Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ስኬቶቹና ጥቅሞቻቸው

0 334

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ስኬቶቹና ጥቅሞቻቸው

                                                      ሶሪ ገመዳ

ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ ተቋማት፣ ከተለያዩ አገራት መንግሥታት፣ ከአጎራባች አገራት ጋር እያደረገች ያለችው ግንኙነቶች እንደ አገር ተጠቃሚነታችን የሚያረጋግጡ ናቸው። በተለይም በዓለም አቀፍና በአህጉራዊ እንዲሁም በቀጠናዊ ጉዳዮች እየወሰደቻቸው ያሉት ዲፕሎማሲያዊ እርምጃዎች ለውጡን የሚደግፉና ወደፊት የሚያራምዱት ናቸው።

እነዚህ የአገራችን እንቅስቃሴዎች በህዝቡ የነቃ ተሳትፎ እየተካሄደ ላለው የለውጥ ሂደት ስኬት ያላቸው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። እንዲሁም ለአገራችን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስተጋብሮች የሚያስገኙት ውጤት ዘርፈ ብዙ ነው።

ምንም እንኳን አዲሱ አመራር ለለውጡ ስኬት በመትጋት ላይ የሚገኝ ቢሆኑም፣ የዲፕሎማሲውን እንቅስቃሴ በህዝቡ ተሳትፎ ወደ ላቀ ከፍታ ማሻገር ያስፈልጋል። ስለሆነም ሁሉም ዜጋ የአገሩ አምባሳደር ሆኖ መስራት ይጠበቅበታል። ይህን ሲያደርግም ለውጡ በታለመለት መንገድ እንዲሄድ ማድረጉ አይቀርም።

አገራችን እንደ ሌሎቹ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ሁሉ በእርስ በርስ ግጭትና ስር በሰደደ ድህነት ውስጥ መኖሯ ይታወቃል። ከዚያም የህዝቡን ኑሮ በሚፈለገው መጠንም መለወጥ አልተቻለም። ሆኖም በጥቂት ወራቶች ውስጥ ሁኔታዎች ተለዋውጠዋል። ግና ምስጋና ለውጡን ለማምጣት መስዋዕት ለሆኑ ወገኖቻችን ይሁንና አዲሲቷ ኢትዮጵያ ገፅታዋን በመለወጥ ላይ ትገኛለች።

በዶክተር አብይ አህመድ የሚመራው የለውጥ ቡድን መንግስትና መላው ህዝቦቿ አንድነት እንዲፈጥሩና በኢትዮጵያዊነት ስሜት እንዲንቀሳቀሱ እያደረገ ነው። ይህ የአንድነት መንፈስ ብሔራዊ መግባባትን የፈጠረ፣ በጎረቤቶቻችንም አመኔታንና ተቀባይነትን እንድናገኝ ያደረገ ነው።

የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና በአገራችን አዲሱ አመራር ላይ ከፍተኛ እምነት አለው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከኤርትራ፣ ከጂቡቲ፣ ከሱዳን፣ ከኬንያ፣ ከደቡብ ሱዳንና ከኡጋንዳና ጋር ጠንካራ ግንኙነቶችን ከመፍጠር ባሻገር አገራቱ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ በመልማት ተጠቃሚ ለመሆን ውል ገብተዋል። ይህም ኢትዮጵያ ከተቀየረች ቀጠናውም ማደግ እንደሚችል ማሳያ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኤርትራ ጋር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ከማጠናከር ባለፈ ለአገራችን የወደብ አማራጮችን እየፈለጉ ነው። በዚህም አሰብ ወደብን በጋራ በማልማት ኢትዮጵያ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የሚያስፈልጋትን የወጭና ገቢ ንግድ የምታከናውንበትን መንገድ ቀይሰዋል። ወደ አሰብ የሚያደርሱ መንገዶች በሁለቱም ሀገራት መካከል እየተሳለጡ ነው። ይህም ኤርትራና ኢትዮጵያ ያለፉትን ሃያ ዓመታት ለማካካስና የወደፊት ጊዜያቸውን በጋራ ተጠቃሚነት ብሩህ ለማድረግ ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያመላክት ነው።

ከጂቡቲ፣ ከሱዳንና ከኬንያ ጋር የተፈጠረው የንግድ፣ የኢንቨስትመንት እንዲሁም ወደብን በጋራ የማልማት ስራም የሀገራችንን ቀጠናዊ የዲፕሎማሲ ድል የሚያመላክት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጂቡቲን ወደብ በጋራ ለማልማት እንዲሁም የሱዳንን ፖርት ሱዳን ወደብ አብሮ አልምቶ ለመጠቀም የደረሱት ስምምነት የዲፕሎማሲያችን ድል ነው። ሱዳን ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሃይል ለመግዛት የሚያስችላትን ሁኔታዎች በመፍጠር በጋራ ተያይዞ ማደግ የሚቻልበት ሁኔታም ተቀይሷል።

ከዚህ በተጨማሪም የኬንያን ላሙ ወደብ በጋራ አልምቶ ለማደግ ከአገሪቱ መንግስት ጋር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የደረሷቸው ስምምነቶች ውጤታማዎች ነበሩ። የጋራ የኢኮኖሚ ማዕከል በማቋቋም የሁለቱን አገራት ህዝቦች ተጠቃሚ ለማድረግ እየተካናወኑ ያሉት ስራዎችም ተስፋ ሰጪዎች ሆነዋል።

ኢትዮጵያና በጠቅላይ ሚኒስትሯ አማካኝነት ከኡጋንዳ ጋር ያደረገችው የሁለትዮሽና አካባቢያዊ ጉዳዮች ስምምነትም፣ የሁለቱን አገራት የንግድና ፖለቲካ ግንኙነት የሚያጠናክር ነው። በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ መጠን ማሳደግ እንደሚገባም ተወስኗል። አገራቱ ቅድሚያ በሚሰጣቸው እንደ ንግድ፣ ሃይል፣ ግብርና፣ ትራንስፖርት፣ ቱሪዝምና የባህል ዘርፎች በትብብር ለመስራት መስማማታቸው ተጠቃሚነታችንን የሚያጠናክር ነው።

በተለይ በሰሜን ኬንያ በኩል የሚያልፍና ሁለቱን አገራት የሚያስተሳስር የመንገድ ፕሮጀክት ለመዘርጋት የተደረሰው ስምምነት አገራቱን በኢኮኖሚ የሚያስተሳስራቸው ነው። ሁለቱ አገራት የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮችን አስመልክተው የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ሃይሎች ወደ ሰላም እንዲመጡ ጥሪ ማቅረባቸው ለቀጠናው ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው። በኢጋድ መሪነት የሚካሄደውን የደቡብ ሱዳን የሰላም ማሳለጫ ፎረምን በማጠናከር በአገሪቱ ዘላቂ ሰላምን እንዲረጋገጥም አድርገዋል። ይህ የአገራቱ ጥረት የደቡብ ሱዳን ሁለቱ ተቀናቃኝ ወገኖች ሰሞኑን ስልጣን ለመከፋፈልና ዳግም ወደ ጦርነት ላለመግባት ካርቱም ላይ እንዲፈራረሙ አድርጓቸል። የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኞች ለዚህ መድረስ ዶክተር አብይና መንግስታቸው የላቀ ሚና ነበራቸው። ይህም የአገራችን ተፅዕኖ ፈጣሪነት በቀጠናው እየተጎናጸፈ ያለውን ተቀባይነት የሚያረጋግጥ ነው ማለት ይቻላል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሌሎች የቀጠናው አገራት ጋር ያደረጓቸው የሁትዮሽ ስምምነቶች ይህንኑ ሃቅ የሚያሳዩ ናቸው።

ኢትዮጵያ በጥቂት ወራቶች ውስጥ በዓለም አቀፉ መድረክም በአዲስ ገፅታ መታየት ጀምራለች። በዚህም ሳቢያ አገሪቱ በዓለም አቀፉ የዲፕሎማሲ መድረኮች ተሰሚነቷ እየጎለበተ መጥቷል። የዲፕሎማሲው ተሰሚነቷ ሁሉንም የቀጣናውን ብሎም የአህጉሪቱን አገራት እየሳበ መጥቷል።

ለዚህም ደፐክተር አብይ የተከተሏቸው የመደመር የዲፕሎማሲ አቅጣጫዎች የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ። ይኸውም ተደምሮ በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ የዲፕሎማሲ መሰረት በመከተላቸው ነው። ይህ መንገድ ብሔራዊ ጥቅማችንን የማስጠበቅና አገራዊ ህልውናችንን የማረጋገጥ ሚናንም እየተጫወተ ነው።

የዲፕሎማሲው ትስስር ገመድ የቀጠናውን ህዝቦች ጥቅም ብቻ ያማከለ ነው። የምስራቅ አፍሪካ ህዝቦች በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ በባህል፣ በታሪክ፣ በአብሮ መኖር፣ በመዋለድና አንዱ የሌላኛውን ሀገር እንደ ሁለተኛ መኖሪያው በመቁጠር የቅርብ ግንኙነት የታጠረ ነው። በመሆኑም የቀጠናው አገራት ይህን ዘመናትን የተሻገረ የህዝቦች ጥብቅ ቁርኝት በዘመናዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ይበልጥ አጥብቀው እንዲያስሩ ዶክተር አብይ በመደመርና በጋራ በመጠቀም መርህ ለመለወጥ እየተንቀሳቀሱ ነው። ውጤቶቹንም በተግባር እያየናቸው ነው።

ኢትዮጵያ በራሷም ሆነ በአካባቢው አገራት ውስጥ የተረጋጋ የፖለቲካ ሂደት እንዲኖር ግጭቶችና ውዝግቦች በሰላማዊ ጥረት እንዲፈቱ ብቻ ሳይሆን፤ የሰላምና የትብብር አድማስ በዲፕሎማሲ ታጅቦ ተደምሮ እንዲሰፋ ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተች ነው። ይህ ተግባሯም በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተገቢውን የእውቅና ስፍራ እንድታገኝ ያደረጋት ነው። በዶክተር አብይ አማካኝነት እውን የሆኑት የዲፕሎማሲ ስኬቶቻችን ጥቅሞችን እያመጣልን ነው። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብና የገንዘብ ተቋማት ከእኛ አዋጭ መንገድ ጋር አብረው ለመስራት እየገለፁ ነው። ስኬቶቹን ማጠንከር ጥቅሞች እያስገኘልን ስለሆነ የተገኙት ስኬቶች እንዲስፋፉ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ሊያበረክት ይገባል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy