Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ስምምነቱ እና ውይይቱ

0 386

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ስምምነቱ እና ውይይቱ

ዳዊት ምትኩ

ሰሞኑን በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ የዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ሪም አል ሃሽሚ መካከል አዲስ አበባ ላይ ውይይት ተካሂዶ ነበር። ሁለቱ አካላት ስምምነት ላይም ደርሰዋል። በኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ በሪል ስቴት፣ በነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ ዝርጋታ እና በሪሶርት ኢንቨስትመንት ላይ ያተኮረው የሁለቱ ወገኖች ውይይት፣ በጉዳዩቹ ዙሪያ በጋራ ለመስራት ስምምነቶች የተደረሱበትም ነው። ይሀም በአራት ወራቶች ውስጥ ብቻ በተደረገው የማግባባት ስራ የኢንቨስትመንት እንዲነቃቃ ማድረጉን ያሳያል።

ከሁሉም በላይ የተባበበሩት አረብ ኢምሬትስም ሆኑ ሌሎች አገራት ከጥቂት ወራቶች ወዲህ ወደ አገራችን በመምጣት ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት መሻታቸው የወደፊት ተስፋችንን ስለተገነዘቡ ነው። በመሆኑም የተስፋችን መሰረት የሆነውና በህዝቡ የነቃ ተሳትፎ እየተከናወነ ያለውን ለውጥ መጠበቅ ያስፈልጋል።

ለዚህም ሰለማችንን አስተማማሽ ማድረግ ይኖርብናል። በተለያዩ አካባቢዎች አልፎ አልፎ የሚታዩ ግጭቶችና ስርዓት አልበኝነት መቆም ይኖርባቸዋል። ሰላምና የህግ የባይነት ከሌለ የኢንቨስትመንት ፍሰቱ ተጠናክሮ ሊቀጥል አይችልም። ስርዓት አልበኝነት በሚስተዋልበት ቦታ የትኛውም ኢንቬስተር ገንዘቡን አውጥቶ ለመስራት አይፈልግም። ይህም ከኢንቨስትመንት ማግኘት የሚገባንን ጥቅሞች የሚገድብ ይሆናል።

እርግጥም ሰላምና የህግ የበላይነት በሌለበት ቦታ ስርዓት አልበኝነት ይገነግናል። መብትም አይከበርም። መብት ሰጪና ነሺዎች ጥቂት ስርዓት አልበኞች ይሆናሉ። ጉልበት ያለው የህግ አስፈፃሚ ይሆናል።

በሰላም ወጥቶ የመግባት ጉዳይም በህግና በስርዓት ሳይሆን በስርዓት አልበኞች የሚወሰን ይሆናል። ስርዓት አልበኝነት እየደረጀም የብዙሃኑ ህዝብ መብቶች አደጋ ላይ ይወድቃሉ። ይህም መንግስት ባለበት አገር ውስጥ ለበጎ ዓላመ የሚሰማሩ ግለሰቦች የጥቃት ሰለባ እንዲሆኑ ያደርጋል።

የህግ የበላይነት ስለማይከበርም ጉልበተኞች ከሚፈልጉት ጊዜና ዕውቅና ውጭ ማንም ሰው መነቃነቅ አይችልም። ህግ የበላይነቱን ስለሚነጠቅም በእነዚህ ሃይሎች እጅ ይወድቅና ሁሉም ነገር ምስቅልቅሉ ይወጣል። ሃይል ያለው ሁሉ በህገ ወጥ መንገድ ሰላምን አስጠባቂ ነኝ ሊል ይችላል። የደቦ ፍትህም ይከሰታል።

ህግ እየተጣሰ ጥቂቶች ራሳቸው ከሳሽ ራሳቸው ፍርድ ሰጪዎች ይሆናሉ። እንዲህ ዓይነት ክስተት ባለበት አገር ውስጥ ኢንቨስትመንት ሊስፋፋ አይችልም። የህዝቡ ተጠቃሚነትም ይቀዛቀዛል። ስለሆነም ህብረተሰቡ ለውዩን ለአደጋ የሚያጋልጡ ስርዓት አልበኝነትን መታገል ይኖርበታል።

እርግጥ ህዝቡ ከሁሉም ነገር በላይ ለአገራዊ ሰላምና መረጋጋት ህዝቡ ቅድሚያ ትኩረት መስጠት አለበት። ለሰላምንና መረጋጋትን ቅድሚያ አጀንዳ ማድረግ ካልቻልን ምንም ዓይነት ውጤት ማግኘት አይቻልም። ኢንቨስትመንትን ማስፋፋትም ፈተና ይሆናል። መንግስት ኢንቨስትመንትን ለማምጣት የሚያደርጋቸውን ጥረቶች ልንደግፍ አንችልም።

እንደሚታወቀው ሁሉ መንግስት በአጭር ጊዜ ውስጥ የአገር ውስጥን ባለሃብቶችን ከውጭ ባለሃብቶች ጋር በማቀናጀት ለመፍጠር እየቻለ ነው። የገበያ ትስስር በመፍጠርም ምቹ የኢንቨስትመንት መሰረትን እየጣለ ነው።

ከእነዚህ ውስጥ የወጪ ንግድ የብድር ዋስትና ሥርዓት መተግበር፣ የውጪ ምንዛሪ ተመን ማስተካከልና የምንዛሪ ዋጋው በገበያ እንዲወሰን ማድረግ እንዲሁም የመንግስት ተቋማትን በሙሉና በከፊል ወደ ግል ባለሃብቶች ለማዞር ያለው ፍላጎት ተጠቃሽ ናቸው።

በተጨማሪም የኤክስፖርት ምርትን ከቀረጥ ነፃ ማድረግ፣ ለኢንቨስትመንት ከቀረጥ ነፃ የሚገቡ የካፒታል ዕቃዎችና ግብዓቶች ያለ ቅድመ ሁኔታ የሚገቡበትን ዕድል የመፍጠር ብሎም ባለሃብቶቹ ለስራቸው የሚሆን መሬት በሊዝ እንዲያገኙ መደረጉ ተጨማሪ አመቺ ሁኔታዎች ናቸው። እነዚህ በመንግስት በኩል አቨስትመንትን ለማበረታታት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች የውጭ ባለሃብቶች ሀገራችን ላይ ዓይናቸውን እንዲጥሉ ያደረጉ ተግባራት ናቸው።

መንግስት የተከተለው ኢንቨስትመንትን የመሳብ መንገድ የአገር ውስጥ ባለሃብቶችን የሚያሳድግና የስራ ዕድልንም የፈጠረ የሚፈጥር ነው። እንዲሁም የአገራችንን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት እንደ የአገር ውስጥ ባለሃብቶች ሁሉ ተመጣጣኝ የውጭ ምንዛሬ ግኝት ማምጣት የሚችሉ የውጭ ባለሃብቶችም ወደ አገራችን መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ያስቻለ ነው። ይህ የመንግስት ጥረት በዜጎች መደገፍ አለበት።

በመሆኑም በአሁኑ ሰዓት በአንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉትን የስርዓት አልበኝነት ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ ህዝቡ ከፀጥታ ሃይሎች ጋር ተባብረው መስራት አለበት። በየትኛውም አገር ውስጥ እውን እንዲሆን የሚፈለግ ሰላም ያለ ህዝቡ ተሳትፎ ምንም ዓይነት ውጤት ሊያመጣ አይችልም። የሰላም ዋጋን ዋነኛ መዛኙ ኃይል ህዝብ ነው። እናመ ህዝቡ ሰላምን የሚያሳጡ የስርዓት አልበኝነት ችግሮች እንዳይፈጠሩ ተግቶ መስራት ይኖርበታል።

እርግጥም ሰላም ለአንድ አገር ልማትና ዕድገት ሰላም ከምንም በላይ የገዘፈ ዋጋ ያለው መሆኑ አያጠያይቅም። ሰላም የሚተመንበት አሊያም የሚሰፈርበት ልኬት የለውም። ከግለሰብ የነገ ማንነት ህልም ጀምሮ እስከ የአገር ህዳሴ ዕውን መሆን ድረስ ሰላም ዋጋው እጅግ የገዘፈ ነው። የዚህች አገር ሰላም የህዝቧቸ እንደመሆኑ መጠን ህዝቦቿ ለሰላማቸው እንቅፋት የሚሆኑ ጉዳዩችን በየአካባቢያቸው ማስወገድ አለባቸው።

ዜጎች መብትና ግዴታዎቻቸውን ሲያውቁና ሌላውን ለማስተማር ሲነሳሱ የአገር ሰላም ይረጋገጣል። ልማትና ዕድገትም ይደረጃሉ፤ ዴሞክራሲያዊ እሴቶችም በዚያው መጠን እያበቡ ይሄዳሉ። ስርዓት አልበኝነት መብትና ግዴታን የማያውቅ ተግባር ነው። ይህን ችግር በየአካባቢው መፍታት ለስርዓት አልበኝነት የማይመች ይፈጥራል። ለውጡንም ይጠብቃል።  

እርግጥ ህዝቡ በያለበት ሆኖ ሰላሙን ከጠበቀ በስርዓት አልበኝነት ሰላምን ለማደፍረስ የሚሮጥ የትኛውም ሃይል አቅም ሊኖረው አይችልም። የሰላምን ምንነት የሚገነዘብ ህዝብ ውስጥ ስርዓት አልበኝነትን ማንገስ አይቻልም።

በመሆኑም ህዝብ የሚጠቀምባቸውን ማንኛውንም ዓይነት ንብረቶችንና የግለሰቦችን ሃብት ለማውደም አይበቃም፤ የደቦ ፍርድም አይፈፀምም። እናም እንዲህ ዓይነቱን ሰላምን የሚያደፈርሱ ጉዳዩችን መፍታት ከተቻለ  እንደ አረብ ኢምሬቶች ሁሉ በርካታ የውጭ ባለሃብቶች ወደ ሀገራችን እየመጡ ኢንቨስትያደርጋሉ። ስለሆነም በጠቅላይ ሚኒስትራችንና በአረብ ኢምሬቶች ልዐካን መካከል የተደረገው ውይይትና ስምምነት የሚያስረዳን ነገር፤ ነገም ሌሎች ባለሃብቶች ወደ አገራችን እንዲመጡ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባ ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy