Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

         ሀገር ያስደመሙ ድንቅ ስራዎች

0 541

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

         ሀገር ያስደመሙ ድንቅ ስራዎች

                                               ይልቃል ፍርዱ

ኢትዮጵያ በታላቅ የዲፕሎማሲ ስኬትና ድል ላይ እየተረማመደች ትገኛለች፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ብሄራዊ ድሎችና ዲፕሎማሲያዊ ስኬቶች ተዘርዝረው አያልቁም፡፡አሁንም ቀጥለዋል፡፡

ዶ/ር አብይ አሕመድ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቃለ መሀላ ፈጽመው በተረከቡ ማግስት ጀምሮ በሕዝቡ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ሰፍኖ የነበረውን የመከፋፈልና የመበታተን በሽታ መክሰም ጀምሯል፡፡  አንዣቦ የነበረውን አደጋ ለመቅረፍም በመጀመሪያ በሶማሊያ ክልል፣ ቀጥለው በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ በአማራ፣ በደቡብ፣ በቤንሻንጉል፣ በአፋር እና በጋምቤላ በመገኘት ከሕዝቡ ጋር ቀጥተኛ ሰፊ ውይይት አድርገዋል፡፡

ሕዝቡም ፊት ለፊት ያሉበትን መሰረታዊ የመልካም አስተዳደር፣ የሙስና፣ የፍትሕና የልማት ችግሮችን በግልጽ አቅርቧል፡፡ መታሰብ ያለበት እንደ ጥንቱ ዛሬም፣ ወደፊትም አብሮነታችን፣ ሕብረታችንና አንድነታችን መሆኑን በአጽንኦት በየሄዱበት የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ከፈፊት ለፊት ተጋርጦ የነበረውን የመከፋፈል ብሔራዊ አደጋ ሙሉ በሙሉ እንዲቀረፍ ማድረግ ችለዋል፡፡

በእርግጥም ዛሬም የሚታየወን የውስጥ  ሰላም ለማደፍረስ የሚታትሩ አልጠፉም፡፡ ለምን ሰላም ተገኘ ብለው ገንዘብ እየረጩና ወጣቶችን እያነሳሱ የእርስ በእርስ ግጭት እንዲፈጠር በማድረግ እኩይ ተግባር ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ክፍሎች ዛሬም ከዚህ ምግባራችው አልታቀቡም፡፡ባይሳካላቸውም ቅሉ፡፡

በጉጂ፣ በሲዳማ፣ በሀዋሳ፣ አሁንም በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎችና በሶማሊያ ክልል እምብዛም ቢሆን እየተንቀሳቀሱ ያሉ አሉ፡፡ ዋና ጥረታቸውም የተጀመረውን ሀገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ማሰናከል እና ለውጡን እየመራ ያለው መንግስት በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ማድረግ አልቻለም የሚለውን መልእክት ለማስተላለፍ ነው፡፡ይህ የተበላ ቁማራቸው በሕዝቡ ዘንድ የተጋለጠ ስለሆነ ውጤታማ መሆን አልቻሉም፡፡ እያንዳንዷን እንቅስቃሴና የተለየ ሕገ-ወጥ ድርጊት  ሕዝቡ እየተከታተለ በማጋለጥ ለሕግና ለፍርድ ያቀርባቸዋል፡፡ የለውጡን ሂደት የመግታት አቅም የላቸውም፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ እየተመራ ያለው ለውጥ ኢሕአዴግ በጥልቅ ተሀድሶው ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት እየተራመደ ያለ ስርነቀል ለውጥ ነው፡፡

ኢሕአዴግ  ከጥልቅ ግምገማው በኃላ ለተፈጠሩት ሀገራዊ ቀውሶችና ስህተቶች ሁሉ ሙሉ በሙሉ ኃላፊነቱን ወስዷል፡፡ ለሕዝቡ አዲስ ለውጥ እንደሚያመጣ፣ ይሄንንም ሰርቶ እንደሚያሳይ፣ ሕዝቡንም ይቅርታ ጠይቆ የጀመረው ለውጥ መሆኑን መዘንጋት አይገባም፡፡ በሀገር ውስጥ ያለው ሕዝብ  በደረሰበት የመልካም አስተዳደር ችግር፣ የፍትህ እጦት፣ የሙስና ግፍ፣ የመሬት ቅርምትና የመሳሰሉት አምርሮ በመቃወምና በመታገል የዛሬውን ለውጥ ማምጣት ችሏል፡፡ የዚህ ለውጥ ባለቤት በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኘው ተቃዋሚ ኃይል አይደለም፡፡ አሁን በሚታዩት ሁኔታዎች እንደ ኦነግ ባሉ አካላት የሕዝቡን ድል የመንጠቅና እኛ  ነን ያመጣነው የሚሉ ከንቱ ድለቃዎች እየታዩ ነው፡፡

ለውጥ እንዲመጣ የታገለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፡፡ የሕዝቡን ጥያቄና ግፊት መሰረት አድርጎ በራሱ ውስጥ ተሀድሶ በማድረግ ስርነቀል የሆነውን ለውጥ የመራው ኢሕአዴግ ነው፡፡ በዚህም መሰረት በመላው ኢትዮጵያ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር እንዲቻል በብዙ ሺህ ታሳሪዎችን ከእስር ፈቶቷል፡፡ እዚህ ውስጥ ታዋቂ የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪዎችም ጭምር ይገኙበታል፡፡

ትግሉ በየትኛውም  ውስጥም ሆነ የውጭ ተቃዋሚ አልተመራም፡፡ይልቁንም ያለፈውን ረስተንና  ይቅር ተባብለን ወደሀገራችሁ በምሕረትና በይቅርታ ገብታችሁ አብረን እንስራ ነው ያለው መንግስት፡፡ይህንን ጥሪ ተቀብለው በርካቶች ወደ ሀገር ቤት ገብተዋል፡፡የለውጡ ስርነቀል ሂደት ከዚህ ይጀምራል፡፡ ይሁን እንጂ ዛሬም ጥቂት ሰዎችን በገንዘብ ገዝተው በማሰለፍ ንጹሀን ዜጎችን እየገደሉና እያስገደሉ በስርዓት አልበኝነት ለማተራመስ ቆርጠው የተነሱ ይገኛሉ፡፡ይሄን መታገስ አንችልም፡፡ ከጀርባቸው እነማን እንዳሉም ይታወቃል፡፡የሀገርና የሕዝብን ሰላም ለማረጋገጥ ሲባል የማያዳግም እርምጃ መወሰዱ ግድ ነው፡፡ ሰላምን የሚያውኩ ኃይሎችን እሹሩሩ ማለት አይቻልም፡፡

በአጠቃላይ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ በ100 ቀናት ውስጥ አያሌ የህዘብ ችግሮች ተፈትተዋል፡፡በእያንዳንዱ እርምጃ ለውጥ የሚሹ የማህበረሰብ ክፍሎችም አያሌ ተስፋዎች ሰንቀዋል፡፡ በተጨማሪም ቀድሞ ያልታዩ ተአምራዊ ተደርገው ሊገለጹ የሚችሉ ለውጦችና የለውጥ እርምጃዎች ተካሂደዋል፡፡

ከጎረቤት ሀገራት ጋር ቀድሞ የነበረን ግንኙነት በጠንካራ መሰረት ላይ እንዲቆም አስችለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡ በ100 ቀናት ውስጥ በሀያና ሰላሳ አመታት የማይሰሩ፣ የማይሞከሩና የማይገመቱ  ስራዎችን ፈጽመዋል፡፡ የኢትዮጵያና የኤርትራን የድንበር ጦርነትና ውዝግብ፣ የሕዝቡን መሰቃየትና ችግር ከግምት ውስጥ በማስገባት ለኤርትራ መንግሰት የቀረበው የሰላም ጥሪ ተቀባይነት አግኝቶ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ አስመራን ሲጎበኙ እጅግ ደማቅ፣ ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡ልዩ ነበር፡፡

ሕዝቡ ከወንድሙና ቤተሰቡ ከሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ተለያይቶ መኖርን እንደማይፈልገው በከፍተኛ ናፍቆትና ደስታ በእልልታ አሳይቷል፡፡ይህን ችግር ለመፍታት አለም አቀፉ ማሕበረሰብ ብዙ የደከመ ቢሆንም በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የ100 ቀናት የአመራር ጊዜያት ችግሩ ተፈቶ ሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች በሲቃና በእንባ ተመልሰው በፍቅር ተገናኝተዋል፡፡የነገ ተስፋቸውም ብሩህ ነው፡፡

የኤርትራው ፕሬዚደንት ኢሳያስ አፈወርቂም በኢትዮጵያ ኦፊሴላዊ ጉብኝት ሲያደርጉ እጅግ ከፍተኛና ደማቅ የሆነ የሕዝብ አቀባበል ተድርጎላቸዋል፡፡ፕሬዚደንት ኢሳያስ የኤርትራና የኢትዮጵያን ሕዝብ የተለያየ አድርጎ የሚያስብ እሱ ሞኝ ነው ብለዋል፡፡ ከኤርትራ ጋር በተፈጠረው ሰላማዊ ግንኙነት ድንበሮቻችንና መንገዶቻችን ለሁለቱም ሕዝቦች ክፍት ይሆናሉ፡፡የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

ወደቦችን መጠቀም እንችላለን፡፡ ጥንትም በብዙ መልክ አንድ የነበርን፣ የተዋለድን፣ የተጋባን፣ በደምና አጥንት የተሳሰርን፣  በአጠቃላይ በርካታ የጋራ ታሪክ ያለን ሕዝቦች ነን፡፡ ወደነበረንበት ቤተሰባዊ ፍቅር የመመለሻው ወቅትም አሁን ነው ሲሉ ሁለቱም መሪዎች መልካም ግንኙነታቸውን አወድሰዋል፡:

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy