Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

   ፓርላማውና አዲሱ በጀት

0 442

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

   ፓርላማውና አዲሱ በጀት

ይልቃል ፍርዱ

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ የዘንድሮውን አመት የመንግስት የስራ አፈጻጸምና የቀጣዩን አመት እቅድና በጀት ሪፖርት አቅርበው በፓርላማው አጸድቀዋል፡፡ሪፖርቱ በበጀትም ሆነ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ግንዛቤን ያስጨበጠና ለወቅታዊ ችግሮች መፍትሄዎችን ያመላከተ ነው፡፡የቀጣዩ አመት የሀገሪቱ በጀት 346.9 ቢሊዮን ብር በፓርላማ ቀርቦ ጸድቋል፡፡ 91.7 ቢሊዮን ብር ለፌደራል መንግስት የመደበኛ ወጪ፣ 113.6 ቢሊዮን ለካፒታል ወጪ፣135.6 ቢሊዮን ለክልል መንግስታት ለድሬዳዋና  ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተመደበ ሲሆን 6 ቢሊዮን ደግሞ ለዘላቂ ልማት ግቦች የሚውል ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ የዘንድሮ በጀት 64 በመቶ ለድሕነት ቅነሳ፣ 55 በመቶ ለካፒታል በጀት፣ 45 በመቶ ለመደበኛ ካፒታል የሚውል መሆኑን ገልጸው ልዩ ድጋፍ ለሚሹ ክልሎች ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡ ባለሀብቶች ሀብታቸውን፣ ጊዜያቸውንና እውቀታቸውን በሀገር ውስጥ ማዋል እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ የሚፈጠር ሲሆን ኢንቨስትመንትን ማበረታታት የሚያስፈልግ መሆኑንም በፓርላማው ንግግራቸው ወቅት ጠቅሰዋል፡፡

በአገልግሎት ላይ ያለው እንግልት በተለይ  ጊዜና ሀብትን ለብክነት የሚዳርግ አሰራርን ለማስቀረት የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት የሚሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ሜጋ ፕሮጄክቶችን በተመለከተ ሜጋ ፕሮጀክቶቹ ሲጀመሩ እንጂ ሲጨረሱ ያልታዩ በመሆናቸው በበጀት ዓመቱ አዲስ ፕሮጄክቶች አይጀመርም፡፡  ምክንያቱም የተጀመሩትን ለመጨረስ ከ 7 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ፡፡

የውጭ ምንዛሪን ለማሳደግ ግብርናን ማዘመን አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቤቶች ግንባታን በተመለከተ ከዜጎች የቤት ፍላጎት ጋር በተያያዘ የቤት ልማት አመራር መታየትና መፈተሽ ለዚህም ዘርዘር ያለ ሁኔታ እንደሚያስፈልገው ጠቅሰዋል፡፡ ሁሉንም ዜጋ የቤት ባለቤት ማድረግ ባይቻልም ቤት መሰረታዊ ፍላጎት እንደመሆኑ መጠን ባለሀብቱም በዚህ ረገድ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡  ዜጋው በኪራይ ቤት የሚያገኝበት ሁኔታም መመቻቸት እንዳለበትና የህብረተሰቡን እንግልት ለማስቀረት መንግስት ከግሉ ዘርፉ ጋር በቅርበት የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኑሮ ውድነት ጋር በተያያዘ  የዋጋ ግሽበት ከአቅርቦትና ፍላጎት ጋር የሚያያዝ በመሆኑ ከበቂ በላይ ምርት ማምረት በተለይ የምግብ ምርቶች፣ የኑሮ ውድነት በተመለከተም መከላከል የሚቻለው የነፍስ ወከፍ ገቢን ከፍ በማድረግ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ገቢ ማሳደግ የሚቻለው የስራ ዘርፍን በማስፋት፣ ኢንቨስትመንትን በማስፋት፣ ኢኮኖሚን በማሳደግና  በማበልጸግ የገንዘብ ስርዓቱን መቆጣጠር እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

የታክስ (ግብር) ስርዓትን ማዘመን አስፈላጊ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግብር የማስገባት አቅም ማሳደግ ለዚህም ባለሀብቶችና ኢንቨስተሮች ለመንግስት እሳቤ ማድረግ እንደሚገባቸው በዚህም ባለሀብቶች ኃብት በመቀነስና ባለማሽሽ፣አንድ ቦታ የሚከማች ኃብት ጥሩ ባለመሆኑ ቤት ውስጥ ከማስቀመጥ በባንክ ማስቀመጥ የሚመረጥ መሆኑን ገልጸው በዚህ ጉዳይም ጥናት በማድረግ ጠንካራ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የገንዘብ ስርዓቱን ለመቆጣጠር በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ጠንካራ ኮሚቴ መቋቋሙን የግል ዘርፉ በኃላፊነት ስሜት የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ ከግብርና ጋር በተያያዘ በሀገሪቱ ምርትና ምርታማነቱን ለማሳደግ የግድ ጠንካራ ስራ መሰራት ያለበት መሆኑን አስምረውበታል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ትንሽ መሰልጠንና መብሰል ካልቻልን እዚህም እዚያም በሚኖሩ ፍትጊያዎች የሚጎዳው የሀገር ኢኮኖሚ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ እዚህም እዚያም በሚነሱ ፍጭቶች እጃቸው ያለበት ፖለቲከኞች አንድ ችግራቸው ነገር ሲሞትና ሲድን የማያውቁ በመሆናቸው ነው፡፡እድሜ ልክ ሀገርን መምራት ከዚህ በኃላ የለም ብለዋል ለፓርላማው፡፡

የክልሎች የበጀት ቀመር አደላደልንና የፍትሃዊ ተጠቃሚነትን አስመልክቶ ለተነሳላቸው ጥያቄ ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ በሰጡት መልስ ሕገ መንግስቱ እኩል መጠቀምና እኩል እድል የማግኘት መብት ሰጥቷል፡፡ በመሆኑም የመርሆውን አተገባበር ማጤን እንደሚገባ ክልሎች የሚያስመዘግቡትን እድገትና ለሀገር የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ እንዲመዘን ማድረግ የፍትሀዊ ተጠቀማኒትን ጥያቄ ለማጤን ይረዳል ብለዋል፡፡

የበጀት ቀመሩ ሕገመንግስታዊ መርሆን የተከተለ ቢሆንም በፌደሬሽን ምክር ቤት ላይ የሚነሱትን የአሰራር ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል ማሻሻያ የሚደረግ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ገልጸዋል፡፡ለክልሎች የሚሰጠው ድጋፍ እንዳለ ሆኖ በፕሮጀክት ደረጃ የሚነደፉ የልማት እቅዶች በጥናት ላይ እንዲመሰረቱ የሚደረግ መሆኑን በስራዎች ላይ የክዋኔ እና የፋይናንስ ኦዲትን ተግባራዊ በማድረግ ውጤታማነትን መገምገምና መለካት የሚያስችል አሰራር ተግባር ላይ እንደሚውል ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስረዱት፡፡

ለዚህም ፓርላማው ቀዳሚ ሚናውን ይወጣል፡፡ በሕግ አግባብም የእርምት እርምጃ እስከ መውሰድ ይደረሳል፡፡የአስፈፃሚ አካላት ከበጀት ጀምሮ ግልፅነት የተሞላበት አሰራር እንዲኖር እስከ ሠራተኛው ድረስ በማውረድ ውጤታማ መሆኑን ማረጋገጥ ይገባቸዋል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ለፓርላማው ገልጸዋል፡፡በሰበብ አስባብ ግጭት አያስፈልግም፡፡
አንዳንድ ሰው ዲሞክራሲ ዝም ብሎ የተከፈተ ስለሚመስለው  ራሱን መግራት ይቸገራል፡፡ይህ ነገር ወደ ሁለት መንገድ ያመራናል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፡፡

አንደኛው መብት መጠየቅ እና ግዴታ መወጣት ድንበር እንዳለው አውቀን ወደ ብስለት ወደታከለበት ዲሞክራሲ እንሻገራለን ወይ ደግሞ ወደ የለየለት አምባገነን መንግስት እንዲፈጠር ይሆናል፡፡አምባገነን መንግስታት የሚፈጠሩት በሕዝባቸው ምላሽ ነው የሚባለው ለዚህ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ  ሰላም የተሻለና በኃላፊነት የሚሰራበት የጋራ ስራ መሆኑን በማያሻማ ሁኔታ አመላክተዋል፡፡

ውሀ ቀጠነ እያልን መኪና የምንሰባብር ከሆነ መንግስት ፖሊስ ስላለው የተለመደውን ነገር ማድረጉ አይቀርም፡፡መንግስት ወደ’ዛ እንዳይገባ ሕዝብ በበሰለ መንገድ እያንዳንዱን እንቅስቃሴ መፈተሸ ያስፈልጋል፡፡ክፍት ነው ብሎ ሕግንና ሕገ-መንግስትን እየጣሱ መሄድ ተገቢ አይደለም፡፡ሕገ-መንግስት ችግር ካለበት ተወያይታችሁ አስተካክሉኝ ብሏል ሕገ-መንግስቱ፡፡በውይይት በምክክር የሕዝቡን ፍላጎት ታሳቢ አድርጎ ማሻሻል ይቻላል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ፡፡የስር ነቀል ለውጥ መሪው ፈጣን እርምጃ ቀጥሏል፡፡

ማጠቃለያ

በቅርቡ በፓርላማ የጸደቀው የዘንድሮው አመት ብሔራዊ በጀት ከቀድሞዎቹ ጋር በንጽጽር ሲታይ ሰፊ ሀገራዊ ስራዎች ለመስራት የሚያስችል አቅም የሚፈጠር ነው፡፡ብክነትን በመከላል ቁጠባን ያበረታታል፡፡አብዛኛውን ሕዝብ ተጠቃሚ የሚያደርግ ስራ ይሰራል፡፡ በእቅድ በመመራት ተዝረክርከው የቀሩ ገንዘብ ተመድቦላቸው ፕሮጀክቶቹ ተግባራዊ ሳይሆኑ ተጀምረው በሙስናና ሌሎች ምክንያቶች ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ወደስራ እንዲገቡ ይደረጋል፡፡በቁጠባ መኖር ብሔራዊ አቅም ይገነባል፡፡በዲያስፖራ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሰፊ እገዛ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡በሕግ የተቀመጠን የተደነገገን መብት አክብሮ መንቀሳቀስ ለሁሉም ዜጋ ተገቢና አዋጭ ነው፡፡ሕግና ስርአት እንደሌለ አድርጎ መንቀሳቀስ ከሕግ ተጠያቂነት አያድንም፡፡ሕጉን የሚተላለፍ ነገር ማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ይጎዳናል እንጂ አይጠቅመንም፡፡ገና ያልበሰለ ዲሞክራሲ፤ገና ያልበሰለ ስርዓት ያለበት ሀገር መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ትክክልም ነው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስተር አቢይ አህመድን ስርነቀል የለውጥ እርምጃዎች ለማሰናከል የሚደረጉት ሴራና ደባዎች በሕዝቡ ርብርብ ይገታሉ፡፡በማሳያነት የአዲስ አበባ መስተዳድር ክ/ከተሞችን ሥራ መቀዛቀዝና እና የፖሊሶችን ችላ ባይነት ጠቁመዋል፡፡ፈጥኖ ሊታረምና ግዜ ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ አይደለም፡፡በሽግግር ጊዜ ሊፈጠር የሚችል ውዥንብርና ክብሪት ጫሪዎች መኖራቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ሁሉም በራሱ ጊዜ እንደሚከሽፍ  የተናገሩት እውነት ቢሆንም ሴራዎቹን ማምከክን ይጠበቅብናል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy