Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በስኬት ላይ ስኬት

0 352

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በስኬት ላይ ስኬት

                                                         ይሁን ታፈረ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሰሜን አሜሪካ ያካሄዷቸው ጉብኝቶች ዲፕሎማሲያዊ ድሎችን አስገኝተዋል። ጉብኝቶቹ ከዲፕሎማሲ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ጥቅምን ያስገኙ ናቸው። በተለይም አገራችን የተያያዘችው ሪፎርም በሌሎች አካላት ትክክለኛ መሆኑ እንዲመሰከርለት ያደረገም ነው።

የጉብኝቶቹ ውጤቶች እዚህ አገር ቤት ውስጥ በመካሄድ ላይ ያለው ሪፎርም ያስገኛቸው ናቸው። ስለሆነም የለውጡ ባለቤት የሆነው የአገራችን ህዝብ የሪፎርሙ ስኬቶች ይበልጥ እንዲጠናከሩ የጀመረውን የለውጥ ሂደት አጠናክሮ መቀጠል አለበት። ይህም በስኬት ላይ ስኬት የሚያስገኝለት መሆኑን ያብራራል።

እንደሚታወቀው ሁሉ አገራችን በምትከተለው የትብብርና የሰላም ዲፕሎማሲ መርህ መሰረት በዓለም ዙሪያ ካሉት ሀገሮች ጋር ያላት ግንኙነት በጋራ ጥቅም ላይ እንዲመሰረት ሆኗል። በዚህም ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስሯ ትልቅ ስፍራ ሊደርስ ችሏል። በተለይ በአገራችን በተካሄደው ሪፎርም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ትስስሩ እጅግ ጠንክሯል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአሜሪካ ጉብኝቶች ይህን ያረጋገጡ ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአሜሪካ ከዳያስፖራዎች ጋር ባደረጉት ውይይት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለን ምስል እንዲቀየር አድርጎታል። በዓለም ፈት አንድ መሆናችን ተረጋግጧል። ኢትዮጵያዊነት አንድነት፣ ፍቅርና ይቅርታ መሆኑን አሳይቷል። ዶክተር አብይ ኢትዮጵያዊያን በየትኛውም ዓለም ሲሄዱ ኢትዮጵያን የዘዋት ይዞራሉ ያሉትን እውነታ የዓለም ህዝብ በገሃድ እንዲያውቀው ማድረግ ችለናል። በዚህም የላቀ ዲፕሎማሲን አስመዝግበናል።

ዶክተር አብይ የጎበኟቸው የአሜሪካዎቹ ዋሽንግተን ዲሲ፣ ሎስ አንጀለስና ሚኒሶታ የፍቅር ከተማዎች ሆነው ቆይተዋል። የተለያዩ መገናኛ ብዙሃንም ይህን የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ሽፋን ሰጥተውታል። ኢትዮጵያኖች በአንድነት የተሳሰርን ህዝቦች፣ ለመቀራረብም ምንም ዓይነት ችግሮችን መሻገር የምንችል መሆናችንን አስመስክረናል። ዓለም ስለ እኛ የነበረውን የተሳሳተ ዕይታ ማስተካከል ችለናል።

ከሐምሌ 19 እስከ ሃምሌ 23 2010 ዓ.ም በሶስት የአሜሪካ ከተሞች በተካሄደው ጉብኝትም 20 የተለያዩ መድረኮች ተዘጋጅተዋል። መድረኮቹም በ100 ሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን፣ 70 የሚሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና በ100 የሚቆጠሩ ምሁራን የተካፈሉበት ነበሩ።

ጉብኝቶቹን በ118 ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን መንገዶች ተከታትለውታል። እንዲሁም በአሜሪካ የሚገኙ 63 የመገናኛ ብዙሃንም በተለያዩ አውታሮች ሽፋን ሰጥተውታል። ይህም ዲፕሎማሲያችንን ለመገንባት ትልቅ ዕድል የፈጠረ ነበር።

ዲፕሎማሲያዊ ድሉ የአሜሪካኖቹ ከተሞችም በዚህ ማንነታችን በመደሰታቸው በየከተማዎቻቸው የኢትዮጵያ ቀን እንዲከበር እንዲያደርጉ ያስቻላቸው ነው። ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያዊያን በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ያልነበረ ትኩረት እንዲያገኙም አድርጓል። ይህ እውነታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሜሪካ ተገኝተው ዳያስፖራውን ማነጋገራቸው አሜሪካኖች ልዩ ትኩረት የሰጡት መሆኑን የሚያመላክት ይመስለኛል። ከዲፕሎማሲያዊ ድል በላይ ለኢትዮጵያዊኑና ለትውልደ ኢትዮጵያኑም ቢሆን ኩራት ነው።

የተገኘው ድል እዚህ አገር ውስጥ የተካሄደውና በመካሄድ ላይ ያለው ለውጥ ያመጣው ነው። በአገራችን ውስጥ የፈጠርነው አንድነት ያስገኘልን ነው። ሪፎርሙ የዜጎችን ሁለንተናዊ ለውጥ እያረጋገጠ ነው።

ሪፎርሙ በአገራችን ውስጥ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት በመንግስት በኩል እየተደረጉ ያሉ ውጤታማ ጥረቶች ማንንም ለማስደሰት አሊያም ለማስከፋት አይደለም። የአገራችን ህዝቦች የታገሉላቸውን ህገ መንግስታዊ መብቶች በፅኑ መሰረት ላይ እንዲቆሙ ከማሰብ የመነጨ ነው።

ቀደም ሲል የኦሮሞ ዴሞክራሲ ግንባር (ኦዴግ)፣ የኦሮሞ አንድነት ነፃነት ግንባር (ኦአነግ) እንዲሁም በደርግ ዘመን ከፍተኛ ባለስልጣን የነበሩት አምባሳደር ዶክተር ካሳ ከበደን ጨምሮ ሌሎች ግለሰቦች እንዲሁም የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እና የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር ፓርቲ (ትዴትፓ) ከውጭ ወደ አገር ቤት ገብተዋል።

የለውጡ ጎዳና ለማንኛውም ኢትዮጵያዊ ፓርቲ ምቹ ሁኔታን የፈጠረ ነው። ዴሞክራሲውም እንዲያብብ አስተማማኝ ምህዳር እየሆነ ነው። በዚህ የለውጥ ጉዞ ላይ ዴሞክራሲን ለማጎልበት በውጭ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሚዲያዎችና ሲቪክ ማህበራት የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ ይገባል።

እንደሚታወቀው ሁሉ የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ዋነኛ መገለጫው አሳታፊነት ነው። የዴሞክራሲ አሳታፊነት ሁሉም ዓይነት አስተሳሰቦች ወጥተው እንዲደመጡ ያደርጋል።

ህዝቦች ሊመሯቸውና ሊያስተዳድራቸው የሚችሉ ጠንካራ ሃሳቦችን በማድመጥ ይሁንታቸውን እንዲሰጡ ያደርጋል። ይህም በህገ መንግስቱ በግልፅ እንደተደነገገውም ስልጣን በህዝብ ፍላጎት ላይ በተመሰረተ ድምፅ እውን እንዲሆን የሚያደርግ ነው።

ያለፉት ዓመታት የፖለቲካ ልዮነታችን አንድነታችን ሆኖ እንዳይቀጥል፣ በመነቋቆርና በመነካከስ እርስ በርሳችን እንድንዳማ እንዲሁም ከአጣብቂኝ ውስጥ ወጥተን ወደ ተሟላ የልማት ስራ በሙሉ አቅማችን እንዳንገባ ያደረጉን ናቸው።

ስለሆነም እነዚህን ችግሮች ለመሻገር በዶክተር አብይ የሚመራው መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሁንም ድረስ ጥሪ ማድረጉ ትክክለኛ ውሳኔ አሳልፏል። ይህም ዲያስፖራው በውጭ አገር እንዲደመርና ለአገሩ እንዲያስብ አድርጎታል።

የዶክተር አብይ የአሜሪካ ጉብኝቶች አሜሪካኖች አብረውን ለመስራት ቃል የገበቡበት ነው። የአሜሪካው ምክትል ፕሬዚዳንት ማይክ ፔንስ ከኢትዮጵያ ጋር በሁሉም መስኮች ተባብሮ ለመስራትና የተገኘውን ለውጥ እንደሚደግፉ አስታውቀዋል። ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ለማከናወን የሚያደርጓቸውን ጥረቶች አገራቸው እንደምትደግፍም ገልጸዋል። ይህ የአሜሪካ አቋም አገራችን ውስጥ የተፈጠረው ለውጥ ያመጣውና ለኢኮኖሚያችም ቢሆን ትልቅ ፋይዳ ያለው ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሜሪካ ከዓለም ባንክና ከገንዘብ ድርጅቱ (አይ ኤም ኤፍ) ጋር መገናኘታቸው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ከፍተኛ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከአለም ባንክ ፕሬዚዳንት ጂም ዮንግ ኪምና ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ.ኤም.ኤፍ) ኃላፊ ክርስቲን ላጋርድ ጋር በዋሽንግተን ዲሲ ያሰደጉት ውይየት ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለችውን ልማት ሊደግፍ የሚችል ነው።

በተለይም አለም ባንክ የኢትዮጵያን ማሻሻያ እንደሚደግፍ መግለጹና አይ.ኤም.ኤፍም የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት እድገት ሁሉንም ያማከለ እና ዘላቂ እንዲሆን በማድረግ ድህነትን ለመቀነስ ከአገሪቱ ባለስልጣናት ጋር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን መግለፁ ልማትን መደገፍ የሚችል ውሳኔ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትራችን በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ሰላም እና እርቅ ማውረድ በመቻላቸውም ለጠቅላይ አለም ባንክ አድናቆቱን ገልጿል። ይህም አገራችን ለልማት የምታደርገውን ተነሳሸነት ባንኩ እንዲደግፈው የሚያደርገው ይመስለኛል። የሰላም መኖር ለልማት ጉልህ ሚናን ያበረክታልና።

ኢትዮጵያ ሰብአዊ ልማት ላይ አትኩራ እየሰራች ነው። ህዝቦችን ከኋላ ቀርነት መደገፍ የግድ ያስፈልጋል። የአዲሲቷ ኢትዮጵያ መንግስት ሙስናን ለመዋጋት ቁርጠኛ በመሆኑ አገር ውስጥ የሚገኘውን ሀብት በሙሉ የኢትዮጵያውያንን ህይወት ለመለወጥ ተግባር የሚውል ነው።

ይህ የመንግስት ህዝባዊ አሰራር በባንኩ ቢደገፍ ውጤታማ መሆን ይቻላል።
በተለይ ዶተር አብይ ወደ ሃላፊነት ከመጡ በኋላ ይፋ ያደረጓቸው የፖሊሲ አቅጣጫዎች የአገራችንን ድህነት የሚቀርፉና ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያደርጉ ናቸው። ሁለቱ የባንክ ሃላፊዎች ለኢትዮጵያ ያላቸውን አድናቆት መግለጻቸው ወደፊት ለምናደርጋቸው የልማት ስራዎች ደጋፊዎች ናቸው።

አዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህን፣ ሰላምንና አንድነትንና አገራዊ ዕድገትን ማምጣት የሚያስችል ለውጥ እውን እየሆነ ነው። ድህነት በተጨባጭ የሚናድበት አውድ እየተፈጠረ ነው። በለውጡ የተገኙት ውጤቶች ሰሜን አሜሪካ ያሉትን ወገኖቻችንን፣ አለም አቀፉን ማህበረሰብ የገንዘብ ተቋማትን ሁሉ በማሳመን ዲፕሎማሲያችንን እያጠናከረ ነው። ኢኮኖያችን እንዲጠነክርም የጎላ ሚና እየተጫወተ ነው። ዶክተር አብይ በአሜሪካ ጉዟቸው ያስገኟቸው ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ድሎች በስኬት ላይ የተገኙ ስኬቶች ናቸው። ስለሆነም ለውጡን አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy