Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መደመር – ሰፊውና ቀናው መንገድ!

0 1,204

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መደመር – ሰፊውና ቀናው መንገድ!

ህላዊ በየነ

በእኔ እይታ ህወሃትና የትግራይ ህዝብ፣ ብአዴንና የአማራ ህዝብ፣ ኦህዴድና የኦሮሞ ህዝብ፣ ደህዴንና የደቡብ ህዝቦች፣ ወዘተ አንድ ሊሆኑ ከቶ አይችሉም። መንግስትና አገር፤ ፓርቲና ህዝብ  ለየቅል ናቸው። በእርግጥ በትግል ወቅት የትግራይ ህዝብ ከህወሃት ጎን ተሰልፎ ከሌላው ህዝብ የበለጠ መስዋዕትነት መክፈሉ የሚካድ አይደለም። ይሁንና ህዝብና ፓርቲ አንድ ናህቸው ማለት ግን አይደለም። ፓርቲንና ህዝብን ከቶ አንድ ሊያደርግ የሚችል ነገር  የለም። በእርግጥ ፓርቲው እንደነገረን የትግራይ ህዝብና ህወሃት አንድ ነን እንዳለው ህዝቡም ይህን አስተሳሰብ የሚደግፍ ከሆነ ምርጫው ነው። በበርካታ ኢትዮጵያዊያን አረዳድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህወሃትንና የትግራይ ህዝብን የገለጹበት መንገድ ተገቢና ትክክለኛ ነው ባይ ነን።  

እንደእኔ እንደእኔ  ፓርቲና ህዝብ አንድ ሊሆኑ ከማይችሉበት የመጀመሪያው አሳማኝ ምክንያት መካከል  ፓርቲ ይሳሳታል፣ ያጠፋል ታዲያ ይህ ስህተትና ጥፋት ወደ ህዝብ እንዳይተላለፍና በህዝቦች መካከል ቅሬታ እንዳያስከትል ነው። ለዚህም ይመስለኛል  ፓርቲና ህዝብ ለይተን እንይ እየተባለ በከፍተኛ ሃላፊዎች ጭምር እየተገለጸ ያለው። ህወሃት የትግራይ ህዝብን ድጋፍ ለማግኘት ሲል ህብረተሰቡን የማይገባ ነገር ውስጥ ለመክተት ሙከራ አድርጓል። በቅርቡ ህውሃት ያወጣውን መግለጫ ሳደምጥ ፓርቲው  በሳል አመራር እንኳን እንደሌለው ተረድቻለሁ። መጀመሪያ በእንዲህ ያለ በብሄርና በቋንቋ በተከፋፈልንበት ወቅት ህወሃት ከትግራይ ህዝብ ጋር አንድ ነን የሚል መግለጫ ማውጣቱ ተገቢ አይደለም።

አሁን ላይ እውነት እውነቱን መነጋገር መልካም ነው። በኢህአዴግ ቤት ህወሃትና ሌሎቹ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት  ሁሉም የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች እኩል ስልጣን ነበራቸው ብሎ ህዝብ ያምናል ብሎ ህወሃት ያምን ከነበረ በጣም ተሳስቷል። ህወሃት አገሪቱን በበላይነት ሲመራ በነበረበት  ባለፉት 27 ዓመታት ለአገራችን መልካም ነገሮች እንዳመጣ የማይካድ ሃቅ እንደሆነ ሁሉ ለመስማት የሚሰቀጥጡ ስቃዮችም እንደፈጸመ ማስረጃ ማቅረብ የሚያስፈልገ አይመስለኝም።

ህወሃት መግለጫ ውስጥ የትግራይ ህዝብና ህወሃት  አንድና አንድ እንደሆኑ ተገልጿል። ይህ ከላይ ባነሷኋቸው ምክንያቶች ህዝብና ፓርቲ አንድ ሊሆኑ አይችሉም። ህወሃት በእንዲህ ያለ ሁኔታ ድጋፍ መፈለጉ አግባብነት የጎደለው አካሄድ ነው። ፓርቲ ይመሰረታል፤ እንዲሁም ይፈርሳል፤  መንግስታት ይመጣሉ በተመሳሳይ ይሄዳሉ፤ ህዝብ ግን ሁሌም ይኖራል። ስለዚህ ህዝብና ፓርቲ አንድ ሊሆኑ አይችሉም።

ሌላው ህወሃት መግለጫ ውስጥ የታዘብኩት ጉዳይ የህወሃት ጉምቱ ወይም መስራች ታጋዮች መንግስትና ኢህአዴግ በክብር እንዲያሰናብቷቸው በመግለጫው ተጠቁሟል። ለመሆኑ እነዚህ ታጋዮች እኮ በ70 እና 80 ዓመታቸው እንኳን ከስልጣን አንለቅም ብለው  በሃይል በወጣቶች ትግል ተገፍተው በሃይል ተጣሉ እንጂ በፍቃዳቸው ከእኛ የተሻለ አመራር አገሪቱን ይረከብ በማለት ስልጣን አላስረከቡም። አገራችን ሁለት ዓመት ሙሉ ስትታመስ እነዚህ ሰዎች ሁኔታውን አገናዝበው እስኪ ምክንያቱ እኛ ከሆን በማለት ስልጣን እንልቀቅ ከእኛ የተሻለ ሰው አገሪቱን ይምራ ለማለት አልፈለጉም። ታዲያ እንዴት እናክብራቸው? እንዴት ተምሳሌቶቻችን ናቸው ብለን ለሽልማት እንጫቸው?

በእኔ አረዳድ እነዚህ ሰዎች እኮ እስከመጨረሻዋ ሰዓት እነአቶ ለማና ዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን እንዳይመጡ በተለያዩ ቴክኒኮችን ሲጠቀሙ እንደነበር  ማስረጃ ማቅረብ የሚያስፈልግ አይመስለኝም። ታዲያ በትግል በመሰዋዕትነት ወደ ስልጣን የመጣ ሃይል ትላንት እንቅፋት ለነበረው ሃይል የክብር አሸኛኘት ማድረግ ተገቢ ነው ብሎ ህወሃት እንዴት ያስባል? ለእነዚህ ሰዎች  ዛሬ ላይ እውቅና መስጠት ትላንት ይህን ለውጥ ለማምጣት በተለይ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች መስዋዕት በሆኑ ወጣቶች ደም እንደመነገድ አይቆጠርምን? ለእኔ የሚሰማኝ ህውሃት የክብር አሸኛኘት ይደረግላቸው ያላቸው ሰዎች እስከመጫረሻው ሰዓት ድረስ ስልጣን አንለቅም እያሉ ሲንገታገቱ  እንደነበር ህወሃት አያውቅም? ወይስ ህወሃት ይህን ሁኔታ የኢትዮጵያ ህዝብ የማያውቅም ብሎ ያስብ ይሆን?

ከዚያም ባሻገር እነዚህ ሰዎች ስልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ ስለፍትሃዊነት እንዲሁም ከስልጣን ከወረዱ ብኋላ የለውጥ ሂደቱን ለማደናቀፍ በየመድረኩ የሚያምዱትን አቋም  ተመልክተን አዝነናል። ተጨባጭ ማድረግ ባይቻልም ከሁከቶችና ነውጦች ጀርባ የሚያጠረጠሩ ነገሮችንም እንዳሉ የአደባባይ ሚስጢር እየሆነ ነው። ህውሃት ውስጥ ጥሩ ፖለቲከኛ የለም ለማለት ያስደፈረኝ ነባራዊ ሁኔታዎችን መርምሮ እንደዚያ ያለ መግለጫ ሲወጣ  ድርጅቱን ከትዝብት ላይ ይጥለዋል ብሎ የተቃወመ አመራር ባለመኖሩ ነው። አሁን ላይ ህወሃት ቢያንስ ዝም ሊል ይገባል።

እንግዲህ እነዚህ ሃይሎች ዛሬም “የትግራይን ህዝብ ከለላ አድርገው ወደ ስልጣን ለመመለስ ህወሃትንና የትግራይ ህዝብ አንድና አንድ ናቸው፤ ሁለቱን ለመነጣጠል የሚደረጉ ጥረቶች እየተስተዋሉ ነው። የትግራይ ህዝብ ተነስ ወዘተ ስሜት የሚሰጡ  መግለጫዎችን ለማውጣት የደፈሩት። ህወሃት በትግራይ ክልል ተመሰረተ እንጂ ሁሉንም ትግራይዋን ይወክላል መለት አይደለም፤ በተመሳሳይ ብአዴንም፣ ኦህዴድም እንደዛወ ናቸው። ሲጀምር ህዝብና ድርጅት አንድ ሊሆኑ አይችሉም። እውነት እንነጋገር ከተባለ ህወሃት  ላጠፋው ጥፋት አንድ ተራ ትግራውያን ዕዳ ከፋይ መሆን የለበትም።

እውነት እንነጋገር ከተባለ ሌባ በሌሎች ድርጅቶች (በብአዴን፣ ኦህዴድና ደህዴን) የሉም ማለት ባይቻልም መረን ያጣ ሌብነትና ሌቦች የተሰገሰቡት ድርጅት  ግን ህወሃት ውስጥ እንደሆ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። በሌብነት ቢሊዮን ገንዘብ የሰበሰበ፣ አስር አስራ አምስት ሰማይ ጠቀስ ፎቅ በየከተማው የገነባ  በሌላ በኩል ሰርቆ አንድ መኖሪያ ቤት የሰራ አንድ አድርጎ ለማቅረብ መሞከር ውሃ የሚቋጥር አካሄድ አይደለም። የኢትዮጵያ ህዝብ ለትግራዊያን ጥላቻም ሆነ የተለየ ስሜት ሊኖረው አይችልም። ትግራዊያን ለዘመናት ከየትኛውም ህዝብ ጋር አብሮ ኖሯል፤ ካልተጋባውና ካልተዋለደው ብሄርም የለም፤ በሃይማኖትም ሆነ በባህል  ከሁሉም ኢትዮጵያዊ ጋር የተሳሰረ፤ አብሮ መኖርን የሚያውቅ ህዝብ ነው።

ትግራዊያን ምርጫቸው የእነርሱና የእነርሱ ብቻ ነው። የዶ/ር አብይን ጥሪ ተቀብለው መደመር አሊያም  ከህወሃት ጋር ጋር ማበር። እኛ ኢትዮጵያዊያኖች የምናምነው አገርና ፓርቲ እንዲሁም ህዝብና ፓርቲ የተለያዩ መሆናቸውን ነው። ሁለቱም በተለያየ መንገድ መታየትና መለካት አለባቸው። “አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ” እንዳይሆን የትግራይ ህዝብ ሌባን ሌባ ይበል።               

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዳንድ የትግራይን ሕዝብ እንወክላለን የሚሉ ግን የማይወክሉ ግለሰቦች በተለያየ ሚዲያዎች ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ የተናገሩትን ነገር  በማጣመም ሌላ ትርግም ለመስጠት ጥረት ሲያደርጉ ይስተዋላሉ። እስኪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩትን ቃል በቃል እንመልከተው፤ “የትግራይን ሕዝብና ሕወሐትን ነጣጥላችሁ እዩ፤ ሕወሐት ባጠፋው የትግራይ ሕዝብ ሊሰደብ ንብረቱ ሊወድም ሕይወቱን ሊያጣ አይገባውም እውነተኛ የትግራይን ሕዝብ ኑሮ ማየት ከፈለጋችሁ ገጠር ሔዳችሁ እዩ” ማለቱ ነው። እዚህ ዐረፍተ ነገር ውስጥ እስኪ  የትኛው ሃረግ ወይም ቃል ነው ስህተት? ወይም ደግሞ ሌላ ትርጉም ሊያሰጥ የሚችለው አገላለጽ?

የትግራይን ሕዝብና ሕወሐትን አትነጣጥሉ የምትሉ ጥቅመኞች የምናስተላልፍላችሁ መልዕክት ቢኖር ፓርቲንና ሕዝብን፤ አገርንና መንግስትን  ለዩ ነው። በኢሕአዴግ ውስጥ ላለፉት 27 ዓመታት ጠንካራ ክንድ የነበረው መቼም ሕወሐት እንደሆነ የሚካድ አይደለም። ነው። ህወሃት አገሪቱን  ባስተዳደረበት ወቅት ያለማው ነገር እንዳለ ሁሉ ያጠፋው ጥፋትም እንዳለ ሊታወቅ ይገባልና ሕወሐት ባጠፋው ምስኪኑና ጥሮ ግሮ ላቡን አንጠፍጥፎ የሚበላው ትግራዋይ የበቀል ተጋላጭ መሆን  አይገባውም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት ያስቀመጡት ይህንን ሐቅ ነውና ጥቅመኛ ፖለቲከኞች ነገር እየሰነጠቃችሁ የትግራይን ሕዝብ ከሌላው ህዝብ ለመነጠል ባትሞክሩ መልካም ነው። ይህን አይነት አካሄድ መጀመሪያ የሚጎደው  የትግራይን ሕዝብ ነው።

ዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን ከወጡ ጀምሮ አየሰሩ ካሉት ዋነኛ ስራዎች መካከል ቂም በቀልን ማጥፋትና ይቅርታ፣ ምህረትን ፍቅርን መስበክ ነው። ይህ ተግባር የትግራይ ህዝብን በየትኛው  መስፈርት ይሆን የሚጎዳው? በፍትሃዊነት የትግራይ ህዝብ ለምን ይጎዳል? ፍቅር፣ ይቅርታን እርቅን መስበክ ክፋቱ እምኑ ላይ ነው? በኢትዮጵያ አንድነትና የመደመር ታሪክ ጉልህ ሚና ያለውና የኢትዮጵያ ሞተር ሲሉ ዶ/ር አብይ በመቀሌው መድረክ  የገለጹት የትግራይ ሕዝብ ከወንድሞቹ አማራዎች፣ ኦሮሞዎች፣ ሶማሌዎች፣ አፋሮች፣ ሲዳማዎች፣ ወዘተ ቢደመር ከማንም በላይ የሚጠቅመው ለእርሱ ነው። በዚህ ዘመን መደመር ምን ያህል አቅም እንደሚፈጥር አውሮፓዊያኖችን መመልካት ይቻላል።በህወሃት የበላይነት አለ በተባለበት ባለፉት 27 ዓመታት የትግራይ ህዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ  የተለየ ጥቅም አላገኘው፤ በእርግጠኝነት በዛሬው አመራርም የትግራይ ህዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ የተለየ ጉዳት ሊደርስበት አይችልም። ስለዚህ የመደመር ፖለቲካው የመጀመሪያውም ሆነ የመጨረሻው አማራጩ ሊሆን ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy