Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በህግ አምላክ

0 409

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በህግ አምላክ

ስሜነህ

 

ሒዩማን ራይትስ  በኢትዮጵያ በብሔርና በሃይማኖት ሰበብ የሚካሄዱ ግድያዎች ከፍተኛ ውጥረት በመፍጠር ላይ ስለመሆናቸው ሰሞኑን ገልጿል። በተለይም በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች የሚፈጸሙ ጥቃቶች በለውጡ ሂደት ላይ እንቅፋት እየፈጠሩ ነው ብሏል ሒዩማን ራይትስ ዎች። በኢትዮጵያ የተለያዩ የማሻሻያ ርምጃዎች መካሄዳቸውን ተከትሎ በሃገሪቱ ትልቅ ተስፋ መፈንጠቁን ሒዩማን ራይትስ ዎች ገልጿል።

 

በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በወሰዱት ርምጃ በሃገሪቱ ሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ድጋፍ እንዳስገኘላቸውም የሰብአዊ መብት ተከራካሪው ድርጅት አስታውሷል። ይህም ሆኖ ግን በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች ለውጡን እንዳያደናቅፉ ስጋት መኖሩን ሒዩማን ራይትስ ዎች ገልጿል።

 

በሶማሌ ክልል በዋናነት፤ በሌሎችም አንዳንድ አካባቢዎች በወገኖቻችን ላይ የተፈጸመው ግድያ፣ ዘረፋና ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ከባድ ጊዜ ውስጥ እንዳለን ያሳያል፡፡ አንድ ክልል ውስጥ ችግር ሲፈጠር “መጤ” በሚባሉ ሌሎች የአገሪቱ ዜጎች ላይ የሚፈጸሙ አስነዋሪ ወንጀሎች ስር እየሰደዱና እየተበራከቱ ነው፡፡በተለይ በአገሪቱ መንግሥት የለም ወይ እስኪባል ድረስ ሰዎችን መግደልና ማሰቃየት፣ ከዚያም አልፎ ተርፎ ቤተ እምነቶችን ማቃጠል የተፈጸመበት የሶማሌ ክልል የሰሞኑ ድርጊት ብዙዎችን አሳዝኗል፡፡ በገዛ አገር እንደ ባዕድ እየታደኑ የተገደሉና የተዘረፉ ወገኖች የሚደርስላቸው አጥተው የግፍ ሰለባ ሆነዋል፡፡

 

አንድ ኢትዮጵያዊ ወገኔ ነው ብሎ በሚያስበው የተደራጀ ኃይል ከሚችለው በላይ ጥቃት እየተፈጸመበት፣ የሚያስጥለው ሕግ አስከባሪ ወይም አለኝታ ሲያጣ በአገሩ ላይ ተስፋ ይቆርጣል፡፡ በሕዝብ ላይ በደል የሚፈጽሙ የሚቆጣጠራቸው ወይም የሚጠይቃቸው ባለመኖሩ ብቻ፣ ሕገወጥነት ከሚታገሱት በላይ እየሆነ ነው፡፡  

 

የሕግ የበላይነት የሕገ መንግሥታዊ የበላይነትን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ የፖለቲካ ሊቃውንትም ሃረጉን ተቋማዊ ስርአትን በሃገር ውስጥ ለማስረዳትና ባለስልጣናትም ሥልጣናቸውን አላግባብ እንዳይጠቀሙበት ለመከላከያነት ያውሉታል፡፡ ሕጉ በአግባቡ እንዲተረጎምና የሕዝቡም ተጠቃሚነት እንዳይስተጓጎል መከላከያ ይሆንና መሰረታዊ የሆኑት ሰብአዊ መብቶች ሳይሸራረፉ እንዲጠበቁና በተግባር ላይ እንዲውሉ ዋስትና ነው፡፡ በኢንቨስትመንት ሂደት ላይ ውል እንዲከበር፤የገበያው ልውውጥ የሰመረ እንዲሆን፤የተረጋጋና ሰላማዊ አካባቢ ለመፍጠር፤የህግ የበላይነት ወሳኝ ጉዳይ ይሆናል። የሕግ የበላይነት በሌለበት ኢንቨስትመንትም ሆነ ልማት ተግባራዊነታቸው ዋስትና ስለማይኖረው ፈላጭ ቆራጮች እንዳሻቸው በማፍረስና ከሕግ በላይ በመሆን ስለሚንዱት የሕግ የበላይነት ወሳኝነቱ የማያጠያይቅ ነው፡፡

 

በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ ጎራዎች የተሠለፉ ኃይሎች አገርን የዘነጉ ይመስላሉ፡፡  ትናንት ለዴሞክራሲና ለሰብዓዊ መብት ሲጮሁ የነበሩ፣ አገሪቱ በለውጥ ጎዳና ውስጥ ሆና ዕገዛ ማድረግ ሲጠበቅባቸው እራሳቸውን ከህግ በላይ ቆልለው ሃገር እያመሳቀሉ ነው። በፌዴራልም ሆነ በክልል የሚገኙ ወገኖች የሕግ የበላይነት ተከብሮ አገር በሥርዓት እንድትተዳደር የማድረግ ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በረባ ባልረባው ምክንያት በየቦታው ሁከት ሲቀሰቀስ በግዴለሽነት የሚመለከቱ አመራሮችም ሆኑ የፀጥታ ኃላፊዎች ራሳቸውን ሊመረምሩ ይገባል፡፡ የአገር አንድነትና ዘላቂ ሰላም የሚረጋገጠው፣ የሚመለከታቸው አካላት እየተናበቡና እርስ በርስ ቁጥጥር የሚያደርጉበት አሠራር ሲሰፍን ነው፡፡ “ማፍረስ ቀላል ባይሆንም መገንባት ግን የበለጠ ከባድ ነው” የሚለውን አባባል በማስታወስ፣ ወጣቱን ትውልድ ለአገራዊ አንድነትና ዘላቂ ሰላም የበኩሉን እንዲወጣ ማድረግ ጊዜ የማይሰጠው ተግባር መሆን አለበት፡፡ ብሔርን መነሻ ያደረገ ግጭትና ውድመት አገርን ያጠፋል፡፡ ሕዝብን ይበትናል፡፡ በሕግና በሥርዓት መመራት ካልተቻለ ውጤቱ የከፋ ይሆናል፡፡

 

የዓለም ባንክና ኢንተርናሽናል ሞኒታሪ ፈንድ ከ1990 ጀምሮ የህግ የበላይነት በአፍሪካ በትክክል በተግባር እንዲውል ከሌሎች ተመሳሳይ ድርጅቶች ጋር በመሆን ሲወተውቱ ዓመታት ቢያሳልፉም ውጤቱ ግን ከንቱ ልፋት ሆኖባቸዋል፡፡የሕግ የበላይነት ስሜት በቀላል አባባል እንደሚከተለው ሊገለጽ ይችላል፤ ሥልጣን ለሙስና ይዳርጋል፤ ፍጹማዊ አምባገነን ሥልጣን ደሞ ለበለጠ፤ ለገነነና መረን ለለቀቀ ሙስና ይዳርጋል በሚል መንፈስ።በሱማሌ ክልል የሆነውም በዚህ ተመሳሳይ ነው። የህግ የበላይነት ይህን ስልጣን ለመቆጣጠርና ፍጹምና አምባገነንም ስልጣን ከገነነ ሙስና እንዲቆጠብ ማድረጊያው ዋና መሳርያ ቢሆንም ይህን በሱማሌ ለማድረግ ሳይቻል ቀናት መቆጠራቸውም የበዛ ዋጋ እንድንከፍል አድርጎናል፡፡

 

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሃፊ ለሴኪውሪቲ ካውንስል በ 2004 ባቀረቡት ዘገባ፤ የሕግ የበላይነትን ተግባራዊነትን፤ ምንነትና መሰረታዊ ሕዝባዊና ሃገራዊ ጥቅሙን ሲያስረዱ፤“ሁሉም ሰብአዊ ፍጡራን፤ ድርጅቶችና አባሎቻቸው፤ ሕዝባዊም ሆኑ የግል፤ መንግሥትን ራሱ ጨምሮ የሕግ ተጠያቂነታቸውን ማረጋገጫ፤ በዓለም  አቀፍ ሰብአዊ መብቶች ድንጋጌ ላይ የተመሰረቱና የመንግሥታት ተቀዳሚ መመርያ ሊሆን የሚገባውነው፡፡” ተግባራዊ ሲደረግም የሕግን የበላይነት በማረጋገጥ ለዚህም ታማኝነትን የሚጠይቅ የሕግን ደንብ የሚያስከብርና ማንም ከሕግ በላይ አለመሆኑን ማረጋገጫ፤ ለሁሉም አላንዳች መድልዎ በእኩልነት የሚያገለግል፤ የስልጣን ክፍፍልን ሚዛን የሚያስጠብቅ፤ በውሳኔ አሰጣጥም እኩልነትን የሚያሳይ፤ከጥርጣሬ የጸዳና ግልጽነትን ያቀፈ ሊሆን ይገባል።”እነ አብዲ ኢሌ ግን ከዚህ በላይ ሆነው በመሰንበታቸው ዋጋውን እጽፍ ድርብ አድርጎብን ከርሟል።

 

የዓለም ባንክም የሕግ የበላይነትን ጥቅም ሲገልጽ የሕግ የበላይነት ባለበት መንግሥታት እራሳቸውን ይቆጣጠራሉ፤ ሕዝቦችንም በሕጋዊና በእኩልነት ለሕግ የበላይነት በመገዛትና የሕብረተሰብ አባላት የሆኑትን ግለሰቦችም መብት በማክበር ያስተዳድራሉ፡፡ በሕግ የበላይነት የሚመሩ በርካታ ድርጅቶችና ተቋማት ጭምር እንቅስቃሲያቸውን በተመለከተ ለዚሁ ተገዢ በማድረግ ላይ እምነታቸውን ያሳርፋሉ፡፡በሱማሌ የሆነው ግን ብዙዎችን ተጠራጣሪዎች አድርጎብን እንደሆነም ፍንጮች ታይተዋል።

 

እንደ ሰሞኑ ዓይነት የጭካኔ ድርጊቶች ሲፈጸሙ ዋነኞቹ ተጎጂዎች ሕፃናት፣ ነፍሰ ጡሮች፣ አራሶችና አቅመ ደካሞች ናቸው፡፡ በተጨማሪም ጥረው ግረው በላባቸው የሚኖሩ ባተሌዎች ናቸው። መንግሥት ደኅንነታቸውን እንደሚያስከብር የሚተማመኑ ሥራ ፈጣሪዎችና የንግድ ሰዎችም እንዲሁ ሰለባ እንደሆኑም አይተናል፡፡ በአገራቸው በፈለጉት ሥፍራ የመዘዋወር፣ የመኖር፣ የመሥራትና ሀብት የማፍራት ሕጋዊ መብት እንዳላቸው የሚገነዘቡ ወገኖች እያጋጠማቸው ያለው ክፋት ተጠራጣሪዎች ቢያደርጋቸው ሊገርመን አይገባም፡፡በእነዚህና ሙስና ባሰከራቸው ሃይሎች ስርአተ አልበኝነት ለጊዜው ቁጥራቸው የማይታወቅ በርካታዎች ሲሞቱ፣ የአካል ጉዳትና ዝርፊያ የተፈጸመባቸው ብዙ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ለሥነ ልቦናዊ ጉዳት የተጋለጡም በጣም ብዙ ናቸው፡፡ በድሬዳዋም አሥር ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ ከሟቾቹ መካከል ሦስቱ ሕፃናት መሆናቸው እጅግ በጣም ያንገበግባል፡፡ የፍትሕ ያለህ ያስብላል፡፡

 

የአገር መከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል ፖሊስ ወደ ሶማሌ ክልል ገብተው ሕግ እያስከበሩ መሆናቸው ተሰምቷል፡፡ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወደ ኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል የገባው በክልሉ አመራር ጥያቄ መሠረት ነው። ዜጎች በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል በሰላም የመኖር መብታቸው ተጥሶ እየተገደሉ እና ቤተ እምነቶች እየተቃጠሉ ባለበት ወቅት እና ሁኔታውን ለመቆጣጠር ከክልሉ አቅም በላይ በሆነበት ሁኔታ በቀረበለት ጥያቄ መሰረት የአካባቢውን ሰላምና መረጋጋት ለመመለስ መግባቱ ህገ መንግስታዊ ነው። እዚህም ላይ አቃቂር በማውጣት ሃገር ወደውድመት እንድትሸጋገር የሚተጉ ሃይሎች ቢቆጠቡ ይሻላል።

 

እነዚህን የሚወስኑትን ድንጋጌዎች እንመልከት፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 50(5) የክልል ምክር ቤት በክልሉ ሥልጣን ሥር በሆኑ ጉዳዮች የክልሉ የሕግ አውጪ አካል መሆኑን ይገልጽና፣ “ይህንን ሕገ መንግሥት መሠረት በማድረግ የክልሉን ሕገ መንግሥት ያዘጋጃል፣ የፀድቃል፣ ያሻሽላል” ይላል፡፡ የፌዴራል መንግሥቱን ሥልጣን የሚወስነው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 51(1) ሕገ መንግሥቱን ይጠብቃል፣ ይከላከላል ይላል፡፡ የክልል ሥልጣን የሚደነግገው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 52(2) ክልሉ ራሱን በራሱ ማስተዳደርን ዓላማ ያደረገ ክልላዊ መስተዳድር ያዋቅራል፡፡ የሕግ በላይነት የሰፈነበት ዴሞክራሲዊ ሥርዓት ይገነባል፣ ይህን ሕገ መንግሥት ይጠብቃል፣ ይከላከላል በማለት ይደነግጋል፡፡ የፌዴራል ሕገ መንግሥት በአንቀጽ አንድ ይህ ሕገ መንግሥት ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ የመንግሥት አወቃቀር ይደነግጋል፣ በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ መንግሥት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ በሚል ስም ይጠራል በማለት ብቻ አይወሰንም፡፡ በአንቀጽ 93(4)(ሐ) ደግሞ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አዋጅ ሥር የሚያወጣቸው ድንጋጌዎችና የሚወስዷቸው ዕርምጃዎች ከሌሎች መካከል በሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ አንድ “… የተቀመጡትን መብቶች የሚገድቡ ሊሆኑ አይችሉም፤” ይላል፡፡ የተጠቀሰው አንቀጽ አንድ “መብት” ባይሆንም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲዊ ሪፐብሊካዊነት የሚያናጋ ተግባር ክልልም፣ ማዕከላዊ መንግሥትም አይወስድም፡፡ የከፋ አስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ እንኳን ይህንን እንዲያናጋ አይፈቀድለትም፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የዚህ ሁሉ ጠባቂ ማዕከላዊ (ፌዴራላዊ) መንግሥት ነው ማለት ነው፡፡ስለሆነም ጣልቃ ገብ የሚለው ህገ መንግስታዊ መሰል መከራከሪያ በህገ መንግስቱ ስር ባለው የህግ የበላይነት አመክንዮ ውድቅ ይሆናል ማለት ነው።

 

በተለያዩ ክልሎች የሚከሰቱ ግጭቶች በሙሉ ከሕዝብ ጋር የሚገናኙ አይደሉም፡፡ ሕዝብ ለዘመናት አብሮ ኖሯል፡፡ ችግር ሲያጋጥምም አንዱ ሌላውን እየሸፈነ ወይም ከለላ እየሰጠ በመኖርም ይታወቃል፡፡ በተለይ በዚህ ዘመን ለሚፈጠሩ ችግሮች ዋነኞቹ ተጠያቂዎች የፖለቲካ አመራሮች ናቸው፡፡ ሥልጣን ላይ ከወጡ በፍፁም መውረድ የማይፈልጉ አመራሮች በሕዝብ ስም እየነገዱ፣ በንፁኃን ዜጎች ደም እጃቸውን ይለቃለቃሉ፡፡ ሥልጣን የሚያስገኘውን ጥቅም ላለማጣት ሲሉም ሕዝብን እርስ በርስ ያባላሉ፡፡በተለይ በስሜታዊነት የሚነዱ ኃይሎችን እያደራጁ ሕዝብ ውስጥ በማሰማራት ግድያ ይፈጽማሉ፣ ይዘርፋሉ፣ ያፈናቅላሉ፡፡በሕግ ስለማይጠየቁም የሕግ የበላይነትን እየደፈጠጡ አገር ያተራምሳሉ፡፡በአሁኗ ኢትዮጵያ ይህ ድርጊት በአስቸኳይ ቆሞ ዜጎች ፍትሕ ማግኘት አለባቸው፡፡ አስነዋሪ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ አመራሮችም ሆኑ ተከታዮቻቸው በሕግ መዳኘት ይኖርባቸዋል፡፡ ሕገወጥነት በሕጋዊነት ላይ እየነገሠ የትም መድረስ አይቻልም፡፡

 

ስለሆነም በንፁኃን ላይ ወንጀል የፈጸሙም ሆነ ያስፈጸሙ ኃይሎች በሕግ መጠየቅ አለባቸው፡፡ ከዚህ ቀደም በሺዎች ለሚቆጠሩ ወገኖች ሞትና ለሚሊዮኖች መፈናቀል ምክንያት የሆኑ ኃይሎችን የጠየቃቸው ባለመኖሩ፣ ግጭቶችን በየቦታው መስማት የተለመደ ትዕይንት ሆኗል፡፡ ከግድያና ከተለያዩ አስፀያፊ የወንጀል ድርጊቶች ሸሽተው በአብያተ ክርስቲያናትና በተለያዩ ሥፍራዎች የተጠለሉና የተደበቁ ወገኖች፣ ከአስቸኳይ ዕርዳታ በተጨማሪ ፍትሕ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ሕገወጦች እንዳሻቸው እየፈነጩ በዜጎች ሕይወት ላይ ቁማር ሲጫወቱ፣ ዜጎችን በማረጋጋትና መልሶ በማቋቋም ስም ፍትሕን ገሸሽ ማድረግ ተገቢ አይደለም፡፡

 

በክልሎች የተደራጁ ልዩ ኃይል የሚባሉና የእነሱ ድጋፍ ሰጪ መደበኛ ያልሆኑ መዋቅሮች በፍጥነት መፈራረስ አለባቸው፡፡ የዜጎችን ደኅንነት ለመጠበቅ በመንግሥት በጀት የሚተዳደሩ የፀጥታ ተቋማት እያሉ፣ በጎንዮሽ የሚደራጁ ኃይሎች ለአገርና ለሕዝብ ጠንቅ እየሆኑ ነው፡፡ በግልጽም እየታየ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት እየተጣሰ ያለው በእነዚህ ኃይሎች መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy