Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ትረስት ፈንድ ምንድነው?

0 480

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ትረስት ፈንድ ምንድነው?

ሚኪ PSIR

ትረስት ፈንድ ህጋዊ አካል የሆነ ለግለሰቦች፣ ለቡድን ወይም ለድርጅት ጥሬ ገንዘብን ወይም ንብረትን የሚያስተዳድር ፈንድ ማለት ነው። የተለያዩ የትረስት ፈነድ ዓይነቶች ያሉ ቢሆንም ሁሉም ሦስት ተመሳሳይ መሠረታዊ ይዘት አላቸው። እነዚህም ጥሬ ገንዘብ ወይም ንብረትን የሚለግስ፣ የሚያስተዳድር እና የፈንዱ ተጠቃሚ አካላት ናቸው። ከሣምንታት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው የ2011 ዓ.ም ረቂቅ በጀትን በሙሉ ድምፅ ባፀደቀበት ስብሰባ ላይ አዲስ ምክረ -ሃሳብ አቅርበው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአገር ዕድገት ይበጃል ያሉት ይህ ምክረ -ሃሳብ፤ የትረስት ፈንድ ማቋቋምን ይመለከታል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ሃሳብ ይፋ ሲያደርጉ ”ዲያስፖራዎች ለአንድ ማኪያቶ እሰከ አምሥት ዶላር ድረስ ያወጣሉ። ከማኪያቶ ወጪያቸው ላይ ለአገራቸው አንድ ዶላር በየቀኑ ቢያዋጡ በወር 30 ሚሊዮን ዶላር ለኢትዮጵያ ያስገኛል ማለት ነው” ብለዋል። በቦርድ የሚመራና ወጪ እና ገቢው በትክክል የሚታወቅ ‘ትረስት ፈንድ’ በማቋቋም ዲያስፖራው በየቀኑ አንድ ዶላር እንዲለግስ እንጠይቃለን ብለዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት እንዳሳወቀው ትረስት ፈንዱ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላትን በማሳተፍ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት ያለመ ነው፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ትረስት ፈንድ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሂሳብ ቁጥር 1000255726725 የተከፈተ መሆኑን ጽ/ቤቱ አስታውቋል፡፡ ለዚህ ተብሎ ድረገፅ እንደሚዘጋጅና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን የSWIFT አድራሻ CBETETAA በመጠቀም በመላው ዓለም የሚገኙ ዲያስፖራ ኢትዮጵያዊያን ወደ ትረስት ፈንዱ ድጋፋቸውን ገቢ ማድረግ እንደሚችሉም ተመልክቷል፡፡

ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በመስራት ላይ የሚገኙ የውጭ አገር ገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶችን መጠቀም እንደሚቻልም መግለጫው አመልክቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገር ቤት የሚልኩት ገንዘብ ህጋዊ መንገድን የተከተለ በማድረግ ”ህገ-ወጥነትን በመከላከል አገራችሁን ጥቀሙ” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈው ነበር። በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃሳብ መሰረት የሚቋቋመው ትረስት ፈንድ መቀመጫውን በኢትዮጵያ ወይም ከኢትዮጵያ ውጪ ያደርጋል። ከዚያም ፍቃደኛ የሆኑ የዲያስፖራው ማህበረሰብ አባላት በተወሰነ የጊዜ ልዩነት ለትረስት ፈንዱ መዋጮ ይፈጽማሉ።

ከቀናት በፊት የትረስት ፈንዱ የሂሳብ ቁጥር ይፋ የተደረገ ሲሆን ፈቃደኛ የዲያስፖራ አባላት በቅርቡ ይፋ በሚደረገው የትረስት ፈንዱ ድረ-ገጽ አሊያም ወደ 22 የሚጠጉ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶችን በመጠቀም ገንዘብ ማስተላለፍ እንደሚችሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍፁም አረጋ አስታውቀዋል።

ጉዳዩን አስመልክተውም የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ኃላፊው አቶ አሕመድ ሽዴ “ሐገራዊ ለውጡን እና የሽግግር ሒደቱን ለመደገፍ የሚያስችል የዲያስፖራ ትረስት ፈንድ ተቋቁሟል። ይህ ትረስት ፈንድም የተቋቋመው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውስጥ ነው” ብለዋል።  

ዴሎይት የተሰኘው የኦዲት እና ማማከር ሥራ ኩባንያ የምሥራቅ አፍሪቃ አገሮች ሥራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ ሲሳይ “ዓላማው መቀመጥ መቻል አለበት። በመጀመሪያ ደረጃ ፈንዱ ለምንድነው የሚውለው? እንዴት ነው የምንጠቀምበት? እንዴት ነው የሚሰበሰበው የሚያስተባብረው አካል ማነው?” የሚሉ ጥያቄዎች መመለስ እንደነበረባቸው ይናገራሉ።

አቶ ቴዎድሮስ እንደሚሉት የገንዘብ ሒሳቡን የመቆጣጠር ኃላፊነት የተሰጣቸው ባለሙያዎች ሊኖሩ ይገባ ነበር። አቶ ቴዎድሮስ የጠቅላይ ምኒስትሩ ሐሳብ በአግባቡ ገቢራዊ ከሆነ ከፍ ያለ ፋይዳ የሚኖራቸው ሥራዎች ለመከወን እገዛ እንደሚኖረው ያምናሉ። ባለሙያው እንደሚሉት የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ትረስት ፈንድ “የሚያስተዳድር፣ ተጠያቂ የሆነ ተቋም” ያስፈልገዋል። አቶ ቴዎድሮስ የባንክ ቁጥር ይፋ ከመሆኑ በፊት “አወቃቀሩ ይኸ ነው። ተጠያቂነቱ ለዚህ ነው፤ ገንዘብ ስታስገቡ ደግሞ ይኼ ኩባንያ ይኼን ያደርጋል” የሚለው ጉዳይ ሊቀድም ይገባ እንደነበር ገልጸዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ጥያቄውን ሲያቀርቡ በቀን ቢያንስ አንድ ዶላር ለመስጠት ፈቃደኛ ከሆኑ ሰዎች የሚሰበሰበው ገንዘብ “በመንግሥት በጀት አይገባም። የራሱ ቦርድ ይቋቋምለታል” ብለው ነበር። ቦርዱ ለመቋቋሙ እስካሁን በይፋ የተገለጸ ነገር የለም። 

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊው አቶ ፍጹም አረጋ በትዊተር ገፃቸው ባጋሩት ደብዳቤ በንግድ ባንክ ከተከፈተው የሒሳብ ቁጥር በተጨማሪ የኢትዮጵያ መንግሥት በቅርቡ ይፋ በሚያደርገው ድረ-ገፅ ጭምር የገንዘብ ድጋፉን ለማሰባሰብ መታቀዱን ገልጸዋል። ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በትብብር ይሰራሉ በተባሉ 20 ዓለም አቀፍ የገንዘብ አስተላላፊዎች ጭምር እገዛውን ማድረግ ይቻላል።

በትረስት ፈንዱ ዙሪያ ዲያስፖራው የተለያዩ ጉዳዮችን እያነሳ ነው፡፡ አቶ ሐብታሙ አበበ አሜሪካን አገር ሜሪላንድ ግዛት ውስጥ ይኖራሉ። ”በእድሜዬ በኢትዮጵያ ውስጥ አያለሁ ብዬ ያላሰብኩትን አይነት ለውጥ እየታዘብኩ ነው። በዚህም በጣም ደስተኛ ነኝ፤ የምችለውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ” ይላሉ። አቶ ሃብታሙ አክለውም ”ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዲያስፖራው አስተዋጽኦ ምን መሆን እንዳለበት በትክክል አስቀምጠዋል፤ እኔም ሆንኩ ባለቤቴ ትረስት ፈንዱ ተቋቁሞ ግዴታችንን ለመወጣት ዝግጁ ነን” ሲሉ ሃሳባቸውን አጋርተውናል።

በተቃራኒው ደግሞ ነዋሪነቷን በአሜሪካን አገር ቨርጂኒያ ግዛት ያደረገችው ፀደይ ብዙአየሁ ”ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሉትን ለመፈጸም በጣም ዝግጁ ነኝ፤ እኔ የምፈልገው እኛን የሚወክሉ ግለሰቦች የትረስት ፈንዱ አካል ሆነው አፈጻጸሙን የሚያሳዩ ወቅታዊ የሆኑ ሪፖርቶችን እንዲያደርሱን ብቻ ነው” ትላለች።

በአሜሪካን አገር ሚኒሶታ ግዛት የሚኖረው እና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያ የሆነው ያሬድ ገብረወልድ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሃሳብ በአዎንታዊ መልኩ ይቀበላል። ”ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ሃሳብ ከማንሳታቸው በፊትም አገራችንን አንዴት መርዳት እንዳለብን በቤተሰብ ደረጃ የምንወያይበት ርዕሰ ጉዳይ ነው” ይላል። ያሬድ ጨምሮም ”በርካታ ሰው አገሩን በገንዘብ መርዳት ይፈልጋል፤ ይሁን እንጂ የሚያዋጣው ገንዘብ ለጦር መሣሪያ ግዢ ይውላል፤ የሙሰኞች ሲሳይ ይሆናል፤ የሚሉ ስጋቶች ናቸው ከመለገስ እንድንቆጠብ የሚያደርጉን። ተጠያቂነት እና ግልፅነት የሰፈነበት አሰራር ካለ የሚጠበቅብንን ሁሉ ለመፈፀም ዝግጁ ነን” ብሏል።

የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎችም በጉዳዩ ላይ ትንታኔያቸውን እንደዚህ እየገለጡ ይገኛሉ፡፡ የቀድሞ የአዲስ አበባና የኢትዮጰያ ንግድ ምክር ቤቶች ፕሬዝዳንት የነበሩት እና የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አቶ ክቡር ገና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃሳብ የሚዋጥላቸው አይመስልም። አቶ ክቡር ”የትረስት ፈንድን የማቋቋም ሃሳብ ከውጪ የሚመጣውን ገዘንብ አጠናክሮ ከማስቀጠል ያለፈ ሌላ ፋይዳ አይኖረውም” ይላሉ። ”ስለ ትልቅ ገንዘብ ነው እያወራን ያለነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሉትን አይነት ገንዘብ ከማኪያቶ ወጪ ላይ በመቆጠብ የሚመጣ አይነት አይደለም። አሁን በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የፋይናንስ ቀውስ ለመቅረፍ ታስቦ የመጣ ሃሳብ ከሆነ፤ ይህ ሃሳብ የሚያስኬድ ስላልሆነ እንደገና ቢታሰብበት እለላሁ” ሲሉ ሃሳባቸውን ይሰነዝራሉ። አቶ ክቡር ”በግሌ በዲያስፖራ አላምንም። ዲያስፖራው በአገሪቱ ምጣኔ ሃብት ላይ የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለው እገነዘባለሁ። ይሁን እንጂ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው አገር ውስጥ ላለው ሃብት ነው” በማለት ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።

ሌላው የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ኑሩ ሰይድ (ዶ/ር) ግን የዲያስፖራውን አቅም ሲያስረዱ ”ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገሪቱ የሚልኩት የገንዘብ መጠን አገሪቱ ወደ ውጪ ነግዳ ከምታገኘው በሁለት እጥፍ ይበልጣል” ይላሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዲያስፖራውን አቅም ስለሚረዱ ነው ይህን አይነት ጥሪ ያደረጉት የሚሉት ዶ/ር ኑሩ ”ከዚህ በፊት መንግሥትን ለመጉዳት ታስቦ ዲያስፖራው ወደ አገር ውስጥ ዶላር እንዳይልክ የተለያዩ ቅስቀሳዎች ይደረጉ ነበር፤ እንዲሁም ህጋዊ መንገዶችን ባልተከተለ መልኩ ገንዘብ ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ ይደረግ ነበር። አሁን ግን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃሳብ ይህን እንኳን ማስቀረት የሚያስችል ከሆነ አገሪቱ በእጅጉ ልትጠቀም ትችላለች” ይላሉ። ነገር ግን ዶ/ር ኑሩም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሉትን የገንዘብ መጠን በትረስት ፈንዱ በኩል ማግኘት ቀላል ሊሆንላቸው አይችልም ይላሉ። ”ይህ ሃሳብ በየትኛውም አቅጣጫ የሚገኘውን የዲያስፖራ ሁለንተናዊ ድጋፍ ለማግኘት የተደረገ የቅስቀሳ አካል አድርጌ ነው የምመለከተው እንጂ እሳቸው የሚሉትን ያክል ገንዘብ ከዲያስፖራው ለመሰብሰብ የሚቻል አይደለም” በማለት ሃሳባቸውን ይሰነዝራሉ።

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy