Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ስንዴውን ከእንክርዳዱ…

0 269

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ስንዴውን ከእንክርዳዱ…

ዳዊት ምትኩ

ባለንበት ወቅት በማህበራዊ ሚዲያ አማካኝነት የሚሰራጩ መረጃዎችን ምንነት እንዲሁም ስለ የመረጃዎቹን ትክክለኛነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል። መረጃዎቹን አስመልክቶ መወሰድ ስለሚኖርባቸው ጥንቃቄዎችም መነጋገር ይገባል። በማህበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉ መረጃዎች ሁሉ ትክክል ናቸው ማለት አይቻልም። የራሳቸው ፍላጎት ያላቸው አካላት የተዛቡ መረጃዎችን ይለቃሉ። ስለሆነም እንደ ፌስ ቡክ ባሉ ማህበራዊ ሚዲያዎች የሚተላለፉ መረጃዎችን ምንነትና ትክክለኛነት እያጣሩ መጠቀም ተገቢ ነው።

ዛሬ መረጃዎቹ የተለያዩ የፎቶ ሾፕ ጥበቦችን በመጠቀም በሌሎች አካባቢዎች የተፈጸሙ ድርጊቶችን በእኛ አገር እንደተፈጠሩ አስመስሎ በማቅረብ ህዝብን እያደናገሩ ነው። በአሁኑ ሰዓት የለውጥ አደናቃፊ ሃይሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ሃሰተኛ አካውንቶችን በመፍጠር የሚያቀርቧቸው መረጃዎች ሆን ተብለው ሃይማኖታዊ እና የብሄር ግጭቶችን ለማቀጣጠል ያነጣጠሩ ናቸው። በመሆኑም ህብረተሰቡ ስንዴውን ከእንክርዳዱ በመለየት በሚተላለፉ መረጃዎች ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል።

የተገኘውን መረጃ ሁሉ ሳናጠራ እንዳገኘን ከተጠቀምነው ለአደጋ ማጋለጡ አይቀርም። የመረጃው ምንጭና መረጃው የተለቀቀበትን ምክንያት ሰከን ብሎ ማገናዘብ ያስፈልጋል። መረጃው አሉባልታ ነው ወይስ ተዓማኒ? ብሎ በመጠየቅ በይዘቱ ላይ መወያየት ታስፈልጋል።

በተለይም ወጣቶች የተለቀቀው መረጃ የማን ነው? ለምን ዓላማ ነው የተለቀቀው? የመረጃው ባለቤት ማነው ብለው ማጣራት ይኖርባቸዋል። ይህም አሉባልታን ከትክክለኛ እውነታ ለመለየት ይረዳናል። ካልሆነ ግን መረጃው ወደ ጥፋት መንገድ የሚመራን ይሆናል።

በቅርቡ በባሌ ጎባ ላይ በውሸት መረጃ የተቀናበረ ወሬ የተፈጠረው ችግር ግልጽ ነው። ይኸውም አሉባልታው ሃይማኖትንና ብሔርን ሆን ብሎ በማንሳት እንዲሁም የፎቶ ሾፕ ጥበብ በመጠቀም ከዓመታት በፊት በሌላ አገር የተፈጸመን ተግባር የኢትዮጵያ አድርገው በማቅረብ ህዝብን ከህዝብ ጋር ለማጋጨት የተደረገ ሙከራ ነው። በኢትዮጵያ ሱማሊ ክልልም ነገሮችን በማጋጋልና ከእውነታው ያፈነገጡ ጉዳዩችን በፌስ ቡክ ላይ የመለጠፍ ስራዎች ሲከናወኑ እንደነበር ይታወቃል።

በሌሎች አካባቢዎችም ተመሳሳይ የሆኑ ጉዳዩችን በማስተላለፍ አንዱን ሃይማኖት ከሌላው ጋር ለማጋጨት፣ ለዘመናት አብሮ የኖር የነበረ ህዝብን ለመለየት ጥረት ተደርጓል። እየተደረገም ነው። ይህን እውነታ ህዝቡ ሰከን ብሎ በማሰብ የመረጃዎቹን ትክክለኛነት ማረጋገጥ ይኖርበታል።  

በመሆኑም ለውጥ አደናቃፊውን ከለውጥ ገንቢው መለየት ይገባል። የለውጥ አዳቃፊው ሀገር ትጥፋ ህዝብም ይለቅ የሚል ህሳቤም የተጠናወተው ነው። የህዝቦች አንድነትን ለማበላሸት የሚሰራ ነው። ሳይሆን የግዛት አንድነት የሚያሳስበው ኃይል ነው። የዚህ ዓለም ዕውነታ የሆነውን ብዘሃነትን ተቀብሎና ተቻችሎ መኖር የእሬት ያህል የሚጎመዝዘው ኋላ ቀር አሳቢ ነው።

ፍላጎቱ ለውጥን ማደናቀፍ በመሆኑም ለእያንዳንዷ ድርጊት አቃቂር ሲያወጣ የሚውል ነው። አንዱን ብሬር ከሌላው ጋር ለማጋጨት ስሙን እየቀያየረ ይሰብካል። ትናንት የአንዱ ብሔር ጠበቃ መስሎ መረጃ የለቀቀን ግለሰብ በሌላ ጊዜ ደግሞ ያንን ብሔር ሲያብጠለጥል ይውላል። ቋሚ ፍላጎት የለውም። ፍላጎቱ በሃይማኖትም ይሁን በብሔር አንዱን ከሌላው ጋር ማባለት ነው።

አንዱ ብሔር ሌላውን በጥላቻና በጥርጣሬ እንዲመለከተው ዕድሉ ሲመቻችለትም እንዲያጠቃና እንዲያጠፋው ተግቶ ይሰራል። በአኩልነት ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ አንድነትን አይቀበልም። ምክንያታዊ ሳይሆን ሃይማኖትንና ብሔርን የሚቀሰቅሱ መረጃዎችን ቶሎ ቶሎ ይለቃል።

እነዚህ አካላት ጥቅማቸው የተነካባቸው ሃይሎች በመሆናቸው ገደብ የሌለው የሥልጣን ጥማቸን ለማርካት በህዝቦች መካከል ግጭትና መተላለቅን የሚፈጥሩ መርዘኛ መረጃዎችን ይረጫሉ።

አንድን መጠነኛ ግጭት ይቀሰቅሱና በል ሲላቸውም ምንም ያያውቁ ወጣቶችን በገንዘብ በመግዛት የሰው ልጅ ህይወት እንዲጠፋ ያደርጋሉ። መልሰው አንዱ በሌላው ላይ እንዲነሳሳ በፌስ ቡክ ላይ ተግባራቸውን መልሰው ይለጥፋሉ። የሚለጠፈው ተግባርም ዜጎችን ሊያስቆጣ እንዲችል አድርገው ያቀነባብሩታል።

የትላንት ገዥ መደቦች በህዝቦች ላይ የፈፀሙትን በደል ሁሉ የአንድ ብሔረሰብ አባላት እንደፈፀሙት አድርጐ የጥላቻ መርዝ መርጨትና አንዱ ብሔር በሌላኛው ላይ ተነሳስቶ እልቂት ሲፈጥር ማየትም ሌላኛው ተግባራቸው ነው፤ ለውጥ አደናቃፊዎቹ።

‘እገሌ የተባለውን ብሔረሰብ እንዲህ እናድርገው ወይም እገሌ ሃይማኖት እንዲህ ስላደረገህ አንተም እንዳትተወው’ የሚል የማያቋርጥ ስብከታቸውን ያሰማሉ። ሃቁ ግን በዚያ ብሔር ውስጥ ጥቂት ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ችግር መፍጠራቸው ነው። እነዚህ አካላት ግን በየፌስ ቡኩ ብሔርን ከብሔር ጋር ለማጋጨት ይሰራሉ።

በወጣቶች እጅ ፍም እሳትን ለመያዝ የሚፈልጉት እነዚህ ለውጡ ጥቅማችንን ነክቶታል የሚሉ ሃይሎች “አኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” የሚል ብሂልን በመከተል እሳት ለመለኮስ የተሰለፉ መሆናቸውን ህብረተሰቡ ሊገነዘብ ይገባል። በተገኘው ህዝባዊ አጋጣሚ ሁሉ ግጭቶች እንዲቀሰቀሱ በማድረግ ለውጡ ልዕልና እንዳይኖረው ይሰራሉ።

ስለሆነም በተለይ ወጣቶች የእነዚህን ሃይሎች በተለይም በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚያስወሯቸውን አሉባልታዎችን መለየት ይኖርባቸዋል። ፌስ ቡክን የመሳሰሉ ሚዲያዎች የጠቃሚነታቸውን ያህል ጥፋታቸውም እየጎላ መጥቷል።

የውሸት ወሬዎች እየተቀነባበሩባቸው የሚተላለፉባቸው መገናኛዎች እየሆኑ ነው። ትክክለኛውን መረጃ ከትክክለኛ ምንጭ ማግኘት ያስፈልጋል። ወጣቶች የተፈበረኩ መረጃዎችን ከትክከለኛው ለይተው ማወቅ አለባቸው።

ወጣቶች በምንም ዓይነት ሁኔታ ለውጡን ለመቀልበስ የሚፈልጉ ሃይሎች በሚያስወሩት አሉባልታ ውስጥ መግባት አይኖርባቸውም። ወጣቶች ለለውጡ የተጉትን ያህል ወደ ልማትም ፊታቸውን ማዞር አለባቸው።

ሁሌም በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚተላለፉት መረጃዎች ትክክል ናቸው ወይ? ብለው ራሳቸውን መጠየቅ አለባቸው። ደግሞ ደጋግሞ ማጣራት ያስፈልጋል። ትክክለኛ መረጃን ለማግኘት ጥንቃቄ በማድረግ ስንዴውን ከእንክርዳዱ መለየት አለባቸው። ወጣቶች ይህን ካደረጉ ከስህተት ይድናሉ። የሚወስዷቸውም እርምጃዎች ሚዛናዊ ይሆናሉ። ይሀም በሁከትና በብጥብጥ ውስጥ እንድንሆንና በጀመርነው የለውጥ ሂደት እንዳንጓዝ የሚያደርጉንን የለውጥ እንቅፋት ሃይሎች የሚመክት ተግባር ይሆናል። የተዛቡ መረጃዎችን በመለየት ፊታቸውን ወደ ልማትና ዴሞክራሲ ግንባታ እንዲያዞሩም ያደርጋቸዋል።

 

  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy