Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አሮጌው የጥላቻ ፖለቲካ በአዲሱ የፍቅር ፖለቲካ ድል ተነስቷል !!

0 542

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አሮጌው የጥላቻ ፖለቲካ በአዲሱ የፍቅር ፖለቲካ

ድል ተነስቷል !!

ስሜነህ

 

በኢትዮጵያ ለዘመናት ስር ሰዶ የቆየው የጥላቻና ቂም በቀል የፖለቲካ ምዕራፍ የሚዘጋበት፤ በምትኩ የይቅርታ፣ የፍቅርና የአብሮነት ፖለቲካዊ ሁኔታ የሚፈጠርበት ስር ነቀል የለውጥ ጉዞ ተጀምሯል። ይህ ሀገራዊ የለውጥ ጉዞ በሀገራችን ኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየ፤ በአይነቱም ሆነ በይዘቱ በእጅጉ የተለየና መላውን የሀገራችንን ሕዝቦች በተስፋና በአንድነት ጎን እንዲሰለፉ ያደረገ ነው።

 

የለውጥ ጉዞው በአጭር ጊዜ ሀገራችንን ገጥሟት ከነበረው ያለመረጋጋት እና የሰላም እጦት የታደጋት ከመሆኑም ባሻገር በሕዝቦቿ ዘንድ ተፈጥሮ የነበረውን የፍርሃትና የጥርጣሬ ስሜት በመግፈፍ ለዘመናት ተሸርሽሮ የነበረው ሀገራዊ አንድነታችን እንዲጠናከር ጉልህ ሚና ተጫውቷል።

 

ከዚህ በተጨማሪ ለውጡን በተግባር በመቀየር የሀገራችን ሕዝቦች ሲያነሱት የነበረውን የዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ችግር ለመቅረፍ እንዲሁም የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት ምልዓተ ሕዝቡን ባሳተፈ መልኩ ሰፋፊ እንቅስቃሴዎች በመደረግ ላይ ይገኛሉ።

 

የተጀመረው ሀገራዊ ለውጥ በመላ የሀገራችን ሕዝቦች ዘንድ ከፍተኛ ተስፋ ያሳደረ ቢሆንም ከለውጡ የማይጠቀሙ ይልቁንም ጥቅማቸው በቀጥታ የሚነካ ኪራይ ሰብሳቢ ግለሰቦችና ቡድኖች ዛሬም ልክ እንደተለመደው በጥቅም በታወረ አስተሳሰብ የሀገርንና የሕዝብን ፍላጎት ወደ ጎን በመተውና ራሳቸውን ብቻ ማዕከል በማድረግ ለውጡን ለማዘግየት ከተቻላቸውም ለመቀልበስ ባለ በሌለ ሃይላቸው የአፍራሽ ሴራቸውን እያራመዱ ይገኛሉ።

 

ይህ ስብስብ ባለፉት ጊዜያት የመንግስት ስልጣንን ተጠቅሞ የብሔር እና የሕገ መንግስት ጭንብል ለብሶ የሀገር እና የሕዝብ ገንዘብ ሲዘርፍ የነበረና አሳፋሪ ተግባር ሲፈፅም የኖረ ስለሆነ የተጀመረው ለውጥ ተጠናክሮ ከቀጠለ የሰረቀውን እንዳይመልስና በህግ እንዳይጠየቅ ስለሚፈራ የተካነበትን እኩይ ተግባር ተጠቅሞ ለውጡን ለማጠልሸትና ብዥታዎችን ለመፍጠር እየሰራ ይገኛል። ይህን በተመለከተ ባሳለፍናቸው አራት ወራት ብቻ የተፈጸሙትን አፍራሽ እንቅስቃሴዎች በማስታወስ ማረጋገጥ ይቻላል።ሚሊዮኖችን ያፈናቀሉ ግጭቶችን ጨምሮ የበርካቶችን ንብረትና ህይወት ያወደሙት እንዚህ ግጭቶች የሃይማኖት ተቋማትን ሳይቀር ወደማውደም መሸጋገራቸው የለውጥ አደናቃፊውን የገዘፈ አቅምና ስጋት የሚያመላክት ነው።

 

በለውጥ አመራር የተሞላው የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚም ሰሞኑን ባደረገው ግምገማ ያረጋገጠው ይህንኑ ሲሆን ለህዝብና መንግስት ያስተላለፈው መልእክት ደግሞ ይህ ሃይል ግና አቅሙ እንዳልተዳከመ እና ያልበቃው እንደሆነ ማጠየቁ ነው በጉዳዩ ላይ የጥፋት ሃይሎችን ስለመከላከል እና በዚህም ለውጡን ስለማስቀጠል እናወጋ  ዘንዳ ያስገደደን።

 

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰሞኑን ባደረገው የሶስት ቀናት ግምገማ በለውጥ ሂደት እንደሚያጋጥሙ የሚጠበቁ ችግሮች የለውጡን ሂደት እየተገዳደሩት ያሉ መሆኑን፣ በተለይ ደግሞ የተገኘውን ነፃነት በአግባቡ በመያዝ ተቋማዊ እንዲሆን ለውጡን መደገፍ ሲገባ ከዚህ ተቃራኒ በሆነ መንገድ የሚደረገው እንቅስቃሴ ከወዲሁ ካልተገታ ስርዓት አልበኝነት እንዲነግስ ሊያደርግ የሚችል ዝንባሌ እየተስተዋለ መሆኑን በአንክሮ ተመልክቶ የህግ የበላይነት ለማስፈን የሚያስችሉ ስራዎች በጥብቅ ክትትል እንዲሰሩ አቅጣጫ በማስቀመጥ፤ በዚህ ረገድ ህዝቡ፣ የፀጥታና ደህንነት አካላት በለውጡ መንፈስ የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ጥሪውን ማስተላለፉ ነው የነዚህ ነውጠኞች አቅም እንዳልተዳከመ የሚያጠይቀው፡፡

 

በአጠቃላይ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በሁሉም መስኮች ሊባል በሚችል ደረጃ ለውጡን ተከትሎ የተከናወኑ ሥራዎች እና የተመዘገቡ ውጤቶች አመርቂ መሆናቸውን እንዲሁም ለውጡን የሚገዳደሩ ችግሮች መኖራቸውን፣ ችግሮቹንም ተቋማዊ አሰራር በመከተል እንዲሁም ህዝቡን በተደራጀ መንገድ በማሳተፍ እየፈቱ መሄድ ብሎም የተጀመረውን ለውጥ ዳር ማድረስ የወደፊት የትኩረት እና የርብርብ ማዕከል እንደሚሆን አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ ለዚህም ስኬት ህዝቡ እያሳየ ያለውን የለውጥ ባለቤትነት እና ድጋፍ ይበልጥ አጠናክሮ እንዲቀጥል ኢህአዴግ ጥሪውን በማቅረብ፤ ለእስካሁኑ ድጋፍም የላቀ አድናቆትና ምስጋናውን አድርሷልና ነው ስለቀረበው ጥሪ እንወያይ ማለታችን፡፡  

 

የመጀመሪያው የአደናቃፊ ሃይል መሳሪያ ማህበራዊ ሚዲያ ነው።  በዚህ መሳሪያ በኢትዮጵያውያን እና የዲያስፖራው ማህበረሰብ ውስጥ ጭምር የሚሰራጩ አሉባልታዎችን፣ የውሸት ወሬዎችን እና የማወናበጃ መረጃዎችን ማንገዋለል ከለውጥ አካላት ይጠበቃል ፡፡

 

በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ደህንነት ዙሪያ  በዚሁ መሳሪያ የተካሄዱት የማስፈራራት መሰረተ ቢስ አሉባልታዎች ምን ያህል አወዣብረውን እንደነበር እና ትናንት እውነታውን ሲነግሩን የተፈጠረውን ነገር ስለዚሁ የማንገዋለል ተገቢነት ልብ ማለት ያሻል።  በእርግጥ በሚናፈሱ አሉባልታዎች ላይ በመንግስት በኩል ይፋ የሆነ የማስተባበያ መግለጫ ባለመሰጠቱ ምክንያት ለሚዥጎደጎደው አሉባልታ ጥቂት እውነታነት ሊኖረው ይችላል በማለት ሰዎች ቢጨናነቁ ተገቢ ነው፡፡ለሚራገቡ ተራ ቅጥፈቶች እና የፈጠራ ወሬ አሉባልታዎች ይፋ የሆነ መንግስታዊ ምላሽ መስጠት የማይገባቸውን ትኩረት እንዲያገኙ በማድረግ በከፊልም ቢሆን ማመንን የሚያመላክት መስሎ ሊታይ ይችላል፡፡በሌላ በኩል ደግሞ  ለአንድ ተራ አሉባልታ ምላሽ መስጠት ከዚህም የበለጠ በርካታ ምላሾችን ለመስጠት በሩን እንደመክፈት ይቆጠራል፡፡ያም ሆነ ይህ ግን እንደጉዳዩ ክብደትና ጥልቀት እየለየ መንግስት አፋጣኝ ምላሽ መስጠቱ አንዱና መሰረታዊው የመከላከያ ዘዴ ነው።

 

ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በኢትዮጵያውያን መካከል አሉባልታዎችን፣ የውሸት ወሬዎችን እና የማወናበጃ መረጃዎችን በማሰራጨት ከበስተጀርባ ፍርሀት እና ጭንቀት በመፍጠር ላይ የሚገኙት እነዚያው የተለመዱት በሌብነት የደለቡ እና የስልጣን ጥማት የሚያቅበዘብዛቸው ሃይሎች ስለመሆናቸው የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ሰሞንኛ ግምገማና የጠቅላይ ሚንስትሩ መግለጫ አረጋግጠውልናል። ተጠርጣሪዎች እንደሆኑ እናምናለን፡፡

 

አሉባልታው በራሱ ላያሳስብ ይችላል። የለውጥ ሃይሎችን ሊያሳስበን ከተገባ እነዚህ  ውሸቶች እና አሉባልታዎች በተወሰኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች ውስጥ በሕዝቦች መካከል አለመረጋጋትን፣ የኃይል እርምጃ መውሰድን፣ ሞትን፣ እልቂትን እና መጠነ ሰፊ የንብረት እና የሀብት ውድመትን እንዲያስከትሉ ሆነው በጥቅም ላይ እየዋሉ የመገኘታቸው ሁኔታ ነው፡፡

 

የአሉባልታ መሳሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድን እና የመንግስታቸውን ሕጋዊ ቅቡልነት ለማሳጣት እና ወገን እና ሀገር ወዳዱ መሪ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ባለው ሰላማዊ የለውጥ ሂደት አንጸባራቂ ኮከብ በመሆን የተጎናጸፉትን ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ አመኔታ ለመሸርሸር እና ለማጥፋት ሲባል ሆን ተብሎ ታስቦበት፣ በስሌት እና በታቀደ መልኩ እየተካሄደ ያለ መሰረተ ቢስ ዘመቻ ነው።

 

ሃገሪቱ ወደ ሕግ አልባነት ስርዓት ተቀይራለች፤ ሕገ መንግስቱ እየተጣሰ  እያሉ በነጋ በጠባ ሽንጣቸውን ገትረው የቅጥፈት ስዕል ለመሳል የሚያደርጉትን ከንቱ መንፈራገጥ እና ባዶ ጩኸት በአርምሞ እና በቁጭት መመልከት ለለውጥ ሃይሎች ለብቻው በቂ አይደለም፡፡ በሕዝብ ላይ እልቂትን እየፈጸሙ፣ ዜጎችን እያፈኑ እያጠፉ፣ አካለ ጎደሉ እያደረጉ፣ በሕዝቦች መካከል ጥላቻን እንደ እህል እየዘሩ፣ የኃይማኖት መቃቃርን እየቀፈቀፉ፣ የጎሳ በረት እያጠሩ፣ አንዱን ብሐር ወርቅ ሌላውን ጨርቅ በማለት እየፈረጁ፣ የሀገርን ሉዓላዊነት እየደፈሩ እና እያስደፈሩ፣ የሀገርን ጥሪት እንደ ባዕድ ወራሪ ኃይል እየዘረፉ፣በዝምታ ብቻ ማለፍ ለለውጥ ሃይሎች ሽንፈት ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝቦች ስንዴውን ከእንክርዳዱ በመለየት ስለህግ የበላይነት ሊዋደቁ ከተገባ ጊዜው አሁን ነው። አሁን በቅርቡ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን በተለይም በሶማሊ ክልል እየተፈጸመባቸው ያለውን ጥቃት ለማምለጥ ሲሉ ከመኖሪያ ቀያቸው በኃይል እየተፈናቀሉ ለመከራ ሲዳረጉ ከጀርባ ሆኖ ለስደት እየዳረጋቸው ያለው ሚስጥር ባለቤት ማን እንደሆነ በውል ተገንዝበናል፡፡ አብዛኞቹ ለዚህ እልቂት እና የመከራ ሕይወት የተዳረጉት ደግሞ ሴቶች፣ አረጋውያን እና ህጻናት ናቸው፡፡ ይህንን አስከፊ ድርጊት ከበስተጀርባ ሆነው የሚያቅዱ፣ አመራር የሚሰጡ እና ከሕዝብ የዘረፉትን መጠነ ሰፊ ገንዘብ ለቅጥር ነብሰገዳዮች እና የጥፋት ኃይሎች በመርጨት የሚያስፈጽሙት ወንጀለኞች እነማን እንደሆኑ ደግሞ ከእጆቻቸው አሻራዎች እና ከእግሮቻቸው ኮቴዎች አንጻር በኢትዮጵያውያን ሕዝቦች ዘንድ በውል ይታወቃሉ፡፡  

በዜጎች ላይ የኃይል ጥቃት የሚሰነዝሩትን ግለሰቦች እና ቡድኖች እንዲሁም ይህንን ዕኩይ የኃይል ድርጊት በመላ ኢትዮጵያ የሚመሩትን እና በገንዘብ የሚደግፉትን በሙሉ ማውገዝ ከለውጥ ሃይሎች ይጠበቃል፡፡

 

አሁን የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እና የሕዝባዊ ተጠያቂነትን ለመመስረት እና ተቋማዊ ለማድረግ መልካም አጋጣሚ አግኝተናል፡፡ ሰብአዊ መብቶች ዋጋ የሚያገኙበት እና የሚከበሩበት ባህልን ለመመስረት መልካም አጋጣሚም አግኝተናል፡፡ ግን ደግሞ ሁሉንም ነገር እንደ ዋስትና መውሰድ አንችልም፡፡ ነጻነትን ለማግኘት ከባድ ነገር ነው፡፡ ሆኖም ግን ነጻነትን ለማጣት ቀላል ነገር ነው፡፡

ሁሉም ኢትዮጵያውያን ዓይኖቻቸውን ካገኘነው ስጦታ ላይ እንዲያተኩሩ ግድ ይላል፡፡ እነዚህን ስጦታዎች ከፍተኛ የሆነ ዋጋ ከፍለንባቸው ያገኘናቸው ናቸው፡፡

በርካታ ኢትዮጵያውያን በአሁኑ ጊዜ ተጎናጽፈነው የሚገኘው የነጻነት ጎህ ይቀድ ዘንድ የመጨረሻ የሆነውን ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ መልካም ነገር በሰይጣናዊነት ላይ ድልን ተቀዳጅቶ ያገኘነው ሁሉም ኢትዮጵያውያን የደም፣ የላብ እና የእንባ መስዋትነትን ከፍለው ነው፡፡

ስለእራሳችን ጉዳይ ማንም ሲነግረን የነበረውን በፍጹም መርሳት የለብንም፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ወደፊትም ማንም እንዲነግረን መፍቀድም የለብንም፡፡

ሁላችንም በአንድነት እንሰቃይ ነበር፡፡ ሁላችንም በአንድነት ደማችንን አፍስሰናል፡፡ በመጨረሻም በአንድነት ሆነን በመዋጋት በአንድነት ድልን ተቀዳጅተናል፡፡ለእኛ ሲሉ መስዋዕትነት የከፈሉትን ወገኖቻችንን የምናስታውሳቸው ኢትዮጵያ በፍጹም ለጨቋኝ አምባገነኖች አገዛዝ እንዳትንበረከክ በማድረግ እና ለነጻነት እና ለዴሞክራሲ የሚደረገውን ረዥሙን ጎዳና ምንም ዓይነት ችግር ቢያጋጥምም እንኳ ያለምንም ማወላወል ከዳር ለመድረስ ጉዟችንን በመቀጠል በድል አድራጊነት ስናጠናቅቀው ብቻ ነው፡፡

በህብረተሰብ ውስጥ ዘለቄታዊ ሰላምን ለማምጣት ጥይትን ሳይሆን የምርጫ ካርድን መጠቀም እንዳለብን ክቡር ጠቅላያችን መሪ አስተምረውናል፡፡ አዲስ የወደፊት እኩልነት እና ለሁሉም ሕዝቦች ፍትህ ለማምጣት የሚቻለው በእውነት እና በብሄራዊ እርቅ ብቻ ነው፡፡ ሁላችንም መናገር እና መፍትሄዎችን መስጠት አለብን፡፡

ከሁሉም የበለጠ ደግሞ ኢትዮጵያ ከአምባገነናዊ ስርዓት ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንድትሸጋገር ለማገዝ የእራሳችንን ሚና መጫወት አለብን፡፡

 

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ሁሉም ዓይነት መልሶች አሏቸው ብለን ማሰብ ለእንቅፋቶቹ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ነው፡፡የኢትዮጵያን ችግሮች ሁሉ መፍታት የሚችሉት ብቸኛው ሰው እርሳቸው ናቸው ብለን የምናምን የሆነ እለት ተበልተናል ፡፡የሀገራችንን ውስብስብ ችግሮች ለመፍታት አንድ ሰው ወይም ቡድን ሁሉም ዓይነት መልሶች አሏቸው ማመን አይገባም፡፡ቢያንስ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ችግሮችን ሁሉ አለመፍጠራቸውን እንገነዘባለን፡፡ እናም ለሁሉም መፍትሄዎች ምንጭ እርሳቸው ናቸው በማለት አንጠብቅ፡፡ የመፍትሄ አካል በመሆን የእራሳችንን ሚና መጫወት አለብን፡፡ የእራሳችንን ሚና መጫወት ማለት በፌስ ቡክ የሚወዱትን የኮምፒውተር ቁልፍ መጫን ወይም ደግሞ በማህበራዊ መገናኛዎች የጥላቻ ጭቃ መቀባባት ማለት አይደለም፡፡

 

የእራሳችንን ሚና መጫወት ስንል በኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲን፣ የሰብአዊ መብት ጥበቃን እና የሕግ የበላይነትን ማደራጀት እና በተግባራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ በመሳተፍ በማገዝ ኢትዮጵያ በሰላማዊ የለውጥ ጎዳና ላይ መሆኗን ማረጋገጥ ነው፡፡

ለመፍትሄዎቹ መንግስት ብቻ ሳይሆን ወደ ሕዝቦችም ማየት ይኖርብናል፡፡ የችግሮቻችን መፍትሄዎች በእጆቻችን በእያንዳንዳችን እጆች ላይ እንጅ በፖለቲከኞች እና በመንግስት ባለስልጣኖች እጆች ላይ አይደሉም፡፡

 

ስልጣናቸውን ያጡ ስልጣናቸውን እንደገና ለማግኘት ሲሉ በእራሳቸው ኃይል ማንኛውንም ነገር ሁሉ እንደሚያደርጉ መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ ይህንን ማድረግ ካልቻሉ ደግሞ ሀገሪቱን ማጥፋት የሚችል ማንኛውንም ነገር ይፈጽማሉ፡፡ ሆኖም ግን ይኸ ጉዳይ ሊሳካላቸው የማይችለው በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን አዲስ ቀን ከላይ በተመለከተው መልኩ መጠበቅ ስንችል ነው፡፡አሮጌው የጥላቻ ፖለቲካ፣ ክፍፍል እና ግጭት በአዲሱ የፍቅር፣ የመግባባት፣ የእርቅ እና የሰላም ፖለቲካ በመቀየር ላይ ነው፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy