Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሰላማዊነት እና ህጋዊነት

0 253

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሰላማዊነት እና ህጋዊነት

                                                           ሶሪ ገመዳ

የሰላም ጠባቂ ዋነኛው ኃይል ህዝብ ነው። በየትኛውም አካባቢ የሚፈጠር ግጭት በአስተማማኝ ሁኔታ መቆጣጠር የሚቻለው ሕብረተሰቡ የሰላም ዘብ ሆኖ ከጸጥታ ኃይሉ ጎን ተሰልፎ ሲሰራ መሆኑ ግልጽ ነው። የፀጥታ ኃይሉ ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት የሚሰራው ከህዝብ ጋር በመቀራረብ ስለሆነ ይህም ጸጥታን የማስከበር ውጤታማነት የማይተካ ሚና ያለው ነው።

ስለሆነም በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች እየታየ ያለው ስርዓት አልበኝነትና የህግ ጥሰት ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም። በአንዳንድ አካባቢዎች አልፎ አልፎ አመራሮች ይነሱልን በሚል ቤቶቻቸውን፣ የመንግስት ተቋማትን ማውደምና መዝረፍ የለየለት ሥርዓተ አልበኝነት እንዲሁም የትኛውንም ወገን የማይጠቅም ተግባር ነው።

ይህን መሰሉ ህገ ወጥ አካሄድ የህብረተሰቡን ጥያቄ ሊመልስ የሚችል አይደለም። የግለሰቦችንና የመንግስት እንዲሁም የህዝብ ንብረት ማቃጠልና መዝረፍ ለየትኛውም ህብረተሰብ ጥያቄ መልስ አሊያም ለችግሮች መፍትሔ ሊሆኑ አይችልም።

ህብረተሰቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎችና ችግሮች ካሉም ሊፈቱ የሚችሉት በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ ሲቀርቡ ብቻ ነው። ምክንያቱም ሰላማዊነትንና ህጋዊነትን ያልተከተሉ ጥያቄዎች ጥፋታቸው እንጂ ልማታቸው ስለማይታወቅ ነው። ስለሆነም ጥያቄዎቻችን ሰላማዊነትንና ህጋዊነትን የተላበሱ መሆን ይኖርባቸዋል።

ሰላማዊነትና ህጋዊነት ለአገርም ይሁን ለህዝብ እጅግ ጠቃሚ ነው። ሰላማዊ መሆን አገር በሰለጠነ አኳሃን እንድትመራ እገዛ ያደርጋል። ሰላማዊ የሆነ ማህበረሰብ ልማትንና ዴሞክራሲን ሊያፋጥን ይችላል።

ኢንቨስትመንትን በመሳብም የስራ ዕድል ሊያገኝ ይችላል። ማንኛውም ባለሃብት ወደ አንድ አገር ውስጥ ለመምጣት ሲያስብ በመጀመሪያ የሚያጣራው በዚያች አገር ያለውን የሰላም ሁኔታ ነው። አገሪቱ ሰላም ያላት ከሆነች የሚያፈሰው መዋዕለ ነዋይ አስተማማኝ መሆንና አለመሆኑን ያረጋግጣል።

ሰላሙ አስተማማኝ ከሆነ ምንም ዓይነት ገንዘብ ለማውጣት አይኑን አያሽም። ይህ ሁኔታም የዜጎችን የስራ ዕድል ያሰፋል። የዜጎች የስራ ዕድል መስፋት ማለት ደግሞ ተጠቃሚነታቸውን በማረጋገጥ የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ ያደርጋል። ስለሆነም ሰላም የግድ ያስፈልገናል። ሰላማዊነትን አጥብቀን መያዝ ይገባናል።

እንደሚታወቀው ሁሉ የኢፌዴሪ መንግስት በአገሪቱ መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ፣ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው የውጭ ባለ ሃብቶችን ለመሳብ የተለያዩ ማበረታቻዎችን በማመቻቸት በሩን ከፍት በማድረግና በተለያዩ አለም አቀፋዊ መድረኮች ተጨባጭ ሁኔታውን በማስረዳት ላይ ይገኛል።

በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ገፅታችንን በመገንባትና ዲፕሎማሲያችንን በማጠናከር ኢንቨስትመንት ይበልጥ እንዲስፋፋ እየሰሩ ነው። ከዚህ ቀደም ለኢንቨስትመንት ማነቆ የነበሩ ጉዳዩችን በመለየትና በሚያሰሩ ሁኔታዎች በመቀየር ምቹ ሁኔታን ፈጥረዋል።

ይህም በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በተለይም በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግና ኢንዱስትሪ ዘርፎች የተሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች ቁጥር በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል። በዚህም ሳቢያ አገራችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከነበረችበት የሰላም ችግር ተላቅቃ ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗን የተገነዘቡ በርካታ የውጭ ኩባንያዎችና ባለሃብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ ላይ ይገኛሉ።

በአሁኑ ሰዓት መንግስት ነፃ የመሬት አቅርቦት ማዘጋጀቱ፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን እየገነባ መሆኑ፣ የኢንቨስትመንት ቦታዎች በመንገድ እና በኤሌክትሪክ እንዲተሳሰሩ መደረጋቸው፣ የታክስ እፎይታ ጊዜ መኖሩ በርካታ የውጭ ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ ሰላማዊ ሁኔታ እንዲመጡ እያደረጋቸው ነው። ህብረተሰቡ ይህ የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዳይስተጓጎል ሰላማዊትን አጥብቆ መያዝ ይኖርበታል።

ያለ ሰለማዊነት ልማትን ማረጋገጥ ስለማይቻል በየትኛውም አካባቢ የሚገኝ የህበረተሰብ ክፍል ሰለማዊ መሆናችንን ዓለም እንዲያውቀው የማድረግ ሃላፊነት ተጥሎበታል። ዶክተር አብይ እያካሄዱ ባሉት የዲፕሎማሲ ስራ የዓለም የገንዘብ ተቋምንና የዓለም ባንክን የመሳሰሉ የልማት ደጋፊ ተቋማትን ጭምር እያግባቡ ነው።

ይህ ጠንካራ የተግባቦት ስራቸው ተጠናክሮ የፋይናንስ ተቋማቱ አገራችን የምትፈልገውን የገንዘብ መጠን እንዲሰጡን እኛም ሰላማዊ ሆነን መገኘት ይኖርብናል። ሰላማዊነታችን መልሶ የሚከፍለው ራሳቸንን ስለሆነ የሰላምን ነገር እንደ ነብር ጭራ አጥብቀን ልንይዘው ይገባል።

ከሰላማዊነታችን ጎን ለጎንም በህጋዊነት መመራት ይኖርብናል። እርግጥ ሰላማዊ ህብረተሰብ ህጋዊነትንም የተላበሰ ነው። ህጋዊነትን ለመፍጠር በቅድሚያ የህግ የበላይነትን ማክበር ያስፈልጋል። በስርዓት አልበኝነት የዜጎችን ህይወት ማጥፋት፣ ንብረታቸውን ማውደምና መቀማት እንዲሁም የመኖር ዋስታናቸውን የመንጠቅ ተግባሮች የህግ የበላይነትን የሚጻረሩ ናቸው።

የህግ የበላይነት በሌለበት ሀገር ውስጥ ማንኛውም ሰው በሰላም ወጥቶ ሊገባ አይችልም። መብት ሰጪዎችና ነሺዎች ጉልበተኞች ይሆኑና ስርዓት አልበኝነት ይነግሳል። ጉልበተኞቹም ሌሎች ዜጎችን እንዳሻቸው በማድረግ የባሪያና ሎሌ ስርዓት ይፈጥራሉ።

ስርዓት አልበኝነት ሲገነግንም ህግን አክብሮ የሚንቀሳቀስ ዜጋ አይኖርም። ሁሉም በየፊናው እየሮጠ የራሱን የበላይነት ለማስጠበቅ ለማረጋገጥ ይጥራል። ይህ ሁኔታም አንድን ሀገር የነበረበትን ሰላማዊ ምህዳር በማወክ በሁከት እንዲታመስ ያደርገዋል።

በሰላም ውስጥ ኖሮ ሀገርን ማበልፀግና ወደ ተሻለ ህይወት መረማመድ ያበቃለታል። እናም ይህን ሁኔታ ለመከላከልና ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የህግ የበላይነት መኖር የግድ ይላል።

ህገ መንግሰቱ ማንኛውም ሰው በህግ ፊት እኩል መሆኑን ይገልጻል። ማንኛውም ዜጋ አገሪቱ ያወጣችውን ህግ የማክበርና በእርሱም የመመራት ግዴታ አለበት። የዜጎች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በህግና ስርዓት የሚመራ ካልሆነ የትኛውም ወገን የመኖር ዋስትና አይኖረውም። ሁሉም ዜጋ የሚንቀሳቀሰው ህግ ባለበት አገር ውስጥ ስለሆነ ህገ ወጥነትንና ስርዓት አልበኝነትን ማራመድ አይችልም።

ስለሆነም የህግ የበላይነትን ለማስጠበቅ ሁሉም ዜጋ በሚደረገው ጥረት የበኩሉን ማድረግ አለበት። ሰላማዊነትን ባጠናከርን ቁጥር የህግ የበላይነትን እናስጠብቃለን። የህግ የበላይነትን ስናስጠብውም ሰላማዊ እንሆናለን። ሰላማዊነትና ህጋዊነት የማይነጣጠሉ ስለሆኑ ለሁለቱም መስራት አለብን።

   

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy