Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ጥላቻን እስከ መቼ ?

0 280

Get real time updates directly on you device, subscribe now.


ጥላቻን እስከ መቼ ?

                                       ኃይማኖት ከበደ

ስለ ሰላም ብዙዎች ብዙ አዚመዋል  ብዙዎችም ተቀኝተዋል ምክንያቱም ሰላም በዋጋ ሊገዛ የማይችል ልዩ የሆነ የሰው ልጆች ትልቅ በረከት ስለሆነ ነው።ይህ ሰላም ለሁሉም ህብረተሰብ እኩል የተሰጠ ልዩ ስጦታም ነው  ለዛ ነው ሁሉም በየ በኩሉ ስለ ሰላም የሚለውን የማያጣው። ዜጎች ሰላም በሰፈነባት ሀገር ቢኖሩ ሁሌም ውጤታማና ስኬታማ መሆን ይችላሉ።ዜጎች ውጤታማና ስኬታማ መሆን ከቻሉ ሀገርም በኢኮኖሚ፣በፖለቲካና በማህበራዊ መስኮች ሁሉ መልካም ውጤትን ማምጣት ትችላለች።

እንደሚታወቀው ሀገራችን ከጥቂት ጊዚያት በፊት ሰላሟ ተናግቶ  ነበር በዚያን ወቅት በሀገራችን መሆን የሌለባቸው ብዙ ነገሮች ሆነው አይተናል። ለአብነት ያህል ብዙ ዜጎች ከሚኖሩበት ሥፍራ ወደ ተለያዩ ቦታዎች ተፈናቅለውና ተሰደው እንዲሁም  ብዙዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።ይህ መቼም የማንረሳው የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው። ለዛም ነው ሰላም ለአንዲት ሀገርና ህዝቦቿ በጣም አስፈላጊና ወሳኝ የሚሆነው።ዜጎች በተሠማሩበት የሙያ መስኮች ትርፋማ በመሆንና ለሀገር ለወገን መድረስ የሚችሉትም ሰላም በምድራቸው  ሲሰፍን ብቻ ነው። በሀገራችን ይህ የደፈረሰው የሰላም ማዕበል መጥራትና ወደ ቀድሞ ቦታው መመለስ ከተጀመረ ሦስት ወራቶችን በማስቆጠር ወደ አራተኛው ወር በመጠጋት ላይ እንገኛለን። ይህ ሰላም እንዲመጣ ሁሉም ዜጎች ከመንግሥት ጎን በመሆን የበኩላቸውን በመወጣትና ችግር ፈጣሪውን አካል በማጋለጥ የተጀመረውን ለውጥ ማስቀጠል ይኖርብናል። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡበት ዕለት አንስቶ በሀገራችን የፍቅር፣የየቅርታና የሰላም ንፋስ  እየነፈሰ ይገኛል።

ሀገራችንም በአሁኑ ሰዐት በከፍተኛ የለውጥ እንቅስቃሴዎችን እያካሄደች ትገኛለች።ይሁን እንጂ በሀገራች እያየን ያለነው ሰላምና የለውጥ ሂደቶች ያላስደሰታቸው አንዳንድ አካላት ይህንን አጣጥመን ያልጨረስነውን ሰላም ሊነጥቁን ደፋ ቀና ሲሉ እያስተዋልን እንገኛለን እነዚህ አካላት አሁን በሀገራችን ውስጥ በጠቅላይ ሚኒስትሩ እየተሠሩ ያሉትን መልካም  ተግባራትን ለማደናቀፍና ዜጎችን ወደ ማያስፈልግ ግጭትና ጥላቻን በህዝቦች ልብ ለመርጨት ሌት ተቀን ሳይሉ እያሴሩ ይገኛሉ።እነዚህ አካላት በአሁኑ ሰዐት በተለያዩ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ በህዝቦች መካከል ልዩነቶችን በመፍጠርና በርከት ያለ ገንዘብን በመጠቀም ወጣቱን በማታለል ለውጡን ለማደናቀፍ በተለያ መንገዶች ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸው የአደባባይ ሚስጢር ነው።ይህንንም በሰኔ 16/2010 በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የተፈጠረው የቦንብ ፍንዳታ አንዱ የጥረታቸው ማሳያ ነው።ሌላኛውና ዋነኛው ሁሉም ሊያውቀው የሚገባው ነገር እነዚህ አካላት የህዝቦችን ፍላጎት መሠረት በማድረግ የለውጥ ሂደቱን ለማደናቀፍ በየአካባቢው የተለያዩ መፍጨርጨሮችን በማድረግ ላይ ይገኛሉ።እነዚህ መፍጨርጨሮች የህዝብን የለውጥ ፍላጎት ሊያቆሙት እንዳይችሉ ህዝብና መንግሥት እጅግ ተቀራርበው መሥራት ይገባቸዋል።ምክንያቱም ህዝቡ ከመንግሥት ጎን በመቆም ይህንን የለውጥ ሂደት ማስቀጠል ስለሚገባ ነው።ለአብነት ያህል ሰሞኑን በምዕራብ ኦሮሚያ የተከሰተውን ሁከት የአካባቢው ወጣቶች ከክልሉ መንግሥት ጋር በመተባበር በወሰዱት እርምጃ አካባቢው በፍጥነት ወደ ሰላምና መረጋጋት መመለሱንና ሁከቱን ለመፍጠር ሲሯሯጡ የነበሩ አካላትንም ወጣቱ ለይቶ በማውጣት ለህግ አቅርቧቸዋል።ይህም መልካም ማሳያ ሊሆን የሚገባው ነገር ነው።እንዲሁም ወጣቱንም ምክንያታዊ እንዲሆን ማድረግ ከተቻለ ማንኛውንም ነገር መፍታት እንደሚቻል ማሳየት ይገባል።በምዕራብ ወለጋ በተከሰት ግጭት የተዘጉ መንገዶች እንዲከፈቱ ያደረገውና ሁከተኞችንም ለህግ አሳልፎ ሲሰጥ የነበረው እራሱ ወጣቱ ነበር ይህ በሁሉም አካባቢዎች ሊለመድና ሊበረታታ የሚገባ ተግባር ነው ምክንያቱም ህዝቡ እራሱ ለራሱ ችግሮችን በመፍታትና በማረጋጋት ረገድ የበኩሉን መወጣት ስለሚገባው ነው።

ሌላኛውና ዋነኛው ማስተዋል ያለብን ነገር በአሁኑ ሰአት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጀመሩ መልካም ተግባራትን ለማስቀጠልና ሰላም በሀገራችን እንዲሰፍን ለማድረግ የምንሰማቸውን የተለያዩ መረጃዎችን ማጣራት መቻል ይኖርብናል። ምክንያቱም አንዳንድ ሀይሎች የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግሮች ሆን ብለው የተለያዩ ትርጉሞችን በመስጠት ለራሳቸው ፖለቲካ ፍጆታ ለመጠቀምና ለህዝቡ ያሰቡ በመምሰል በህዝቦች መካከል ግጭቶችን ለመፍጠር ሲሯሯጡ ይስተዋላሉ።ስለዚህ ህዝቡ የሚሰማውን መረጃ ታማኝነቱን ማረጋጋጥ ይገባዋል በተለይ በአሁኑ ሰዐት በተለያዩ ድረ ገፆች ላይ የሚለቀቁ መረጃዎችን በመመልከት ወደ አላስፈላጊ ነገር መግባት አይገባም።ለአብነት ያህል “ፀጉረ ልውጥ” የሚለውን አገላለፅ አሉታዊ ትርጉም በመስጠት ሰላማዊ የሆነውን ሰው ሁሉ በመጥፎ ዕይታ ውስጥ እንዲወድቅ ለማድረግ ከፍተኛ  ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

“ፀጉረ ልውጥ” ተብለው የተጠቀሱት ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሱ ሁከትና ግጭትን ለመፍጠር የሚሯሯጡ ሃይሎችን እንጂ ሰላማዊ ሰዎችን እንዳልሆነ ህብረተሰቡ ሊያስተውለው የሚገባ ነገር ነው። ማንኛውም ሰው በየትኛውም አካባቢ በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት ያለው ሲሆን “ፀጉረ ልውጥ” ተብለው የተጠቀሱት የህዝብን የለውጥ ፍላጎት በመሸርሸርና ሽብር በመንዛት ለማስቆም ቦንብና ሌላ ተቀጣጣይ ነገሮችን ይዘው ከቦታ ቦታ የሚሯሯጡ ሃይሎችን መሆኑን ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ሊገነዘቡት ይገባል። ከዚህ በተጨማሪም አሁን ላይ በህብረተሰቡ የተለየ ስሜት እንዲፈጠርበት ለማድረግ በተለያዩ አካባቢዎች የተካሄዱትን የድጋፍ ሰልፎችን በማንቋሸሽ ኢ-መንግሥታዊ እንደሆኑ ለማስመሰል በርካታ ጥረቶችን በማድረግ ህዝብና መንግሥትን ለማለያየት የተለያዩ ነገሮችን በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ህዝቡም ሊያውቀው የሚገባው ትልቁ ነገር እነዚህ የድጋፍ ሰልፎች በየትኛውም ሥፍራ ቢካሄዱም የህዝብና ህዝብ ብቻ ናቸው። ምክንያቱም መንግሥት ያደራጃቸውና በመንግሥት የሚመሩ ባለመሆናቸው ህዝቡ ስሜቱን ይገልፅልኛል ባለው መንገድ ሁሉ የተለያ ባንዲራዎችንና መልዕክቶችን ይዞ በመውጣት ድጋፉን መግለፅ ችለዋል። ይህ ለምን ሆነ እንዴት እንዲ ይሆናል  እያሉ የራሳቸውን ግላዊ አመለካከትን በመግለፅ ህዝብና መንግሥትን ለመለያየት በመትጋት ላይ ይገኛሉ። መንግሥትም በእነዚህ የድጋፍ ሰልፎች ላይ የነበረውን ነገር ሁሉ ህብረተሰቡ ለመንግሥት ያለውን ቀና ድጋፍና ይሁንታን የገለፀበት መንገድ በመሆኑ ሁሉንም ነገሮች በቅንነት ተመልክቶታል።ይህ ያላስደሰታቸው አካላት ግን ጥቃቅን ነገሮች ትልቅ እንዲሆኑና ሀገርን ለመያየት ቆርጠው ተነስተዋል ስለዚህ ህብረተሰቡ በሚሰማው ነገር ሳይታወክ ከመንግሥት ጎን በመሆን የእነዚህን አካላት መጥፎ ተግባር በማጋለጥ የተጀመረውን ለውጥ ማስቀጠል ይኖርበታል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy