጠሩ ዜጎች ይቅርታ አድርጓል። በውጭ ሃገራት በትጥቅ ትግል ላይ ለነበሩ ቡድኖች ምህረት ለመስጠት እንዲያመች የምህረት አዋጅ ጸድቋል። ከምህረት ውጭ ወደሃገር ውስጥ ገብተው መንቀሳቀስ ለሚችሉ ቡድኖችና ግለሰቦች በተላለፈ ጥሪ መሰረት ወደሃገር ውስጥ ገብተው ሰላማዊ የፖለቲካ ተሳትፎ ለማካሄድ ማኮብኮብ የጀመሩ የፖለቲካ ድርጅቶች አሉ። ከዚህ ቀደም በጸረሽብርተኝነት አዋጁ መሰረት በአሸባሪነት ተፈርጀው የነበሩት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)፣ የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) እና ግንቦት 7 የተሰኙ ድርጅቶች የአሸባሪነት ፍረጃው እንዲነሳላቸው ተደርጓል።  ይህ በሃገሪቱ የተጀመረው የይቅርታ፣ ፍቅርና መደመር መገለጫ ነው።

ይቅርታ፣ ፍቅርና መደመር በአንድ ወገን ብቻ የሚከወኑ አይደሉም። በተለያየ ምክንያት በጥርጣሬ ይተያዩ የነበሩ ሁሉም ወገኖች አንዱ ሌላውን ይቅር ሊሉ፣ ሊያፈቅሩ፣ አንዱ ከሌላው/ከሌሎች ጋር ሊደመሩ የግድ ነው። የአንድ ወገን ይቅርታ እርቅ አያወርም። አንድ አይደመርም። የተወሰኑ ወገኖችን ብቻ ነጥሎ የሚሰጠ ይቅርታ ምሉዕ ሃገራዊ እርቅ አያወርድም። ድምሩም ጎዶሎ ይሆናል። መንግስት ይቅርታና ምህረት በማድረግ ፍቅሩን እንዳሳየው ሁሉ ህዝብ እርስ በርሱ፣ ቡድኖች እርስ በርሳቸው፣ ህዝብ ለመንግስት ይቅርታ እንዲደራረጉና እንዲደመሩ ይጠበቃል።

መንግስትና ኢህአዴግ ባለፉ አመታት የተፈጸሙ ስህተቶችን አምነው ህዝቡን ይቅርታ ጠይቀዋል። ይህ ኢህአዴግና መንግስት የፈጸሙትና ይቅርታ የጠየቁበት ስህተት በአንድ፣ በሁለት ወይም በጥቂቶች አመራር ላይ በነበሩ ሰዎች እንድተፈጸመ ሳይሆን እንደተቋም ጥፋት ታይቶ ነው ይቅርታ የተጠየቀው። በመሆኑም ይቅርታው በተለያየ ደረጃ በድርጅቱ ውስጥና በመግስት ሃላፊነት ደረጃ ላይ የነበሩ ሁሉንም ሰዎች ይመለከታል። ህዝብ ለቀረበለት የይቅርታ ጥያቄ ምላሽ ሰጥቷል፤ ይቅርታ አድርጓል። ለኢህአዴግ የሰጠው የመጨረሻ እድል የዚህ ይቅርታ ውጤት ነው። በዶ/ር አብይ አህመድ የሚመራው የለውጥና የተሃድሶ አመራር ቡድንም የዚህ የህዝብ ይቅርታ ውጤት ነው። ህዝብ ለመንግስትና ኢህአዴግ ይቅርታ ባያደርግ ኖሮ፣ አሁን በሃገሪቱ የሚታየውን ተስፋ የፈጠረው የእነ ዶ/ር አብይ አመራር ወደሃላፊነት መድረክ ባልመጣ ነበር።

ይሁን እንጂ፣ በአማራ ክልል በደብረማርቆስ ከተማ የተፈጸመው አይነት ከይቅርታና ምህረት ያፈነገጠ ሁኔታ ታይቷል። በደብረማርቆስ ከተማ በአድማ ጥቃት ሊፈጸምባቸው የነበሩት የብአዴን ከፍተኛ አመራር ለአማራ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መብቶችና ነጻነቶች መከበር የወጣትነት እድሜያቸውን መስዋዕት አድርገው ታግለዋል። ከዚያም የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት የተረጋገጠበት ፌደራላዊ ስርአት እንዲቆም በተለያየ የሃላፊነት ደረጃ የአቅማቸውን ያህል ሰርተዋል። ይህ ገሃድ እውነት ነው። ለዚህ ገሃድ እውነት የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በሙሉ እውቅና ይሰጡታል። ይህ እውነት ሁሉንም ወገን ያስደስታል ማለት ግን አይደለም።

አመራሩ በኢትዮጵያ ብሄሮችና ብሄረሰቦች እውቅና የሚሰጠው በጎ ታሪካዊ ተግባር የተወጡ ቢሆኑም፣ የሚመሩት ድርጅት ኢህአዴግ በፈጸማቸው ስህተቶች ከመወቀስ አይድኑም። ድርጅቱ ይህን ስህተቱን አምኖ ለህዝብ ያቀረበው የይቅርታ ጥያቄ እርሳቸውንም ይመለከታል። ህዝብ የሰጠው ይቅርታም ለእርሳቸውም ይደርሳል። ይቅር ተባብለን በመደመር ሃገራችንን ለመገንባት በተነሳንበትና ተስፋ ባየንበት ወቅት፣ ይቅርታውን ሽሮ በአድማ የቀድሞ አመራሮችን እያሳደዱ እርምጃ ለመውሰድ መነሳት ያየነውን ተስፋ ከማለምለምና ለውጡን ከማሳካት ይልቅ ማጨለሙና ማደናቀፉ የሚያይል መሆኑን ማስተዋል ብልህነት ነው። ከቀድሞ አመራሮች መሃከል በህግ የሚያስጠይቅ ጥፋት የፈጸሙ ቢኖሩ እንኳን፣ ጉዳዩ ህግ በሚያዘው አኳሆን ብቻ ነው መያዝ ያለበት። የህግ የበላይነት ፈርሶ ሰዎች የጠሉት ላይ እርምጃ የሚወስዱ ከሆነ ስርአተ አልበኝነት ይሰፍናል። ስርአተ አልበኝነት ሃገር ያፈርሳል።

በዚሁ ሰሞን በዚሁ በአማራ ክልል፣ ሃዊ ዞን፣ ዚገም ወረዳ፣ ቀላሽ ከተማ የመሰረተ ልማት ጥያቄያችን ምላሽ ተነፍጎታል በሚል በአድማ በዞን አመራሮች ላይ የተወሰደው የእገታ እርምጃም በተመሳሳይ የህግ የበላይነት መርህን የሚጻረር ነው። በኦሮሚያ፣ ምዕራብ ሃረርጌ ዞን፣ ሚኤሶ ከተማም የድሬ ቴሌቪዥን ጋዜጠኞች ላይ ሰላይ ናቸሁ በሚል የተፈጸመው የአድማ ድብደባም እንዲሁ የህግ የበላይነትን የጣሰ ነው። አነዚህ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች የተፈጸሙ የህግ የበላይነትን የሚጻረሩ ድርጊቶች ከወዲሁ ካልተቀጩ በሃገሪቱ ስርአተ አልበኝነት መስፈኑ አይቀሬ ነው።

የአዊ ዞን አመራሮች ለመሰረተ ልማት ጥያቄ ምላሽ አልሰጥ ብለው፣ ጥያቄው ምላሽ እንዳያገኝ አደናቅፈው ከሆነ፣ ወይም ለመሰረተ ልማት ዝርጋታው የተመደበውን ሃብት መዝብረው ከሆነ ይህ በማስረጃ ተረጋግጦ በህግ ሊጠየቁ ይችላሉ። የስልጣናቸው ምንጭ መለኮት ሳይሆን ህዝብ በመሆኑ ከስልጣናቸው እንዲሰናበቱ ማድረግም ይቻላል።

ሚኤሶ ላይ ሰላይ ተብለው የተደበደቡ ጋዜጠኞችን በተመለከተም፣ ህዝብን ግጭት ውስጥ ለመክተት እየሰለሉ መሆኑን የሚያመለክቱ ማስረጃዎች ካሉ ለህግ አስከባሪ ሃይል ጥቆማ ከማድረግ አልፎ ተሰባስቦ በሆይ ሆታ የተወሰደው የጥቃት እርምጃ የህግ የበላይነትን የሚጻረር ብቻ ሳይሆን ጸያፍም ነው። ይህ አካሄድ በቀልን በመጠንሰስ በአካባቢው ግጭት ከመቀስቀስና ሃገሪቱን ወደትርምስ ከማስገባት ያለፈ የሚያስገኘው ፋይዳ የለም። ይህ የህግ የበላይነትን የሚጻረርና ጸያፍ አካሄድ አሁን የተያዘውን የፍቅር፣ ይቅርታና መደመር መርህ ይጻረራል። በይቅርታ፣ ፍቅርና መደመር ሊገኝ የታሰበውን ሃገራዊ ለውጥም ሊያደናቅፍ ይችላል።

በአጠቃላይ ፍቅር፣ ይቅርታና ምህረት በሁለትና ከዚያ በላይ በሆኑ ወገኖች መሃከል የሚደረግ በመሆኑ፣ በሁሉም ወገኖች ዘንድ ቂምና በቀልን የማስቀረት ጉልበት አለው። ፍቅርና ይቅርታ ጥላቻና ጸብን አይቀላቅልም። ኢትዮጵያውያን ይቅር የተባባልነውና በመሃከላችን ፍቅር ለማበልጸግ የተስማማነው፣ ተደምረን ችግሮቻችንን በመፍታት የተሻለ ህይወት መኖር የሚያስችል ሁኔታና አቅም ለመፍጠር ነው። እዚያም እዚህም የሚታዩት የጥላቻ ስሜቶች፣ የቂም ቋጠሮዎች፣ ግጭቶች ተደምረን ፍላጎታችንን ማሳካት የማንችል ደካሞች እንድንሆን እንደሚያደርጉን ልብ በሉ። ጥላቻና ቂም ድምር ያፈርሳል እንጂ አይደምርም።  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy