Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ተምሳሌታዊው አካሄድ

0 348

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ተምሳሌታዊው አካሄድ

                                                          ታዬ ከበደ

ሰሞኑን የቻይናው የዜና ወኪል ዥንዋን ጨምሮ በርካታ መገናኛ ብዙሃን በመንግስታቱ ድርጅት የስዊዲን አምባሳደር የሆኑት ኦሎፍ አስጉግ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ሰላም እንዲሰፍን በማስቻላቸው በቀጣይ መስከረም በሚካሄደው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስብሰባ ላይ የክብር ተናጋሪ ሆነው እንዲቀርቡ መጠየቃቸውን ዘግበዋል።

እርግጥ አምባሳደሩ ተስፋ የቆረጥንበትን የሁለቱን ሀገራት ፍጥጫ በአጭር ጊዜ መፍትሄ የሰጡ መሪ በማለት አድናቆታቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትራችን መግለጻቸው ተገቢና ትክክል ነው። ዶክተር አብይ ታላላቅ መንግስታት ሞክረው ያልተሳካላቸውን ሁለቱን አገራት የማሸማገል ጉዳይ እልባት የሰጡ መሪ ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተከተሉት ተምሳሌታዊ አካሄድ ሌሎች አገራት ከጎረቤቶቻቸው ጋር ስለሚኖራቸው ግንኙነት በአርአያነት ሊቀርብ የሚችል ነው።

በተለይ አምባሳደር አስጉግ “በገንዘብ፣ በዲፕሎማሲውና በወታደራዊ በኩል የሚወጣውን መዋዕለ ነዋይ እንደዚህ ዓይነት ሰላማዊ መፍትሄዎችን ለማምጣት ለሚደረግ ጥረት ብናውለው የተሻለ ይሆናል” ማለታቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሳም ባለቸው ፍላጎት ብቻ ያለ ሌላ ወገን አሸማጋይነት የሰላሙን መንገድ በብቃታቸው እውን ማድረጋቸውን የሚያረጋግጥ ነው።

ዶክተር አብይ ያደረጉት ተግባር የፀብና የቁርሾ ፅላሎት መጋረጃው መቀደዱ ለሁለቱም ሀገራት አዲስ የሰላም ብርሃን እንዲፈነጥቅ ያደረገ ነው። እርግጥ ጥላቻና ብሽሽቅ አሁን በምንገኝበት የስልጣኔ ዘመንም ይሁን ዕድሜ አዋጭ አይደለም። ሰላምና ፍቅር እንጂ፣ ሁከትና ጥላቻ ፋይዳ ቢስ በዙህ ዘመን ዋጋ ቢስ ናቸው።

የዶክተር አብይ የሰላም መንገድ በጋራ ተጠቃሚነት እሳቤ ተባብሮ የመስራት ፍላጎቱ እስካለ ድረስ ተያይዞ ማደግና የሀገራቱን ህዝቦችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻልየሚያስረዳ ነው። ለትክክለኛ ሰላም፣ ፍቅርና ለህዝቦች አንድነትና ተጠቃሚነት አብሮ መስራት የሚያስችል ነው።

ኤርትራም ለሰላም ያላት ጠንካራ ፍላጎት የተራራቁ ህዝቦችን ይበልጥ የሚያቀራርብና ሊገኝ ከሚችለው የጋራ ተጠቃሚነት በአዲስ መንገድ እንዲተሳሰሩ የሚያደርግ ነው። አንዱ ከሌላው ልምድ እየቀሰመም ልማትን እንዲያጎለብት ዕድልና ምቹ ሁኔታ ይከፍታል። እናም ይህ የተከፈተው የሰላም በር የዕድገት ማስተሳሰሪያ ሊሆን የሚችል ነው።

የሁለቱ አገራት ህዝቦች አንድም ሁለትም ናቸው። ርግጥ የኤርትራና የኢትዮጵያ ህዝቦች ተለያይታችሁ ኑሩ ቢባሉ ሊለያዩ የሚችሉ አይደሉም። ያለፏቸው የህይወት መንገዶች የቁርኝት ሰንሰለታቸውን አጋምዶታል። የቋንቋ፣ የደም፣ የአብሮነት፣ የመቻቻልና አብሮ የመኖር መስተጋብራቸው እንዲሁ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

 

ኢትዮጵያና አብሯቸው እስከ መጨረሻው የሚዘልቅ እንደ ድርና ማግ የተዋደደ ትስስር ያለው ነው። እናም እነዚህ ህዝቦች ከአንድነትና ተሳስቦ በእኩል ተጠቃሚነት ከመኖር እንጂ በተናጠል ህይወትን መግፋት አያዋጣቸውም። የሀገራቱ በጋራ መኖር በቀጣናው ያለውን የተፈጥሮ ፀጋ እየተሳሰቡ ሊጠቀሙ ይችላሉ።

ኢትዮጵያና ኤርትራ ትናንትን ዛሬያቸው ውስጥ አምጥተው አልተመለከቱም። ከ20 ዓመት በፊት የተከሰተን ግጭትና ጥፋት ረስተው በጋራ መበልፀግ በሚቻልበት ጉዳይ ላይ እየመከርን ለመስራት ተስማምተዋል። በስምምነታቸው መሰረትም ዛሬ አሰብንና ምፅዋን በጋራ ለማልማት እንቅስቃሴ ጀምረዋል። ሰሞኑንም የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦን ከአሰብ እስከ አዲስ አበባ ለመዘርጋት ተስማምተዋል።

የዶክተር አብይ የሰላም ጥረት በሁለቱ አገራት መካከል ስምምነቶች ተካሂደዋል። በተለይ በኤርትራ የሚገኙ እስረኞችና ምርኮኞች እንዲሁም የድንበር ጉዳዮች፣ የወደብ አጠቃቀም፣ የአልጀርስ ስምምነት አተገባበር ብሎም ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን ያካተቱ ነው። የስምምነቶቹን ተፈጻሚነት የሚከታተል ኮሚቴም ተቋቁሞ ስራ ጀምሯል።

በትራስንስፖርት ረገድም የአየርና የየብስ ትራንስፖርት ታሪፎችንና ሌሎች ጉዳዮችን በዝርዝር ይመለከታል። ይህ ሁኔታ ተሰብሮ የነበረውን የሁለቱን ሀገራት የሰላም፣ የፍቅርና የደመር ድልድይን ከመጠገን ባለፈ፣ ላለፉት 20 ዓመታት ሀገራቱ ያጡትን የጋራ ጥቅም የሚክስ ነው።

ኢትዮጵያና ኤርትራ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ከማሻሻል ባለፈ በዓለም አቀፋዊና በቀጣናዊ ጉዳዩች ተጋግዘው ለመስራት የሚችሉበት ዕድልም ይከፈታል። በዚህም አገራችን በሁሉም መስኮች ለምታደርገው ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች አንድ አጋዥና ተደማሪ ኃይል ታገኛለች።

የሁለቱ አገራት ግንኙነት በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ውስጥ ገንቢ ሚና ማበርከት እንድትችል ዘንድ የተጣለባት ማዕቀብ እንዲነሳ ኢትዮጵያ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እንድትሰራ ያደርጋታል። በተጨማሪም ኤርትራ ወደ ምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት በመግባት በቀጣናው የሰላም ኃይል ሆና በጋራ የምትሰራበትና ከሌሎች እህት አገራት ጋርም በቅንጅት የምትሰራበት ሁኔታ የሚያመቻች ነው።

ይህን መሰሉ ተግባርም ኢትዮጵያና ኤርትራ እንደ ወንድምና እህት ህዝቦች ዓለም አቀፋዊም ይሁን ቀጣናዊ ሚናቸው ጎልቶ እንዲወጣ የሚያደርግ ነው። ኢትዮጵያ የኤርትራ አቅም የምትሆነውን ያህል ኤርትራም የኢትዮጵያ አቅም ሆና እንድትሰራ የሚያደርጋትም ጭምር ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በሁለቱ አገራት መካከል ሰላም እንዲፈጠር ማድረጋቸው እነዚህ የሁለትዮሽና ቀጠናዊ ትብብሮች እንዲፈጸሙ አድርገዋል።  

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባደረጉት የሰላም ጥረት የአገራቱ ህዝቦች እንዲተባበሩ ብቻ ከማድረግ ባሻገር የቀጣናውን ሀገራት በጋራ ሰላም አምጭዎች እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ሊገኝ የሚችለው ሰላምም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እንዲጠቅም የሚያደርግ ነው።

የምስራቅ አፍሪካን የተፈጥሮ ፀጋዎች በጋራ ለመጠቀምም የሚያስችል ነው። ምስራቅ አፍሪካን ወደ ልማት የሚወስድ ነው። የቀጠናው አገራት የትብብር ማዕቀፍ ውስጥ እንዲገባም የሚያደርግ ነው። ይህም የቀጠናው ህዝቦች ከሚታወቁበት የድህነት፣ የስደት፣ የድርቅና የጦርነት ታሪክ ወጥተው ወደ ዕድገት ምዕራፍ እንዲሸጋገሩ የሚያደርጋቸው ነው። በተመድ የስዊዲን አምባሳደር ኦሎፍ አስጉግ ጠቅላይ ሚኒስትራችንን በሰላም አምጭነታቸውን በተምሳሌታዊ አካሄዱ ያደነቋቸው እነዚህን ሁሉ ቱሩፋቶች ማስመዝገባቸውን በመገንዘባቸው ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy