Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለሠላም አውድ እንትጋ!

0 491

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለሠላም አውድ እንትጋ!

አባ መላኩ

ስለ ልማት ከመጨነቅ ስለዕድገትና ብልፅግና ከመጠበብ በፊት የሠላም መረጋገጥ ዋስትና ሊያገኝ ይገባል። ሠላም ከሌለ ምንም ነገር የለም። ሰርቶ መለወጥ፣ ወጥቶ መግባት፣ ጎጆ ቀልሶ ወልዶ መሳም የሚቻለው ሁሉም የሚያምረው ሠላም ሲኖር ነው። እናም ሁሉም ዜጋ ስለ አገሩ ሠላም ይበልጥ ማሰብ፣ መጠበብና መጨነው ይኖርበታል።   

ከሁሉ ከሁሉም በላይ የሰው ልጅ በህይወት ለመኖር ቅድሚያ የሠላሙ ባለቤት መሆን ግድ ይለዋል። የሰው ልጅ ስለ ሌላው መሠረታዊ መብቶቹ ከማሰላሰሉ በፊት ስለ ሠላሙ መስፈን መጨነቅ ይኖርበታል።

ሠላም ከሌለ ምንም ነገር የለም። የሠላም ጉዳይ ለድርድር አይቀርብም። ሠላም ከሌለ የትኛውም የኅብረተሰብ ክፍል የሚመኘውን ከዳር ለማድረስ ብሎም ተጠቃሚነቱን ለማሳካት አይቻለውም። ሠላም ከሌለ ልማትን ለማስፋፋት ይሁን ዴሞክራሲን ለማበልፀግ ሆነ ለማረጋገጥ ከቶ አይቻልም። ሠላም በሌለበት ከእነዚህ መሠረታዊ መብቶች ባሻገር ዋነኛውና በህይወት የመኖር ዋስትና ሊኖር አይችልም።

በእርግጥም ሠላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ አይነጣጠሉም። ሠላም ከሌለ ስለ ልማትና ዴሞክራሲ አይታሰብም። እንደ ኢትዮጵያ ያለች ከድህነት ለመውጣት የምትታትር አገር ሠላምና መረጋጋቷን ማስጠበቅ ወሣኝ ተግባሯ ይሆናል።

ለአንድ አገር ልማት ሆነ ዕድገት ሠላም ከምንም በላይ የገዘፈ ዋጋ አለው። ይህ  አያጠያይቅም። እንደ እውነቱ ከሆነ የሠላም ዋጋ በምንም ዓይነት ምድራዊ ዋጋ አይለካም።   

የኢትዮጵያ ህዝቦች ሠላም ለማስፈን በእጅጉ ታግለዋል። ሠላምን ጨምሮ የረዥም ዓመታት ጥያቄያቸው የነበሩትን ልማትና ዴሞክራሲን እውን ለማድረግ በብርቱ ታግለዋል። ህይወት ገብረዋል፤ አካል ሰውተዋል። በጥቅሉ አያሌ መስዋዕትነቶችን ከፍለዋል። እንደሚታወሰው የኢትዮጵያ ህዝቦች በቀደምት ሥርዓቶች በርካታ ግፎች ተፈጽመውባቸዋል። በከፈሏቸው መስዋዕትነቶች ያን ሁሉ በደል ሽረዋል።   

 

መንግሥትና ሕዝብ እጅ ለእጅ ተያይዘው በርካታ ቁምነገሮችን ሊከውኑ የበቁት ሠላምና መረጋጋት ለአንድ አገር ብልጽግና ያላቸውን ፋይዳ በመገንዘብ ነው። በመሆኑም በመላ አገሪቱ ያለውን አንጻራዊ ሠላምና መረጋት አሁን ካለው በላይ ይበልጥ አስተማማኝ ለማድረግ በሚካሄደው ጥረት ሁሉም የየድርሻውን ሊወጣ ይገባል።  

የኢትዮጵያ ሕዝቦች በሁከትና ግጭቶች በሚፈጠሩ አለመረጋጋቶች የተነሳ የተቋደሱትን ሠላም ብሎም የተጎናፀፉት ልማትና የተያያዙት የዴሞክራሲ ጉዞ የኋሊት እንዲቀለበስባቸው አይሹም። ይህ በመራራ ትግላቸው የተጎናፀፏቸው ድሎች እንዲጓተቱባቸው አይፈቅዱም። የሠላምን ዋጋ ጠንቅቀው ያውቃሉና በዚህ መሠረታዊ ጉዳይ ላይ አይደራደሩም።

የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ያለፈውን ዓይነቱን የሰቆቃ ህይወት መምራትን አይፈቅዱም። የጥይት አረሮች ድምጾችን ማዳመጥ አይመርጡም። ቀደም ባሉት ዓመታት የነበሩት መጥፎ ትውስታዎች በሠላም ትሩፋቶች ተተክተዋል። ይህ መልካም ሁኔታ የኋሊት እንዲቀለበስ አይሹም። የኢትዮጵያ ሕዝቦች አትኩሮታቸውን ዛሬ በልማትና በዴሞክራሲ ባህል ግንባታቸው ላይ አኑረዋል። በተገኘው አስማማኝና ዘላቂ የሠላም ቁመና ታጅበውም ህዳሴ እውን ለማድረግ እጅ ለእጅ ተያይዘዋል። በሠላማቸውና በመረጋጋታቸው ከፍታቸውን ለማረጋገጥ ተዘጋጅተዋል። እናም እዚህም ሆነ እዚያ ይህን የሠላምና የመረጋጋት መንገድ ለመዝጋት የሚፈልጉ የውስጥም ይሁን የውጭ ኃይሎችን ጨርሶውኑ አይታገሷቸውም።  

በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች ተፈጥሮ የነበረው ግጭት በአሁኑ ወቅት በሕዝቡ፣ በፌዴራልና በክልል መንግሥታት የጥምረት ሥራዎች አንጻራዊ በሚባል ደረጃ  በቁጥጥር ሥር ውሏል። በአንዳንድ አካባቢዎች ቀሪ ሥራዎች ቢኖሩም ይህንን በማስፈፀም ሂደት ላይ የህግ የበላይነት ከምንም በላይ መከበር ይኖርበታል።

ዜጎች በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉትን የሠላምና የመረጋጋት ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ተባብረው በመሥራት ላይ ይገኛሉ። በእርግጥም በየትኛውም ሥፍራ ሠላም እንዲሰፍን ከተፈለገ ያለ ሕዝብ ተሳትፎ ውጤት አይመጣም – የሠላምን ዋጋ ዋነኛ መዛኙ ኃይል ሕዝብ ነውና። ሕዝብ የሠላሙን ዋጋ የሚተምነው ጥቅሙን ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ነውና።

ሠላም የሚተመንበት አሊያም የሚሰፈርበት ልኬት የለውም።  ሠላም ዋጋው እጅግ የገዘፈ ነው። የአንድ አገር ሠላም የሕዝቧቿ ሠላም ነው። በመሆኑም ዜጎች መብትና ግዴታዎቻቸውን ሲያውቁና ሌላውን ለማስተማር ሲነሳሱ የአገር ሠላም ይረጋገጣል። ልማትና ዕድገትም ይደረጃሉ፤ ዴሞክራሲያዊ እሴቶችም በዚያው ልክ ያብባሉ።

እዚህ ላይ ሁሉም ወገን ሊያውቅ የሚገባው ቁም ነገር አለ። ይኸውም የአገርን ሠላምና ደህንነት መጠበቅ የመንግሥት ኃላፊነት ብቻ አለመሆኑን ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ዋነኛው ተዋናይ የሆነው የአገሪቱ ሕዝብ ነው።  ሕዝቡ በያለበት ሆኖ ሠላሙን ከጠበቀ ሠላምን ለማደፍረስ የሚሯሯጥ የትኛውንም ኃይል በቁጥጥሩ ሥር ማድረግ ብዙ አያዳግትም።

የሠላምን ምንነት የሚገነዘብ ሕዝብ ውስጥ ፀረ ሠላምነትን ማንገስ በእጅጉ ይከብዳል።  ሕዝብ የሚገለገልባቸውን ማንኛውንም ዓይነት ንብረቶችንና የግለሰቦችን ሀብት ለማውደም አይቻልም — ሕዝቡ በራሱ ይጠብቃቸዋልና። ለፀረ ሠላም ኃይሎች ከንቱ ፕሮፖጋንዳ የማይፈታ የትኛውም ዜጋ ንብረቱ በምንም ዓይነት መንገድ እንዲወድም አይሻም።

በተለይ ወጣቱ እንደ ማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል ከሠላም ተጠቃሚ መሆን ይሻል። ተጠቃሚነቱን ለማሳካትም በህጋዊና ህጋዊ መንገድ ብቻ ነው መንቀሳቀስ የሚኖርበት። በእርግጥ ወጣቱ ትውልድ በአገሪቱ ውስጥ ከተገኙት የልማት ውጤቶች አቅም በፈቀደ መጠን ተጠቃሚ መሆን ይኖርበታል። ተጠቃሚነቱ ሊረጋገጥ የሚችለው ደግሞ በሠላማዊና ህጋዊ መንገድ ብቻ ነው። በሁከትና ብጥብጥ ምንም ነገር ማሳካት አይቻልም።

ለዴሞክራሲ ግንባታም ሆነ ለልማት መጠናከር ወሣኝ የሆነውን ሠላምን በጋራ ለማቆም መንግሥትን ጨምሮ ሁሉም አካል ሠላማዊ አካሄድን መምረጥ ይኖርበታል። ሠላምና ልማት ወዳዱ የኢትዮጵያ ሕዝብ የፀረ ሠላም ቡድኖችና ጥቅመኞች እኩይ ሴራዎቻቸውን ጠንቅቆ ያውቃል። ሠላሙን ለማናጋትና በአገሪቱ እየተመዘገበ ካለው ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት በየደረጃው ተጠቃሚ እንዳይሆን የሚሹ አካላትን ከቶ አይፈልጋቸውም። ዛሬም ለሠላሙ ሲል በጽናት ይታገላቸዋል።

ከሠላም በተቃራኒ ቆመው በአገር ላይ ችግር ለመፍጠር የሚባጁ ኃይሎች ፍላጎታቸው የሠላም አይደለም፤ የብጥብጥና የሁከት እንጂ። ዕቅዳቸው የመብት ተጠቃሚነት ሳይሆን የመብት አዋኪነትና የኪራይ ሰብሳቢነት ነው። ዓላማቸው ሁሉም በየደረጃው የሚጠቀምበትን ሁኔታ ለመፍጠር ሳይሆን ሲያራምዱት የከረሙት ጥቅም እንዳይስተጓጎልባቸው ነው። ፀረ ሠላም ቡድኖቹ ፍላጎታቸው የመከባበርና የመቻቻል፣  ስሜታቸው የነጻነት መንገድን መያያዝ ሳይሆን ሁከትና ግርግር መፍጠርን ነው። ይህ ሁሉ ከኢትዮጵያ ሕዝብ የሚሰወር አይደለም። የተገኘው ሠላምና ልማት ብሎም የተያያዝነው የለውጥ ጉዞ በሠላምና መረጋጋት የመጣ መሆኑን ይበልጥ በመረዳት መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሠላም አውድ መትጋት ይገባል።

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy