Artcles

ፍቅርና መደመር— በኢትዮ-ኤርትራ ሰማይ ስር

By Admin

July 13, 2018

ፍቅርና መደመር— በኢትዮ-ኤርትራ ሰማይ ስር

                                                      እምአዕላፍ ህሩይ

(ክፍል ሁለት)

በክፍል አንድ ፅሑፌ ላይ ቃል በገባሁት መሰረት ቀሪውን የፅሑፌን ክፍል ይዤ ቀርቤያለሁ። በዚህ ክፍል በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረገው ስምምነት ፋይዳዎችን ከሀገራቱ ብሎም ከቀጣናው ተጠቃሚነት አኳያ በመመልከት ቀጣዩን የሁለቱን ሀገራት ጉዞ አብረን እንመለከታለን። መልካም ንባብ።..  

የስምምነቱ ፋይዳዎች

ርግጥ የወንድማማችነትና የእህትማማችነት ፍቅርን የተጠሙ ህዝቦች ድንበር አይገድባቸውም። “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” እንደሚባለው፣ ሁለቱ ሀገራት በጋራ ተጠቃሚነት መንፈስ ከሰሩ የምስራቅ አፍሪካ ጠንካራ ኢኮኖሚ ባለቤቶች ሊሆኑ ይችላሉ። በኤርትራ በኩል ምርቶቿን ለኢትዮጵያ ገበያ የማቅረብ፣ በኢትዮጵያ በኩልም የቀይ ባህር ፀጋዎችን የመጠቀም ዕድሎች ይሰፋሉ። ተቃቅፎና ተደጋግፎ በጋራ ማደግ የማይቻልበት ምክንያት የለም።

እንዳልኩት ሁለቱ ሀገሮች የፈረሟቸውን የሰላምና የወዳጅነት ስምምነቶችን በአስመራ ተፈራርመዋል። ስምምነቶቹ በኤርትራ የሚገኙ እስረኞችና ምርኮኞች እንዲሁም የድንበር ጉዳዮች፣ የወደብ አጠቃቀም፣ የአልጀርስ ስምምነት አተገባበር ብሎም ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን ያካተቱ ነው። የስምምነቶቹን ተፈጻሚነት የሚከታተል ኮሚቴም ተቋቁሞ ስራ ጀምሯል። ኮሚቴው በትራስንስፖርት ረገድም የአየርና የየብስ ትራንስፖርት ታሪፎችንና ሌሎች ጉዳዮችን በዝርዝር ይመለከታል። ይህ ሁኔታ ተሰብሮ የነበረውን የሁለቱን ሀገራት የሰላም፣ የፍቅርና የደመር ድልድይን ከመጠገን ባለፈ፣ ላለፉት 20 ዓመታት ሀገራቱ ያጡትን የጋራ ጥቅም የሚክስ ነው።

ኢትዮጵያና ኤርትራ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ከማሻሻል ባለፈ በዓለም አቀፋዊና በቀጣናዊ ጉዳዩች ተጋግዘው ለመስራት የሚችሉበት ዕድልም ይከፈታል። በዚህም አገራችን በሁሉም መስኮች ለምታደርገው ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች አንድ አጋዥና ተደማሪ ኃይል ታገኛለች። የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከኤርትራ መልስ እንዳሉት፣ ኤርትራ አሁን ካለችበት ሁኔታ ወጥታ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ውስጥ ገንቢ ሚና ማበርከት ትችል ዘንድ የተጣለባት ማዕቀብ እንዲነሳ ኢትዮጵያ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር ትሰራለች። በተጨማሪም ኤርትራ ወደ ምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) በመግባት በቀጣናው የሰላም ኃይል ሆና በጋራ የምትሰራበትና ከሌሎች እህት አገራት ጋርም በቅንጅት የምትሰራበት ሁኔታ እንደሚመቻች ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል። ይህን መሰሉ ተግባርም ኢትዮጵያና ኤርትራ እንደ ወንድምና እህት ህዝቦች ዓለም አቀፋዊም ይሁን ቀጣናዊ ሚናቸው ጎልቶ እንዲወጣ የሚያደርግ ነው። ኢትዮጵያ የኤርትራ አቅም የምትሆነውን ያህል ኤርትራም የኢትዮጵያ አቅም ሆና እንድትሰራ የሚያደርጋትም ጭምር ነው።

ታዲያ አንዱ ለሌላው አቅም ሊሆን እንደሚችል የሚያረጋግጥ ምሳሌን እዚህ ላይ ማንሳት ተገቢ ይመስለኛል። ይኸውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ከአስመራ እንደተመለሱ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ጋር አዲስ አበባ ተገናኝተው በተወያዩበት ወቅት በኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዲነሳ መጠየቃቸው ነው። ርግጥ ይህ ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስመራ ጉብኝታቸው ወቅት “…ከወንድሜ ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ጋር ስንወያይ፣ የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆኜ አቶ ኦስማንን በመወከል እንድሰራ ሾመውኛል። ምናልባት አንዳንዴ ስለ ኤርትራ ስናገር ብትሰሙ የስራ መዛነፍ እንዳይመስላችሁ” በማለት የተናገሩት ቀልድና ቁም ነገር ምላሽ ነው ብዬ አስባለሁ።

አንቶኒዮ ጉተሬዝም ኢትዮጵያና ኤርትራ መደበኛ ግንኙነታቸውን ለመጀመር መስማታቸውን ተከትሎ፣ ምክር ቤቱ በኤርትራ ላይ የጣለው ማዕቀብ ከዚህ በኋላ ተግባር ላይ የሚቆይበት ምክንያት የለም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። እንዲያውም ሁለቱ ሀገራት ከድንበር ጋር በተያያዘ የደረሱት የድንበር ማካለል ጉዳይ እንዲሳካ የመንግስታቱ ድርጅት ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ዝግጁ ነው ብለዋል።

እንግዲህ ይህ ጥያቄ መቅረቡ በራሱ ኢትዮጵያንና ኤርትራን እንደ አንድ ህዝብ የሚያስተሳስራቸው አመላካች የሰላም ቁርጠኝነት ነው። የዲፕሎማሲው ትብብር በይፋ መጀመሩን ያመላከተ ተግባርም ነው። የሰላም ስምምነቱ የሚደመር ተጨባጭ ርምጃዎችን እያስቆጠረ መሆኑም ጭምር።

ርግጥ ኢትዮጵያ አሁን ላይ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሀገር ናት። ይህ ሁኔታም ለኤርትራ ምቹ ነው። ኢትዮጵያ ድጋፍ በምክር ቤቱ ውስጥ ለኤርትራ ድጋፍ ማድረግ ከቻለች ማዕቀቡን ማንሳት የሚቻልበት እድል መኖሩ አይታበይም። ሁለቱ ሀገራት አብረው ሲሰሩም ኤርትራ በማዕቀቡ ምክንያት በዓለም አቀፍ ደረጃ አጋጥሟት የቆየው መገለል ሙሉ ለሙሉ ይቀየራል።

በአስመራና በአዲስ አበባ መካከል የተጀመረው የሰላም ስምምነት የሀገራቱ ህዝቦች እንዲተባበሩ ብቻ ከማድረግ ባሻገር የቀጣናውን ሀገራት በጋራ ሰላም አምጭዎች እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ሊገኝ የሚችለው ሰላምም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እንደሚጠቅም ጥርጥር የለውም። ቀጣናው ስትራቴጃካዊ ከመሆኑም በላይ እጅግ በርካታ የተፈጥሮ ፀጋዎችን በውስጡ አምቆ የያዘ ነው። እነዚህ ፀጋዎች ሁሉም ሀገራት ያላቸው አይደሉም። አንዱ ያለው ሌላው የለውም።

ታዲያ በሚገኘው ሰላም ሁሉም ሀገራት በጋራ ተጠቃሚነት መርህ አንዱ የሌለውን ከሌላው በመጠቀም ዕድገትን ሊያሳልጡ ይችላሉ። ይህም ቀጣናው የትብብር ማዕቀፍ ውስጥ እንዲገባ ያደርግና ሁሉም ሀገራት ተያይዘው እንዲያድጉ የሚያደርጋቸው ነው። ምስራቅ አፍሪካም ላላፉት 40 እና 50 ዓመታት አይታ በማታውቀው የልማት ሃይሎች ትከበባለች። ህዝቦቿም ከሚታወቁበት የድህነት፣ የስደት፣ የድርቅና የጦርነት ታሪክ ተላቅቀው ሌላው የአፍሪካ ክፍል ወደ እነርሱ በመምጣት ከልማቱ ተጠቃሚ ይሆናሉ።

ይህ ይሆን ዘንድም የኢትዮ-ኤርትራ የሰላምና የትብብር እንዲሁም የፍቅርና የመደመር ብስራተ ዜና ስር ሰዶ ብሎም ኤርትራ ማዕቀቡ ተነስቶላት እንደ ሀገርና ህዝብ በዓለም አቀፉም ይሁን በቀጣናው ሁለንተናዊ የትብብር ማዕቀፎች ውስጥ ተሳታፊ ሆና የኢትዮጵያ አጋዥ እህት ሀገር መሆን ይኖርባታል። ይህ እንዲሆንም የሁለቱም ሀገራት መሪዎች በቀጣናው፣ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተባብረው ለመስራት ስምምነት ላይ ደርሰዋል። ከላይ እንደጠቀስኩት ስምምነቱን ተፈፃሚ የሚያደርግ ኮሚቴ ከመኖሩም በላይ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድም የመጀመሪያውን በረራ ባሃብቶችን በመያዝ እንደሚያደርግ ተነግሯል። ይህ ለአራት ቀናት የሚቆየው በረራ የሀገራችንና የኤርትራን ባለ ሃብቶች የሚያገናኝና በጋራ ሊሰሯቸው በሚገቧቸው ጉዳዩች ላይ የሚመክር ነው። እንዳልኩት በመንግስት ለመንግስት ከሚደረገው የጋራ ተጠቃሚነት ስራ ባሻገር፣ አንዱ የሌለውን ሌላው ማቅረብ የሚችልበትን ዕድል የሚፈጥር ነው። ወደ ኤርትራም ይሁን ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት የሚሰጠው ቪዛ በመዳረሻ ላይ ይሆናል። ይህም ሀገራቱ የአንዱ ዜጋ ወደ ሌላኛው ከቪዛ ነፃ በሆነ መንገድ የሚገባበትን ሁኔታ እስከሚያመቻች ድረስ የሚቆይ ነው። መረጃዎች እንደሚያመላክቱት የቀድሞው በኢትዮጵያ የኤርትራ ኤምባሲ የነበረው ህንፃ እድሳት እየተሳለጠ ነው። ይህ ሁኔታም የሁለቱ ሀገሮች ቁርኝት በፍጥነት እየተሻሻለ መሆኑን የሚያመለክት ነው። ርግጥ ከመዘግየት ምንም አይገኝም። ሀገራቱ ላለፉት 20 ዓመታት ያመለጧቸውን ዕድሎች ሁሉ በአፋጣኝ ማግኘት ይኖርባቸዋል።

ቀጣዩ ጉዞ

የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦች ቀጣይ ጉዞ የሰመረ እንደሚሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ የተገኙት ለውጦች በቂ ማሳያዎች ይመስሉኛል። ያለ ሶስተኛ ወገን አሸማጋይነት ሁለቱ ሀገራት ግንኙነታቸውን አድሰው በሰላምና በወዳጅነት አብሮ ለመስራት የደረሱባቸው ስምምነቶች ዋነኛ መገለጫዎች ናቸው። አዲስ ዘመን ጋዜጣን ጨምሮ ሰሞኑን የሚወጡት የማህበራዊ ሚዲያ መረጃዎች፤ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ አዲስ አበባን እንደሚጎበኙ እየገለፁ ነው። አቶ ኢሳይያስ በኢትዮጵያ የሚያደርጉት ኦፊሴላዊ የስራ ጉብኝት የሀገራቱን የወደፊት ብሩህ ተስፋ የሚያጠናክርና ሀገራቱ ለተስማሙባቸው ስምምነቶች ፈጣን ተፈፃሚነት የራሱ ፋይዳ ያለው መሆኑ ግልፅ ነው።

የሰላምና የወዳጅነት ስምምነቶቹ ገቢራዊ ሆነው ሁለቱም ሀገራት እስካሁን ያጡትን የጋራ ተጠቃሚነት ሊያጣጥሙ ይገባል። ለዚህ ደግሞ በሁለቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የሚመራው ኮሚቴ ስራውን እንዲያፋጥን የሀገራቱ መሪዎች ድጋፍ ወሳኝ ነው። ድጋፉ በተለይም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ እንዲጠናከርና የጋራ ጥቅሞች ፈር እንዲይዙ እንዲሁም ሀገራቱ የአፍሪካ ብሎም የዓለም ተምሳሌት ሆነው እንዲጠቀሱ የሚያደርግ ነው። ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ወደ ሁለተኛ ሀገራቸው በመምጣት የሚያደርጉት ጉብኝት የተጀመረውን የስምምነት ማዕቀፍ እንዲሳለጥ የሚያደርግ ጭምርም ይመስለኛል። ሰላም ለኢትዮጵያና ለኤርትራ። ሰላም ለቀጣናው ህዝቦች። ሰላም ለአፍሪካ።